Print this page
Saturday, 24 September 2022 17:47

እልም አለ አውቶብሱ...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሚስቱ ክፉ ባቄላ እራቱ፣ ብሳና እንጨቱ፣ ሀዘን ነው ቤቱ
ሚስቱ ደግ ስንዴ እራቱ፣ ወይራ እንጨቱ፣ ደስታ ነው ቤቱ፣
የምትል የቆየች ስንኝ አለች፡፡ ያው እንግዲህ ‘የትምክህተኞች’ ዘመን አልነበር! ያኔ ይቺ አባባል ስትፈለሰፍ’ አብዮቱ  ፈንድቶ  ቢሆን ኖሮ... አለ አይደል... ምድረ ሾቭኒስት  ሁላ “የምናምን  ወጠጤ፣ ምናምኑ  ያበጠ...” የሚል የማርሽ ባክግራውንድ ያለው መግለጫ ይለቀቅለት ነበር፡፡  እሺ፣  እኔ የምለው  ባሏ  ክፉስ የሆነች ሚስትስ፣ ስለ እስዋስ ምን ይባል! እንደውም የምንጠቅሰው የምርምር ሰነድ አይኑር እንጂ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከክፉ ሚስቶች ይልቅ ክፉ ባሎች ባይበዙ ነው! እንዴት ነው የሚታወቀው ብሎ መጠየቅ ሸጋ ነው፡፡
እስቲ ቦተሊካችንን ተመልከቱ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የተቆጣጠሩት ወንዶቹ አይደሉ እንዴ! ከቦተሊካ ጀርባ ሆነው መከራችንን የሚያበሉን ወንዶች አይደሉም እንዴ! እናማ... በአደባባይ ይህን ያህል ክፉ የሆኑ፣ ለራሳቸው ግለሰባዊ፣ ቡድናዊ ጥቅም ሲሉ ይህን ያህል ሰውን ከሰው ለማጋጨት ቀን ከሌት ወገባቸውን አስረው ነገር ሲጎነጉኑ የሚኖሩት ወንዶች አይደሉ እንዴ!  ታዲያላችሁ... በአደባባይ ለዚህ ሁሉ ህዝብ ክፉ የሆኑ፣  በየቤታቸው ምን  ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ ነው፡፡  
ስሙኝማ ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እንደው ተዙሮ እዛው፣  ተዙሮ እዛው! ጭራሽ ባለስልጣናትም እንዲህ ይሁኑ! እኔ የምለው... የበቀደሙ የለንደኑ አውቶብስ ስንት ቁጥር ነበር? ያ የአፍሪካ መሪዎች ተሳፍረውበት ምድረ የፈረንጅ ሚዲያ የተቀባበለው ነዋ! ደግሞ እኮ እንደ ሰበር ዜና  ምን ያህል በተለይ የምዕራባውያኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተቀባበሉት እንደሆነ ስታዩ፣ ነገርዬው የሆነ ነገር እንዳለው ትጠረጥራላችሁ፡፡ እንደው የእነ ባይደን አይነት መኪና ቢያጡ በአውቶብስ!
ሌላው ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ... እነኛን ሁሉ መቶ ሚሊዮኖች አፍሪካውያን እንወክላለን የሚሉ ሰዎች እንደዛ ሲሳሳቁ (ሌላ ቃል ላለመጠቀም ነው እንጂ ምን፣ ምን የመሳሰሉ ‘ሲሳሳቁ’ የሚለውን ቃል የሚተኩ ቃላት በኖሩ ነበር!)  ...አለ  አይደል... ልክ ለሽርሽር ብሔረ ጽጌ ምናምን የሚሄዱ የመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች ይመስላሉ፡፡ ሀገርና ህዝብ ወክለው አይደለም እንዴ እዛ የሄዱት! ነው ወይስ በአውቶብስ የሄዱት ፈረንካቸው የተቀመጡባቸውን  የባንኮቹን  ደህንነት  እግረ  መንገዳቸውን  ለማረጋገጥ ነው! ቂ....ቂ....ቂ...
የምር እኮ እንደፈረንጅ  በኮሜዲ ጣራ አልፎ የሄደ የለም፡፡ በራሳቸው ባንክ ቢሊዮኖች ዶላሮቹን አከማችተውላቸው፣ በራሳቸው ዋና ከተሞችና መዝናኛ አካባቢዎች ምን የመሳሰሉ ቪላዎች ሲገዙና ሲገነቡ እንዳላየ ጀርባቸውን እያዞሩ..."የአፍሪካ መሪዎች ህዝቡን እየዘረፉ..." ምናምን ይሏችኋል፡፡  የምር ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አውቶብሶቹን እንግሊዞቹ አዘጋጅተውላቸው ነው ወይስ ራሳቸው መርጠው! አይ እንግሊዝ!  
ይህ ነገር የሆነው ትንሽ ወደኋላ ሄዶ ነው፡፡ አንድ የበዓል ወቅት ነው፡፡ ቤት ውስጥ ያሉት ባልና ሚስቱ ሁለቱ፣ አንዲት ስድስት ሰባት ዓመት የሚሆናት ልጃቸው ነች፡፡ የአቅማቸውን ያህል ተዘጋጅተዋል። እናላችሁ... በበዓሉ ቀን ምን ቢሆን ጥሩ ነው...ሦስት የእሱ ጓደኞች እየተሳሳቁ ከች፡፡ ማንም አልጋበዛቸው፣ ቀደም ሲል በበዓል ቀን የመምጣት ልምድ የላቸው፣ ወይ ደግሞ በዓሉን ለማሞቅ ብለወ ይዘው የመጡት ነገር የለ!
እናላችሁ... እሷ ክው ትላለች፡፡ የበዓል ምሳ ማቅረቢያው ጊዜ የደረሰ ስለሆነ ምኑን ከምን ታድርገው! አይደለም ሦስት ሆዳቸውን አስፍተው የመጡ የበዓል ድንኳን ሰባሪ እንግዶች ለመቀለብ ቀርቶ፣ ቤተሰቡ በማንኛውም እለት እንኳን ብክነት እንዳይኖር ሁሉም ነገር በልክ የሚዘጋጅበት ነበር፡፡ ለካስ ባልም ብሽቅ ብሎ ነበር፡፡ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው...ድንገት ብድግ ይላል፡፡ ለሚስቱ እንዲህ ይላታል... “ቅድም ያልኩሽን እቃ ገዝቼ ልምጣ፡፡ እግረ መንገዴን እነሱንም ልሸኛቸው፣” ብሎ ቁጭ! ምን ያድርጉ! አይደለም አብረው ማዕድ ሊቀርቡ፣ አይደለም “ሻይ፣ ቡና በሉ እንጂ...” ሊባሉ.. በቅጡ እንኳን ተቀምጠው ሳያበቁ በተዘዋዋሪ “ደህና ሁኑ...” ሲባሉ የሚሰማቸውን አስቡትማ፡፡ አባወራው ወደ በሩ ሲሄድ የግዳቸውን ተከተሉታ! እሱም ሦስቱን ሸኝቶ ምንም ነገር ሳይገዛ ቤቱ ሲመለስ ሚስቱ በደስታ ተጠመጠመችበት ነው የሚባለው፡፡
“ብረት መዝጊያ የሚሆን...” ይላችኋል እንዲህ አይነቱ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ጓደኛ የተባሉትና መሶብ ሊገልብጡ ሄደው ክው ያሉት  ቀሺሞች ሰላምታቸው ሁሉ እንደነገሩ ሆኖላችኋል፡፡ የሚገርመው ምን መሰላችሁ...ሁለቱ ሰዎች ቤተሰቦች ማለትም የትዳር አጋሮችና ልጆች ያሏቸው ናቸው!
እኔ የምለው...የትናንት ‘ብልጥነት’ እኮ ዛሬ አይሠራም፡፡ የቤቱ መሶብ ባዶ ሆኖ እያለ በፊት፣ በፊት ተሰብስባ ድርቆሽ ትሆናለች የምትባል ትርፍራፊ እንጀራ ሁሉ በመደበኛነት ደግማ ደጋግማ በምትቀርብበት ጊዜ ጠግቦ ትንፋሽ ያጠረውን መቀለብ ብሎ ነገር አይሠራም፡፡ ወላ ዘመድ፣ ወላ ጓደኛ፣ ወላ አብሮ አደግ--- ራስን መቻል ነው፡፡
በፊት ጊዜ አንድ የሚዲያ ሰው ነበር፡፡ ስታዩት እኮ አይደለም “ዛሬ ምሳ ልግዛለት፣” “ቅዳሜ እራት ልጋብዘው...” ሊያሰኝ ቀርቶ ገና የሚቀጥለውን ሦስት ወር ቀለብ አስቀድሞ ያስገባ ነው የሚመስለው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ... (የምር ግን እኮ እንደዛ የመሰሉ ሰዎች እኮ አሉ.! ልክ ነዋ... አለ አይደል...መስከረም ላይ ሲታዩ እስከ ጥር ድረስ ሰውነታቸው የሚያስፈልገውን ምግብና መጠጥ  አስቀድመው ‘ኢን ያደረጉ’ የሚመስሉ!)
ታዲያላችሁ...ይህ የምላችሁ ሰው ቅዳሜ፣ ቅዳሜ አንድ ልምድ ነበረው። ከቀትር በኋላ መሀል ከተማ አካባቢ ባሉ ቡና ቤቶች ገባ፣ ወጣ ያበዛል፡፡ ለምን መሰላችሁ... የሚያውቀው ሰው ፍለጋ፡፡ ደግሞም ያገኛልም፡፡ እናንተ ቡና ወይ ሻይ ይዛችሁ ቁጭ ብላችኋል እንበል። አጅሬ ከች ይልላችኋል፡፡ ለመጨባባጥ እጃችሁን ከመሰንዘራችሁ በፊት እሱ ወንበር ስቦ ተቀምጧል፡፡ ልክ እኮ ቀጠሮ ያላችሁ ነው የሚመስለው፡፡ ጥሩ እሺ ይቀመጥ፡፡ የእረፍት ቀን ስለሆነ የሚጨዋወቱት ሰው ማግኘት ክፋት የለውም፡፡ ግን አጅሬው የራሱን ጨዋታ ይጀምራርላችኋል፡፡
“ማነሽ... እስቲ አንድ ጃምቦ ድራፍት አምጪልኝ!” ጃምቦ! እናንተ እኮ ሻይ ያዘዛችሁት የአምሮት ጉዳይ ሆኖባችሁ ሳይሆን የኪስ ጉዳይ ሆኖባችሁ ነው፡፡ አጅሬው ወር በገባ በአስራ ሰባት ብር ኬት አምጥቶ ነው! ልክ ነዋ...የሞዴል ስድስት ቀን ካለፈ እንኳን እኮ አስራ አምስት ቀን አልፏል፡፡
ጃምቦው መጥቶ ካጋመሰው በኋላ ነው ‘አፉ የሚፈታለት፡፡’
“ጠፋህ እኮ!” በበፊተኛው ቀን እኮ አራት ጊዜ ነው መንገድ ላይ የተገናኛችሁት፡፡ ለነገሩማ የአጅሬውን ባህሪይ ካላወቃችሁ ነው እንደዛ የምታስቡት፡፡ ይልቅ ዋናው ጨዋታ... “ክላማይክሱ” ቢባልም ክፋት የለውም....የሚመጣው በኋላ ነው። ሁለተኛውን ጃምቦ ይገለብጥና በል አትጥፋ፣ ቀጠሮ ስላለብኝ ነው ብሎ ውልቅ! የእናንተ ደግሞ ምናችሁ፣ ምናምናችሁ ሁሉ ውልቅ! ሁለት ጃምቦ ማለት እኮ ወሩን እዘልቅበታለሁ ያላችሁትን ፍራንክ እስከ መጨረሻዋ ሳንቲም ነው የሚያራግፋችሁ።
የምር ግን ዘንድሮ እኮ ሌላውን ሰው የሆነ ነገር ያለመጋበዝ፣ ሳትጋብዙት በራሱ ጊዜ  ለተጠቀመበት ምግብና መጠጥ በይሉኝታ ሂሳብ አለመክፈል ቆንቋናነት አይደለም፡፡
የሆኑ የምናውቃቸው ባልና ሚስት ነበሩ፣ ቆየት ባለው ዘመን ማለት ነው፡፡ ባልና ሚስቱ በተለይ ምሳ በሚመገቡበት ጊዜ አንድ ትልቅ ጠረጴዛ ጋር አብሮ የተሠራ ትልቅ መሳቢያ ላይ ነበር፡፡ እየተመገቡ እያለ ድንገት በር ከተንኳኳ ቶሎ ብለው መሳቢያውን ወደ ውስጥ ይገፉታል። በእነሱ ቤት በጣም ብልጥ መሆናቸው ነው። ግን ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ... ይህን ባህሪያቸውን ዘመዶቻቸውም፣ ወዳጆቻቸው የሚባሉት ሁሉ የሚያውቁት ነው፡፡ ደግሞላችሁ ፍራንክ እኮ እንደልብ ያላቸው ነበሩ!
አሁን ግን መጀመሪያ ላይ አይደለም መደበቂያ መሳቢያውን ማግኘት፣ የሚደበቀውንም ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ ነው...በር የሚያንኳኳ ግን እንደቀድሞው ባይበዛም አሁንም አለላችሁ፡፡ እናማ...ህዝቤ በር ቆልፎ ቢመገብና ቢጠጣ ወዶ አይደለም፡፡ ኑሮው ነው፡፡  መጀመሪያ እስቲ እሱ አንጀቱ ጠብ የሚል ነገር ያግኝ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... የአፍሪካ መሪዎች በአውቶብስ ተጭነው የመሄድ ነገር የመጨረሻ ደስ የማይል ነገር ነው፡፡ የአንዲት ትንሽዬ አፍሪካዊት ሀገር መሪና እነባይደንና ማክሮን የሀብት መጠን ይለያቸው እንደሆነ እንጂ ‘የተሻለ ሰው’ የሚባል ነገር የለም፡፡ እና አውቶብሱ ለሁሉም ያልቀረበበት ምክንያትሳ! ጉደኛ ዓለም ነች እኮ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1433 times