Saturday, 20 October 2012 10:35

የውኃ ድር

Written by  ዋሲሁን በላይ (አዋበ)
Rate this item
(5 votes)

የወረደው
.
.
.
እንደተጠበቀ ነው፡፡
የኦሪት ልብ እንዳይኖር፡፡

ይሔ ህግ ግን … ያልተገደበ ነው … (በእኔ ህሊና) ሰው ያወጣውን ሰው የመጣስ መብት አለው…! ህግ ህግ ሆኖ የሚቀረው ስንስማማበት ብቻ ነው፡፡ ያልተስማሙበት ህግ … የህጉ አካል ነው ከተባለ ሊሆን ይችላል፤ (የሰፈረ) እንጂ የሆነው እንዲሆን የሚሆነው ሊሆን ግድ ስለሆነ፡፡
ሐዲሱ ይስማማናል፣ … ከፍተኛ መስዋዕት ስላስከፈለ … ከመፍጠር ማዳን ልቋል፡፡ ወደን … መርጠን የላዩን ጠንቅቀን እናስከብራለን… የስሩን ባናስከብረውም አንንቀውም፡፡ የላይኛውን መንገድ ስለዘጋ!!!
እባቢቱን ለሚከተል … ፍርሃቱ የፈጠረበትን ለገዛ አምሳሉ (ለሁሉም ለማይሆን) ለሚንበረከክ አተርፍ ባይ አጉዳይ ቆሞ ለሚሳብ፣ እየሄደ ለማይደርስ፣ በያዘው ለማይረካ፣ የጨበጠው ለሚሟሟበት አዳም… ቀድሞ ህልሙን ካልፈታ፣ ተልኮውን ካለወቀ፣ ከንፈሩ ምስጋናን ከከለከለች … ወየውልህ ትለዋለች … የገዛ ነፍሱ … ለሚሻርና ለሚያልፍ ስም ልባችን ላይ ጣኦት አንትከል፡፡
***

“አይኔ አይንሽን ሲያየው የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” 
“እንጀራ አባቱ ስለሆንክ”
“የእንጀራ አባቱ…? ወይስ የፍቅር አባቱ?”
“እሺ የአይን አባቱ፡፡” አይኗን ሳምኳት፤ ባያምሩም አያስጠሉም፡፡ የደስ ደስ እንጂ ውበት የላቸውም፤ የደስ ደስነቷ ውበት ስለሆናት ውበት ምንድን ነው? … ፊቷ አይገፈትርም … ርህራሔዋ ትኩስ ቅቤ የተቀባ እንጐቻ ነው፡፡ ሳቋ ስስ የብርሃን መጐናፀፊያ ነው የሚመስለው፤ ዐይኗ በሙካሽ የተጠለፈ ምርጥ መባ ትመስላለች፤ ጭልጭል እያለችም ታጓጓለች፡፡ ነጠላ ለብሳ ቤተ ክርስቲያን ስትሔድ እምትመለስ ስለማይመስለኝ … አብዝቼ እፀልይ (እለምን) ነበር …
“አባት ሆይ ስታበጃትም ፍቅር አብዝተህባት ነውና ስትነሳም ስታርፍም በምስጋና የተሞላች የመላዕክት ክንፍ የመሠለች ፍጥረትህን ለእኔ ስትል የመናኝ ልብ አትስጣት!” (አብዝቼ እለምን ነበር)፡፡ ስስታምነቴ በ’ሷ ላይ ብሷል፡፡
ወንድሞቿ ከኩርኩም ጋር ምክር ለገሱኝ “ብትደርስባት … በማንኛውም መልኩ አብረሃት ብትሆን ጥርስህን ኪስህ ውስጥ እንከትልሃለን” አሉኝ፡፡ ማን ወላቃ ሆኖ ይቀራል፣ (የድሮ አራዳ ይመስል)
እየደወድኳት ራቅኋት … ብርቃትም ቀረበችኝ … ተደብቃ ታገኘኛለች … እኔ ስጋቱ ስላስጨነቀኝ በጣም ይሸክከኝ ነበር፤ እንዲያም ሆኖ ያላደረገችልኝ ያላስደረገችኝ ነገር የለም … ከእነሱ ቤት ጀርባ መደዳውን እንጀራ የሚሸጡበት ሰፈር ሁለት ጊዜ አዲስ ምድጃ ከነወጡ ሰርቄ፣ ድስቱንም ምድጃውንም ለቆሬ ሸጬ ብሔረ ፅጌ ወስጄ ኮምኩሜአታለሁ፡፡ እሷ ከቤት እያመጣች ያልፖሸርነው እቃ የለም፡፡ የምር ምስራቅን ሐጢያትም እየሠራሁ እወዳታለሁ፡፡ ሁሌም አስባታለሁ … “ነይ” ባልኳት ቁጥር ትመጣለች … “ሒጂ!” ብዬ ማስቀረት ግን አልቻልኩም … እቺ ፍንጭት ድምቡሽቡሽ … ልቤን እንደሞላችው አለች፡፡
***
ከላይ የተፃፈው ትዕዛዝ (በደማቅ እሣት) የማይሻር የማይለወጥ እንደሆነ ልቦች ያውቃሉ … እያወቁም ያጠፋሉ፤ አጥፍተውም “ምህረት” የሚሉ ጥቂቶች ናቸው … ለዛውም ደጅ ለማያሐጠና ልመናና ምህረት … ለአንድ ትንሽዬ ልብ … ትንሽዬ ልብ በቂው ነው፡፡ ይሔንምም እናውቃለን አውቀንም ለመፈፀም እያቅማማን እንገኛለን፡፡ አይናችን ከአዕምሮአችን ጋር የተቀያየመ ይመስል … ባለመመልከት መሀል እያየ አያይም … ደልዳላው ገደል፣ ውኃው ጠጠር፣ ሥጋው ቅጠል፣ ሊሆንብን እየሆነ ይመስላል፡፡
***
ፀሐይዋ አመለኛ መካን የመንደር ሴት ይመስል ትጠብሳለች፡፡ ያለ ምክንያት ያፋሽመኛል፡፡ አሁን … አምስት ደቂቃም አይሞላኝ ከቤቲ ጋር ኪሪያዚስ ብቻዬን ሁለት ጎጆ ኬክ እንደውኃ ፉት ብሎ ከመጣሁ፤ አናቱ ላይ ማኪያቶ ያለ ስኳር ደረብ አድርጌበት … እና … ሆዴ ግን ምንም ያየም የቀመሠም አይመስልም፡፡ በርጫ ከተውኩ ዛሬ ሃያ አንድ ቀኔ ነው … ታዲዎስ እና አዲስ ለመወስወስ ሞከሩ ሞከሩ … አልሞክራትም … አልኳቸው! ተስፋ ግን አልቆረጡም … እስከ አሁንም የተሸወድኩት ይቆጨኛል … ያ ባሪያማ ሱሱ እላዩ ላይ ቤቱን ሠርቶበታል … ከወንድዬ ጋር ሆኖ የገዛ አልጋቸውን ከተሠቀለበት አውርዶ ሸጦ ቅሞበታል … አሁንም እነ አይኖም ምድር ቤት ተቀምጠው እየቃሙ ነው …፡፡ አብሬአቸው መጫወት እፈልግ ነበር … ግን መወስወሴ ስለማይቀር ይብራብኝ፡፡
እቺን ፀሐይ ብጠላትም ቤት ውስጥ ማንበብ ብቻ ሥለደበረኝ … እነ አጅዋ በረንዳ ላይ ብቻዬን ቁጭ ብዬ ወጭ ወራጁን እከልማለሁ፡፡ የተጨበጨበለት የሽንት ቤት ፍሳሽ ፊት ለፊቴ ያለከልካይ ይንጐማለላል፣ ሽታውን ሁላችንም የሰፈር ልጆች ምርጫ ስለሌለን ለምደነዋል … ዋው! አንድ ቀን እኔና ሐይልዬ … ወደ ዘጠኝ ቤቶች ይሆናሉ አዋጡና እናሰራው ብለን ብር ሠበሠብን … ያለ ከልካይ ተምነሽነሽንበት፤ ከዛ እኛው በረጅም እንጨት ጐርጉረን ለአንድ ሳምንት እፎይ ካስባልነው በኋላ ተመልሶ ገነፈለ (አንዳንዴ አዲስ ጀበናም ይመስለኛል) አሁን ሁሉም ስለሠለቸው ያለከልካይ ይወርዳል … /ጤናችንን እንጠብቅ በሚባልበት ዘመን/ በዚህ በጠራራ ፀሐይ እኔና እሱ ተፋጠን እሱ ይወርዳል እኔ ተቀምጫለሁ፤ እነ ድባቤ አጥር ስር … እንደ ጐራዳ የደስ ደስ ያላት ልጃገረድ እምታምር ጥላ አለች፡፡ እዛች ጋር ሔጄ ለመቀመጥ ሳስብ … ትላትን ማታ ያቺን ፍንጭት የውኃ ድፎ ዳቦ የመሠለች ድንቡሽ … የቆርቆሮውን ተገን አድርገን ሳሩ ላይ ተንጋለን … የሳምኳት አሳሳም … ዋው ባይነጋ ብዬ ተመኝቼ ነበር …፡፡ ከንፈሯ የገብረትንሣኤን ቦክሠኛ ኬክ ይመስል ጣፋጭ ነው፤ በርከት ያሉ ከንፈሮችን ከሷ በኋላም በፊትም ስሜያለሁ … የምስራቅ ግን ጐመን በስጋ ከአይብ ጋር ነው (ኬክነቷ እንዳለ) ቴዲ አይቶኝ ቢሆን ኖሮ … እንደቴዘር ስልክ እንጨት ላይ ሰቅሎ ይጠልዘኝ ነበር፡፡ አንድ እሁድ ማታ ጥጓን አስደግፌ ፊልሜን ስሰራ … ከነ ጩኒ ቤት ዘቢባ ውኃ ደፋችብኝ … ወይ ፍንክች! የጋለን ልብ ውኃ ሊያቀዘቅዘው? ሞኟን ትፈልግ፡፡ (ሌላ ቀን ግን ዘቢባን ሰራሁላት … ሰክራ ስትመጣ ጠብቄ አታልዬ ሐይልዬ ጋር አሳደርኳት… ስጠይቀው ሲያበናት አደረ… በድርጊቴ ተደስቶ ሙሉ ቀን ስፖንሰር አደረገኝ)
እንደ ጅል ቦታዋን እያየሁ ሳቅሁ … (ከከንፈር ግን አልዘለልኩም)
***
ወጣትነት ጉብዝና ነው … የህሊናም የጡንቻም … የመብረር ጊዜዋ እንደደረሠ እርግብ ትር … ትር ያሻዋል፣ ጡንቻው እጃችን ላይ ነው … ማስተዋሉን ግን ፍለጋ ይጠይቃል፤ ያማረ ሁሉ አያምርም! ሥሜት እውነት አይደለም … ማሰብ ወደ መንገዱ ይወስዳል እንጂ ግቡ ራሱ አይሆንም፡፡ እርግጥ ግብ ያለ ውጥን ባዶ የንብ ቀፎ ነው… አውራው ከሌለ ሌሎች መች ይኖራሉ (የንቦች ባህሪ እንዲህ ነው ‘አውራ’ ይሻሉ!) ወጣት መሆንም በራሱ ስሌት ነው … አንዳች ነገር ይነዳል … ያንደረድራል … አይን ያማረውን በጉልበቱ ለልቡ ማቀበል ይፈልጋል … አይን የምላስን ያህል ያጣጥማል … ይሔ እንግዲህ ትኩስነት የሚፈጥረው ክስተት ነው፡፡
***
እቺን ይወዳል መረቁ-ወይኔ መበላት … አይኔ ተርገበገበ… በጣም ቆንጅዬ ልጅ ናት … “ዘምባባ” እድሜዋን አይደለም፤ ለምለምነቷን ነው … ወይ ግሩም! እንዲሁ ተፈጥሮ እንደምታዳላ በዚህች ጣዝማ በመሠለች ቆንጆ ማወቅ ይቻላል፣ ረጅሙ ቁመቷ ላይ ረጅሙ ቀሚሷ አብሯት የተፈጠረ ነው የሚመስለው (የቺክ ደረጃ መዳቢዎች ቢቋቋም ምናለበት … ሴቶችን እንዲሁ አይቼ መመዘን እችላለሁ) መስቀያው አይደለ የልብስ ውበቱ … ቆማ ተነስንሳለች … ወንዳታ ኢትዮጵያ… አንድዬ እንኳን እዚች አገር ላይ ፈጠረኝ (አወዳይ አወዳይ የመሠሉ ልጃገረዶች ሞልተዋል) እንደውኃ ይፈሳሉ … እኛ በምን እንፈስ…?
ቋሚ የፍቅር ጓደኛ ባይኖረኝም የአይን ርሃቤን አዱ ገነት የአራዶች እናት ሸገር ላይ እወጣለሁ … (ለመሴሠን ግን አይደለም) ሠላጣ ሠላጣ የመሠሉም … ቶሎ “ዳይጀስት” የሚሆኑ “ቺኮች” ለጉድ ሞልተዋል፤ ሳላስበው ቆምኩ… እቺ ዘምባባ የመሠለች የእንስቶች እንስት (የምድር) ልቤን ባለበት ገተረችው፡፡
“አቦ ይመችሽ … እግዜርን ቀሽት ነሽ እሺ” እንደሚጥም ፉጨት ውበቷን ነገርኳት “ቁመትሽ ሎጋ ነው የኔ አለም ሰንደቅ ያሰቅላል ሆድዬ … የተባለው ላንቺ ነው…”
የኔንም ልብ እኮ ሠቀልሽው…? ውይ ማማር! ለስላሣ ከሀር የተሠራ ውኃ ሰማያዊ ቀሚስ ለብሳለች … ከላይ እስከ ታች እንደማይዘጋ የአምልኮ በር ሁሉም ነገሯ ይታያል … ብርሃን ይመላለስባታል … የተጫማችው ስስ ሸበጥ ከማማሯ የዘለለ … ጣቶቿን ለእይታ አጋልጦታል … ውይ ውይ የእግር ጣት … ቁርጥምጥም አድርገን ሲጥ ሲጥ እንደምናደርጋት የበከል ሥጋ ለአይን ምግብ ናቸው … ሳልዳብሳቸው ይለሠልሳሉ …
(ምናለ እኔን እየተጫማች በሔደች) የተረከዟ አቀማመጥ ራሱን ችሎ ወገበ ቀጭን ሞንዳላ ዳሌ የምትጣቀስ ቆንጅዬ ልጃገረድ ይመስላል፡፡ ውይ አምላኬ ከመቼ ጀምሮ ነው ግን እንዲህ ቀሚስ በተውለበለበ ቁጥር ነፋስ ሆኜ የቀረሁት…?! ጉረኛ እኮ ነኝ … ደረቴን አየር ሞልቼ ተጠጋኋት … “ይመችሽ አቦ …” ልቤም ይመችህ …! ቆንጆ ማን ይጠላል … እቺ ዘንጣፋ ወደነ ይጌ ሠፈር ቀስ እያለች ሔደች … ተከተልኳት … “ኮሮኮንቹ እንዳያምሽ … ከስር እኔ ልሁንልሽ…?” ዝምታ ነው መልሷ … ይሔ የቀትር ጠራራ ፀሐይ ለልቤ ድፍረት እና ሙቀት ሆነኝ እንጂ ምንም ያህል አልተሠማኝም፤ (እውቀት ቢሆነኝ ምናለበት) ውበቷ ጥላ ሆኖኛል … ርችት የመሠለችን ቆንጆ ተሞዳሙጄ ካበሠልኩ፣ ልቤን በድምቀቷ ካደመቀችው ብደምቅላት ምናለበት …፤ ከኋላዋ ስከልማት ጣት የምታስቆረጥም ሥንግ ቃሪያ ነው የምትመስለው፤ በጨዋ ደንብ እንደደረሠ ጐረምሳ እያፏጨሁ እያወራሁ ሳላስጠጣ እየተከተልኳት ነው፡፡ ከበስተኋላዋ የማየው የሠርከስ ትርኢት ልቤን ውኃ እንደሸረሸረው ቀይ አፈር እያንሸራተተው ነው፡፡ ለጉድ ትወዛ.ወ..ዘ.ዋ.ለች፤ (ህዝብ ለህዝብን አስታወሠኝ) እኔም ልቤም ለጉድ ተወዛወዝንላት፡፡
***
ህሊና እየራቀን ይመስለኛል … ልባችን ወይራ መሆን ይጠበቅበታል … ስስ ከሆነ ጀንፎ ያስፈልገዋል… ለዛውም የብረት፡፡ እምንመራው እና እሚታዘዘን ሥሜት ከሌለን ፈረስን ያለ ኮርቻ ያለ ልጓም መጋለብ ነው፤ … ሁሉም ተሠጥቶናል ግን ሁሉም አይጠቅመንም፤ እንዲጠቅመን የምንፈልገውን ነገር እንጠቀምበት እንጂ አይጠቀምብን፡፡
***
ራስህን ለምን ታዘብከው አትበሉኝ እና ራሴን ታዘብኩት፤ የሔዋኖች ውበት ለሷ ብቻ የተሠጠ እስኪመስል ቀናሁባት … ጠረኗ tasty ነው… ቦታውን አስውባዋለች፤ በርሃውን ልቤን ለጊዜውም ቢሆን ድርቀቱን በአይን ልምላሜ ታድጋኛለች፣ …(አዳሜ በጥቁር መነፅር የአይኑን ማረፍያ ጋርዶ ማንም ስለማይሾፈው በልቡ … ሥንት ቦታ ይሾፍራል መሠላችሁ)
አገጮ ጠቀሠኝ … ፌስታሉን በጀርባው አንጠልጥሎ በሽራፊ ከልሞኝ በባዶ ሜዳ ምራቁን ዋጠ… በታጣ ምራቅ፤ እነዛ የሰፈራችን ቆንጆ ነን ባዮች በአይን ጠረባ ዘርጥጠዋት አለፉ … በልባቸው እኮ “ስታምር” ብለዋል … ችኮች ደማቸው እስኪረጋ በቆንጆ ችኮች ጭው ብለው ሲቀኑ አይጣል ነው፡፡ እቺ ዘንባባ ጥላ ቦታ ላይ ስትደርስ ውበቷ ጐላ … ወይኔ ሰውዬው … “የኔ እመቤት … እእ… አጠገብሽ ስደርስ ፀሐይዋ በውበትሽ ቀንታ አፍራ ነው መሠለኝ ተደበቀች፣ ጉልበትሽ ስር የተንበረከከች ነው የሚመስለው… እባክሽ ምህረት አድርጊላት…?...እ…” ዞራ ለማየት ተጠየፈችኝ “በጣም ውብ ልጅ እኮ ነሽ … ምነው አመሠግናለሁ አይባልም?” ዝምታዋ ከውበቷ ጋር አብሮ የተፈጠረ ይመስላል … “ለነገሩ ተይው … አንቺን የመሠለች የውቦች ውብ … ከማውራት በልቧ የምትመሠክረው ይጥማል፣ አይደል እንዴ የኔ አበባ…? እኮ እውነትሽን ነው… ዝምታም ለእንዳንቺ አይነቷ ቋንቋ ነው”
እንዲህ አይነት ምላስ ከየት አመጣሁ … ግራ ገባኝ … ልጅቷ ግን ልጅ ናት፡፡ “ለሆነው ላልሆነው ነገር እያወራሽ እንዲደክምሽ አልፈልግም … ልቀፍሽ እንዴ…?” በሆዷ ስትስቅ ታወቀኝ “ይገርማል ቁመናና ዛላ አሉ … ጥላ ላይ ሳይሽ ደግሞ በማታ መሬት ላይ እንደተበተኑ ከዋክብት … ታንፀባርቂያለሽ … እርግጠኛ ነኝ ስለውበትሽ ከእኔና ከእናትሽ በስተቀር ማንም አልነገረሽም፡፡ እማዬ ትሙት እናትሽ እንኳን ወለዱልኝ…”
***
ሌጣው ፈረስ የልቡ አይን እየደከመ ሽምጥ እየጋለበ ነው፤ ጥልቀት ወዳለው ገደል፡፡ ተከታዩ የሚያስከትለው ይሆነው አይሆነው ሚዛንን የመሠለ ህሊና የተነጠቀ ይመስል ለስሜት ተንበርክኳል፤ ወደፊት መመልከት የቆሙበትን መርሳት ማለት አይደለም … ተገልጦ የሚነበብ ህይወት ቋንቋውና ታሪኩ ጥዑም ነው፣ ህይወት ነጠላ ሰረዝ ናት … አካፋይ ሥትሆን … ድርብ ካደረግናት ደግሞ ህግጋቷን ትፈፅማለች፤ ተልዕኮ … የሌለው ማንነት ማህፀን ውስጥ የሞተ ሽል ነው… ያ የአባቱ ሀጢአት ርግማን የሆነበት፡፡ የእናት ሆድማ ተልዕኮው ያልተጓደለ ነው፡፡ ለራስ ጊዜ መስጠት ለህይወት መነበብ ነው፤ እምንፈሠው ከገዛ የልባችን ምንጭ ከሆነ … ለሌሎች ደራሽ ወንዝ መሆን የለብንም፡፡
***
“ባይገርምሽ ጉንጭሽ ላይ ያሉት ስርጉዶች … የእናት እቅፍ ነው የሚመስሉት … ስታወሪ እኮ ከኪስሽ ገንዘብ አልወስድብሽም … ተጫወቺ … ጭውቴሽ የውሮ እናት ቤትን እርጐ ካስናቀ እሸልምሻለሁ…እሙ… ግን … አንቺን ለመጥበስ ልደራጅ እንዴ…?”
ድምፅ ሳታወጣ ሳቀች “አዎ የኔ ማር … እንደሱ ነው… ሳቂ ሳቂ እኔ እከፍልልሻለሁ፤ በደንብ ሳቂ … አትሣቀቂ …” የማን አባቱ አኞ ነው እንደምትል ተሥፋ አደርጋለሁ፡፡
“እሙካዬ … እምትሔጂበት ድረስ እየዘፈንኩ ብሸኝሽ ቅር ይልሻል… እ…? ተወዳዳሪ ስለሌለ እሚያሸንፈኝ አይኖርም… ካንቺ በቀር … እ…የኔ ዘንባባ …? አይ ሲ… አንቺን የመሠለች እህት አለችሽ አይደል?” ወየው መዘላበድ! ወየው መቀላመድ! ድሮም ሥሜቱ የነዳው ወንድ እንዲህ ነው…! “ምነው ልቤ? ምነው ምነው … እኔ ብሸወድ አንተ ትሳሳታለህ…?! … “እ… ማለቴ…” “እ… ማለትህ!” ብትለኝኮ … ኤድያ… አጉል የቃላት ትራስ ለሴት ልጅ መሞዳሞጃ ምንም ሙድ የላቸውም፡፡ በተለይ በተለይ እቺን ለመሠለች ቆንጆ፡፡ ከላይ ካልተሠጠ ማን የራሱን አብስሎ በላ!… የእናት ጣት የፈተፈተው ፍትፍት የመሠለች ደመግቡ… “እሙካ ከየትና የት አብረን እንደመጣን አስበሻል… እየተከተልኩሽ እንደሆነ ያወቅሽ አልመሠልሽኝም … እ… እሙ… የኔ ዘንባባ… የኔ ዘንጣፋ … ኧረ ለሞራሌ እንኳ ትንፍሽ በይ…? በእናትሽ…? … ተይ ይቆጭሻል… ወይ ሳቂልኝ…? እሺ በጥፊ በይኝ እና ልመለስ…?” ዞራ አየችኝ … አይኗ ስር የተኳለችው ኩል ሥሥነቱ አዲስ የተሠራ የቀለበት መንገድ ይመስላል፤ ቆመች፡፡
ቆምኩ፡፡
የራሱ እንዲወደድለት የሚፈልግ የሌሎችን መውደድ አለበት፤ ምነው ልቤ? ፈራህ እንዴ? … ለምን አትፈራ …፤ አዳም ሞኙ እስከመቼ ነው እንዲህ ቆንጆ እየተከታተለ እንደ ውኃ የሚፈሠው … ማነው ውብ ሴት እየተከተለ ከመነሻው በቀር መድረሻው ላይ የደረሠ?!...
“የኔ ቆንጆ … ካሰብሽው ሠላም ድረሺ … የዚህን ያህል አምላኬን ቢሆን የተከተልኩት … የለመንኩት እንዲህ እንዳንቺ መልስ አይነፍገኝም ነበር…”
አስተያየቷ ቋንቋው ተደበላልቋል … አይተረጐምም … “
“እሺ ስጪኝ…?” አቋቋሟ ያምራል … እጇን ለቡጢ ጨበጠች … ኩስትርናዋ ቀለም ያልተቀባ አዲስ ቤት አይነት ነው፣ መቆጣት አትችልበትም …
“ስምሽን ነው ሌላ አይደለም” ሳቀች … ድምፅ ነበረው … ግርማ ይፍራሸዋ በጣቱ እንደሚያዋራው ፒያኖ ይርበተበታል … ሳቋ ከምታቃጥለው ፀሐይ በላይ ደማቅ ነው፡፡
“የምሬን ነው ሸልሚኝና ልመለስ?” ልመናዬ ደረቅ እንደሆነ ገባኝ … እንደ ዘመኑ ኮሜዲ ፊልም የላይ የላይ እንጂ ከልብ አይደለም፤ ግንባሯን ቅጭም አደረገች … አተኩሬ ተመለከትኳት … ገጿ ውኃ ጥም ይቆርጣል፡፡
የውኃ ድር ናት … ተበተበችኝ … በጠራራ ፀሐይ እርጥብ ፈገግታ … ለጨበጣት ሙልጭ … ለረገጣት ዘጭ …፤ ትንፋሽ ሰበሰብኩ … እግዜር ምስክሬ ነው … ሥም የወጣላት የአንድ ክፍለ ከተማ ሰዎች ተሠብሥበው ተወያይተው መሆን አለበት … ለዚህች ወለላ ሔዋን የቁንጅናም፣ የርጋታም፣ የደስደስም መገለጫ ሥም … “ቻው ውኃዬ … እኔ ፈሠሥኩ … ከቻልሽ ቅጂኝ …”
እየሳቀች … ነካችው፡፡
ነካሁት … እየተገረምኩ፡፡
***
ዐይን ውበት አይቶ ሲከተል … በቀን ይመሻል፡፡ ልብ ሚዛን ካበጀ … ቆንጆ በጠዋት አረጀ፡፡ የላይኛው ህግ ሲከበር … የስሩ ከተናቀ እንዲህ ፈሠው መቅረት አለ፡፡ ከመዝገብ መሠረዝም፡፡ አለምን ያልናቀ አለም ትንቀዋለች፤ መከተል አይደለም ትርጉሙ… የሚከተሉትን ማመን ነው … ማመን ብቻም በቂ አይደለም … የዘንባባ ዛፍ ላይ ብርቱካን አይበቅልም፡፡ የሆነው ካልሆነው እንዲሆን ማኳኋን ከንቱነት ነው!፡፡
ፀሐይዋን ማለፍ ይቻላል፡፡ እምንቀመጠው ለአይናችን ሳይሆን አይናችንን ለህሊናችን መቀመጥ አለበት … ወጣትነት ያስጨበጥነውን ይሠጠናል … አጥንታችን ሲጠነክር … ለእርጅና ዘመናችን ስንቅ ይሆናል … ለዘርና፣ ብኩንነት የምንይዘው እኛው ነን፡፡ ህግ ሁሉ ህግ አይደለም! ፍቅር ግን ህግ ይሆናል፡፡ የኦሪት ልብ አያስፈልግም፡፡

 

Read 5373 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 10:51