Saturday, 24 September 2022 17:27

መስከረም እየገፋ ሲሄድ የኢሬቻ ክብረ-በዓል ይደምቃል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  እንደ አንዳንድ በጉዳዩ ላይ ጥናት እንዳካሄዱ ፀሐፍት፤ በሚስጥራዊነታቸውና በድምቀታቸው የሚታወቁ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ክብረ-በዓላት ጥቂት ናቸው- ከነዚህ መካከል ኢሬቻ አንዱ ነው፡፡ “ኢሬቻ” በኢትዮጵያ ደጋማ ክፍሎች ዝናብ ማቆሙን የሚጠቁም የመጀመሪያው የኦሮሞ ባህላዊ ክብረ-በዓል ነው። በኦሮሞ ባህል በአንድ አምላክ ከሚያምነውና ዋቃ ከሚባለው የተፈጥሮ አምላክ ጋርም የሚዛመድ ነው የሚባለው እሬቻ፤ በየዓመቱ በመስከረም ማብቂያ አካባቢ የሚከበር ክብረ-በዓል ነው። ምንም እንኳን ይህ ክብረ በዓል በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ቢከበርም፤ በጣም በሰፊው የሚከበርበት ቦታ ደብረዘይት የሚገኘው ሆራ ሐይቅ ነው፡፡
እንደ ባህላዊ እሳቤው በኢትዮጵያ ያሉ የኦሮሞ ህዝቦች በደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ሀብታቸውን፤ ማለትም ውሃን ስለሰጣቸው፤ ለፈጣሪ ምስጋናቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡
ከግዙፉ ዋርካ ዛፍ ሥር ሣርና ለምለም ቅጠል ይነሰነሳል፤ ባህላዊው የቡና ማፍላት ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ ይህ ሥነ ስርዓት ባለ ጎፈር ጀግና የሚታይበት፤ በአርሲ ኦሮሞ በቆዳ ቀሚስ ያማሩ ቆንጆ- ቆንጆ ሴቶች ተውበው የሚደምቁበት፤ ብዙ ኦሮሞ ሴቶች አደይ አበባ ይዘው የሚገኙበት፤ የሆራ ሐይቅ አስደናቂ ትርዒት ነው፡፡ ወጣት ወንዶች ወደ ክብረ-በዓሉ መጨረሻ አካባቢ ጭፈራ ይጀምራሉ፡፡ ያ ግዙፍ ዋርካ ለዘመናት የነበረ ነው፡፡ የገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን “የዋርካው ሥር ትንግርት” (oda oak oracle) ያስታውሰናል፡፡ በመጨረሻም ብቸኛው አባ ገዳ -በገዳ ሥርዓት የተመረጡት ባህላዊ መሪ- ከነግርማ- ሞገሣቸው ይታያሉ፡፡ ይህ ፅሑፍ ሲፃፍ በኢትዮጵያ 1992 ነው፡፡ አባ- ገዳው ያኔ 90 ዓመታቸው ነበር፡፡
የኢሬቻ ባህላዊ ክብረ- በዓል ምናልባት በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በአባይ ዳርቻ ይኖሩ የነበሩ የኩሽ ህዝቦች የጀመሩት ሳይሆን አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ መንፈሱ በአንድ አምላክ ከማመንና የተፈጥሮን ቁጣ ከሚያረግበውና የተፈጥሮን ህግ ይደነግጋል በሚል ከሚታመነው ከዋቃ ጋር ተጣምሮ የተመሰረተ እምነት ነው፡፡ አማንያኑ ውለታ ይጠይቁበታል፡፡ ይሳሉበታል፡፡ ልጅ እንዲወልዱ ይለማመኑበታል፡፡ ጤናና ሀብት ይመኙበታል፡፡
በመሰረቱ፤ ሆራ ሀይቅ አካባቢ የሚከበረው ኢሬቻ በዓል፤ ከሁለት ክብረ በዓላት አንዱ ነው። የመጀመሪያው ትክክለኛ ስሙ “መልካ-ኢሬቻ” ነው፡፡ ሌላኛው ክብረ-በዓል “ጠራራ-ኢሬቻ” ሲሆን የሚከበረው በተራሮች አናት ላይ ነው፡፡
የክብረ በዓል ማዕከላቱ የተቀደሱ ዛፎች አናቶች ላይ የሰፈሩት መንፈሶች ሲሆኑ በተለይ ጥንታዊ የሆነ የጥድ ዛፍ አካባቢ፤ ቦታ ይመረጥና አማንያኑ ይሰበሰባሉ፡፡ የእንስሳት ደም በዛፎቹ ሥር ይፈስሳል፡፡
ግንዱ ቅቤ፤ሽቶ እና ካቲካላ ይቀባል፡፡ ዛፉ ሥር ምግብ ተከፋፍሎ ይበላል፡፡ ቡና፤ጠላ ይጠጣል፡፡ የተጠበሰ ሥጋ፤ አረቄና፤ የተጠበሰ በቆሎ ይታደላል፡፡
ይህ ክብረ-በዓል አብዛኛውን ጊዜ የሚከናወነው መስቀል (“የዕውነተኛው መስቀል መገኛ በዓል”) በዋለ በሚከተለው እሁድ ነው፡፡ ስለዚህም ወደ መስከረም መጨረሻ ግድም ነው ማለት ነው፡፡
ዛር- የዛር ዳንኪራ- የመንፈስ ሐሴትና ዘመናዊ ዳንስ
(በ”ሔና ሙን” የተጠና)
ስለ ዛር ብዙ ነገር ይባላል፡፡ የሚከተለው ስለ ዛር መሠረታዊ መነሻ የሚጠቀስ አንድ ንድፈ ሀሳብ ነው፡፡ የዚህን ተቃራኒ የሚጠቅሱም አሉ። ዛር አንዳንድ የዓለም ክፍሎች ዛሬም በተግባር የሚታይ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በህግ የታገዳል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሥነ- ስርዓቱ በሚሥጥር ይካሄዳል፡፡ አንድ ጊዜ በዛር ሥርዓት ውስጥ በምስክርነትም ሆነ በመካፈል ከገባችሁ ስሜታችሁ  ሊለውጥ የሚችል ጠንካራ ተሞክሮ ያጋጥማችኋል፤ ይላሉ ጠበብቱ፡፡
የእኔ ግንዛቤ ይላሉ ሔናሙን፤ ዛር እንደአንድ ራስን ለማንፃት እንደሚካሄድ መንፈሰዊ ዳንስ ቀና አመለካከት ወይም ቅዱስ ልቡና ሊቸረው ይገባል የሚል ነው፡፡ እንደተመክሮ ስናየው ደግሞ ዛር መንፈሳዊ ኃይል የሚሰጥና በስሜት  የሚንጥ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ዛር፤ በሱዳን የተጀመረና ጥንታዊ የምናባዊ -ምጥቀት ዳንስ መሆኑን ብዙ ምሁራን ይስማማሉ፡፡ ዛር፤ ከሱዳን ተነስቶ ወደ ብዙ ቦታዎች የተስፋፋ ሲሆን ጥንታዊቷ ግብፅ አንዷ ማረፊያው ናት፡፡ ከጊዜ በኋላ ዛር - አለብን የሚሉ ሰዎች የራሳቸውን ትርጓሜና ዘይቤ አክለውበታል፡፡ ይሄ የተለያየ ትርጓሜ የዛርን ምንነት አወዛጋቢ እንዳደረገውም ይገመታል፡፡
በጥንታዊቷ ሱዳን ልጃገረዶች የሚያገቡት በጣም በልጅነት ዕድሜያቸው ነበር፡፡ ከዚያም ወዳገባቸው ሰው መንደር ይወስዳሉ፡፡ አንድም በልጅነት በማግባታቸው፤ አንድም ከቀዮአቸው ርቀው ሰው መንደር በመሆናቸው፤ የመደበርና ተስፋ- የመቁረጥ የመንፈስ ስብራት ይፈጠርባቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህ እሳቤ መሰረት ወንድየው ፤መንደሩንና የሙሽራይቱን ቤተሰብ ወይም መንደራቸውን፤ ወደ “ባለዛር” እንዲመጡ ይጋብዛል፡፡
በዛሩ ሥነ ስርዓት ወቅትም፤ ልጃገረዷን እንድታዝንና እንድትታመም ያደርጋትና የያዛት “ሠይጣን” ወይም “መንፈስ” እንዲወጣላት ይደረጋል፡፡ ባለዛሩዋ እየጨፈረች ሠይጣኖቹን በማጫወትና በማባበል ልጅቷን ለቅቀው እንዲወጡና ወደ ራስዋ ሰውነት እንዲገቡ፤ ከዚያም ከባድ እስክስታ፤ መንቀጥቀጥና መንዘፍዘፍ እንዲሁም መርገፍገፍ፤ በማድረግ የገዘሳ ኃይሏን ከውስጧ በማውጣት እሷንም ለቅቀው እንዲሄዱ ታደርጋለች፡፡ ስነ ስርዓቱ እየሞቀና እየጠነከረ ሲሄድ ባለዛሩዋ (በአበሻ አባባል “አዶክበሬዋ”) ጭንቅላቷን ክፉኛ በመነቅነቅ ራሷን እስክትስት ድረስ ታሽከረክረዋለች፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሠይጣኖቹ በመጨረሻ ሙጥኝ የሚሉት ፀጉር ላይ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡
በዛር ሥርዓት ጊዜ ድቤ በቅኝት ይመታል-ብዙ ዓይነት ጭፈራና ዳንኪራ ይካሄዳል። ይህም ሥርዓትን በወጉ የተከተለና ለዛሩ ስኬትም ስፈላጊ ነው፡፡ የድቤው ምት ቀስ ብሎ የሚጀምርና የተያዘውን ሰው ስሜት በዝግታ እየተጫነና እየተዋሃደ እንዲቆጣጠር ተደርጎ ሲሆን፤ እግረ- መንገዱን መንፈሶቹን እያባበለ “ከታማሚዋ” አውጥቶ ወደ አዶ- ከበሬዋ (ባለዛሯ) ሰውነት እንዲገባ የሚያደርግ ነው፡፡ የዳንሱ ምት እየጨመረ፤ እየጋለ፤ እየናረ ሄዶ፤ የጨፋሪዋም እንቅስቃሴ ፍፁም በአስገራሚ ፍጥነት ይቀጥልና በመጨረሻ ባለውቃቢዋ ተዝለፍልፋ ትወድቃለች፡፡ ድቤዎቹና ጭፈራዎቹ እንግዲህ ለባለዛሯና ለበሽተኛዋ መጠበቂያ መከታ ናቸው፤ ማለት ነው፡፡
ቀጥሎም ምግብና መጠጥ ይታደላል። ሙሽራይቱ ደስተኛ መስላ ከታየች ዛሩ ተሳክቶለታል ማለት ነው፡፡ (ዛር በዕውነት ሠይጣንን ማባረሪያ (ማስወጫ) ነው ወይስ ሙሽራይቱ ወዳጆቿንና ቤተሰቦቿን በማየትዋ መንፈሷ ሽቅብ ከፍ ብሎና ስሜቶችዋ ያሻቸው ተሟልቶላቸው ነው?)  
በአንዳንዶች አገላለፅ ፤ ዛር በሥርዓተ - ሂደቱ ውስጥ ድቤ በመምታትና በመደነስ/ በመደንከር “የታመሙ” ሰዎች “የማዳኛ ዕምነት” ነው፡፡ ዛር የአባት- ሥርዓት ባለበት ባህል ውስጥ ሴቶች ዕውቀትን የሚጋሩበት ለጋሥ ማህበረሰብ ነው ለማለትም ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ባለዛሮች ሴቶች ናቸው፡፡ ተሳታፊዎቹም/ ታዳሚዎቹም ቢሆኑ ሴቶች ናቸው፡፡ ብዙ ፀሐፍት ያዢው መንፈስ ወንድ መሆኑንና የምትያዘው ግን ሴት መሆኗን ይጠቁማሉ፡፡
በአጠቃላይ ግን ሥርዓቱ በአባት - ሥርዓት ውስጥ ለሴቶች እፎይታን የሚሰጥ ነው እየተባለ ይነገራል፡፡
የዛር ሥርዓት በሱዳን በ1820 ተጠናክሮ የተቋቋመ ሲሆን በሸሪያ ህግ መሰረት በ1983 በህገ ወጥነት ታግዷል፡፡ ሆኖም እንቅስቃሴው ከመመንመን ይልቅ እየተባባሰ ሄዷል፡፡ ድቤዎቹም መመታታቸው ቀጥሏል፡፡
ዛር ሊወረስ ይችላል የሚሉ አሉ፡፡ ሱማሊያዊው ዲሪዬ አብዱላሂ፤ ዛር ከጥንት የአፍሪካ አማልክት መካከል ወደዚህ ዘመን የቀረ እምነት ነው- ዛር በምዕራቡ ዓለም ቩዱ (voodoo) እንደሚባለው ነው፡፡ የጥንቱ የአፍሪካ አማልክት ሁለት ነበሩ፡፡ አንዱ አዙዛር (ከኦሲሪስ ጋር የሚዛመድ ወንድ አምላክ) ናት፡፡ አውሲቱ  (በምዕራቡ አይሲስ በመባል የምትታወቀው ሴት አምላክ) ናት። ዛሬም በሶማሊያ ነብሰ-ጡሮች በሰላም እንዲገላገሉ ስለት የሚያገቡላት አምላክ ናት፡፡
እንደ ዲሪዬ አገላለፅ፤ በተለይ ዕድሜያቸው በገፉ ሴቶች የሚከበር የዳንስ ክብረበዓል ነው ይለዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በጥንቶቹ የአፍሪካ ሃይማኖቶች ውስጥ አሮጊት ሴት ቀሳውስት የነበሩበት ዘመን ፣መሆኑ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ዕምነት፤ ወጣት ሴቶች በተለይ ያላገቡ ሴቶች በዛሩ አይጎበኙም ነበር ይባላል፡፡
በዓለም ላይ በርካታ የዛር ተከታዮች ያሉት በሱዳን፤ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ነው፡፡ ከዛሬዋ  ግብጽ የጠፉት የዛር ልማዶች በነዚህ አገሮች ዛሬም አሉ፡፡ በዛሬ ዘመን ዛር ለተጨነቁ ወይም ለተረበሹ ሰዎች እንደመዝናኛና እንደመንፈሳዊ ማዳኛ የሚያገለግል ሆኗል፡፡ በተደረጉት ጥናቶች መሰረት፤ የሚሰዋው እንስሳ የዚህ ዘመናዊ ክብረ- በዓል አካል ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡

Read 1110 times