Saturday, 24 September 2022 17:15

አወዛጋቢው የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

 ሪፖርቱን ምዕራባውያንና ህወሓት ሲቀበሉት፤ ኢትዮጵያና በርካታ አገራት ተቃውመውታል
              
        የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች  መርማሪ ኮሚሽን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዙሪያ ያወጣው የምርመራ ሪፖርት እያወዛገበ ነው። መንግስት ሪፖርቱን “በምርመራ ሪፖርት ስም የቀረበ ፖለቲካዊ መግለጫ ነው” ሲል አጣጥሎታል።
የመንግስታቱ የተመድ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የመብት ጥሰት ምርመራ ሪፖርት፤ ቀደም ሲል በራሱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ የተደረገውን ምርመራ የሚቃረን ነው ብሏል።
መርማሪ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ረሃብ፣ መደፈርና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን አመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በትግራይ ተፈፀሙ ያላቸውን ግድያዎች፤ አካላዊ ጥቃቶች፤ መደፈርና ወሲባዊ ጥቃቶችን በሪፖርቱ በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ እንዲወያይበትም ጠይቋል፡፡
የኮሚሽኑን ሪፖርት “የተምታታ፤ ተጨባጭነት የሌለው፤  በመረጃ ያልተደገፈና ያልተሟላ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም” ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ሪፖርቱ ቀድሞ የታሰበውን ኢትዮጵያን የመወንጀልና ዝቅ አድርጎ የማቅረብ ፖለቲካዊ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መቀመጫ በሆነችው ጄኔቭ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዘነበ ከበደ፣ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል  ኤኤፍፒ በሰጡት ማብራሪያ ፤መርማሪ ቡድኑ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ሪፖርቱም ወገንተኛና እርስ በርሱ የሚቃረን ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡ ሪፖርቱ በህውሓት ታጣቂ ሀይሎች የተፈፀሙ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን ችላ ያለ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የሪፖርቱ ድምዳሜዎችም እርስ በርሳቸው የሚቃረኑና አድሏዊ ናቸው ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በኮሚሽኑ አጣሪ ቡድን ይፋ የተደረገው ሪፖርት የህወሃትን ሕልውና ለማራዘም ሆን ተብሎ የተፈበረከ የሃሰት ትርክት ነው የሚሉት የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር ደሳለኝ ምህረቴ በበኩላቸው፤ ሪፖርቱ ለአሸባሪ ቡድኑ አይን ያወጣ ውግንናን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስም ፖለቲካዊ አላማን ለማራመድ ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ሪፖርቱ ምዕራባውያኑ  የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈፀም የሚሄዱበትን ርቀት አመላካች ነው ሲሉ ነቅፈውታል፡፡
የህውሓት በስልጣን ላይ መቆየት የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈፀም እንደሚጠቅማቸው የተረዱት እነዚህ አገራት፤የታጣቂ ቡድኑን የስልጣን ዕድሜ ለማራዘም ያስችላሉ የሚሏቸውን ተግባራት ሁሉ ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይሉም ገልጸዋል።
ይህንኑ በአጣሪ ኮሚሽኑ የቀረበውን የሰሞኑን ሪፖርት እንደሚቀበሉ ያስታወቁት የህውሓት ታጣቂ ሃይሎች፤ አለማቀፉ ማህበረሰብ  ድርጊቱን በጋራ እንዲያወግዝና የጦር ወንጀል መፈፀሙን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡ አሁን ለኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን አስፈላጊ መረጃዎችን ለመስጠት ነባራዊ ሁኔታዎች አይፈቅዱልኝም ያለው ታጣቂ ሃይሉ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን ወደ ትግራይ ገብቶ ምርመራ ማድረግ እንዲችል ዓለማቀፉ ማህበረሰብ  በመንግስት ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳድር ጠይቀዋል፡፡
በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያቀረበ ሲሆን፤ አብዛኞቹ የአውሮፓ ህብረት አገራትና ምዕራባውያን ለሪፖርቱ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
በተቃራኒው ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኩባ፣ ቬንዝዌላና በርካታ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ አገራት ሪፖርቱን በመቃወም ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።


Read 21035 times