Saturday, 24 September 2022 16:45

አስቀድሞ መካላከል ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

የሰዎች የመራቢያ አካልን የሚያጠቁ በሽታዎች በሴቶች እና በወንዶች ላይ የሚከሰቱ ሲሆን የተለያየ መንሰኤ አላቸው።
በግብረ ስጋ ግንኙነት የመተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ የሆነ እና በግብረ ስጋ ግንኙነት የመተላለፍ እድላቸው አነስተኛ የሆነ በሽታዎች ይገኛሉ።   
ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ እንደሚናገሩት በግብረስጋ ግንኙነት የመተላለፍ እድላቸው አነስተኛ ከሆኑት በሽታዎች መካከል በሴቶች ላይ ለሚከሰቱት በሽታዎች አንደኛው መንሰኤ የሚሆነው የሴቶች ፔኤች [potential of hydrogen] ለውጥ ነው።
የሴቶች ብልት አብዝቶ በሳሙና ሲታጠብ ፔኤች ከአሲድነት ወደ ቤዚክ እንዲለወጥ [እንዲጠጋ] ያደርገዋል። ይህም በመራቢያ አካል ላይ በሽታ የሚያመጡ ተዋህሲያንን የመከላከል አቅም በመቀነስ ተዋህሲያኑ እንዲራቡ እድል ይከፍታል።
በፈንገስ አማካኝነት የሚከሰቱ የመራቢያ አካልን የሚያጠቁ በሽታዎች በሴቶች እና በወንዶች ላይ የሚከሰቱ ሲሆን በሴቶች ላይ የሚከሰተው የፈንገስ ኢንፌክሽን በአለማቀፍ ድረጃ ከ4 ሴቶች ውስጥ 3 ሴቶች በህይወት ዘመናቸው የዚህ በሽታ ተጠቂ እንደሚሆኑ ይገመታል።
በፈንገስ አማካኝነት ከሚፈጠሩት በሽታዎች መካከል ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን ከ3 እጥፍ በላይ የሚያጠቁት ቲኒያ እና ኩሪሪስ የተባሉት በሽታዎች ይገኛሉ።
እርጥበት አዘል ሙቀት በሰውነት ላይ ሲፈጠር፣ ውፍረት፣ ሰውነትን የሚያጣብቅ የውስጥ ልብስ [ሱሪ] መልበስ እና የውስጥ ልብስ በጋራ መጠቀም ለእነዚህ በሽታዎች መንስኤ ወይም የመተላለፊያ መንገድ መሆኑን የህክምና ባለሙያዋ ዶ/ር ረድኤት ተናግረዋል።
በሽንት ቤት አጠቃቀም ወቅት እና በጽዳት ጊዜ ከፊንጢጣ አከባቢ ባክቴሪያ ወደ መራቢያ አካል የሚሄድበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል።
በተጨማሪም በሽታ የመከላከል አቅምን በሚቀንሱ የስኳር እና መሰል በሽታዎች የተጠቁ ሰዎች በመራቢያ አካላት  በሽታዎች የመያዝ እድል ሊኖራቸው ይችላል።  
የመራቢያ አካላትን በሚያጠቁ በሽታዎች የተጠቃ ሰው ላይ የሚታዩ ምልክቶች
ከብልት የሚወጣ ፈሳሽ በሴቶች ላይ ከተለመደው የፈሳሽ አይነት ቀለም የተለየ፣ ሽታ እና ብዛት ያለው ሲሆን በወንዶች ላይም ፈሳሽ ያመጣል፡፡
ማሳከክ እና ማቃጠል፤
ብልት አከባቢ ህመም እና እብጠት፤
ለዚህም፡-
መቶ በመቶ ከጥጥ የተሰሩ የሆኑ የውስጥ ልብሶችን [cotton] መጠቀም፣
ሰውነትን የሚያጣብቁ የውስጥ ልብሶችን አለመጠቀም፣
ሰውነትን ከታጠቡ ወይም ከውሀ ዋና አሊያም ከማንኛውም እስፖርታዊ እንቅስቃሴ በኋላ እርጥበት እና ሙቀት እናዳይፈጠር በደንብ ማድረቅ፣
ንጽህና መጠበቅ፣ በሳሙና ደጋግሞ አለመታጠብ፣
በሽንት ቤት አጠቃቀም ወቅት ከብልት ወደ ፊንጢጣ[ከፊት ወደ ኋላ] እንጂ ከፊንጢጣ ወደ ብልት[ከኋላ ወደ ፊት] ማጽዳት እንደማይገባ ይመከራል። እነዚህ መከላከያ መንገዶች በግብረ ስጋ ግንኙነት የመተላለፍ እድለቸው አነስተኛ ለሆኑ በሽታዎች የሚያገለግል ነው።
በግብረ ስጋ ግንኙነት የመተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑት የአባላዘር በሽታዎች መንስኤ እና መከላከያ መንገዳቸው ከመተላለፍ እድላቸው አነስተኛ ከሆኑት ጋር የተለያየ ነው። ነገር ግን ተቀራራቢ ወይም ተመሳስይ ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ። ከአባላዘር በሽታዎች መካከል
ቂጥኝ [Gonorrhoea] ሽንት ሲሸና ማቃጠል፣ ከብልት የሚወጣ መግል ወይም ፈሳሽ፣ የማህጸን በር ላይ የማቃጠል ስሜት ይኖረዋል፡፡
ጨብጥ [Syphilis] ብልት አከባቢ ህመም፣ ውሀ የቋጠረ እብጠት እና ማሳከክ፤
ባምቡሌ [Inguinal bubo] ብልት አከባቢ ህመም እና እብጠት፤
ከርክር [Chanchroid] የሽንት ቧንቧ እና የማህጸን በር የመመርቀዝ አይነት ምልክት ያሳያል፡፡
ኤች አይ ቪ ኤድስ እና ኪንታሮት እና ሌሎችም፤
በተጨምሪም ቀስለት፣ የብልት ፈሳሽ ቀለም መቀየር እና ሽታ፣ ንፍፊት እና የዳሌ ህመም የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ሲሆኑ በብልት ላይ ብቻ ሳይሆን በፊንጢጣ አከባቢ ሊስተዋሉ ይችላሉ።
ማንኛውም ልቅ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርግ ሰው በአባላዘር በሽታ ተጠቂ የመሆን እድል አለው። በስኳር እና መሰል በሽታ ተጠቂ የሆኑ እንዲሁም የኤች አይ ቪ ኤድስ የተጠቁ ሰዎች በበሽታው የመያዝ እድል አላቸው፡፡  
“በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ አንድ ጊዜ በሚፈፀም የግብረ ስጋ ግንኙነት የአባላዘር በሽታ አይተላለፍም” የሚል እሳቤ መኖሩን ዶ/ር ረድኤት የተናገሩ ሲሆን ይህም የተሳሳተ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።   የህክምና ባለሙያዋ እንደሚናገሩት የአባላዘር በሽታ አንድ ጊዜ በሚፈፀም የግብረ ስጋ ግንኙነት ሊተላለፍ ይችላል። እንዲሁም በመራቢያ አካል ከሚደረግ የግብረስጋ ግንኙንት በተጨማሪ በሌሎች የሰውነት ክፍሎች አማካኝነት የሚፈፀም የግብረ ስጋ ግንኙነት በሽታውን ሊያስተላልፍ የሚችል ሲሆን ከአባላዘር በሽታ ውስጥ የሚመደበው የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ደግሞ በመሳሳም ጭምር የመተላለፍ እድል አለው።
የአለም የጤና ድርጅት እኤአ በ2022 ባወጣው መረጃ መሰረት በአለማቀፍ ደረጃ በአንድ አመት ውስጥ 374/ሚሊዮን ሰዎች የአባላዘር በሽታ ተጠቂ እንደሚሆኑ የሚገመት ሲሆን ይህም ማለት በ1 ቀን ውስጥ 1ሚሊዮን ሰዎች የበሽታው ተጠቂ ይሆናሉ ማለት ነው።
ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ከ1 ጊዜ በላይ የአባላዘር በሽታዎች ሊጠቁ ይችላሉ። እንዲሁም ለበሽታው ህክምና ያገኘ ሰው ጥንቃቄ ካላደረገ በተመሳሳይ የአባላዘር በሽታ ሊጠቃ ይችላል። ስለሆነም በበሽታው ዳግም ተጠቂ ላለመሆን ጥንዶች በጋራ እንዲታከሙ የህክምና ባላሙያዋ ይመክራሉ።
የመራቢያ አካል ላይ የሚከሰት የማሳከክ፣ የማቃጠል እና የቁስለትን ስሜት ይቀንሳል ተብለው የሚታሰቡትን እንደ ሎሚ፣ ሙቅ ውሀ በጨው እና መሰል ግብአቶችን መጠቀም ይመከራል።
የአለም የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው የአባላዘር በሽታ ልጅ ያለመውለድ ችግር (መሀንነት)፣ ካንሰር፣ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች እንዲሁም ለኤችአይቪ ሊያጋልጥ ይችላል።
ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ በአጠቅላይ የመራቢያ አካልን የሚያጠቁ በሽታዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት በዝርዝር ያስቀመጡ ሲሆን እነዚም;
በእርግዝና ወቅት ምጥን ማፋጠን፣
ኤች አይ ቪ ኤድስን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ሊድኑ የማይችሉ የአባላዘር በሽታዎች መኖራ ቸውን የህክምና ባለሙያዋ የጠቀሱ ሲሆን አስቀድሞ መካላከል ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብዋል የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል።  
አስቀድሞ መከላከል ተብለው የሚጠቀሱት የ’መ’ ህጎች የሚባሉት መታቀብ፣ መወሰን እና ኮንዶም መጠቀም ናቸው።
በመራቢያ አካል ላይ የሚከሰት በሽታ ጉዳቱ እየከፋ የመሄድ አጋጣሚ እንደሚኖረው በመግለጽ ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ መልእ ክታቸውን አስተላልፈዋል።

Read 11522 times