Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 October 2012 10:14

የታዳጊዋን ሕይወት ለቀጠፈው የውሃ ችግር የተሰጠ ምላሽ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ስስታችን ለምግብ ሳይሆን ለውሃ ነበር”
ድሮ ከቤት እሳት ተይዞ ወደ ጫካ የሚኬደው ለማር ቆረጣ ነበር፡፡ ብርድ ልብስ ተይዞ የሚኬደው ደግሞ ራቅ ወዳለ አገር ለጉዳይ ሲኬድ ነበር፡፡ የፎፋ ከተማና አካባቢዋ ሴቶች ግን ብርድ ልብስ እሳት ለማገዶ የሚሆን ጉቶ ወይም እንጨት ይዘው ወደ ወንዝ ወይም ኩሬ የሚሄዱት ውሃ ለመቅዳት ነበር፡፡ “ውሃ ለመቅዳት የሚያስፈልገው ማሰሮ ወይም ጀሪካንና ባሊ እንጂ ብርድ ልብስና እሳት ምን ያደርጋል?” ይሉ ይሆናል፡፡ ንባብዎን ይቀጥሉና ምክንያቱን ይረዳሉ፡፡
በፎፋ ከተማና አካባቢዋ የሚኖሩ እናቶች፣ ልጃገረዶችና ልጆች ትናንት ብርድ ልብስና እሳት ይዘው ወንዝ የሚወርዱት በአካባቢው ከፍተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ስለነበር ነው፡፡ የየመንደሩ ሴቶች ተቀጣጥረውና ተጠራርተው ያላቸውን የውሃ መቅጃ ሸክፈው፣ ከሌሊቱ 7 ወይም 8 ሰዓት ላይ ውሃ ፍለጋ ወደ ወንዝ ወይም ወደ ኩሬ ይሄዳሉ፡፡

ውሃው ቦታ ሲደርሱ ቀደም ብለው የደረሱ ሴቶች ውሃውን ጨርሰው ከሆነ ዘግይተው የደረሱት ቀጂዎች ጥለው አይመለሱም፤ እዚያው ቆይተው ይጠባበቃሉ - የውሃውን መጠራቀም፡፡
ለምን መሰላችሁ እዚያው የሚቆዩት? በቤታቸው ጠብታ ውሃ ስለሌለ ነው፡፡ መቅጃዎቻቸውን አሰልፈው ተራ በማስያዝ እዚያው አድረው ውሃው እስኪጠራቀም ይጠብቃሉ፡፡ አንዲት ሴት ተራዋ ደርሶ ውሃ ቀድታ ለመመለስ 24 ሰዓት ልትቆይ ትችላለች ይላሉ ያነጋገርናቸው ሴቶች፡፡
አሁን የብርድልብስና የእሳቱ ጥቅም ምን እንደሆነ የታያችሁ ይመስለኛል፡፡ ብርድ ልብሱን፣ ለብሰው እሳቱን አንድደው እየሞቁ፣ የሌሊቱንና የጧቱን ብርድ ይከላከሉበታል፡፡ ኧረ ከዚህም የባሰ ችግር አለ፡፡ ባለትዳር ሴቶችና ልጃገረዶች እዚያ ረዥም ጊዜ ሲቆዩ ይደፈራሉ፡፡ የተደፈሩ ልጃገረዶች ሊያረግዙ ይችላሉ፡፡ በዚህ የተነሳም ትምህርታቸውን አቋርጠው ያልተፈለገ ጋብቻ ሊፈፅሙ ወይም አገር ጥለው ሊጠፉ ይችላሉ፡፡
ኧረ ከዚህም በላይ የከፋ ጉዳት አለ - ሕይወት ማጣት፡፡ ከፎፋ ከተማ ትንሽ ራቅ ብሎ መለካ የሚባል ቀበሌ አለ፡፡ ከዚያ ቀበሌ በግምት 10 ዓመት የሚሆናት ታዳጊ ውሃ ልትቀዳ ሄዳ ኩሬ ውስጥ ገብታ ሕይወቷ አልፏል፡፡ በስፍራው የነበሩ ሴቶች የድረሱልን ጩኸት አሰምተውና ወንዶች ደርሰው ልጅቱን ቢያወጡም ሕይወቷን ግን ማትረፍ እንዳልቻሉ ወ/ሮ መነን ኃ/ሚካኤል ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ግን በአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ የልማት ፕሮግራም ያ ችግር ታሪክ ሆኖ መቅረቱን የፎፋ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪ ሴቶች በደስታና በምስጋና ይናገራሉ፡፡
ለመሆኑ ፎፋ ማናት? ሳይሉ እንዳልቀሩ እገምታለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ ወደ ጅማ በሚወስደው መንገድ እየተጓዙ ነው እንበል፡፡ የግቤን በረሃ አቋርጠው ድልድዩን ተሻግረው ለጉምሩክ ፍተሻ ወርደው፣ ሻይ ቡና እየጠጡ ወይም ውሃ፣ ሎሚ፣ ብርቱካን፣ … ከገዙ በኋላ (ከፈለጉ ማለቴ ነው ግዴታ ግን አይደለም) ወደ መኪናዎ ገብተው የዳገታማውንና ጠመዝማዛውን መንገድ ጉዞ ይቀጥላሉ፡፡
ከአዲስ አበባ 132 ኪ.ሜ እንደተጓዙ አዲሷ የየም ልዩ ወረዳ ዋና ከተማን ሳጃ ያገኛሉ፡፡ ከዚያም በስተግራ ታጥፈው በስተምሥራቅ 27 ኪ.ሜ እንደተጓዙ የየም ልዩ ወረዳ ዋና ከተማ የነበረችውን ፎፋ ከተማ ያገኛሉ፡፡ የዚህች ከተማ ነዋሪዎች ናቸው እንግዲህ ጭቃና ጐርፍ አጥልሰው ከመጠጣት ወጥተው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ስላገኙ ደስታቸውን በእልልታና በጭፈራ የገለጹት፡፡
“አንድ ሴት ውሃ ልትቀዳ ስትሄድ ውሃውን አጥታ ስትጠብቅ ብዙ ሰዓት ልትቆይ ትችላለች፡፡ ያኔ የቤት ሥራ ይጓደላል፡፡ ልጆች ሊራቡ፣ ከብቶች ላይታለቡና ወደ ውጭ ላይወጡ፣ ምግብ ላይዘጋጅ፣ … ይችላል፡፡ ባሎች ደግሞ የውሃ ችግር እንዳለ ቢያውቁም ሴቷን አይረዷትም ወይም አያግዟትም፡፡ በዚህ የተነሳ በአካባቢያችን ብዙውን ጊዜ የባልና ሚስት ጥል በውሃ የተነሳ ነው” ያሉት የአራት ልጆች እናትና የፎፋ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ፀሐይነሽ ወልዴ ናቸው፡፡
“ወደ ወንዝ ስሄድ 2 ሰዓት ሊወስድብኝ ይችላል፡፡ ቀድቼ ስመለስ ደግሞ ውሃ ተሸክሜ ስለሆነ 3 ሰዓት ልጓዝ እችላለሁ፡፡ ሦስትና አራት ጀሪካን ይዤ ስለምሄድ ውሃውን ወደ ቤት ሳመላልስ 5 ሰዓት ሊወስድብኝ ይችላል፡፡ ቀድሞ የደረሰ ነው ውሃ የሚያገኘው፡፡ ውሃው ካለቀ እዚያው አድረን ከቤት በወጣን 24 ሰዓት ልንመለስ እንችላለን፡፡ ካለፈው ግንቦት ወር አንስቶ ግን ከዚህ የውሃ ችግር ነፃ ወጥተናል - ዕድሜ ለአክሽን ኤይድ፡፡ አሁን ሁለቱ ጉድጓዶች አንድ ላይ ሲሆኑ ውሃ በቧንቧ ቤታችን ድረስ እናስገባለን የሚል ተስፋ ነው ያለን” በማለት የነበረባቸውን ችግርና ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
“አሁን እኛ መቅዳት ካቃተን ነው እንጂ ንፁህ ውሃ በቧንቧ ሰፈራችን ድረስ ቀርቦልናል” ያሉት የስድስት ልጆች እናት ወ/ሮ ወይንሸት ዓለማየሁ ናቸው፡፡ “እኛ ውሃ የምንቀዳው ከሀንጐሎ ወንዝ ነበር፡፡ ስስታችን ለምግብ ሳይሆን ለውሃ ነበር፡፡ አንድ ብርጭቆ ውሃ ሁለትና ሦስት ልጆች እንዲጠጡ ነበር የምናደርገው፡፡ ፊትና ልብሳችንን እንኳ አፅድተን አናጥብም፡፡ ቀድሞ የደረሰ ነው ውሃ የሚያገኘው፡፡ ዘግይተን ከደረስን ከድፍድፍ ጭቃና ከረግረግ ውስጥ ትንሽ ውሃ ብቅ ሲል በሲኒ እየቀዳን ነው ዕቃችንን የምንሞላው፡፡ ያንን ቆሻሻ ውሃ ቤት ወስደን እንዲጠል እናደርጋለን፡፡ ልጆች ያንን ውሃ ሲጠጡ ይታመማሉ፡፡ ሐኪም ቤት ስንወስዳቸው ጃርዲያ ነው ይሉናል፡፡
“በዚህ ላይ ውሃ ለመቅዳት ወንዝ ስትወርድ መከባበር የለም፡፡ ወጣቶቹ እኛን አሮጊቶቹን ያቀሉናል፣ ያዋርዱናል፡፡ ድብድብ አለ፡፡ ያንን ጠልተን ወንዝ አንሄድም ካልን፣ ግማሹ ጭቃ የሆነውን ድፍርስና ቆሻሻ ውሃ 20 ሊትር የሚይዘውን አንድ ጀሪካን በ3 ብር እንገዛለን፡፡ አሁን ያ ሁሉ ችግር ተወግዶ ንፁህ ውሃ ስላገኘን እኔ በጣም ነው ደስ ያለኝ” በማለት ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ አስቴር ማሞ የሁለት ልጆች እናት ናቸው፡፡ አንድ ሌሊት ያጋጠማቸው ነገር እንደማይረሳቸው ይናገራሉ፡፡ “ጨረቃ ነበረች፡፡ 8 ሰዓት ላይ ተነስቼ ልጄን ይዤ ወንዝ ወረድኩ፡፡ ውሃውን ከቀዳሁ በኋላ የነጋ መስሎኝ ልጄን እዚያው ትቼ አንዱን ጀሪካን ቤት ለማድረስ ሄጄ ሰዓት ስጠይቅ ለዘጠኝ ሰዓት ሃያ ጉዳይ ነው ተባልኩ፡፡ “ይኼኔ ልጄን ጅብ በልቷታል” በማለት እያለቀስኩና እየጮህኩ ወደ ወንዙ ሮጥኩ፡፡ እዚያ ስደርስ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በሰላም አገኘኋት፡፡
“በሌላ ጊዜ ደግሞ የ14 ዓመት ልጄ ውሃ ልትቀዳ ወንዝ ወርዳ፣ በወረፋ የተነሳ ከሌሎች ልጆች ጋር ተጣልታ ስትደባደብ የአንገት መስቀሏን በጠሱባት፡፡ የውሃን ችግር ሳስብ እነዚህ ነገሮች ትዝ ይሉኛል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አምና ልጃቸውን ሲድሩ የነበረውን የውሃ ችግር የገለጹት ደግሞ የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ቦጋለች ሸንኮሬ ናቸው፡፡ “ባለፈው ዓመት ልጄን ስድር ከፍተኛ ችግር የሆነብን ውሃ ነበር፡፡ ዘመድና ጐረቤቱ ሁሉ በጣም ተጨንቀው ነበር፡፡ ባለቤቴን “አዲሱ፣ ውሃ ከየት አምጥተህ ለመዳር ነው የምታስበው?” በማለት ስጋታቸውን ይገልጹ ነበር፡፡ ከዚያም ቦሪ ከሚባል አካባቢ የአራት ሰዓት መንገድ ተጉዘን በአራት አህዮች ውሃ አመላልሰን፣ ከጐረቤት በርሜል ተውሰን በዚያ እየተሞላ ነው የተደገሰው፡፡ የነበረብን የውሃ ችግር በጣም አስከፊ ነበር፡፡ አሁን ግን አክሽን ኤይድ ችግራችንን አይቶ ንፁህ ውሃ ስላስገባልን በጣም እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡
ብዙ ሕፃናት፣ ልጆችና አዋቂዎች በውሃ ወለድ በሽታ ይታማመሉ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሲታመም የገቢ ማግኛ ሥራ ይስተጓጐላል፤ ገቢ ይቀንሳል፣ ወጪ ይጨምራል፣ የቤተሰብ ሕይወት ይናጋል፡፡ ይህን የተገነዘበውና በየም ልዩ ወረዳ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እያካሄደ ያለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ የም የልማት ፕሮግራም፤ የፎፋ ከተማ ነዋሪዎች ያለባቸውን ከፍተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ምን ማድረግ እንዳለበት ያጠና ጀመር፡፡
ድርጅቱ የፎፋን ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና፣ የሳኒቴንሽና የሃይጅን ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው በ2003 ቢሆንም የፕሮጀክት ጥንስሱ የተጀመረው ከሰባት ዓመት በፊት አክሽን ኤይድ በየም ልዩ ወረዳ ልማታዊ እንቅስቃሴ በጀመረበት በ1996 እንደነበር የድርጅቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የተለያዩ የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎች ቢታቀዱም የተለያዩ እክሎች እየገጠሙት ሊሳካ አልቻለም፡፡ የአክሽን ኤይድ ሁለተኛው የሦስት ዓመት ፕሮግራሙን ሊያጠናቅቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ስለደረሰ፤ ፕሮጀክቱን በእንጥልጥል መተው አልፈለገም፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ ከሀገራዊ ፕሮግራም፣ ከሌሎች የልማት አካባቢዎችና የልማት ሥራዎች ዓመታዊ በጀት በመቀነስ 8.3 ሚሊዮን ብር መድቦ የፎፋ ንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የጤና፣ የሳኒቴሽንና ሃይጅን ፕሮጀክት እንዲጀመር ማድረጉን ገልጿል፡፡
በዚሁ መሠረት፣ ከየም ልዩ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት፣ ከደቡብ ክልል የውሃ ሥራዎች ቢሮና የውሃ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ፣ ከፎፋ ሴቶች ውሃ ልማት ማኅበር፣ ከልዩ ወረዳው ፋይናንስ ኢኮኖሚ ጽ/ቤት፣ ከወገሬት ኮንስትራክሽንና ከልዩ ወረዳው ዋሽ ኮሚቴ ጋር በመነጋገርና በመተባበር ፕሮጀክቱ እንዲጀመር አድርጓል፡፡
የመጠጥ ውሃው ሥራ ተጀምሮ፣ ሁለት ጥልቅ ጉድጓዶች (አንዱ በክልሉ መንግሥት) ተቆፈሩ፣ ለሁለቱም ጉድጓዶች ፓምፕና ጀነሬተር፣ 13 ኪ.ሜ የቧንቧ መስመር ዝርጋታ፣ ከሁለቱ ጉድጓዶች ወደ ታንከር የሚወስድ ዋና የቧንቧ ማስተላለፊያ 50ሺህ ክቶቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ታንከር፣ ሁለት የጀነሬተርና የጥበቃ ቤቶች ግንባታ ተከናውኗል፡፡
በጤና፣ ሳኒቴሽንና ሃይጅን በኩል ደግሞ ሦስት ደረቅ የሕዝብ ሽንት ቤት፣ ሦስት የልብስ ማጠቢያ ገንዳ፣ ፎሴት የተገጠመላቸው 354 የእጅ መታጠቢያ ጀሪካን ግዥ፣ 550 የሽንት ቤት ጉድጓድ ልባስ (ስላቭ) ተሠርቷል፡፡
በውሃ እጦት ችግር የሚሰቃየው መላው ኅብረተሰብ ቢሆንም ከወንዝ በመቅዳትም ሆነ በቤት ውስጥ ሥራ በውሃ ችግር በይበልጥ የሚሰቃዩት ሴቶችና ሕፃናት ልጆች ናቸው፡፡ ስለዚህ አክሽን ኤይድ የም የልማት ፕሮግራም፤ ከልዩ ወረዳው ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የመጠጥ ውሃው ፕሮጀክት ሥራ ሲጀመር የውሃውን ተቋም የሚያስተዳድር የፎፋ ሴቶች ውሃ ልማት ማኅበር ከማቋቋሙም በላይ እንዲጠናከር የተለያዩ ድጋፎች አድርጓል፡፡ በሂሳብ አያያዝና አመራር፣ በአካባቢና በግል ንፅህና አጠባበቅና ክብካቤ ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ለፎፋ ከተማ ሴቶች ውሃ ልማት ማኅበር ከወረዳው የተሰጠው አራት ክፍል ጽ/ቤት፣ መቀመጫም ሆነ የቢሮ ቁሳቁስ እንደሌለው የጠቀሱት የወረዳው ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ሰርባ አክሽን ኤይድ ጽ/ቤቱን በቁሳቁስ በማደራጀት፣ ኮምፒዩተር ከነሙሉ አክሰሰሪው፣ ትልቅና ትንሽ መደርደሪያዎች፣ የኃላፊና የባለ ጉዳይ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ካዝና፣ ሞተር ሳይክል መግዛቱን፣ የተለያዩ የገቢ፣ የወጪ፣ የንብረትና የገንዘብ ሰነዶች ማሳተሙን፣ የውሃ ማኅበሩን የአመራሮች ቲተር (ማኅተም) አስቀርፆ መስጠቱን፣ የውሃ ተቋሙን አቅም ለመገንባት ለስድስት በርሜል ነዳጅ መግዣ ገንዘብ ሰጥቶና ግዥው ተፈፅሞ እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ አስቴር 13 የውሃ መሸጫ ኪዮስኮች መገንባታቸውንና ዘጠኝ ነባር የውሃ ቦኖዎች ከአዲሱ መስመር ጋር መገናኘታቸውን ጠቁመው፤ አክሽን ኤይድ የሴቶች የውሃ ልማት ማኅበር ከወረዳው ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ጋር በመሆን ለዋሽ ኮሚቴ አቅርቦ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ ማድረጉን እንዲሁም ቀደም ሲል የተቋቋመው የሳጃ ከተማ ሴቶች የውሃ ማኅበርን ጨምሮ በውሃ አስተዳደር፤ በጤና አጠባበቅ፣ በሂሳብ አያያዝና አመዘጋገብ፣ በአመራር ዙሪያ ከተለየዩ ሴክተር መ/ቤቶች ባለሙያዎችን በመጋበዝ ከ7-10 ቀናት ለሦስት ዙር ለ72 ሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
የፎፋ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ለብዙ ዘመናት የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ተንሰራፍቶባቸው ቆይቷል፡፡ በዚህ ችግር የቅድሚያ ተጠቂዎች ሴቶች ናቸው፡፡ ውሃ ለማግኘት ረዥም ርቀት ከመሄዳቸውም በላይ ምንጭ ዳር የሚያድሩባቸውም ጊዜያት በርካታ ነበሩ፡፡ አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ከወረዳው ዋሽ ኮሚቴ ጋር በመሆን ግንባር ቀደም የውሃ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑትን ሴቶች በማኅበር አደራጅቶ፣ የከተማዋን የመጠጥ ውሃ ተቋም በኃላፊነት እንዲመሩ በማድረጉ በጣም እናመሰግነዋለን ያሉት ደግሞ የፎፋ ከተማ ሴቶች ውሃ ልማት ማኅበር ሰብሳቢ ወ/ሮ ውቢት አየለ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ውቢት አክሽን ኤይድ ከወረዳው ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ጋር መተባበር ለዘመናት ሲቸገሩበት የነበረውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ 500 ሜትር ባልሞላ ርቀት ውስጥ እንደልብ እንዲያገኙና የበርካታ ጥቅሞች ባለቤት እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ ወንዶች ለዘመናት ይዘውት የቆዩትን የተዛባ አመለካከት እንዲቀረፍ በማድረግ፣ ሴቶች የመምራትና የማስተዳደር አቅም እንዳላቸው በእኛ በማኅበሩ አባላት እንዲረጋገጥ በማድረጉ፣ በማኅበሩ ስም ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል፡፡ አክሽን ኤይድ የም የልማት ፕሮግራም፤ በልዩ ወረዳው መንቀሳቀስ ከጀመረበት ከ1996 አንስቶ 44 አነስተኛ ምንጮች ከማጐልበቱም በላይ፣ ከእያንዳንዱ የውሃ ተቋም አምስት አምስት የውሃ ተንከባኪና አስተዳዳሪ ኮሚቴ አባላት በውሃ ንፅህና አያያዝና መጠነኛ ብልሽት ሲያጋጥም ጥገና ማድረግ የሚያስችል ሥልጠና ለ220 ሰዎች መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የሳጃ ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሟላት የውስጥ የውሃ ማስተላለፊያ መስፈሮችን፣ ሰባት የውሃ መሸጫ ኪዮስኮች ግንባታ፣ ለኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ዝርጋታ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡ እንዲሁም የሳጃ ከተማ የውሃ ማኅበር ጽ/ቤት እንዲኖረው፣ ጽ/ቤቱ በውስጥ ቁሳቁስ እንዲሟላና የሂሳብ ሠራተኛ እንድትቀጠር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሥራ የልማት ፕሮግራሙ ዋነኛ አጋር ለሆነው ለየም ልዩ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ሁለት ሞተር ሳይክሎች፣ ኮምፒዩተር ከአነክሰሰሪው፣ ጂ ፒ ኤስና ሌሎች የጥገና መሳሪያዎችን መስጠቱ ታውቋል፡፡
አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ የም የልማት ፕሮግራም በወረዳው በቆየባቸው ጊዜያት የምግብ ዋስትናና በአደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ፣ በትምህርት፣ በመሠረታዊ ጤና ክብካቤና ኤችአይቪ ኤድስን መቆጣጠርና መከላከል፣ የሴቶች ልማት በተሰኙ አራት ዋና ዋና ዘርፎች የልማት ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱና ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ታውቋል፡፡

Read 6448 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 10:35