Saturday, 17 September 2022 13:19

ቀስ በቀስ ዕንቁላል በእግሩ ይሄዳል!

Written by 
Rate this item
(3 votes)


       ከዕለታት አንድ ቀን፣ ለንግድ ስራ ወደ ሌላ አገር ሄዶ ከርሞ ወደ ቤቱ የተመለሰ አንድ ነጋዴ በራፉ ጋ ሲደርስ የጎረቤቶቹን ሰዎች ያገኛል፡፡
የመጀመሪያውን ጎረቤት፤
“ለመሆኑ ሰፈር ደህና ነው ወይ ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ጎረቤትየውም፤
“ወዳጄ፤አንተ ከአገር ከወጣህ እኮ ከዓመት በላይ አልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ፤ብዙ ልጅ ተወልዷል፡፡ ብዙ አዋቂ ሞቷል” ይለዋል፡፡
ነጋዴውም፤
 “እንዲያው ለነገሩ እህልስ እንዴት ነው? መሬቱ እንደልብ ይሰጣል?” ሲል፤ሁለተኛውን ጎረቤት ይጠይቀዋል፡፡
ሁለተኛው ጎረቤትም፤
“ምንም አይልም፡፡ መሬት እኮ በጊዜ ከመነጠሩት፤ ካለሰለሱት፤ በሰዓቱ ካረሱትና ከዘሩት መስጠቱ አይቀርም፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት ድርቅም ስላልነበረ፤ እህሉ መልካም ነበረ፡፡”
ነጋዴው ወደ ሶስተኛው ጎረቤቱ ሄዶ፤
 “ወዳጄ ወደ ቤቴ ከመጣሁ ቆይቻለሁ፡፡ እንደው ባለቤቴ ደህና ናት?” አለና ጠየቀው፡፡
ጎረቤትየውም ፤
“እሷስ ደህና ናት ፤ ሌላ ነገር አላውቅም ” ይለዋል፡፡
ነጋዴው የሚስቱ ደህና መሆን እያስደሰተው፤ እሱ ወደ ሩቅ አገር ሊሄድ ሲነሳ ነብሰ-ጡር እንደነበረች ያውቃልና፣ ማናቸውም ጎረቤቶቹ ስለ ልጁ ስላላነሱ ውስጡን ጭንቅ ብሎታል፡፡ ሰውን መጠየቁንም ፈራው፡፡
በመጨረሻ ግን  ቤቱ ገብቶ ሁሉንም አረጋግጦ ቢወጣለት ይሻላልና ወደ ቤቱ ገባ፡፡
ሚስቱ፤ ባላሰበችው ሰዓት በመምጣቱ እጅግ ተደስታ እልልታዋን አቀለጠችው፡፡                   ትልቅ ፌሽታ ሆነ፡፡ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ ተበላ! ተጠጣ!
ለመተከዣ የሚሆን መጠጣቸውን በጅ በጃቸው እንደያዙ ፤የማይቀረውን ጥያቄ ጠየቀ- ሚስቱን፡፡
“ለመሆኑ ነብሰ-ጡር አልነበርሽ? ልጁስ እንዴት ሆነ?”
ሚስቲቱም፤
“ልጁማ ታሞ ፤ብዙ ተሰቃይቶ ፤ህይወቱ አለፈ!” አለችው ፡፡
ባል፤
“ምኑን ነበር ያመመው?”
ሚስት፤
“እንደው እንደ ትኩሳት አድርጎ ጀመረውና ፤እየቆየ ብሶበት ለሞት አበቃው”
ባል ጥቂት ተከዝ ብሎ፤
“ለመሆኑ ስሙን ማን ብለሽ አወጣሽለት?”
ሚስት፤
“ሰባጋዲስ ነበር ያልኩት፡፡ በጀግንነት እንዲያድግ ብዬ ነው!”
ባል ፤
“ተይው ተይው አሁን በምን እንደሞተ ገባኝ”
ሚስት፤
 “በምን ሞተ ልትል ነው?”
ባል ፤
 “ስሙ ከብዶት ነው የሞተው!” አላት ይባላል፡፡
***
በሀገራችን ስም ስናወጣ እጅ ከበድ ከበድ ያሉ ስሞችን ማውጣት የተለመደ ነው፡፡ ጀግንነትን የሚያመላክቱ፤ ቅዱስነትን የሚሰብኩ፤ ምሁርነትን የሚያስመኙ፤ ጥበበኛነትን የሚጠቁሙ ድንቅ ድንቅ ስሞች አሉ፡፡ ሁሉም ለልጁ መልካሙን ሁሉ ለመመኘትና ለትውልድ የሚቆይ ሰብዕናን ለማጎናፀፍ ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ ምኞት አይከለከልም፡፡ ለልጅ ደግ ማሰብ የወላጅ ዋነኛ ስሜት ነው፡፡ ከፍ ያለ ቦታ እንዲደርስ ከመመኘት የመነጨ ነው፡፡ አንዳንዱ ቀጥተኛ የዓረፍተ ነገር ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ አንዳንዱ ረቂቅ ቅኔያዊ ፍቺን የሚያገናዝብ ነው፡፡ አንዳንዱ እንዲያው ውበትንና “ከሌላው ስም የበለጠ ነው የኔ ልጅ ስም ” ለማለት የወጣ ነው ፡፡
ከላይ የጠቀስነው ባህላዊ ስም አወጣጥ በሂደት ከሰው አልፎ ለኳስ ቡድን ፤ ለማህበር፤ ለድርጅትና ለፓርቲም ይሰጥ ጀመር፡፡ በዚህ መልኩ ረዣዥምና ሐረግ የመሰሉ ስሞች ይወጣሉ፡፡ ትርጉማቸው ውስብስብ የሆኑም አሉባቸው ፡፡
አንዳንዶቹ ሥልጣንን ለማሳየት ነው የሚረዝሙት፡፡ የድርጅት መሪነት፤የፓርቲ መሪነት፤ የሪፐብሊክ መሪነትና ፕሬዚዳንትነት አንድ ላይ ለአንድ ሰው ሲሰጡ “ስሙ ከብዶት ሞተ!” ያሰኛሉ!  
ችግር የሚመጣው ፤ምንም “ስምን መልዓክ ያወጣዋል” ብንል፤ ተግባሩ ግን ከራሳችን የሚመጣ ሲሆን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስናጤነው ብዙ ቦግ ቦግ ያሉ ስሞች፤ የስማቸውን ያህል ተግባር ተጎናፅፈው አናይም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ተቃራኒው ሆኖ ይገኛል፡፡ ስንት ምኞቶች ተፃራሪው ገጠማቸው? ስንት ዕቅዶች ተሰረዙ? ስንት ፕሮግራሞች ታጠፉ? ስንት የሚያማምሩ  ዝግጅቶች ተቀጩ? ይህ የሆነው አንዳንዶቹ ምንም አማራጭ ስላልተቀመጠላቸው ሳይሳኩ ሲቀሩ በዚያው ስለሚሞቱ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ክትትል ስለሚጎላቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ ቀድሞውኑ ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ ስለማይመደብላቸው ነው! ከሁሉም ወሳኙ ይሄ “ለትክክለኛው ቦታ ትክክለኛውን ሰው አለመመደብ” ነው፡፡ /The Right Man at The Right Place እንዲሉ/ ይህ ደግሞ የሰው ኃይል አቅምን ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ የዕውቀት ጎደሎ የሚመጣው ከመቸኮል፤ ጥናትን ካለማስቀደምና መንገድን አጥርቶ ካለማወቅ ነው፡፡ በጥልቀት እናስተውል፡፡ በብስለት፣ በብልሀትና በጥራት መጓዝ ጊዜ ጠብቆ አገርንና ህዝብን በሚገባ መምራትን ያመጣል፡፡ ከዚህ ደግሞ አዲስ ለውጥ ይወለዳል፡፡
 አዲሱ ዓመት ይህንን እናሳካ ዘንድ ልብና ልቡና እንዲሰጠን እንመኛለን! ቀስ በቀስ ዕንቁላል በእግሩ ይሄዳል ይላልና፣ በዝግታ ወደ ፊት እንራመድ! ሁሉም ይደረሳል! መልካም አዲስ ዓመት ከበለፀገ አዕምሮ ጋር!!

Read 12178 times