Tuesday, 06 September 2022 00:00

በጦርነት ውስጥ የተከበረው የነጻነት ቀን

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)

“ወደ ሩሲያ ተመልሼ አልሄድም፤ ዩክሬን እናት አገሬ ናት”
                     
      የዛሬ 31 ዓመት፣ነሐሴ 24 ቀን 1991 ዓ.ም ነበር፣ ዩክሬን ራሷን ከሶቭየት ህብረት ነጥላ ነፃነቷን ያወጀችው። ከዚያን ጊዜ ወዲህም ቀኑ፣ የአገሪቱ የነጻነት ቀን ሆኖ፣ በየዓመቱ ሲከበር ቆይቷል።
ምንም እንኳን የዘንድሮው የነጻነት ቀን፣ እንደ ወትሮው በወታደራዊ ሰልፎች፣ በደማቅ ሪችቶችና ኮንሰርቶች ባይታጀብም፣ ቀኑ ከመቼውም በላይ ትርጉም ያለው እንደሆነ አዛውንቶቹ ዩክሬናውያን ይናገራሉ። የዘንድሮውን የነጻነት ቀን ልዩ የሚያደርገው አንድም በጦርነት መሃል በመከበሩ ሲሆን፤ አንድም ደግሞ የሩሲያ ወረራና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ስድስተኛ ወር ጋር በመገጣጠሙ ነው፡፡
ጦርነቱ እንደዘበት 6 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ 17.7 ሚሊዮን ሰዎች የሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ ሆነዋል። ከመኖሪያና ከትውልድ ቀዬ በጅምላ መፈናቀሉ የቀጠለ ሲሆን፤ 6.4 ሚሊዮን ዩክሬናውያን ወደ አውሮፓ ሲሰደዱ፣ ተጨማሪ 6.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ  በዚያው በአገሪቱ ውስጥ የተሻለ ደህንነት ወዳሉባቸው ስፍራዎች ተፈናቅለዋል።
አዛውንቶችን በሚደግፈው “HelpAge International” ሪፖርት መሰረት፤ ከዩክሬን አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ ሩብ ያህሉ ከ60 ዓመት በላይ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው። ከዚህም ጦርነት አስቀድሞ ከ2014 አንስቶ በዘለቀው የምስራቃዊ ዩክሬን ግጭት፣ ከሶስት ሰዎች አንዱ መጎዳቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በጦርነቱ ሳቢያ ከተፈናቀሉት ወይም ከተሰደዱት ዩክሬናውያን መካከል ዕድሜያቸው የገፋ አዛውንቶችም ይገኙበታል። በሌላ በኩል፤ በምርጫቸው ሳቢያ አሊያም መጓዝ ባለመቻላቸው ምክንያት ባሉበት የቀሩም አሉ። ብዙዎቹ ደግሞ በጤና ክብካቤ፣ በሥነ-ልቦና ድጋፍ፣ ለማግኘት አስቸጋሪ በሆኑ መሰረታዊ አቅርቦቶች ረገድ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ናቸው፤ ነገር ግን የአዛውንቶች ፍላጎት በሰብአዊ ድጋፍ አሰጣጥ ሂደት ብዙውን ጊዜ እንደሚዘነጋ የ”HelpAge” ሪፖርት ያመለክታል።
እንዲያም ሆኖ ታዲያ እገዛ የሚያሻቸው ወገኖችን ለመደገፍ የሚችሉትን ሁሉ በበጎ ፍቃደኝነት ከማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ በርካታ አዛውንቶች አሉ።
አልጀዚራ ከእነዚህ በጎፈቃደኛ አዛውንቶች መካከል ጥቂቶቹን ያነጋገረ ሲሆን የዩክሬን ነፃነት ትውስታቸውን፤ከሶቭየት ዘመን ወዲህ ባሉት አስርት ዓመታት ህይወት እንዴት እንደተለወጠ፤ እንዲሁም በሩሲያ ጦርነት የተጋረደው የዘንድሮው የነፃነት ቀን፣ ምን ትርጉም እንደሚሰጣቸው አጋርተዋል፡፡ እኛም የተወሰኑትን መርጠን እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡  
“በዚህ ዓመት የነጻነት ቀን በእርግጠኝነት የላቀ ትርጉም ይኖረዋል” ያሉት ከHelpAge ጋር እገዛ የሚሹ አዛውንቶችን የሚደግፉት የ62 ዓመቷ ታትያና ሚልኮ ናቸው። “አሁን አገሪቱ ወደ አንድነት መጥታለች። ከዚህ ቀደም የነጻነት ቀን እንደ ማንኛውም በዓልና እረፍት ነበር የሚቆጠረው። ቀልድ ሁሉ እንቀልድ ነበር። አሁን  ግን የዩክሬናውያንን ውስጣዊ ጥንካሬና ኩራት የሚወክል ሆኗል። ወደፊት ግሩም፣ ደስተኛና ነፃ እንደምንሆን አውቃለሁ። ሁሉም ነገር የዩክሬን ሆናል።” ብለዋል- ለአልጀዚራ በሰጡት ቃል።
ቪራ ኦክህሪሜንኮ (71)
“በ1991 ነፃነት ሲታወጅ፣ እኔ ከወንድ ልጆቼ ጋር በማይዳን አደባባይ ነበርኩ” ሲሉ ያስታውሳሉ፤ በኬይቭ የሁለት ወንዶች እናት የሆኑት የ71 ዓመቷ ቪራ። “በጣም አያሌ ሰዎች ነበሩ፤ሁኔታው የአገር ፍቅር ስሜት የሚቀሰቅስ ነበር።” ብለዋል።
በሶቭየት ህብረት ያደጉትና የዩኒቨርስቲ ድግሪያቸውን እዚያው ያገኙት ቪራ፤ በአቪየሽን ዘርፍ ማለፊያ ሥራ ነበራቸው።  ከመንግስት በተሰጣቸው የመኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት። በመንግስት ሥራቸው አማካኝነትም ወደ ኡዝቤኪስታን የተጓዙ ሲሆን በዚያም ለአንድ ዓመት ያህል ኖረዋል። “ከዚያ በኋላ ነው ዩክሬናዊ መሆኔን የተገነዘብኩት። በ1978 ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼ ወደ ትውልድ አገሬ ተመለስኩ።” ይላሉ፤ ቪራ።
ከዚያ ወዲህ የአገር ፍቅር ስሜታቸው ይበልጥ ናረ። የ1989 የቋንቋዎች ህግ፤ ዩክሬንኛ የሥራ  ቋንቋ መሆኑን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፤ “ከሌሎች አገራት በተለየ ሁኔታ እኛ በራሳችን ቋንቋ ለምንድን ነው የምናፍረው ስል ራሴን ጠየቅሁኝ። ከዚያ በኋላ ከልጆቼ ጋር በዩክሬንኛ ቋንቋ ማውራት ጀመርኩ፡፡ በሥራ ቦታም ዩክሬንኛ ነበር የምጠቀመው።” ብለዋል።“ከነፃነት በኋላ በዩክሬን ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል።” ይላሉ ቪራ። “ነፃነቱ ለህብረተሰባችን ድጋፍ ሆኖታል። በ90ዎቹ መጀመሪያ ላይ  ህይወት አስቸጋሪ ነበር፡ ነገር ግር ´ለራሳችን ህይወት ሃላፊነቱን የምንወስደው ራሳችን ነን፤ የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን እንወስናለን´ የሚል ስሜት ተፈጥሮ ነበር።”
በህይወት መኖር ፈታኝ ነበር፤ ከዚያ ወዲህ ህይወት በዩክሬን ተሻሽሏል- ይላሉ አዛውንቷ።
“ከፌብሯሪ 24 ወዲህ ሁሉም ነገር ተገለባበጠ” የሚሉት ቪራ፤ “በፊት ሰላማዊ ዕቅዶችና ፕሮጀክቶች ነበሩኝ፤ አሁን ዕድሜዬ ቢገፋምና ጡረታ ብወጣም ቅሉ፣ አገሬን መርዳት እንዳለብኝ ተረድቻለሁ።” ብለዋል።
አዛውንቷ በአሁኑ ወቅት በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፤በሹራብ ሥራ፣ ሰዎች የሚፈልጉትን መድሃኒት እንዲያገኙ በመርዳት እንዲሁም ድንበር ተከላካይ ሃይሎች መሰረታዊ አቅርቦቶችን እንዲያገኙ በመደገፍ።
“የጦር ሰራዊታችንና መከላከያችን በአይበገሬነታቸው እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ ዓመት የነፃነት ቀን ማለት ከመቼውም የላቀ ትርጉም አለው። ያለፈው ስድስት ወር ብዙ አስተምሮኛል።
“ለሩሲያ እኛን እንድታወግዝ እንዲሁም ማን በህይወት መኖር እንዳለበትና ማን መኖር እንደሌለበት የመወሰን መብት የሰጣት ማነው?  እንዴት መኖር እንዳለብን እነሱ ሊነግሩን አይችሉም። እኛ ነፃ - ሉአላዊ አገር ነን፤ እናም በራሳችን መንገድ መኖር እንሻለን። ለወደፊት የመጀመሪያው ተስፋዬ፣ በጦርነቱ ድል እንደምንቀዳጅ ነው።” ሲሉም ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።
ቭላድሚር ሻቬሪን (71)
“ለእኔ የነጻነት ጉዳይ የተወሳሰበ ነበር” ይላሉ የ71 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ቭላድሚር። “ሶቭየት ህብረትን በተመለከተ የሰዎችን ዕይታ መፈተሸ እችላለሁ። አንዳንዶች በፍፁምነት ሲያመልኳት፣ አንዳንዶች ደግሞ አስፈሪ ጭራቅ ያደርጓታል።”
ትውልዳቸው ከሩስያ የሆኑት ቭላድሚር፤ በሶቭየት ዘመን ጦር ሰራዊቱን አገልግለዋል - በ1968 በኬዪቭ ወታደራዊ ኮሌጅ ገብተው፤ በ1992 ጡረታ ወጥተዋል።
“ቅድመ-ነጻነትና ድህረ-ነፃነትን በተመለከተ በጎም መጥፎም ነገሮች አሉ” የሚሉት ሶስት ልጆች ያፈሩት አዛውንቱ፤ ጉዳዩ ጥቁርና ነጭ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።
“በሶቭየት ህብረት ስለ መጪው ህይወትህ እርግጠኝነት ይሰማህ ነበር፤ በተለይ በጦር ሰራዊቱ ውስጥ ስትሆን ግሩም መኖሪያ ቤትና አስተማማኝ ጡረታ ይኖርሃል። ራሴን በትክክለኛው ቦታ ላይ እንዳስቀመጥኩ ነበር የሚሰማኝ፤ ስለ ራሴም እርግጠኛ ነበርኩ። እንደኔ ያሉ መኮንኖችም ይከበሩ ነበር።” ሲሉ የሶቭየት ህብረት ዘመን ትዝታቸውን ለአልጀዚራ አጋርተዋል።
ሆኖም የዩክሬን ነፃነት፣ ለራሳቸው አዳዲስ የቢዝነስ ተስፋዎችንና ለልጆቻቸው የነገ ህይወት አማራጮችን ጨምሮ፣ በርካታ ዕድሎችን ይዞ መምጣቱን አልሸሸጉም።
“በሶቭየት ህብረት የተለየሁ ሰው እሆን እንደነበር አውቃለሁ፤ ነፃነት ተከትሎ ለራሴ የበለጠ ክብርን ሰጥቻለሁ። በህይወቴ አንድ ምዕራፍ ላይ ወደ መንፈሳዊነት ገብቼ ነበር። ዓለምን በማይበት መንገድና ሰው ማለት ምንድነው በሚለው ትርጓሜ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል። የሶቭየት ህብረት ህይወቴ ያንን ጥያቄ አልመለሰልኝም ነበር።”
በሩሲያ ጦርነት ደስተኛ ያልሆኑት ቭላድሚር፤ ለ20 ዓመታት በአባልነት በዘለቁበት የሮታሪ ክለብ ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ይሳተፋሉ- በምግብና በህክምና አቅርቦት በመደገፍ እንዲሁም እርዳታ ለት/ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ለወታደሩ በማድረስ።ቭላድሚር ጓደኞቻቸውን በጦርነቱ አጥተዋል። “ሁላችንም ሰው መሆናችንን እንደምንረዳና ሩሲያውያንና ዩክሬናውያን ከሚለው እሳቤ እንደምንላቀቅ ተስፋ አደርጋለሁ።” ይላሉ፤ አዛውንቱ።
ስለ ዩክሬን መጪ ዘመን ሲናገሩም፤ “ጦርነቱን ካሸነፍን፣ ባለስልጣናቱ መለወጥ አለባቸው።  ከዚህ በኋላ ህዝቡ ሙስናን መታገስ አይችልም፤ በዚህ አካሄድ አገሪቱ መሻሻልና ማደግ ትጀምራለች።” ሲሉ ሃሳባቸውን አንጸባርቀዋል።
ታትያና አንቶኖቫ፤ (69)
“በውስጤ ዩክሬናዊነት ይሰማኛል” ይላሉ በምስራቃዊ ሩሲያ የተወለዱት የ69 ዓመቷ ታትያና። አባታቸው ወታደር ቤት ስለነበሩ፣ ቤተሰባቸው ከቦታ ቦታ ብዙ ተንቀሳቅሷል። በ1975 በዩክሬኗ የዛፖሪዝህያ ግዛት መኖሪያቸውን  አደረጉ።
“የመጀመሪያ መሠረቴን እዚህ አኖርኩ። ከዚያ በኋላ ነው በነፃነት ጉዳይ  ማመን የጀመርኩት” ይላሉ ታትያና፤ የአገሪቱ የነፃነት ህዝበ ውሳኔ ሲካሄድ፣ ሂደቱን የተቆጣጠረው የድምፅ አሰጣጥ ኮሚሽን አካል እንደነበሩ በመግለጽ፡፡
“ሩሲያ ምን እንደምትመስል ጠንቅቄ አውቃለሁ። ብዙዎቿን ነገሮች አይቻለሁ” የሚሉት አዛውንቷ፤ “ዩክሬን ስደርስ አገሪቱ ምቹና እንግዳ ተቀባይ እንደሆነች ተሰማኝ።” ብለዋል። ሁለት ነፍስ ያወቁ ወንድ ልጆች ያደረሱት ታትያ፤ አሁንም በሩስያ ቤተሰብና ጓደኞች አሏቸው። ከእነሱ ጋር እንደ ድሮው ማውራት ግን ቀላል እንዳልሆነ  ይናገራሉ።
“ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ እዚህ እየሆነ ያለውን በጄ ብለው ስለማይቀበሉ፣ ሩሲያ ከሚገኙ  ጓደኞቼ ጋር አላወራም። ከእህቴ ጋር አሁንም እንገናኛለን፤ ነገር ግን ስለ ጦርነቱ አናወራም። ሩሲያ እዚህ እየፈፀመችው ስላለው ነገር  መስማት አትፈልግም።”የወደፊት ምኞታቸው፤ ዩክሬን ጦርነቱን በተቻለ ፍጥነት እንድታሸንፍ ነው። እስከዚያው ድረስ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ ይሳተፋሉ- ባንዲራዎችንና አንዴ ተለብሰው የሚጣሉ የውስጥ ልብሶችን በመሥራት፤ ሰዎችን በመመገብ፤ ለተፈናቀሉ ሰዎች አልባሳትን በማሰባሰብና በጭንቀትና በመደበት ለሚሰቃዩ የምክር አገልግሎት በመስጠት።“ወደ ሩሲያ ተመልሼ አልሄድም። ዩክሬን እናት አገሬ ናት።” ይላሉ፤ታትያና።“የነጻነት ቀን በዚህ ዓመት የተለየ ትርጉም አለው።” ሲሉም ያክላሉ፤ አዛውንቷ። “እኛ ዩክሬናውያን ነፃነታችንን እናፈቅራለን። የምናምንበትን መናገር እንችላለን። በሩሲያ የሚገኙ ጓደኞቼ ዲሞክራሲ አለን ይላሉ። ጦርነትን ጦርነት ብለህ መጥራ የማትችል ከሆነ፣ ምን ዓይነት ዲሞክራሲ ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ፤የዕድሜ ባለጸጋዋ፡፡


Read 8573 times