Saturday, 03 September 2022 14:21

“እናቶች ህይወት ለመስጠት ህይወት እንዳያጡ…”

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አንድ ሰው ወይም ጥንዶች በሚመሰርቱት ወይም በመሰረቱት ቤተሰብ ውስጥ ልጆች መቼ፣ ስንት፣ በምን ያህል የጊዜ ልዩነት መውለድ እንደሚፈልጉ እና ካልተፈለገ እርግዝና ለመከላከል ምን አይነት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት[አማራጮች] መጠቀም እንዳለባቸው የሚወስኑበት[የሚያቅዱበት] ሂደት ነው። በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ እናቶች እና ህጻናት ላይ የሚሰሩ አቶ ኤፍሬም ረጋሳ እንደተናገሩት አንድ ልጅ ተወልዶ በአመጋገብ እና በሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ጤናማ ሆኖ እንዲያድግ የቤተሰብ ዝግጁነት አስፈላጊ ነው። ስለሆነም ለልጆች ይሄን መሰረታዊ ጉዳይ ለማሟላት ገቢ[ገንዘብ] ወሳኝ እንደመሆኑ የተፈለገውን ጊዜ በቤተሰብ እቅድ አማካኝነት ማግኘት ይቻላል። አቶ ኤፍሬም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ወጣቶች ትዳር መስርተው ልጅ ከመውለዳቸው አስቀድሞ መማር ወይም መስራት ቢፈልጉ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ትልቅ ሚና እንደሚያበረክት ነው። “የቤተሰብ እቅድ ዋናው አላማ የእናቶች እና የህጻናትን ጤና መጠበቅ ነው” ብለዋል አቶ ኤፍሬም።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የተለያዩ መንገዶች ሲኖሩት መታቀብ; የግብረስጋ ግንኙነት ከመፈጽም መቆጠብ አንዱ እራስን ካልተፈለገ እና ከእቅድ ውጪ ከሚከሰት እርግዝናና እራስን የመቆጠብ መንገድ ነው። ኮንዶም; ለወንዶች እና ለሴቶች የተዘጋጀ ሲሆን ያልተፈለገ እና ያልታቀደ እርግዝናን ከመከላከል ባሻገርም በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችንም ይከላከላል። ወሲብ ከተፈጸመ በኋላ የሚወሰድ መከላከያ [emergency pills]; የግብረስጋ ግንኙነት ከተፈጸመ በኋላ በ24 ሰአት፣ በ3 እና በ5 ቀናት ውስጥ የሚወሰዱ ናቸው። አንዲት ሴት መድሀኒቱን ከወሰደች በኋላ በድጋሚ የግብረ ስጋ ግንኙነት ከፈጸመች መከላከያው አይሰራም። ሌላው በኪኒን መልክ በአፍ የሚወሰድ መከላከያ [pills]; ማህጸን እንቁላል እንዳይለቅ ወይም የወንድ ዘር ከእንቁላል ጋር እናዳይደርስ ተደርጎ የተስራ መድሀኒት ነው። አንዲት ሴት በየቀኑ በተመሳሳይ ሰአት መከላከያውን መዋጥ አለባት። ከተረሳ የማርገዝ አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ከጤና ሁኔታ ጋር በተያያዘም ተቅማጥ ውይም ማስመለስ ካለም ላይሰራ ይችላል። በመርፌ የሚወሰድ [Depo Provera]; በክንድ ላይ በመርፌ አማካኝነት የሚሰጥ ሲሆን ለ3 ወር ያገለግላል። በየ3 ወር ህክምና ተቋም በመሄድ መወሰድ ይኖርበታል። ከጊዜ በኋላ እራሷ በክንዷ ማስገባት የምትችልበት አሰራርም አለ። ፕሮጄስቶሮን የተባለ ሆርሞን ስላለው ማህጸን እንቁላል እንዳይለቅ እና ማህጸን ጫፍ ባለ ፈሳሽ አማካኝነት የወንድ ዘር ከእንቁላል ጋር እንዳይገናኝ መንገድ ይዘጋል።
የረጅም ጊዜ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ፡- በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ [implant]; በክንድ ቆዳ ውስጥ በመቀመጥ ለ3 አመት የሚያገለግል ነው። ማህጸን እንቁላል እንዳይለቅ ወይም ፕሮጄስቶጂን የተባለ ሆርሞን የማህጸን ጫፍ ላይ ያለውን ፈሳሽ በመቀየር የወንድ ዘር ፈሳሽ እንቁላል ጋር እናዳይደርስ ያደርጋል።
ማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ (IUS) የ‘T’ ቅርጽ ያለው ሆኖ በማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ ሆርሞን ያለው የእርግዝና መከላከያ ነው። እስከ 5 አመት ያገለግላል። ቀላል የወር አበባ ወይም ምንም የወር አበባ ላይኖር ይችላል።
ማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ ሉፕ [IUCD]; በማህጸን ውስጥ በ‘T’ ቅርጽ የሚቀመጥ ከ10 እስከ 12 አመት የሚያገለግል ነው። መቶበመቶ ከሆርሞን ነጻ ሲሆን የወንድ ዘር ፈሳሽ የሚንቀሳቀስበትን አቅጣጫ የሚቀይር ነው። የአባላዘር ወይም ኤድስ ደረጃ ላይ የደረሰ ኤችአይቪ በሽታ ያለባት ሴት እስክትታከም ድረስ ባትጠቀም ይመከራል።
ቋሚ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት፡-
አንዲት ሴት ወይም ወንድ ከዚህ በኋላ ልጅ መውለድ አልፈልግም ብለው ከውሳኔ ሲደርሱ የሚሰጣቸው አገልግሎት ነው። ዘር የሚያልፍበት የሴቷ እና የወንዱ አካል ላይ ቀዶ ጥገና ይሰራል። ቋሚ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ከሌሎች የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ጋር ሲነጻጸር ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከለካል ሙሉበሙሉ በሚባል መልኩ ውጤታማ ነው። እንዲሁም አንድ ጊዜ ከተከናወነ በኋላ ወደ ልጅ መውለድ ሂደት መመለስ አይቻልም።  የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ወይም የወሊድ መቆጣጠሪያ ለሴቶች እና ለወንዶች የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን ለረጅም እና ለአጭር ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ ሲዘጋጅ ከሴት ልጅ የወር አበባ ጋር ተስማሚ እንዲሆን ተደርጎ የተቀመመ በመሆኑ አመዛኙ የሴቶች ነው። ነገር ግን ለአጭር ጊዜ ኮንዶም ለቋሚ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ደግሞ የዘር ፍሬው ወደ ሴቷ እንዳይሄድ ቀዶጥገና በማድረግ ወንዶችም ተጠቃሚ ናቸው።
የጤና ሁኔታ፡-
ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት፣ የደም መርጋት፣ ከ35 አመት በላይ ሆነው ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች፣ የልብ በሽታ፣ ስትሮክ እና መሰል በሽታዎች ያሉባቸው ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ሲጠቀሙ ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር እንዲሆን ይመከራል።
ጡት ማጥባት እና ያልተፈለገ እርግዝና፡-
ጡት ማጥባት እርግዝናን ሊያዘገይ ይችላል። የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የጤና ትምህርት ክፍል ባወጣው መረጃ መሰረት ጡት ማጥባት እንደ ወሊድ መቆጣጠሪያ የሚያገለግለው የተወለደው ልጅ ሌሎች ተጨማሪ ምግቦችን ሳይወስድ የእናት ጡት ብቻ ሲመገብ፣ እናት ቢያንስ በ4 ሰአት ልዩነት ጡት ካጠባች እና የወር አበባ የማታይ ከሆነ ነው። ጡት የሚያጠቡ ሴቶች ለ6 ወር ያህል የተወለደው ልጅ ተጨማሪ ምግብ መመገብ እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ የተጠቀሰውን መንገድ ከተጠቀሙ ውጤታማነት ይኖረዋል። ይህም ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ እንዳስቀመጠው 99በመቶ ይሰራል። ማለትም ጡት ከሚያጠቡ 100 ሴቶች መካከል 2 ሴቶች ላይ የማርገዝ እድል ሊያጋጥም ይችላል።  
የወር አበባ መምጣት ከጀመረ ማህጸን እንቁላል ወደማምረት ሂደት መመለሱን ወይም እየተመለሰ መሆኑን ስለሚያሳይ እርግዝና ሊፈጠር ይችላል። እንዲሁም በአንዳንድ ሴቶች ላይ ልጅ ከተወለደ ከ3 ሳምንት በኋላ የወር አበባ ሳይመጣ እርግዝና ሊከሰት ይችላል። ስለሆነም ጡት የሚያጠቡ እናቶች ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ከፈለጉ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙ ይመከራል። ሁሉም የወሊድ መቆጣጠሪያ ለሚያጠቡ እናቶች ተስማሚ ተደርገው የተሰሩ ናቸው። ነገር ግን የትኛው የወሊድ መቆጣጠሪያ የተሻለ ነው የሚለውን ከህክምና ባለሙያ ጋር በመነጋገር መጠቀም ይመከራል።
የወሊድ መከላከያ መድሀኒት ለመሀንነት ያጋልጣል?
በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ እናቶች እና ህጻናት ላይ የሚሰሩ አቶ ኤፍሬም ረጋሳ እና አዋላጅ ነርስ ዘምዘም አማን እንደተናገሩት ሰዎች ላለመውለድ ወስነው ቋሚ የቤተስብ አገልግሎት ተጠቃሚ ካልሆኑ በቀር የትኛውም የወሊድ መቆጣጠሪያ ልጅ ላለመውለድ ምክንያት አይሆንም። አንዲት ሴት በየትኛውም ጊዜ እየተጠቀመች የነበረውን የወሊድ መቆጣጠሪያ ስታቆም ማርገዝ ትችላለች።
አቶ ኤፍሬም እንደተናገሩት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ካልተፈለገ እርግዝና በመከላከል ሰዎች ጽንስ ወደ ማቋረጥ እናዳይሄዱ ትልቁን ሚና ይጫወታል። “እናቶች በህይወት ውስጥ የህይወት ዋጋ እንዳይከፍሉ መታደግ ይገባል” በማለት የተናገሩት አቶ ኤፍሬም ሰው ከእናት እንደመምጣቱ እንዲሁም ከእናት ጀርባ ቤተሰብ እና ሀገር እንደመኖሩ “ሁላችንም ባለንበት ሙያ ለእናቶች እና ህጻናት ጤንነት መስራት ይገባናል” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።    

Read 11380 times