Print this page
Saturday, 27 August 2022 12:06

አንገት ከማስደፋት ደረት ወደ ማስነፋት

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ውሸት በዛ፣ ቅጥፈት በዛ፣ መካካድ በዛ! የምር ማን ያምጣብን ማን አንድዬ ይወቀው እንጂ በፊት አንገት ያስደፋ የነበረ፣ በር አስቆልፎ ያስቀመጥ የነበረ፣ ከዘመድ ወዳጅ ያርቅ የነበረ ዋሾነት፤ አሁን ከማስጨብጨብ አልፎ ልክ በልጅነት “ሳድግ ዶክተር እሆናለሁ፣” “ሳድግ ኢንጂነር እሆናለሁ፣” ይባል እንደነበረው፣ ነገና ከነገ ወዲያ “ሳድግ ውሸታም እሆናለሁ፣” እንዳያስብል ተብሎ ቢያሰጋ አይገርምም፡፡
“የዋሾ ሰዎች ቅጣት ሌሎች እነሱን ያለማመናቸው አይደለም፤ እነሱ ማንንም ማመን አለመቻላቸው እንጂ...” የምትል ነገር አለች፡፡
ጥንዶቹ ሠላሳኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን እያከበሩ ነው፡፡ በደስታ የሚፍለቀለቀው ባል ሚስቱን ይጠይቃታል...
“ውዴ አስራ ሁለት ልጆች አሳድገናል፡፡ ጆኒ ግን ከሁሉም የተለየ ነው፡፡ ማናቸውንም አይመስልም፡፡ ሳትደብቂ ንገሪኝ፡፡ አታለሽኛል እንዴ?”
“አዎ፣” ትለዋለች፡፡
“እስቲ እንዴት እንደሆነ ንገሪኝ፡፡”
“ጆኒ እውነተኛው የአንተ ልጅ ነው፡፡”
እርፍ! ንገሪኝ፣ ንገሪኝ ብሎ መርዶውን ሰማና አረፋታ!
አስራ አንዱ ልጆች የእሱ አይደሉማ! “አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፣” ይሏችኋል ይሄ ነው፡፡ ለነገሩ ምን መሰላችሁ... አንዳንዴ የሁለት ልጆች አባት፣ የሦስት ልጆች አባት የሚባሉ አባወራዎች በሚያርፉበት ጊዜ ከየስርቻው፤ “ልጁ ነኝ፣” “እነኚህ ሁለት  ከእሱ የወለድኳቸው ናቸው፣” ምናምን እያሉ ብቅ የሚሉት መአት ናቸው ይባላል፡፡
 የምር ግን...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በፊት እኮ የሆነ ሰው ‘ዓይኑን በጨው አጥቦ’ ውሸት ሲያወራ በሆዳችን...አለ አይደል... “እንደው እንዲህ ሲቀጥፍ አፉን ትንሽ እንኳን ያዝ አያደርገውም!” ምናምን እያልን እንታዘብ ነበር፡፡ ወይ ደግሞ ፊት ለፊት “አቤት ቀደዳ!  ቆይ፣ ቆይ ወራጅ አለ...” ምናምን እያልን አፍ፣ አፉን እንለው ነበር፡፡ አሁን እሱ ሁሉ ‘ሂስትሪ’ እየሆነ ነው፡፡
በፊት...
“የሚገርምህ በዚህ ዓመት አንድ ጂ ፕላስ ቱ ቤት ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ እገዛለሁ ብያለሁ፣” ይለን የለ፣ እኛ ደግሞ...
“አቤት ቀደዳ! አቤት ቀደዳ! ቤት፣ ያውም ጂ ፕላስ ቱ? በዚህ ሸሚዝ በማያስገዛ ደሞዝህ ነው የምትገዛው ወይስ ልትዘርፈው ያሰብከው ነገር አለ?” ምናምን አይነት ነገር ብለን ኩም ልናደርገው እንሞክር ነበር፡፡ አሀ...ልክ ነዋ! ከዕለታት አንድ ቀን ዘቢብ ኬክ በቡና በወተት ከገዛላችሁ እኮ መንፈቅ የሚያወራ አይነት ነው፡፡
አሁን...   
 “የሚገርምህ በዚህ ዓመት አንድ ጂ ፕላስ ቱ ቤት ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ እገዛለሁ ብያለሁ፣” ይለን የለ፣ እኛ ደግሞ...
“አትለኝም!”
“ሦስት ወይ አራት ወር ቢፈጅብኝ ነው፡፡”
“አንተ እኮ ድሮም ብሪሊያንት ነበርክ።” (ኸረ ቀስ! አሀ...ለምን የፈለገ አይነት ሞራል ጥበቃ አይሆንም! እንዲህ አይነት ‘ጥበቃ’ አለ እንዴ! ለነገሩ እኮ...መጀመሪያ ሞራሉን ለመጠበቅም እኮ የሚጠበቅ ሞራል አለው ወይ ማለት ያስፈልጋል። ቂ...ቂ...ቂ...ብዙ ስናወራ እንደ ፈላስፋነት ይሞክረናል መሰለኝ!) እናማ... አይደለም ጂ ፕላስ ምናምን ሊያስብ ከወር ወር እንዴት እንደሚደርስ ታውቃላችሁ እኮ። ግን ደግሞ...(“ግን ደግሞ...” የምትል ወሽመጥ ነገር ስትገባ፣ “አለ ነገር ወንዙን ስንሻገር፣” የሚባለው ያን ጊዜ ነው!) እናላችሁ...ዘንድሮ ግን ደግሞ አይደለም ጂ ፕላስ ምናምን፣ እገዛለሁ ካለው በላይም አቅም ሊኖረው ይችላል። አዎ...እንቆቅልሹ፣ የሚሊዮን ብሩ ጥያቄ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ከየት? እንዴት? በምን አይነት ተአምር? ምናምን የሚሉ ጥያቄዎች የሚደረደሩት ይሄኔ ነው፡፡
ከዛላችሁ... የሆነ ሰው ሹክ ይላችኋል...
“ስማ... አጅሬው የዋዛ መሰለህ! ከባለጉዳዮች እኮ በመቶ ሺዎች ነው አሉ ብራይብ የሚቀበለው!”
እንዲህ አይነት ነገር ስትሰሙ...እንደቀድሞው ቢሆን ኖሮ... አማትባችሁም ይሁን፣ ሽቅብ ከፈጣሪ ጋር ሙግት ገብታችሁም ይሁን፣ ወገባችሁን ይዛችሁም ይሁን...
“ከድሀ ጉሮሮ ላይ እየነጠቀ የሚወስደው... እንደው የሰላም እንቅልፍስ ይወስደዋል?”
“ምን አይነቱ አረመኔ ነው እባካችሁ! እንደው የእናት አባቴ አምላክ...” እያልን ወይም እርግማኑን፣ ወይ ደግሞ ቅልጥ ያለውን የእንትን ሰፈር የስድብ መአት እናወርድበታለን፤ ወይ እናወርድባት ነበር፡፡
“ዌል እንግዲህ...” የሚለው ማን ነበር! ዌል እንግዲህ....ፈረንጅ “ዜን ዋዝ ዜን! ናው ኢዝ ናው!” እንደሚባለው፣ አሁን የጨዋታ ሜዳው ሰፍቶ የጨዋታ ህጉም ኦፊሴል ባልሆነ መንገድ የተለወጠ ይመስላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰውን የሚሰድብ፣ የሚረግም፣ ሽቅብ ፈጣሪን “ይህን እያየህ ዝም ትላለህ” የሚሉ ቢኖሩ በጣም ጥቂት ቢሆኑ ነው...ብርቅዬ ምናምን እንደሚባሉት አይነት ማለት ነው፡፡ አሁን ከምንም በላይ ብዙዎቻችን ማወቅ የምንፈልገው ምን መሰላችሁ... የተባለው ሰው የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ማወቅ፡፡
“ስማ እንዲህ የሚሳካለት ምን አይነት ዘዴዎችን ቢጠቀም ነው?”
“እኔም ግርም የሚለኝ እሱ አይደል! ሰውየው እኮ ቆቅ ቢጤ ነች አሉ፡፡ ሁሉንም ነገር በድብቅ ነው የሚያደርገው፡፡ ሚስቱ ብታያት በቃ የሀገር ንግሥት ነኝ ለማለት ምንም አልቀራት፡፡”
“ስማ ግን እሱን የሚያውቅ ሰው አታውቅም?”
“አንድ በፊት ጎረቤታችን የነበረ ሰው፣ ጓደኛው ነው ብለውኝ እያፈላለግሁት ነው፡፡ ሰዉ ፍራንክ በፍራንክ ሲሆንማ፣ እኛ እጃችንን አጣጥፈን ልንቀመጥ አንችልም፡፡ ይሞታል እንዴ!”
እናላችሁ...ግርም የሚል ጊዜ ውስጥ ነን። ትልቁም ትንሹም... ሚጢጢውም የሰማይ ስባሪ የሚያክለውም... ፍራንክ የሌለውም ፍራንክ ሞልቶ የፈሰሰበትም...አለ አይደል... “ውሸት እንደተርጓሚው ነው...” ያለ ነው የሚመስለው፡፡
በፊት አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ይጠየፋቸው የነበሩ ነገሮች ሁሉ አሁን የለየለትና የሚያስጨበጭቡ ነገሮች ሲሆኑ...አለ አይደል...ይልቅ መስጋት ከታች ለሚመጣው ትውልድ ነው፡፡ ልጆች የገንዘብ ማግኛ፣ የምናምን ሚሊዮን ብር ባለቤትና የጂ ፕላስ ምናምን ህንጻ ባለቤት ለመሆን የሚያስችለው እውቀትና ሥራ ሳይሆን፤ ብልጥነት መሆኑ ውስጣቸው እየሰረጸ ሲሄድ፣ ነገና ከነገ ወዲያ የሚፈጠረውን አስቡትማ!
ስሙኝማ... መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አሁንም ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የውሸት ፈቃድ እንደቀድሞው በአክስትና በአጎት “ሞት” ማሳበቡ እንዳለ ነው እንዴ! አንድ አጎት ብቻ የነበረው ሰው፣ በአራተኛ አጎቱ ህልፈት ምክንያት ፈቃድ ሲጠይቅ “አንተ ሰውዬ ከመሥሪያ ቤት የሥራ ባልደረቦችህና ከአጎቶችህ የትኞቹ በቁጥር ይበልጣሉ?” ብሎ ማፋጠጥ ነበር፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
እግረ መንገድ ይቺን ነገር ስሙኝማ...ሰውየው የአካል ብቃት አስተማሪ ነው አሉ፡፡ ሜዳ ላይ ተማሪዎች ተሰልፈው ሳለ እንዲህ አላቸው...
“የምታጨሱ ተማሪዎች ወደዚህ ኑ፡፡”
የተወሰኑ ተማሪዎች ወደ እሱ ይጠጋሉ፡፡ ቀሪዎቹን ደግሞ...
“እሺ እናንተ የማታጨሱት ስምንት መቶ ሜትር ሩጡ፣” አለና አጠገቡ ወደነበሩት ዞሮ ምን ቢል ጥሩ ነው... “እነሱ ሮጠው እስኪመጡ እኛ ሲጋራችንን እናጭስ፣” ብሏቸው አረፈ አሉ። ነገርዬዋ የፈረንጅ ብትሆንም እንዲህም አይነት ነገር አለ ለማለት ያህል ነው፡፡
እናላችሁ... ውሸት አንገት ማስደፋቱ ቀርቶ ደረት የሚያስነፋበት ዘመን ላይ መድረሳችን ያሳዝናል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1656 times