Saturday, 20 August 2022 13:15

ሩሲያውያን ፊታቸውን ወደ ኮከብ ቆጣሪ አዙረዋል

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(2 votes)

    “ከጦርነቱ በኋላ ሩሲያ የዓለም የስበት ማዕከል ትሆናለች”
                      
       ጦርነት የሚጀመርበትን ጊዜ እንጂ የሚያቆምበትን ጊዜ ማወቅ አይቻልም የሚባለው መቶ በመቶ ትክክል ነው፡፡ በዕቅድ ሊጀመር ይችላል። በዕቅድ ግን አይቆምም። ቆሞም አያውቅም።  የህወኃት አማጺ ቡድን ጦርነቱን የጀመረው አቅዶ ነው፤ በዚህ ቀን እጀምራለሁ ብሎ፡፡ ብቻውን  መክሮና አቅዶ የገባበትን ጦርነት ግን መቼ እንደሚያቆመው በዕቅዱ አላስቀመጠም፡፡ እነሆ በቅጡ ሳያስብ የጀመረው ጦርነት፣ ሁለተኛ ዓመቱን  አስቆጥሯል፡፡ ዛሬም እንኳን የጦርነቱን ማብቂያ ቀን አያውቀውም፡፡ ማወቅም አይፈልግም፡፡ ጦርነቱ እንዲቆምም አይሻም፡፡ ጦርነቱ ከቆመማ ህልውናውም ያቆማል፡፡
ሩሲያ የዛሬ 6 ወር ገደማ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻውን ስትጀምር፣ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተልዕኮዋን እንደምታጠናቅቅ አስታውቃ ነበር፡፡ ጦርነቱን ባቀደችው ቀን ጀምራ ባቀደችው ቀን ልታጠናቅቅ ማለት ነው። ይሔ ግን ከተለመደው የጦርነት ህግ ያፈነገጠ በመሆኑ አልተሳካም፡፡ እነሆ ጦርነቱም 6 ወራትን እያስቆጠረ ነው፡፡
በጦርነቱ እስካሁን 80 ሺ የሚደርሱ የሩሲያ ወታደሮች መገደላቸውን ወይም መቁሰላቸውን የአሜሪካ የመከላከያ ዲፓርትመንት ያወጣው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ በዩክሬን በቀን ከ100-200 የሚደርሱ ወታደሮች እየተገደሉ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ በኩል፤12ሺ ገደማ ሲቪሎች መገደላቸውም ተዘግቧል፡፡ የዩክሬን ከተሞች፣ተቋማትና መሰረተ ልማቶች እንዳይሆኑ ሆነው ወድመዋል፡፡
አሜሪካ ዩክሬንን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ማስታጠቋን የቀጠለች ሲሆን እስካሁን የ10 ቢ. ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጓ ታውቋል፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን የሁለቱ አገራት ደም አፋሳሽ ጦርነት መች እንደሚያበቃ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እስካሁን ጦርነቱን በድርድር የመቋጨት ፍንጭ ከሁለቱም ወገኖች አልታየም፡፡ የዪክሬኑ ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ለዓለም አገራት መሪዎች ባደረጉት ንግግር፣ ጦርነቱ በማርች 2023 ይቋጭ ዘንድ እንደሚሹ ጠቁመው ነበር። ምኞት ይሁን እቅድ ግን አልታወቀም፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ የኒውክሌር ጦርነት እንዳይከሰትና ጥፋቱ በእጅጉ የከፋ እንዳይሆን መላው ዓለም ስጋት አድሮበታል፡፡  
ሩሲያ በምዕራባውያን በምትደገፋዋ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻዋን አጠናክራ መቀጠሏን ተከትሎ ታዲያ፣ በርካታ ሩሲያውያን ፊታቸውን ወደ ኮከብ ትንበያ ጠበብቶች (አስትሮሎጀሮች) እያዞሩ መምጣታቸውን የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል፡፡
የሩሲያ ሁለተኛዋ ከተማ በሆነችው ሴይንት ፒተርስበርግ፣ መነፅር ዓይናቸው ላይ የሰኩት የ63 ዓመቷ አስትሮሎጀር ኢሌና ኮሮልዩቫ፣ ደንበኞቻቸውን በመኖሪያ አፓርትመንታቸው ውስጥ እየተቀበሉ ያስተናግዳሉ፡፡
“ሩሲያ ከቀረው ዓለም ጋር ተቆራርጣ ዕጣ ፈንታዋ ምን እንደሚሆን ሰዎች ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡” ሲሉ የኮከብ ትንበያ ጠበብቷ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል፡፡
ለነገሩ በአገረ-ሩሲያ የኮከብ ትንበያ አዋቂዎችና ዕጣ ፈንታ ተንባዮች አዲስ ክስተት አይደሉም፡፡ በህዝቡ ዘንድ ለዘመናት ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በነውጥና መከራ ጊዜ ተፈላጊነታቸው በእጅጉ ይጨምራል - ገበያቸው ይደራል፡፡ አሁንም በሩሲያ የሆነው እንዲሁ ነው፡፡
በትምህርታቸው ፊሎሎጂ ያጠኑትና ሽበታሟ ኢሌና ኮሮልዩቫ፤ ምክራቸውን ሽተው ወደ እሳቸው ዘንድ የሚመጡ ደንበኞችን አረጋግተው ነው የሚሸኙት - የኮከብ ካርታቸውን እያጣቀሱ።
ሞስኮ የኢኮኖሚ ማእበሉን ያለምንም ችግር ማለፍ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱንም በድል  አድራጊነት እንደምትወጣው ተንብየዋል፤ አዛውንቷ አስትሮሎጀር፡፡
በመስከረም ወር ላይ አደጋውና ጥፋቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይጠናከራል፤ይሁንና ሩሲያ ግን ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ተረጋግታና በልጽጋ ትወጣለች፡፡” ብለዋል፡፡
ለእያንዳንዱ የምክር አገልግሎት 5ሺ ሩብልስ (90 ዶላር) እንደሚያስከፍሉ የሚናገሩት አስትሮሎጀሯ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን ከላኩበት ከፌብሯሪ 24 ወዲህ የደንበኞቻቸው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ - መጠኑን በቁጥር ለማስቀመጥ ባይደፍሩም፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ እንደሚከሰት አስቀድሜ ተንብዬአለሁ ማለቱን ተከትሎ በሞስኮ ዝናን የተቀዳጀው ሌላው አስትሮሎጀር፣ ኮንስታንቲን ዳራጋንም እንዲሁ፣ ሩሲያ ጦርነቱንም ሆነ ከምዕራባውያን ጋር የገባችበትን ግጭት በድል ትወጣዋለች፤ ይላል፡፡
በቅርቡም በማህበራዊ ሚዲያ፤ “ሩሲያ ከጦርነቱ በኋላ የዓለም የስበት ማዕከል ትሆናለች፡፡” ሲል ተናግሯል።
ከበረራ ምህንድስና (ኤሮኖቲካል ኢንጅነሪንግ) ወጥቶ ዝነኛ አስትሮሎጀር ለመሆን የበቃው ኮንስታንቲን ዳራጋን፤ የትውልድ ቀዬው የሩሲያ ሠራዊት ከምንም በፊት ሊቆጣጠረው ከጅሎት የነበረው የዳንባስ ግዛት ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት ሚኒስትሮችን፣ የባንክ ባለሙያዎችንና የዩክሬን የደህንነት አገልግሎትን ሳይቀር ማማከሩን ይገልጻል፡፡
በዩክሬን እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም ምዕራብ-አፍቃሪያን ባለሥልጣናት የአገር መሪነቱን ሚና መውሰዳቸውን ተከትሎ፣ወደ ሞስኮ የተሻገረው ኮንስታንቲን ዳራጋን፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚደግፍ ይናገራል - የትውልድ ከተማው በጦርነት ብትፈርስም፡፡
ለሱም ታዲያ የኮከብ ትንበያ ገበያው ደርቶለታል፡፡
በሌቫዳ የምርምር ማዕከል የማህበራዊ ሳይንስ አጥኚው አሌክሲ ሌቪንሰን እንደሚሉት፤ ለብዙዎቹ “ግራ የተጋቡ” ሩሲያውያን፤ አስትሮሎጂ፣ እውነታውን የመጨበጪያ መንገድ ነው፡፡
“አንዳንዶች ከመሪዎቻቸው ይልቅ ክዋክብትን እንደ አቅጣጫ አመላካች (ኮምፓስ) መውሰድ ይመርጣሉ” ብሏል አስትሮሎጀሩ፡፡
“ዛሬ አስትሮሎጂ እንደ ሳይኮቴራፒ ወይም አዲስ ሃይማኖት ዓይነት ሆኗል።” ሲልም አክሏል።
በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙትና ከኮከብ ትንበያ ጠበብቱ ደቀመዛሙርት አንዱ የሆኑት አና ማርከስ፣ ኮከቦችን የሚያነቡት፣ “በምድር ላይ ለሚከሰቱ ኹነቶች አመክንዮ ለማግኘት” ነው ይላሉ።
ለጦርነቱ ብቸኛዋ ተጠያቂ (ጥፋተኛ) ተደርጋ የተበየነችው ሩሲያ ናት፤ ነገር ግን እውነተኛው ተጠያቂ ሦስተኛ አገር መሆኑ ይታወቃል፡፡” ብለዋል- ለኤኤፍፒ በሰጡት ቃል፡፡
አሜሪካ ጥፋተኛ መሆኗን የሚያረጋግጥ የክዋክብት ካርታ እንዳላቸውም ተናግረዋል- አና ማርከስ።
ከድንበር ማዶ ብዙ ድብደባና ውድመት በደረሰባት ዩክሬን ደግሞ ኮከቦቹ የሚያሳዩት ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡
በዩክሬን መገናኛ ብዙኃን ዘንድ በእጅጉ የሚታወቀው አስትሮሎጀር ቭላድ ሮስ፤ ፑቲን “ክፉኛ ታሟል፤ ከማርች 2023 ዓ.ም አያልፍም” ይላል- ክዋክብቱን ቆጥሮና ቀምሮ፡፡
“የሩሲያ ኮከብ ሳተርን ሲሆን የዩክሬን ኮከብ ኡራነስ ነው፤ የኛ ድል አድራጊነት ምንም ቢሆን  አይቀሬ ነው” ትላለች፤ ሌላዋ የዩክሬን አስትሮሎጀር፣ አንጄላ ፐርል- ከግንቦት መገባደጃ ወዲህ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተመልካች ባገኘላት የቪዲዮ ንግግሯ፡፡
ጦርነቱ ጭንቀትና ጥበት ውስጥ የከተታቸው ዩክሬናውያን፤ በግንባር ላይ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ከሞት ይተርፉ እንደሆነ ወይም ከሚገሰግሱት የሩሲያ ወታደሮች መሸሽ ይኖርባቸው ከሆነ፤ ፍንጭ (ምልክት) ለማግኘት፣ ፊታቸውን ወደ ኮከብ ትንበያ ጠበብት እያዞሩ ይገኛሉ-ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት፡፡
ዩክሬናውያን “የኒውክሌር ጦርነት ይከሰት እንደሆነ፣ ወዳጆቻቸው በአደጋ ላይ ይሁኑ አይሁኑ፣ በግንባር የሚዋጉ ልጆቻቸው በህይወት ይተርፉ እንደሆነ” ለማወቅ ይፈልጋሉ፤ ስትል ፐርል ለኤኤፍፒ አስረድታለች፡፡
የ39 ዓመቷ የቀድሞ ሙዚቀኛና ጦርነቱን ተከትሎ፣ከዩክሬን ሸሽታ ስዊዘርላንድ የገባችው የኮከብ ትንበያ ጠበብቷ ኢሌና ኡማኔትስ፤ “ሩሲያ በማርች 2023 ትፈነዳለች” ስትል ተንብያለች፡፡
100 ዶላር እያስከፈለች በኢንተርኔት የኮከብ ትንበያ ምክር የምትለግሰው አስትሮሎጀሯ፤ በግንባር እየተዋጋ ያለው የባለቤቷ ጉዳይ ያስጨነቃትን ደንበኛዋን አረጋግታ ሸኝታለች፡፡
በኬይቭ የቴሌቪዥን ፕሮዱዩሰር የሆነችው ክሪስቲና፤ በሰኔ ወር ላይ ለኮከብ ትንበያ ጠበብቷ በጻፈችላት የምስጋና ቃል ይኼንኑ አረጋግጣለች።
“ባለቤቴ አሁን ደወለልኝ። ሌሊቱን ከሞት ተርፎ በማደሩ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቧል። ለባለቤቴ እፀልይለት ዘንድ ስላበረታታሽኝ አመሰግናለሁ፤ይህን ሃላፊነት ከክዋክብቱ ጋር በመጋራቴ እፎይታ አግኝቻለሁ።”
በመጨረሻም ፈጣሪ ሰላም ያውርድልን እላለሁ!!

Read 1263 times