Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 October 2012 09:48

ባራክ ኦባማ እና ሚት ሮምኒ አንገት ለአንገት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አሁን ግን ውድድሩ ከሯል፡ ባራክ ኦባማ በግማሽ ነጥብ እየተመሩ ነው
በፕሬዚዳንታዊው ፉክክር የሚነሱ፤ ከባድ ቁምነገሮችና ተራነገሮች
የዛሬ አራት አመት፤ በ7 ነጥብ ልዩነት ያሸነፉት ባራክ ኦባማ፤ ዘንድሮም እስከ መስከረም ድረስ በነበረው የምርጫ ዘመቻ ተፎካካሪያቸው ሚት ሮምኒን በ4 ነጥብ ልዩነት ሲመሩ ቆይተዋል። ከጥቅምት ወዲህ ግን ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ አንገት ለአንገት ሆኗል። ኦባማን ጉድ ያደረጋቸው፤ የቴሌቪዥን የቀጥታ ክርክር ነው። ለወትሮው “አንደበ ርቱዕ ተናጋሪ” ተብለው ይወደሱ የነበሩት ኦባማ፤ መስከረም 23 ቀን በተካሄደው የአንድ ሰዓት ተኩል ክርክር፤ ህይወት ያለው ነገር መናገር ያቅታቸዋል ብሎ ማን ገመተ? ግን አቃታቸው። ንግግራቸው እጅግ ችኮና ለዛ ቢዝ ከመሆኑ የተነሳ፤ ቀንደኛ ደጋፊዎች ሳይቀሩ በኦባማ ተናድደዋል።

ዘወትር ኦባማን በማዳነቅና የኦባማን አሸናፊነት በመተንበይ የሚታወቁ በርካታ ፀሐፊዎችና ጋዜጠኞች በክርክሩ እርር ብለዋል። ደግሞም አይፈረድባቸውም። እስከ ክርክሩ ዋዜማ ድረስኮ፤ የመራጮች ድጋፍ ወደ ኦባማ ያዘነበለ ነበር። ከህዝብ የተሰበሰቡ የናሙና መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ከክርክሩ በፊት ኦባማ መሪነት ነበራቸው (44% ያህል መራጮች የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ ሚት ሮምኒን፤ 49% ያህሉ ደግሞ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ባራክ ኦባማን ይደግፉ ነበር)። በክርክሩ ዋዜማ ላይ የነበራቸው የ5 ነጥብ ብልጫ ግን፤ በክርክሩ ማግስት በአንዴ ተንዶ ጠፋ። ለዚህም ነው የኦባማ አድናቂዎች ከመናደድ አልፈው፣ አለወትሯቸው ፕሬዚዳንቱን አምርረው እስከመተቸት የደረሱት። 
የኒውስዊክ ፀሃፊ ጆ ክሌን፤ ዘወትር ኦባማን በማድነቅ የሚታወቅ ቢሆንም፤ በክርክሩ ማግስት አባማን አላስተረፋቸውም። “በሕይወት ዘመኔ በርካታ የፕሬዚዳንት ክርክሮችን አይቻለሁ” የሚለው ክሌን፤ እንደ ኦባማ አይነት አቅመቢስ ክርክር አጋጥሞኝ አያውቅም ብሏል። “ኦባማ በፈቃደኝነት ትጥቅ የፈታ ይመስላል፤ ደግሞስ ለምንድነው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የማይናገረው?” በማለትም ቁጭቱን ተናግሯል። “ኦባማ፣ የተድበሰበሱ የፖለቲካና የቢሮክራሲ ቃላት ያበዛል” ማለቱ ነው። በኦባማ አድናቂነቱ የሚታወቀው የኤምኤስኤንቢሲ ጋዜጠኛ ክሪስ ማቲው በበኩሉ፤ “ኦባማ የክርክር መድረኩ ላይ ምን ሲሰራ እንደነበር አላውቅም። ወጥሮ ከመከራከር ይልቅ የመጣውን ትችት ተሸክሞ 90 ደቂቃውን ለማሳለፍ አንገቱን ቀብሮ ነበር” ብሏል።
በተቃራኒው ከአፋቸው በሚወጡ ቃላት ሁሉ ትችት ሲቀርብባቸው ለነበሩት ሚት ሮምኒ፤ የክርክር መድረኩ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል - ጠንካራ ተፎካካሪና አስተማማኝ መሪ መሆናቸውን ለማሳየት። የኢኮኖሚና የስራ አጥነት ችግሮችን አንድ በአንድ እየጠቀሱ፤ በዚያውም የብዙ አሜሪካዊያንን ቁስል እየነካኩ፤ የኦባማን ስህተቶችና ውድቀቶች ዘረዘሩ። ደግሞም ኦባማን ማሳጣት ያን ያህል ከባድ አይደለም። ኦባማ የዛሬ 4 አመት ሲመረጡ፤ ለአሜሪካዊያን የገቧቸው የተስፋ ቃላት ብዙ ናቸው። ታዲያ እነዚያ የተስፋ ቃላት የት ደረሱ?
በቀውስ የተመታው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራና በየአመቱ በ4 በመቶ እንዲያድግ አደርጋለሁ ብለው ነበር - ኦባማ። ነገር ግን፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙም አላገገመም - እድገቱ ከሁለት በመቶ በታች ነው። የስራ አጥነትን በአስር ሚሊዮን እቀንሳለሁ ብለው ነበር - ኦባማ። ግን የስራ አጦች ቁጥር አልቀነሰም፤ 23 ሚሊዮን አሜሪካዊያን ስራ አጥ ሆነዋል። ከዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ወጣቶች መካከል፤ ግማሾቹ ብቻ ናቸው የሥራ እድል የሚያገኙት። ታዲያ፤ ሚት ሮምኒ ኦባማን ለመተቸት አለመቸገራቸው ምኑ ይገርማል!
የነዳጅ ውድነት የብዙ አሜሪካዊያን ሕይወት እንደሚነካ የተገነዘቡት ሚት ሮምኒ፤ ኦባማን ተጠያቂ አድርገዋል። “አስር ወይም ሃያ ወፎች ተገድለዋል” በሚል አስቂኝ የአካባቢ ጥበቃ ውንጀላ ሳቢያ፤ የነዳጅ ፍለጋና የቁፋሮ ስራዎች እንደተስተጓጎለ የገለፁት ሮምኒ፤ በዚህም የቤንዚን ዋጋ በአራት አመታት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል። የኦባማ መንግስት ኢኮኖሚውን አነቃቃለሁ በሚል ሰበብ፤ ለበርካታ ኩባንያዎችና ድርጅቶች 800 ቢሊዮን ዶላር ብድር ቢሰጥም ለውጥ አላመጣም። ከልዩ በጀቱ ውስጥ ትልቅ ድርሻ የወሰዱትስ እነማን ናቸው ብለው ይጠይቃሉ ሚት ሮምኒ። ከመንግስት ከፍተኛ ድጎማና ብድር የተሰጣቸው ኩባንያዎች፤ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ግንኙነት ያላቸው (ከፀሐይ እና ከነፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ቁሳቁሶችን እናመርታለን) የሚሉ ኩባንያዎች ናቸው። ብድሩና ድጎማው ተቃውሞ ሲቀርብበት እንደነበረ ይታወቃል። “መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ እየገባና ወገን እየለየ መደጎምም ሆነ ማበደር የለበትም። የነፃ ገበያ ስርዓትን የሚሸረሽር ነው” ተብሎ ተተችቷል። ባራክ ኦባማ ግን፤ ኩባንያዎቹ ለበርካታ አሜሪካዊያን የስራ እድል እየፈጠሩ ነው በማለት ትችቱን ሲያጣጥሉ ቆይተዋል። አሁን ግን በሙሉ ልብ መከራከር አልቻሉም። ብድርና ድጎማ የተሰጣቸው ትልልቅ ኩባንያዎች በኪሳራ ተዘግተዋልና።
ይህም ብቻ አይደለም። ኦባማ፣ የመንግስትን እዳ በግማሽ ለመቀነስ ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን፤ የኢኮኖሚ ማነቀቂያና የችግረኞች መደጎሚያ እያሉ የሚመድቡት በጀት ከፍተኛ በመሆኑ፤ የመንግስት እዳ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም። 10 ትሪሊዮን የነበረው እዳ አሁን 16 ትሪሊዮን ደርሷል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አለመነቃቃቱ፤ የሥራ አጥነት ችግር አለመቃለሉ፣ የነዳጅ ዋጋና የኑሮ ውድነት መባባሱ፤ የመንግስት እዳ ጣሪያ መንካቱ... ተደማምረው ለባራክ ኦባማ ራስ ምታት ሆነዋል። አሳማኝ መከራከሪያና ምላሽ ለማቅረብ የተቸገሩትም በዚህ ምክንያት ነው። በእርግጥ፤ “ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ከጆርጅ ቡሽ የወረስነው የኢኮኖሚ ቀውስ ካሰብነው በላይ ውስብስብ ስለነበር፤ የተመኘነው ያህል እድገት አልተገኘም” ብለው ተከራክረዋል። ብዙዎችን ሊያፅናና የሚችል መከራከሪያ አይደለም። በዚያ ላይ፤ “ላለፉት አራት አመታት በፕሬዚዳንትነት የቆዩትኮ እርስዎ ነዎት” በማለት ሚት ሮምኒ አፀፋውን ይመልሳሉ። “የኢኮኖሚ እድገት እየወረደ እንጂ እየተሻሻለ አይደለም” የሚሉት ሚት ሮምኒ፤ “ከካቻምናው የአምናው ወርዷል፤ ከአምናው ደግሞ የዘንድሮው ያንሳል” በማለት ኦባማን ተችተዋል።
ሥራ አጥነትን በተመለከተ፤ “ባለፉት አራት አመታት፣ አምስት ሚሊዮን የስራ እድሎች ተፈጥረዋል” በማለት ኦባማ መከራከሪያ ቢያቀርቡም፤ ብዙም አልጠቀማቸው። “23 ሚሊዮን አሜሪካዊያን በስራ አጥነት ተቸግረዋል” በማለት ሚት ሮምኒ አፀፋውን መልሰዋላ። በየአቅጣጫው ባራክ ኦባማ የገጠማቸው ፈተና እጅግ ከባድ ነው። በአገሪቱ የ50 አመታት ታሪክ ውስጥ፤ ከ7 በመቶ በላይ ሥራ አጥነትንና ቀርፋፋ ኢኮኖሚን ተሸክሞ በድጋሚ ለማሸነፍ የቻለ ፕሬዚዳንት የለም። አሁን ያለው የስራ አጥነት መጠን ደግሞ ወደ 8 በመቶ ገደማ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። የአሜሪካ ፖለቲካ፤ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በሁለት አቅጣጫዎች ተወጥሯል። “ቲፓርቲ” እና “ኦኩፓይ” የሚባሉት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች፤ የዚህ ውጥረት ምልክቶች ናቸው።
አፍቃሬ ካፒታሊዝም የሆኑ ዜጎች የተሰባሰቡበት የቲፓርቲ እንቅስቃሴ፤ የመንግስት ቅነሳ ያስፈልጋል ባይ ነው። “መንግስት ለተለያዩ ግዙፍ ባንኮችና ለትልልቅ ኩባንያዎች፤ እንዲሁም ለችግረኞችና ለአናሳ ማህበረሰቦች፣ ወገን እየለየ ድጎማና ብድር መስጠት የለበትም” ይላሉ የቲፓርቲ ሰዎች። የዜጎች ገቢ እና የቢዝነስ ስራዎች ላይ የተጫነው የታክስ ሸክም እንዲቀነስም ይጠይቃሉ። በቲፓርቲ እንቅስቃሴ ውስጥ ተደጋግመው ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል፤ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የነፃ ገበያ ተከራካሪ ፍሬደሪክ ባስቲያት፤ ኖቤል ተሸላሚው ኢኮኖሚስት ፍሬደሪክ ሃየክ፣ እንዲሁም የካፒታሊዝም አቀንቃኟ ፈላስፋና ደራሲ አየን ራንድ ይገኙበታል።
“ኦኩፓይ ወልስትሪት” በሚል የተጀመረው ሌላኛው እንቅስቃሴ ደግሞ፤ የመንግስት ቅነሳን ይቃወማል። ሶሻሊስት ፓርቲዎችን በማማከር የሚታወቁት ኖቤል ተሸላሚ ኢኮኖሚስት ጆሴፍ ስቲግሊትዝ፣ እንዲሁም ፊልም ሰሪ ማይክል ሙር፤ የ”ኦኩፓይ” ንቅናቄን በመደገፍ ይታወቃሉ። “መንግስት ለባንኮችና ለኩባንያዎች (ለሃብታሞች) ድጋፍ ከመስጠት ተቆጥቦ፤ ለችግረኞች ድጎማና ድጋፍ መስጠት አለበት። ችግረኞችን ለመደገፍ ሃብታሞች ላይ ተጨማሪ ታክስ ይጫንባቸው” ባዮች ናቸው የእንቅስቃሴው መሪዎች።
የሚት ሮምኒና የባራክ ኦባማ ፉክክርም፤ ከእነዚህ ተቃራኒ አቅጣጮች ጋር ይዛመዳል። “አሜሪካዊያን፤ ከአመት ገቢያቸው ውስጥ ግማሽ ያህሉን በተለያየ የታክስ አይነት እየተነጠቁ ለመንግስት ይገብራሉ” የሚሉት ሚት ሮምኒ፤ ከፍተኛውን የታክስ ክፍያ ወደ 20 በመቶ እንደሚያወርዱት ተናግረዋል። “የመንግስት ቢሮዎችንና የሰራተኞቹን ቁጥር በመቀነስ፤ እንዲሁም የመንግስትን ድጎማና ብክነት በማስወገድ፤ የመንግስትን ወጪ (በጀት) እቀንሳለሁ” ይላሉ። ለምሳሌ የአካባቢ ጥበቃ በሚል ሰበብ፣ ለወፎች ጥናትና እንክብካቤ የሚመደበውን በጀት እሰርዛለሁ ብለዋል። የሕዝብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለሚባሉት ተቋማት የሚሰጣቸው የመንግስት ድጎማም እንደሚቋረጥ ሚት ሮምኒ ገልፀዋል። የመንግስት ወጪ በመቀነስ የበጀት ጉድለትን ማስወገድ ይቻላል የሚሉት ሚት ሮምኒ፤ በታክስ ቅነሳ ኢኮኖሚው ሲነቃቃና የስራ እድሎች ሲፈጠሩ፤ የታክስ ከፋዮች ቁጥር ይበራከታል፤ የመንግስት ገቢም ይጨምራል፤ እናም እስካሁን የተከማቸውን የመንግስት እዳ ማቃለል ይቻላል ሲሉ ይከራከራሉ። በምንም አይነት መንገድ፤ የትኛውም አይነት ታክስ አይጨመርም በማለትም ቃል ገብተዋል።
ባራክ ኦባማ በበኩላቸው፤ “ከ200ሺ ዶላር በታች አመታዊ ገቢ ለሚያገኙ ዜጎች ታክስ እቀንሳለሁ፤ በሃብታሞች ላይ ግን ታክስ እጨምራለሁ” ይላሉ። “ሚት ሮምኒ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በመዘንጋት ሃብታሞችን ብቻ ለመጥቀም ይፈልጋሉ” የሚሉት ኦባማ፤ ከዳር እስከ ዳር የታክስ መጠን ወደ 20 በመቶ መውረድ የለበትም ሲሉ ይከራከራሉ። ለምን? “ታክስ ከተቀነሰ፤ የመንግስት ገቢ በጣም ይቀንሳል። በዚህም ምክንያት መንግስት ችግረኞችን መደገፍ ያቅተዋል። የመንግስት እዳም ሊቃለል አይችልም” በማለት ሚት ሮምኒን ይተቻሉ።
ሚት ሮምኒ፣ ለኦባማ ትችት ምላሽ ለመስጠት አልተቸገሩም፤ “የባራክ ኦባማ እቅድና ሃሳብ ለውጥ እንደማያመጣ ባለፉት አራት አመታት አይተነዋል። ብዙ ሚሊዮን አሜሪካዊያን ለስራ አጥነት ተዳርገዋል” በማለት ጣታቸው ኦባማ ላይ ይቀስራሉ።
በእርግጥ ፉክክሩ የበረታባቸው ባራክ ኦባማ፤ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሚት ሮምኒን ለማጣጣል ወደኋላ እንደማይመለሱ አያጠራጥርም። “በአመት ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያገኙት ሚት ሮምኒ፤ በጣም ሃብታም ከመሆናቸው የተነሳ የብዙ አሜሪካዊያንን ችግር አይገነዘቡም፤ እኔ እሻላችኋለሁ” ይላሉ - ኦባማ። እንዲህ አይነቶቹ የኦባማ ቅስቀሳዎች ውጤታማ ናቸው ማለት ይቻላል። በርካታ አሜሪካዊያን በሚት ሮምኒ ላይ እምነት ለመጣል ሲቸገሩ ይታያሉና። ነገር ግን፤ ብዙ አሜሪካዊያን ኦባማን አቅፈው ለመቀበል ፍቃደኞች ናቸው ማለት አይደለም። ብዙ አሜሪካዊያን በኦባማ ላይ የነበራቸው እምነት ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መጥቷል - የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለመሻሻሉና ሥራ አጥነት ባለመቃለሉ ምክንያት። እናም፤ ከአራት አመታት በፊት ተፎካካሪያቸውን በሰፊ ልዩነት እየመሩ ሆይሆይ ተብሎላቸው በምርጫ ለማሸነፍ የቻሉት ኦባማ፤ የዘንድሮው ምርጫ ከባድ ፈተና ሆኖባቸዋል።
የዛሬ አራት አመት ምርጫኮ፤ ለኦባማ ሽርሽር ነበር ማለት ይቻላል። ለወራት በዘለቀው የምርጫ ዘመቻ፤ በመራጮች ዘንድ የኦባማ ተቀባይነት ከፍተኛ ነበር። የያኔው ተፎካካሪያቸው ጆን ማኬን ከባራክ ኦባማ ጋር የሚቀራረብ ተቀባይነት ለማግኘት የቻሉት በመስከረም ወር ለሁለት ሳምንታት ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ፤ ለበርካታ ወራት በተካሄደው የምርጫ ዘመቻ፤ ባራክ ኦባማ ያለማቋረጥ ሲመሩ ነበር። በተለይ ከመስከረም በኋላ የኦባማ መሪነት እየሰፋ ሄዶ፤ በምርጫው እለት በሰባት ነጥብ ልዩነት አሸንፈዋል።
ዘንድሮ ግን፣ ፉክክሩ አልጋ ባልጋ ሳይሆን አንገት ለአንገት ሆኗል። በእርግጥ አጀማመሩ ለኦባማ ምቹ ይመስል ነበር። ከተፎካካሪያቸው ከሚት ሮምኒ የተሻለ ድጋፍ በማግኘት እየመሩ ከመቆየታቸውም በተጨማሪ፤ በመስከረም ወር ልዩነታቸውን በማስፋት መሪነታቸውን ለማጠናከር ችለው ነበር። ለምሳሌ መስከረም 20 ላይ የተሰበሰቡ የመራጮች አስተያየት እንደሚያሳየው፤ በ4 ነጥብ ልዩነት እየመሩ ነበር (ባራክ ኦባማ በ49%፣ ሚት ሮምኒ በ45%)። ከዚያ ወዲህ ግን፤ ፉክክሩ ትንቅንቅ ሆኗል። መስከረም 23 ቀን በተካሄደው ክርክር፤ ሁሉም ነገር ተቀያየረ። ተፎካካሪዎቹ በቴሌቪዥን ከሚያካሂዷቸው ሶስት ክርክሮች መካከል የመጀመሪያውን ለማካሄድ ሲዘጋጁ፤ ባራክ ኦባማ በአንደበ ርቱዕነት ገንነው እንደሚወጡ ተገምቶ ነበር። 70 ሚሊዮን ያህል አሜሪካዊያን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የተከታተሉት የኦባማና የሮምኒ ክርክር ግን፣ ከተጠበቀው ውጭ የተገላቢጦሹ ሆነና አረፈው። ሮምኒ ጠንካራ ተፎካካሪነታቸውን ባስመሰከሩበት አስገራሚ ክርክር የተነሳም፤ የኦባማ መሪነት ተጠራርጎ ጠፋ። እንዲያውም በጠባብ ልዩነት ሮምኒ መሪነቱን ለመያዝ ችለዋል። በእርግጥ ሰሞኑን ማክሰኞ እለት በተካሄደው ሁለተኛው ክርክር፤ ባራክ ኦባማ ድክመታቸውን አስተካክለው ብርቱ ተከራካሪ ሆነው ቀርበዋል። ነገር ግን፤ ሚት ሮምኒም የዚያኑ ያህል በብርታት ተከራክረዋል።
በክርክሩ መድረክ ከተነሱት ቁምነገሮች በተጨማሪ፤ የተፎካካሪዎቹና የሚስቶቻቸው የልብስ አይነት ከነዋጋው፣ የጋዜጦች ርእስ ሆኗል። ቱጃሩ ሚት ሮምኒ፣ የጋዜጦቹ የመጀመሪያ ኢላማ መሆናቸው አይገርምም። ሚስታቸው አን ሮምኒ፣ 1700 ዶላር ገደማ የሚያወጣ ቀሚስ አድርገው ወደ ክርክሩ አዳራሽ እንደገቡ ዩኤስ ዊክሊ ዘግቧል። “ቅንጦተኛ” ያስብላል? ፎክስኒውስ በበኩሉ፤ የባራክ ኦባማ ሚስት ሚቼል ኦባማ ያደረጉት ልብስ፤ ከ3ሺ ዶላር በላይ ያወጣል ብሏል - በዚያውም ኦባማን ለማጣጣል። ይህም ፉክክር መሆኑ ነው።
የሆነ ሆኖ፤ በመጪው ማክሰኞ በሶስተኛው ክርክር ምን እንደሚፈጠር ባይታወቅም፤ የሁለቱ ተወዳዳሪዎች ፉክክር፤ እንዲህ እንደተካረረ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል። በተለያዩ ተቋማት የተሰበሰሰ የመራጮች አስተያየት ተጨምቆ በማየት፤ ኦባማና ሮምኒ አንገት ለአንገት እንደተያያዙ ማረጋገጥ ይቻላል። ሪል ክሊር ፖሊቲክ ሐሙስ እለት ይፋ ባደረገው አማካይ ውጤት፤ ኦባማና ሮምኒ በመራጮች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እጅግ ተቀራራቢ እንደሆነ ይመሰክራል። ሚት ሮምኒ 47.4 በመቶ፤ ባራክ ኦባማ ደግሞ በ46.9 በመቶ ፉክክሩ ተጋግሏል።
ሁለት ሳምንት በቀረው ምርጫ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት፤ ሁለቱ ተፎካካሪዎች የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። እስካሁን እንዳደረጉት፤ የራሳቸውን መልካም ጎን ለማግዘፍና ተፎካካሪያቸውን ለማጣጣል አገሪቱን በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ያጥለቀለቋታል። መራጮችን ለመማረክና ድጋፍ ለማግኘት፣ ከ60 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አሜሪካዊያን የስልክ ጥሪ ያደርሳሉ - የምረጡኝ ዘመቻ የሚያካሂዱ ቀስቃሾች። ። ከመቶ ሚሊዮን ለሚበልጡ መራጮች፤ በኢሜይል፣ በፌስቡክና በትዊተር መልእክት ይልካሉ። የበርካታ ሚሊዮን አሜሪካዊያን በር ይንኳኳል። ተፎካካሪዎቹ፣ ምርጫውን በአሸናፊነት ለመወጣት፤ ያለ የሌለ አቅማቸውን አሟጥጠው ይጠቀማሉ። ለዚህ ሁሉ ግን ገንዘብ ያስፈልጋል። አሁን ነው ገንዘብን በብልሃት መጠቀም!
በገንዘብ በኩል፤ ባራክ ኦባማ ከተፎካካሪያቸው የተሻለ አቅም አላቸው። ለምርጫ ዘመቻው ግማሽ ቢሊዮን (500 ሚ.) ዶላር ገደማ ከደጋፊዎች የሰበሰቡት ኦባማ፤ እስካሁን 400 ሚ. ያህሉን ለምርጫ ዘመቻው እንደተጠቀሙበት ይገመታል። ሚት ሮምኒ በበኩላቸው ወደ 350 ሚ. ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ አግኝተዋል። ከተፎካካሪዎቹ በተጨማሪ፤ ብዙ ገንዘብ የሰበሰቡ ማህበራትም አሉ። በየፊናቸው የሚስማማቸውን ተፎካካሪ እየደገፉ፤ የማይስማማቸውን ደግሞ እየተቃወሙ፤ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ቀን ከሌት ያሰራጫሉ - እስካሁን ወደ 300 ሚ. ዶላር ገደማ ወጪ አድርገዋል።
ይህም ብቻ አይደለም። ዲሞክራቲክ ፓርቲና ሪፐብሊካን ፓርቲ ለምርጫ ዘመቻው ባቋቋሟቸው ኮሚቴዎች፤ 1.3 ቢሊዮን ዶላር አሰባስበዋል። ለኮንግረስና ለሰኔት የሚፎካከሩ የሁለቱ ፓርቲዎች ፖለቲከኞች በየግላቸው ያሰባሰቡት ገንዘብም፤ ወደ 1.5 ቢሊዮን ይጠጋል። በአጠቃላይ የዘንድሮው ምርጫ ከ4 ቢ. ዶላር በላይ ይፈስበታል።

Read 4880 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 10:02