Saturday, 20 August 2022 12:38

የሰለሞን ቦጋለ “የራስ መንገድ” ፊልም ሰኞ ይመረቃል፤ በ2ሺ ብር የመግቢያ ዋጋ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

          ገቢው በ2 ቢ. ብር ለሚገነባው የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል ማስጀመሪያ ይውላል

      ድርሰትና ዝግጅቱ የአርቲስት  ሰለሞን ቦጋለ የሆነው “የራስ መንገድ”የተሰኘው  ፊልም የፊታችን ሰኞ  ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በስካይ ላይት ሆቴል ይመረቃል፡፡
የምረቃ ሥነሥርዓቱ የመግቢያ ዋጋው 2ሺ ብር ሲሆን እራትን ይጨምራል ተብሏል፡፡
በዕለቱ የሚሰበሰበው ገቢም በ2 ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባው ግዙፉ የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል ማስጀመሪያ እንደሚውል አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያውያን የኩላሊት ታማሚዎች፣ በሀገራቸው በአቅማቸው የሚታከሙበትን ሆስፒታል ለመገንባት፣ በህብረት ለበጎ ድርጅት፣  በለገጣፎ 60 ሺ ካሬ ቦታ መረከቡን አርቲስቱ ሰሞኑን ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ላይ ተናግሯል፡፡
የኩላሊት ህክምና ሆስፒታሉን ለመገንባት ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገለፀ ሲሆን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያግዙ 14 የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች መቀረጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከእነዚህም መካከል አንዱ የፊታችን ሰኞ  በስካይ ላይት ሆቴል፣ እራትን ጨምሮ በ2ሺ ብር የመግቢያ ዋጋ የሚከናወነው የፊልም ምርቃት ሥነሥርዓት ነው፡፡
የምረቃ ሥነሥርዓቱ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በቀጥታ የሚሰራጭ ሲሆን የመግቢያ ትኬቱ በአሜዚንግ ማስታወቂያና ኤቨንት ቢሮ ማግኘት እንደሚቻል ተነግሯል፡፡
በአርቲስት ሰለሞን ቦጋለና ጓደኞቹ ተነሳሽነት ለሚገነባው የኩላሊት ታማሚዎች ሆስፒታል፣ ከወዲሁ ታዋቂና አንጋፋ አርቲስቶች በነፍስወከፍ እስከ 40 ሺ ብር እያዋጡ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መላ ኢትዮጵያውያን የሆስፒታሉ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አውን ይሆን ዘንድ የመግቢያ ትኬቱን እንዲገዙ አርቲስት ሰለሞን  ጥሪውን አቅርቧል፡፡

   

Read 22042 times