Sunday, 14 August 2022 00:00

“እንደየስራው ለእያንዳንዱ” ነው ፍትህም እውነትም።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 “አባቶች ጎምዛዛ ፍሬ በሉ፤
የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ።”… እያላችሁ ምሳሌ የምታነበንቡት ምን ለማለት ነው?
ከእንግዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ምድር አትመስሉም።…

“What is wrong with you, who recite this proverb on the soil of Israel, saying:
The fathers ate unripe fruit
and the sons’ teeth were blunted.
ምን ለማለት ፈልጎ ነው? ወላጆች በሰሩት ሃጢያት ወይም፣ አያቶች በፈፀሙት ጥፋት፣ ልጆች ተወነጀሉ። የልጅ ልጆች ተቀጡ።
አባቶች የልባቸውን አደረሱ። አያቶች የምኞታቸውን አደረጉ።  ወላጆቻቸው ያሰኛውን የጣፈጣቸውን በበሉ፤ የልጆች ጥርስ ጠቆረ። በለዘ። ተሸራረፈ እንደማለት ነው?
ወላጆች “ቁርጥ ሥጋ” እያማረጡ በበሉና በጠገቡ፤ የልጅ ልጆች በሆድ ቁርጠት ተንገበገቡ ለማለት ነው?
ለቀልድና ለጨዋታ ታስቦ የተፈጠረ የዘመናችን አባባል አይደለም። ድንገት የተራገበ እለታዊ የማላገጫ አባባል ሊመለስ ይችላል። ማላገጫ ቢሆንማ፣ በማግስቱ ተረስቶ ይቀር ነበር። ለአንድ ቀንም ከዘለቀ ነው።
 ዛሬ ዛሬ፣ ሁሉንም ነገር ጊዜያዊ እያደረግነው አይደል! ድንገት እየተግለበለበ ይናፈሳል። በሚግስቱ ይረግባል። ይነፍስበታል። እንደገና እንደ አዲስ ቀሰቅሰው እስኪያራግቡት ድረስ፤ ማን ያስታውሰዋል?
ድሮ ድሮም ወረት ነበር። ነገር ግን፣ “ወረት” ብለው የሚያናንቁት ነገር፣ ከሳምንት በላይ እንደማይቆይ ለመግለጽ ነበር። ከአንድ ወር በላይ እድሜ የለውም እንደ ማለት ነው ወረት ማለት። ዛሬ ግን፣ የአንድ ቀን እድሜም በጣም ረዥምና አሰልቺ እየሆነ ነው።
“ወላጆች በቁርጥ ስጋ ተዝናኑ። ልጆች በሆድ ቁርጠት ተያዙ” የሚል ሃሳብ ዛሬ እንደ ቁም ነገር ቢቆጠር እንኳ፣ ለአንድ ቀን ብቻ ነው።
ያኔ በጥንቱ ዘመን ግን፣ ከቀን ወደ ቀን እየተዛመተና ስር እየሰደደ  ለብዙ ዓመታት ተተርቶበታል። የዘመኑን መራራ ኑሮ ለመግለጽ የሚያገለግል አባባል ሆኗል። የብዙ ሰዎችን አንጀት የሚያሳርር አባባል።
አባቶች ጥሬውን በሉ። የልጀችም ጥርሶች ተበሉ።
“ምሳሌያዊ አባባል”፣ ነገርን አጉልቶ አግንኖ ማሳየት ይችላል። ከአነጋገር ለዛ ጋር ሲሆን ደግ ጉልበቱ ይጨምራል። ሊያናንቁት ለሚሞክሩ አይመቻቸውም። በቁጣ ላባርረው ቢሉም ይከብዳቸል። ምሳሌያዊ አባባል፤ አነጋገርን አለዝቦ ቅሬታን አምርሮ ለመግልጽ ያገለግላል።
የዘመኑ ሰዎች ደግሞ እጅግ አምርረው ለመናገር ከበቂ በላይ ምክንያት ነበራቸው።
ነገር ግን፣ ምሬታቸው በአምላክ ላይ ነውና፣ አነጋገራቸው ላይ መጠንቀቅ አለባቸው። ምሳሌያዊ አባባል መጠቀማቸውስ ለዚህ አይደል?
የዘመኑ ሰዎች፣ “የአያቶች ተግባር የልጅ ልጆች እዳ እየሆነ ነው” ብለው ማሰባቸው አይገርምም። (አዲስ የአማርኛ ትርጉም ተብሎ የታተመው መጽሐፍም በዚህ ይስማማል።) በሙሴ ትምህርት ውስጥ ተመሳሳይ ሃሳብ እንደተጻፈም ተጠቅሷል።
“እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የአባቶችን ኃጥያት በልጆች ላይ የማመጣ…” የሚል ማስጠንቀቂያ ተጽፏል። ይህን የሙሴ ትምህርት ቃል በቃል ከተረጎሙት፣ በጥሬው ከጎረሱት፤ ምሬትን እንደሚፈጥር አያከራክርም።
ይህን ማስጠንቀቂያ አምነው የተቀበሉ ይመስላሉ፤ በያኔው ዘመን በኑሮ መከራ የተማረሩ ሰዎች። “አያቶች አጠፉ፤ የልጅ ልጆች ተቀጡ” የሚል መልዕክት ያለው አባባል እጅግ የተስፋፋውም በዚህ ምክንያት ነው። ግን መረር ያለ ቅሬታ ጭምር በውስጡ ይዟል።
ያለ ጥፋታችን አበሳችንን በላን፤ ይህም ቀና የፍትህ መስመር አይደለም የሚል ነው ቅሬታቸው።
በማን ላይ ነው ቅሬታቸው? እስከ አራት ትውልድ የወላጆችን ኃጥያት በልጆች ላይ በሚያመጣ አምላክ ላይ! በለዘብታ የቀረበው ምሬት የብዙዎችን ኑሮና ሃሳብ የሚገልጽ ከመሆኑ የተነሳ፣ ከሦስቱ “ትልልቅ ነብያት” መካከል የሁለቱን ትኩረት ስቧል።
ኤርሚያስ፤ የድሮውን የሙሴ ትምህርት ፊት ለፊት አያፈርስም።
 ነገር ግን፤  በዝምታም አያልፈውም። ወደፊት ሰው ዳግመኛ እንደማይማረር ይተነብያል። እንዲህ  አይነቱን አባባል የሚሽር አዲስ ተፈጥሯዊ ትምህርትና አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚገለጥ ኤርሚያስ ያበስራል።
 “አባቶች ያልበሰለ ፍሬ በሉ። የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ” የሚለውን አባባል የሚያስቀር ጊዜ እንደሚመጣ ይገልጻል። እያንዳንዱ ሰው በገዛ በደሉ ቅጣት ይቀበላል። ጎምዛዛውን ፍሬ የሚበላ ጥርሶቹ ይጠዘጥዙታል በማለት፣… የፍትህ ቀና መንገድን ያውጃል- የኤርሚያስ ትረካ። ይህም ብቻ አይደለም።
 በአያቶች ተግባር የልጅ ልጆች ተቀጡ የሚለው ቅሬታ እጅግ ከመስፋፋቱ የተነሳ፣ የኤርሚያስ ትምህርት በቂ አይደለም። ሕዝቅኤልን የከነከነውና ሰፊ ማብራሪያ ለመስጠት የፈለገውስ ለምን ሆነና!
…ልጅ በአባቱ ኃጥያት አይቀጣም።
አባትም በልጁ ኃጥያት አይቀጣም።
ጻድቁ የጽድቁን ፍሬ ያገኛል።
ኃጥያተኛው የኃጥያቱን ዋጋ ይቀበላል።
የሚል ነው የሕዝቅኤል ምላሽ። ግን አሳምኗቸዋል?
ታሪኩ እንዲህ ነው።  ሕዝቅኤል በስደት ባቢሎን ውስጥ ሆኖ ነው የሚብሰለሰለው። ነገሩ የሚጀምረው ከሕዝቅኤል በፊት፣  እዚያው ከምድረ ባቢሎን ግድም ነው። ከሺ ዓመታት በፊት ነው።
እንግዲህ ኃይማኖታዊው ትረካ እንደሚገልፀው ከሆነ፣ የእስማኤል የይስሐቅ አባት፣ ማለትምየኤሳውና የያዕቆብ አያት አብርሃም፣ ታሪኩን የሚጀምረው በስደት ነው።
ዛሬ ኢራቅ ተብሎ በሚታወቀው በጥንታዊ የስልጣኔ አካባቢ ነው፤ አብርሃም የተወለደው። ከአብርሃም በፊት ያለው ትረካ ከሞላ ጎደል  እዚያው በጥንታዊ ኢራቅ ላይ ያተኮረ ነው።
 በሰሜን ኢራቅ እነ ነነዌ፣ ካለህ እና ኦሶር የተሰኙ ከተሞችን ይጠቅሳል።
በማዕከላዊ ኢራቅ የባቢሎን ገናናነትን አግዝፎ ይተርካል።
በደቡብ ኢራቅም “ኢሬች” ወይም ኢሩክ የተሰኘችው ጥንታዊ ከተማ ተጠቅሳለች።
“የዓለማችን የመጀመሪያ ትልቅ ከተማ” የሚል ማዕረግ በተመራማዎች የተሰጣት ኢሩክ፣ ለዛሬ የአገሪቱ ስም መነሻ እንድትሆን ተመርጣለች:: ኢራቅ እንዲሉ ነው። ለማንኛውም፣ ከዚህች ከተማ አጠገብ ሌላ ዝነኛ የጥንት ከተማ  አለች። የዛሬ 4000 ዓመት ገደማም ከሌሎች ሁሉ በልጣ ገነነች። ዑር ትባላለች። ይሄ፣ በቁፋሮ፣ በምርምርና በሳይንሳዊ ጥናት የተገኘ እውቀት ነው።
በሃይማኖታዊ ትረካ መሰረት ደግሞ፣ አብርሃም ከዑር ከተማ ተነስቶ የስደት ጉዞ የጀመረው የዚያ ዘመን ገደማ ነው። ፍልስጥኤም እና እስራኤል ወደ ምንላቸው አካባቢዎች መጣ።  ኑሮው ግን አልሰከነም። ክፉ ድርቅ ወይም ረሃብ ተፈጠረና ወደ ግብፅ ተሰደደ። እንደገና ተመለሰ።
በተመሳሳይ ምክንያት ከነቤተሰቦቹ ወደ ግብፅ የተሰደደው ያዕቆብ ግን፣ ኑሮውን እዚያው አደረገ። ልጆቹና የልጅ ልጆቹም እንደዚያው። እስከ ሙሴ ዘመን ድረስ ለ400 ዓመታት ማለት ነው።
ያው፤ እንደገና መከራ ገጠማቸው። ከግብፅ በስደት ወደ ዛሬው የፍልስጤም የእስራኤል አካባቢ በአስቸጋሪ የመከራ ጉዞ ተንከራተቱ።
“የተመረጠ ሕዝብ፣ ወደ ቃል ኪዳን ምድር ገባ” የሚል አስደሳች የትረካ መደምደሚያ አልተፈጠረም። የመከራው ብዛትና ዓይነት ተዉት። ወረራ፣ጦርነት፣ረሃብ፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣…. ማለቂያ የለውም።
ትንሽ እርጋታና ሰላም የተገኘው ከንጉሥ ዳዊት በኋላ እንደሆነ ትረካው ይጠቁማል። የዛሬ 2900 ዓመት መሆኑ ነው። ግን ብዙም አልቆየም። አገሬው ለሁለት ተከፈለ።  ጦርነት፣ አመፅ፣ ጭካኔና ግፍ ቁጥር ስፍር የለውም። ፋታ አይሰጥም። ያነሰ ይመስል ሌላ መዓት መጣ።
የዛሬ 2700 ዓመት ገደማ፣ የአሲሪያ ንጉስ ሰናቸሪብ እስራኤልን ወረረ። ልዩ ጥላቻ ኖሮት አይደለም። ዋና ከተማውን በነነዌ አድርጎ ግዛቱን እስከ ቱርክ፣ ግብፅና ኢራን ድረስ እያስፋፋ ነበር። እንዲያውም ከቀደምቶቹ ጦረኛ ንጉሦች ጋር ሲነፃፀር ሰናቸሪብ ለዘብ ያለ ነው። እንደባቢሎን ንጉሦች በከተማ ግንባታ ላይ የማተኮር ፍቅር አድሮበታል። ግንባታ፣ በትንሹም ቢሆን ከጦርነት ሱስ ያዘናጋል። ደግሞም ነነዌን አሳምሮ ገንብቷታል።
እንዲያም ሆኖ ከጦርነት አልራቀም። ያው፣ ወደ እስራኤልም ዘምቷል። የንጉሡ ጦር አገሬውን አተራምሶ የገደለውን ገድሎ ከነዋሪዎቹ መካከል ሩብ ያሉ በምርኮና በበእስር ይዞ ወደ ኢራቅ አጋዛቸው። ኢየሩሳሌም ከተማ ለትንሽ ነውየተረፈችው። የእድል ጉዳይ ነው እንጂ፣ ሰናቸሪብ ለዘብተኛ ነኝ ቢልም እንኳ፣ በጭካኔ የንጉሡ ጦር ለምንም የሚመለስ አልነበረም።
እንዲያውም፣ ሰናቸሪብ ተደርጎ የማይታወቅ ነገር አድርጓል። ባቢሎንን አፍርሷል።
የትኛውም ሃይለኛ ንጉሥ ባቢሎንን በወረራ ቢያሸንፍ፣ የባቢሎን ወዳጅና አለኝታ ይሆናል እንጂ ከተማዋን አያፈርስም።
ስናቸሪብም እንደተለመደው ባቢሎንን ካሸነፈ በኋላ፣ ከተማዋን አልዘረፈም፤ አላፈረሰም። እዚያው ከከተማዋ ውስጥ ንጉስ ሾመላት።
 ግን ብዙ ሳይቆይ አመፅ ተፈጠረ። ሴናቸሪብ፣ የራሱን ልጅ በባቢሎን ላይ አነገሰ። አላፈረሳትም። ከተማዋን ይወዷታል። እንደ አርአያ ያከብሯታል። እንደገና ሌላ አመጽ ተቀስቅሶ ጦርነት ተካሄደ። የሴናቸሪብ ልጅ ተገደለ።
ሰናቸሪብ ባቢሎን ላይ ብቻ ሳይሆን እስከታች እስከ ፋርስ ባሕረሰላጤ ድረስ ከከተማ ከተማ ዘመተባቸው። ባቢሎንን ግን፣ ፈጽማ እንድትፈርስና እንድትቃጠል ወሰነ። ቀሪውን ፍርስራሽ ትቶ እንዲሁ ለመሄድ አልፈለገም። ከታላቁ ወንዝ የተጠለፉና ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ ቦዮችን በርግዶ በውሃ አጥለቀለቃት።
ታዲያ ኢየሩሳሌም ከሴናቸሪብ ወረራ መትረፏ ትልቅ እድል አይደለም?
አስገራሚው ነገር፣ ባቢሎን ፈርሳ አልቀረችም። እንዲያውም፤ ባቢሎንን እንደገና እንደ አዲስ መገንባት የጀመረው የሴናቸሪብ ልጅ ነው። ከሰሜንም ከደቡብም፣ ባቢሎንን እንደ አርአያ የሚከብሯት ከተማ ስለሆነች ጨክነው አይጨክኑባትም። ከጎኗ የሚሰለፉ ወዳጆችም አታጣም። ደግማ ደጋግማ የማንሰራራት አቅሟም አልተንጠረጠረም። በእርግጥም ቶሎ አንሰራርታለች።
በናቡብላጸር ዘመን ባቢሎን ዳግም በጣም ገነነች። ንጉሷም የአሲሪያ ከተሞች ላይ ዘመተባቸው።
የነነዌ ንጉስ ሰናቸሪብ ባቢሎን ላይ የፈጸማቸው ነገሮች እንደገና ተደገሙ- በራሷ በነነዌ ላይ።
 የባቢሎን ንጉስ ናቡብላጸር ወደ ነነዌ ዘመተ። አፈራረሳት። አቃጠላት።
የነነዌን አመድ ይዤ ነው የምመለሰው ብሎ እንደማለ፣ በመዳፉ አመድ አፈሰ። በነነዌ ንጉስ የተገነቡ ቦዮችን ተጠቅሞ ነነዌን አጥለቀለቃት። ታላቋ የነነዌ ከተማ እንደገና የማንሰራራት እድል አላገኘችም።
የናቡብላፀር ልጅ ከነገሰ በኋላም የባቢሎን ኃያልነት ገነነ እንጂ አልቀነሰም። ናቡከደነፆር ይባላል። ግዛቱን እስከ ግብፅ ድረስ አስፋፍቷል። በኢየሩሳሌም አመጽ የተነሳበት ጊዜም፣ የንጉሡ ጦር ዘመተባት። ግን አላፈረሳትም። ከእዚያው አገር አዲስ ንጉሥ መርጦ ሾመ።
ከኢየሩሳሌም ሶስት ሺ ታዋቂ ሰዎችንና ልጆችን በግዞት ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንደገና ዓመጽ ተፈጠረ። የናቡከደነፆር  ጦር ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ። ግንቦቿን ሁሉ አፈረሰ። ቤተመቅደሷን ጭምር ከተማዋን አቃጠለ።
ብዙ ሺ ነዋሪዎችን አስሮ ወሰደ። የዛሬ 2600 ዓመት ነው።
ታዲያ የዚያ አካባቢ ነዋሪዎች፣ በመከራ ብዛት ቢማረሩ ይገርማል? ምን አጠፋን? ምን በደልን? ብለው በእሮሮ ቢጮሁ ይፈረድባቸዋል?
ብንፈርድባቸው ያን ያህልም አዲስ አይሆንባቸውም።
“ገና ሳንወለድ ነው የተፈረደብን። ወደ ጦርነት ወደ ስደት ነው የተወለድነው። ወደ ቅጣት ነው የመጣነው” ማለታቸው አይቀርም።
ያለ ጥፋታቸው እንደተቀጡ እርግጠኛ ናቸው። ገና ሳይወለድ በፊት ሃጥያት የሚሰራ ሰው፣ ወይም ክፉ  ጥፋት የሚፈጽም ሰው የለም።
በወላጆች ጥፋት ወይም በአያቶች ሃጥያት ሳቢያ፣ ልጆችና የልጅ ልጆች ላይ ቅጣት ይመጣል ከተባለስ? መቼስ ምን ይባላል?
አባቶች ጥሬ ቆረጠሙ። የልጆች ጥርስ በለዘ? ጠረሰ?...
አሁን ይህ ፍትህ ነው? ይሄ ቀና ፍርድ ነው?
የሕዝቅኤል ትረካ፣ ለዚህ መራራ ቅሬታ ነው መልስ ለመስጠት የሚሞክረው።
“የእግዚሄር ቃል እንዲህ ሲል ወደእኔ መጣ”… በማለት ይጀምራል  የሕዝቅኤል ምላሽ።
“ወላጆች ጎምዛዛ ፍሬ በሉ፤
የልጆችንም ጥርስ አጠረሰ።”… እያላችሁ ምሳሌ የምታነበንቡት ምን ለማለት ነው?
በሕያውነቴ እምላለሁ! ከእንግዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ምድር አትመስሉም ይላል እግዚሄር።…
እነሆ፣ ነፍስ ሁሉ የኔ ናት። የአባት ነፍስ የኔ እንደሆነች ሁሉ፣ የልጅም ነፍስ የኔ ናት። ኃጥያት የምትሰራ ነፍስ፣ እርሷ ትሞታለች።… በማለትም የሕዝቅኤል ትረካ  ወደማብራሪያ ይሸጋገራል።
በቅንነትና በትክክል የሚሰራ፣ ጻድቅ ሰው ቢገኝ…
እጁን ከበደል ይሰበስባል።
በሰውና በሰው መካከል በትክክል ይፈርዳል።…
ይህ ሰው ጻድቅ ነው።
ፈፅሞ በሕይወት ይኖራል።
ነገር ግን ይህ ሰው፣ ደም አፍሳሽ አመፀኛ ልጅ ወይም ከሚከተሉት ኃጥያቶች መካከል ማናቸውንም የሚፈፅም ልጅ ቢኖረው፣…
እንዲህ ዓይነቱ ሰው በሕይወት ይኖራልን? ከቶ አይኖርም። እነዚህን አጸያፊ ነገሮች አድርጓልና፣ ፈፅሞ ይሞታል። ደሙም በገዛ ራሱ እጅ ይሆናል።  በሕዝቅኤል ማብራሪያ በዚህ አያበቃም።
ይህም ልጅ ደግሞ በተራው ልጅ ቢወልድና፣
ልጁም አባቱ ያደረገውን ኃጥያት ሁሉ አይቶ ባይፈጽም፣…
ሰውን ባይጨቁን፣…
በጉልበቱ ባይቀማ፣…
ደሃን ከመበደል እጁን ቢሰበስም፣…
ሕጌን ቢጠብቅ፣ ሥርዓቴን ቢከተል፣…
በሕይወት ይኖራል እንጂ፣ በአባቱ ኃጥያት ሳቢያ አይሞትም።
አባቱ ግን፣ በድሏልና፣ ከወንድሙም ቀምቷልና፣ በሕዝቡም ዘንድ ያልተገባ ነገር ስላደረገ፣ በገዛ ኃጥያቱ ይሞታል።
“ልጅ ስለ አባቱ ኃጥያት አይቀጣም ወይ?” ያላችሁ እንደሆነ፣ ልጁ ቅንነትንና ትክክለኛ ነገርን ስላደረገ፣ ሥርዓቴንም ሁሉ ተከትሎ ስለሰራ፣ በሕይወት ይኖራል። መሞት የሚገባት ኃጥያት የሰራችው ነፍስ ናት።
ልጅ በአባቱ ኃጥያት አይቀጣም።
አባትም በልጁ ኃጥያት አይቀጣም።
ጻድቁ የጽድቁን ፍሬ ያገኛል።
ኃጥያተኛው የኃጥያቱን ዋጋ ይቀበላል።… በማለት የእግዜር መንገድ የፍትህ መንገድ ነው ብሎ ይሰብካል- የሕዝቅኤል ትረካ።
ኃጥያተኛ ከሰራው ኃጥያት ሁሉ ተመልሶ ሥርዓቴን ሁሉ ቢጠብቅ፣ ቅንነትንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ ፈፅሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም፣ በጽድቅ መንገድ ሄዷልና በሕይወት ይኖራል።
በውኑ ኃጥያተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን? ይልቁን ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር ደስ አይለኝምን?
ጻድቅ ሰው ግን፣ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጥያት ቢሰራ፣… አስጸያፊ ነገር ቢፈፅም፣ ይህ ሰው በሕይወትን ይኖራልን? ከሰራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም። ታማኝነቱን ሲያፈርስና ኃጥያት ሲሰራ፣ ከእነዚሁ የተነሣ ይሞታል።
እናንተ ግን፣ የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም ትላላችሁ።…
ቀና ያልሆነችውስ የናንተ መንገድ አይደለችምን?
… ስለዚህ፣ እንደየስራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ ይላል እግዚሄር።
በኃጥያታችሁ እንዳትጠፉ፣ ከኃጥያታችሁ ተመለሱ። …
ማንም እንዲሞት አልሻምና።
የሕዝቅኤል ማብራሪያና የፍትህ መስመር አሳማኝ ይመስላል። የብዙ ሰዎችን ስህተት ይፈውስ ይሆናል።
እንግዲህ፤ አባትና እናትን አማርጦ፣…ከጥሩ ዘመን ወይም ከመከራ ዘመን አማርጦ የሚወለድ ሰው የለም። የእድል ጉዳይ ነው እንበለው። አያኮራም አያሳፍርም። በኃጥያት ወይም በጽድቅ ምክንያት የሚመጣ አይደለም።
እንኳንና በዘር ተወላጅነትና በሃይማኖት ተከታይነት ይቅርና በወላጅና በአያት ቆጠራ  የሚገኝ ጽድቅ፣ የሚመጣ የሃጥያት ሸክም የለም።
የአገራችን ዘመናችን ወሬ ሁሉ በዘር በብሔር በብሔረሰብ የማቧደን ቅዠት መሆኑ ታዲያ፣ በምን አይነት ትምህርት ይፈወሳል?

Read 892 times