Saturday, 13 August 2022 00:00

ካልታዘልኩ አላምንም፤ አለች ሙሽሪት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የሚከተለው ታሪክ የውጭ ትርክትና ልምድ ነው። ለእኛ እንደሚያመች አድርገን ተርከነዋል። የተሬ ውሎ ብለነዋል።
ተረፈ ዋለልኝ (ጋሽ ተሬ ስልጡኑ) ማታ የጃፓን ስሪት የሆነችው ሰዓቱን ለጠዋት 12 ሰዓት ሞልቷት ነበርና ታማኙ ሰዓቱ አነቃችው።
በቻይና በተሰራው ጀበና የሚፈላው ቡናው እስኪንተከተክ፣ አጅሬ ጋሽ ተሬ፣ ከሆንግ ኮንግ የተሰራ ጺም መላጫውን ሶኬቱ ላይ ሰክቶ፣ ጺሙን መላጨት ቀጠለ። ቁም ሳጥኑን ከፍቶ ከሲሪላንካ የተሰራውን ሸሚዙንና የሲንጋፖር ስሪት የሆነውን ጅንስ ሱሪውን ለበሰ።
ከዛም በኮሪያ የተሰራውን የሜዳ ቴኒስ መጫዎቻ ጫማውን አደረገ። በኢንዲያ በተሰራው በአዲሱ የምግብ ማብሰያው ቁርሱን ጠባብሶ እየበላ፣ የሜክሲኮ ስሪት በሆነው የሒሳብ መሥሪያ ካልኩሌተር፤ ዛሬ ምን ያህል ገንዘብ ለማጥፋት እንደሚችል ማስላት ያዘ።
በታይዋን የተሰራች ሰዓቱን አስተካክሎ ሞላ። በሬዲዮ ዜና ሰዓት ምልክት እንድትሰጠው አድርጎ ነው ያስተካከላት። (ዜና አያመልጠውም ሁልጊዜ)።
ቀጥሎም የጀርመን ስሪት በሆነችው መኪና ገብቶ፣ ወደ ቤንዚን ማደያ ሄደና፣ ከኳታር የሚመጣውን ነዳጅ ሞላ።
እንግዲህ ከዚህ ወዲያ ነው ደህና ደመወዝ ይከፍላል ወደሚባለው የአሜሪካን ኩባንያ ስራ ፍለጋ የሄደው።
በሚቀጥለው ተስፋ-አስቆራጭና ፍሬ-ቢስ ቀን፣ የማሌዥያ ስሪት የሆነውን ኮምፒውተሩን ተመልክቶ ካረጋገጠ በኋላ ጥቂት ዘና የማለት ሀሳብ መጣለት።
ሰንደል ጫማውን አጠለቀ- በብራዚል የተሰራ ነጠላ ጫማ ነው። ትንሽ ወይን ጠጅ ከማብረጃው ቀዳ፡፡ ወይኑ ፈረንሳይ የተጠመቀ ወይን ነው፤ ምርጥና ጣፋጭ፡፡
ቀጥሎ እንግዲህ እንደ ሁልጊዜው ወደ ቴሌቪዥኑ ዞረ። ቴሌቪዥኑ ኢንዶኔዥያ ስሪት ነው።
ከዚያ ማሰብ ጀመረ።
 “ለምንድነው በአሜሪካን አገር ጥሩ ደመወዝ የሚያስከፍል ስራ ያላገኘሁት?” አለ።
ምናልባት አዲሱ ፕሬዚዳንት ይረዳው ይሆን?
ተስፋ አደረገና ከቤት ወጣ!
***
ተሬ ያላለፈለት ከላይ የተጠቀሰው ሸቀጡ ሁሉ ማራገፊያ ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም። ገንዘቡ ሁሉ በዚህም ሆነ በዚያ ወደ ባህር ማዶ ተሻግሯል። ራሱ የሚያመርተው የሌለው አገር የሌላ ማራገፊያ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። ብልጭልጩ የገና ዛፍ (የፈረንጁ አገር ማለት ነው) ይህንን እውነታ በየአመቱ ይነግረናል። ልጆቻችን ህልምና ምኞታቸው ሁሉ ውጭ መሄድ ነው። ከዚያስ? ዘመዶቻቸውን ወደ ውጭ መውሰድ!
ወደ ውስጥ የሚያስበው እየመነመነ፣ ወደ ውጪ የሚያስበው እየበረከተ መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ ነው።
ዳን ብራውን የተባለው ገጣሚ እንዳለው፤
“… ደግሞም ማወቅ ማለት፡-
ከውጭ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ!” ነው።
አገራችን ብዙ ቃል የሚገባባት፣ ጥቂት ብቻ በስራ ላይ የሚውልባት ናት። አያሌ እቅዶች ይነደፋሉ። አያሌ ትልሞች ይጀመራሉ። ውለን አድረን ግን  ውጤትና ፍሬያቸውን አናይም፡፡ አንድም፣ ተከታትሎ አስፈጻሚ፤ አንድም አስፈጻሚውን ተከታታይ የለም። የሚገርመው ይህንንም ችግር ደጋግመን ስናወራ መኖራችን ነው።
እንደ ሰሞነኛ ካህን ለአንድ ሰሞን ብቻ አታሞ ማብዛት፣ ከበሮ መደለቅ እንደ ድል እየተቆጠረ፣ “የፋሲካ ለት የተወለደች ሁሌ ፋሲካ ይመስላታል” ዓይነት ሆነን እንሰነብታለን፡፡ ጉዳዩ ግን ውሃ ወቀጣ ሆኖ ቁጭ ይላል! ድግግሞሹ ሲበዛብን እንደ ሁልጊዜው “ከልኩ አያልፍም” እንላለን። ሕይወትም በዚያው ሐዲድ ላይ መንሻተቱን ይቀጥላል።  ይህን የድግግሞሽ መንገድ ለመስበር  ሁሌ ባል መጥቶልሻል መባል እንደታከታት እንደ ሙሽሪት፤ “ካልታዘልኩ አላምንም!” ማለት ነው የሚያዋጣን፡፡
የነገ ሰው ይበለን!!

Read 6957 times