Saturday, 13 August 2022 00:00

አድማስ ትውስታ

Written by  ደረጀ አለማየሁ (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

 “ጀግንነት ትልቅ የኋላቀርነት ምልክት ነው”
                
       ዋነኛ የሚባሉ… የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በምን መንገድ፣ የሀገሪቱን ሀብትና ማዕከላዊ ስልጣን ቢከፋፈሉ ሰላም ሊወርድ እንደሚችል አላውቅም። የቁጥር መበላለጥ መብትን መበላለጥ በማያስከትልበት መንገድ ተግባብተው መኖር አለባቸው። የሀገሪቷ ሀብትም ሆነ በልመና የሚገኘው፣ በዚህ ትብብር ላይ በተመረኮዘ የሰለጠነ መንገድ የየብሔረሰቡ አባሎች በማንኪያ የሚቋደሱት “ገንፎ” እንዲሆን ነው ምኞቴ። በማእከላዊ ስልጣን ውስጥ የሚኖረውን የአንድ ብሔረሰብ ክብደት የካላሺ ብዛት የሚወስን ከሆነ፤ የአገሪቱ ሀብት የየብሔረሰቡ ንኡስ ከበርቴ፣ በካላሺ ሳንጃ ቆርጦ የሚከፋፈለው “ድፎ ዳቦ” እስከሆነ ድረስ ሰላምና ዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም። ዋና የሥልጣን ክብደት በካላሺን ሃይል ተደግፎ፣ የአንዱን ብሔረሰብ አባል የዚህ ሚንስትር፣ የዛኛውን የዚያ ሚንስትር ማድረግ፣ አይን እያየ መሸዋወድ እንጂ የትም አያደርስም።…
የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሁሉም ተባብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ብቻ ናት ሰላም የሚኖርባት። ማንኛውም ሁለት ወይንም ሶስት ብሔረሰቦች፣ በአንድ ወይንም ሁለት ሌሎች ብሔረሰቦች ላይ የሚያደርጉት ህብረት፤ ግጭቶችንና ጦርነቶችን የሚጋብዝ ህብረት ነው።
ከጭቁን ብሔረሰቦች ጋር አማራን ማዳከም፣ ወይንም ደግሞ ከአማራ ጋር ትግሬን ማዳከም፣ ወይንም ከአማራ ጋር ኦሮሞን ማዳከም ወዘተ የሚሉ ታክቲኮች ወደ ሰላም አይወስዱንም። የትግሬን የበላይነት ለመቃወም ተብሎ የሚቋቋምን የማንኛቸውንም ሁለት ብሔሮች የጋራ ግንባር መቃወም፣ የትግሬን የበላይነት ለማጠናከር TPLF ከማንኛውም ብሔር ጋር የሚያደርገውን የጋራ ግንባር መቃወም፣ በዚህ መሰረት ላይ ብቻ ነው ለብሔረሰቦች ችግር ሰላዊ መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው።…
“ዲሞክራሲ የፈሪዎች ስርዓት ነው” … ይህንኑ አባባል በሌላ መልኩ ባስቀምጠው፣ ዲሞክራሲ ሰው ለእምነቱ ሲልም ሆነ በእምነቱ ምክንያት የማይሞትበት ስርዓት ነው ማለት ነው።… በእምነት ምክንያት ከሚገድል የፖለቲካ ስርዓት እኩል፣ ለእምነቱ ሲል መሞት ፈሪ አያሰኝም።… ስታሊን “በታላቁ መሪ በስታሊን ላይ በማመጼ ይቅርታ” እያስባለ ስገደላቸው ስለነቦካሪን ቃል አወሳሰድ ሰምተህ፣ “ለፈሪነታቸው” ስቀህባቸው አለፍክ ወይስ የስታሊን ዘዴ ዘገነነህ?...
ሟች ነው እንጂ ፈሪ ገዳይ አንበሳ ነው!...
እያንዳንዱ ሰው በየራሱ መንገድ እንደሚኖር ሁሉ ከሞቱም ጋር በየራሱ መንገድ የሚፋጠጥ ይመስለኛል። ሞት፣ ሼክስፒር በሐምሌት አንደበት እንዳለው፣ የሄደ መንገደኛ ተመልሶ ያልመጣበት አገር ስለሆነ፣ “ስትሞት እንዴት ነበር?” ብሎ መጠየቅ አይቻልም።
“ለህዝብ ተሰውተው ነጻነት ለመቀዳጀት መነሳቱ በእርግጥም ቁርጠኝነትንና ጽናትን” ስለሚጠይቅ፣ እየሞቱ ነው ትግል፣ እየታገሉ ነው ድል። ለምን እንደ አዲስ ነገር ትተርከዋለህ ትሉ ይሆናል። እኔ ግን፣… ከዚህ በላይ ካነሳኋቸው ሁኔታዎች እና ከሌሎችም ከዚህ በታች ከማነሳቸው ጉዳዮች ጋር ተያይዞ፣ እንኳን እራሴ ልመለስበት ቀርቶ ሰብአዊ ፍጡር ላይ እንዳይደርስ የምንመኝ አድርጎኛል።… ጀግንነት የብዙ ወንጀሎች መነሻ፣ ትልቅ የኋላቀርነት ምልክትና ምክንያት ነው የሚለው እምነቴ ነው- “ጎበዝ ፈሪ” ያደረገኝ።…
ከሞት ጋር በቀጥታ የመፋጠጥ ታሪኬ፣ በግል ጠባዬ ላይ የለወጠው ነገር ይኑር አይኑር አላውቅም።… የፖለቲካ ህይወቴ ግን አንድ ትልቅ ምዕራፍ የተዘጋበት ታሪክ ነው። “ቅጽበታዊ ወኔ” ብቻ ሳይሆን ሙሉ ህይወቴን የፖለቲካ ጀግንነት አጠገብ ላለመድረስ አስወስኖኛል፣ የግል ታሪኬን ለመዘርዘር ስላልተነሳሁ በአጭሩ ለምንም ዓላማ ለመሞት ዝግጁ መሆን የለብኝም፣ ለፈለገው ዓላማ ለመሞት ዝግጁ የሆነንም በአድናቆት ሳይሆን በጥርጣሬ ማየት አለብኝ የሚል እምነት ከያዝኩ ቆየሁ።… ህይወትን በመውደድ ክስ ብትከሰኝ ክርክር ውስጥ አንገባም። በዚህ ወንጀል ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ። መከራከር የሚኖረው ለእናንተ ጀግኖች “የመሞት ግዴታ”፣ “መስዋዕትነት የመክፈል ዝግጁነት” አድናቆት ሳይሆን፣ ክስ ይዤ ስመጣ ነው። ሞት አይፈሬነታችሁ እንደ ቡድሂስቶች ቤንዚን እራሳችሁ ላይ አርከፍክፋችሁ እንድታቃጥሉ የሚያደርግ አሳዛኝ የግለሰብ ባለወኔነት ሳይሆን፤ ህዝቦችን የሚያፋጅ ወኔ ሲሆን ደግሞ ከክስም አልፌ ወደ መወንጀል እሻገራለሁ። ለዚህ ውንጀላ መነሻ የሆነኝን፣ ሞትን ለመቀበል ዝግጁ ከነበረ አብዮታዊነት፣ ለፖለቲካ ሞትን ለራሱ ብቻ ሳይሆን ሰው ለተባለ የማይመኝ ፈሪ ወደመሆን የለወጠኝ የግል ታሪኬ ነው።…
ለዚሁ ለመስዋዕትነት ዝግጁ የመሆን ጉዳይ፣ በተለይ አምስት ዓመት የተሸናፊዎች ዩኒቨርስቲ በሆነው እስር ቤት ቆይቼ ወደ ጀርመን አገር እንደገና ከተመለስኩ በኋላ ብዙ አንብቤአለሁ። ብዙ ክርክሮች ተከታትያለሁ። በመጀመሪያ የጀርመን ቆይታዬ ጊዜ አሸናፊዎችን፣ የጀግኖችን ታሪክ ተስገብግቤ ያነበብኩትን ያህል፣ በአሁኑ ቆይታዬ ደግሞ የተሸናፊዎችን፣ “የፈሪዎችን” ታሪክ አነበብኩ፤ እያነበብኩም ነው። የሩስያ፣ የቻይና ወዘተ አብዮቶች ታሪክ ከተሸናፊዎች አንጻር ሲነበብ፣ ተራ የወንጀሎችና የወንጀለኞች ታሪክ ነው የሚሆነው።…
ሌኒን እንዳለው፤ ሰንሰለት መጀመሪያ  የሚበጠሰው የላላው ቀለበት ላይ ነው። ከዚህ በአብዮት ስም ወንጀል ካስቻለ ርዕዮተ ዓለም ጋር ካቆራኘኝ ሰንሰለት እራሴን ለማላቀቅ ቀለበቱ የላላልኝ በስታሊን በኩል ነበር።…
ሌኒን ወደ ስልጣን በሚያደርገው ሩጫ፣ ተቃዋሚ የገጠመበትን መሰናክል ሲዘል፤ እራሱ በተራው መሰናክል ሲያስቀምጥ፤ እንኳን ጠላት ወዳጅ ሳይነቃ አቅጣጫ ሲለውጥ አፍ ስለሚያስከፍት፣ “ቆም ብሎም” ይህ ሰውዬ ወዴት ለመድረስ ነው እንዲህ የሚሮጠው?” ብሎ ለመጠየቅ ፋታ አይሰጥም። (በነገራችን ላይ በዚህ የስልጣን ሩጫ አሸነፍኩ ተባለ እንጂ እንዳላሸነፈ ያወቀ የመጀመሪያ ሰው ሌኒን ነበር ለማለት ይቻላል። ከሌኒን “ስብስብ ስራዎች ቅጽ 28” በኋላ ያሉት ጽሁፎቹ በጥንቃቄ ሲነበቡ፣ “ለዚሁ ነበር እንዴ ይሄ ሁሉ ሩጫ” የሚል ይመስላል። ማኦም ቢሆን ቀን ቀን በጎረቤቶቹ ላይ የፈለገውን ሴራ ሲሸርብ ቢውልም ማታ ማታ ጋያውን ይዞ “ልጆች እንግዲህ ዶሮ ድንጋይ ብትታቀፍ እንቁላል ስላልሆነ ጫጩት አትፈለፍልም” የሚል ዲያሌክቲካዊ ተረት የሚያወራ ሽማግሌ ገበሬ ስለሚመስል ተረቱ ይጥማል። ስታሊንን ግን “ምሁራዊ ውቃቢዬ” ከመጀመሪያውም አልወደደውም ነበር፤ በምን ሳበኝ ታዲያ? ከቋንቋው ቋንቋው አይጥም፣ በቃሉ የሸመደደውን የሚተፋ ተራ የዲያቆን ሰበካ ነው። ከሀሳብ ሃሳብ የለው፣ አንድና አንድ ሁለት ነው የሚለውን ተራ ሒሳብ- ካልኩለስ ያስተማረ ለማስመሰል የሚሞክር ግብዝ መሃይም ነው። የማርክስን ´የአይሁዶች ጥያቄ´፣          ´የጀርመን ርዕዮተ ዓለም´ የመሳሰለ ዶሮ ወጥ በተመገበ አዕምሮዬ፣ የስታሊንን ´የሌኒኒዝም መሰረተ ሀሳቦች´ ስበላ አሸር ባሸርነቱ ሳይታወቀኝ ቀርቶ አያውቅም ነበር።…
በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ የደረሰብኝ ሽንፈት፣ ለስታሊን ወንጀሎች ዓይኔን ከፈተው። ከዚያ በፊት የላይብረሪ መገደቢያ ያጣበቡ ቁጥር የለሽ መጽሐፎች ያልቻሉትን።
 “መሸነፍ ብልህ ያደርጋል” ይላል ጀርመን ሲተርት።…
(አዲስ  አድማስ፣ መጋቢት 10 ቀን 1997)

Read 6864 times