Saturday, 13 August 2022 00:00

ለ"ክልልነት" የሚከፈለው የህይወት ዋጋ ግጭት - መፈናቀል - ሞት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

• አዳዲስ ክልሎች የሌላ ብሔር ተወላጆችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል
   • ሲዳማ ክልል የበርካቶችን ህይወት ከቀጠፈ ግጭት በኋላ፣ 10ኛው ክልል ሆኖ ተዋቅሯል፡፡
   • በቅርቡ ምዕራብ ኦሞ፣ቤንች ሸካ፣ ከፋ ዳውሮና ሸካ ተጣምረው 11ኛውን ክልል መስርተዋል
   • የክልልነት ጥያቄ ካነሱ የደቡብ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ወላይታ ዞን ውጥረት እንደነገሰ ቀጥሏል
   • የጉራጌ ዞን በክላስተር  እንዲደራጅ ከመንግስት የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል
   • የጋሞ ህዝብ ከዓመታት በፊት  ያቀረበው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ፣ ወደ ቀጣይ እርምጃ ይገባል ተብሏል
   • በጂንካ ከክልል እንሁን ጥያቄ ጋር ተያይዞ አያሌ ዜጎች ለጥቃት ተዳርገዋል
       
     ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በተዋቀረው ፌደራላዊ ስርዓትና ይህንም ተከትሎ ተግባራዊ በሆነው የአገሪቱ ህግ መንግስት ለብሔሮች በሚሰጠው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሳቢያ፣ ብሔርን መሰረት አድርገው የሚዋቀሩ ክልሎች ጉዳይ አሁንም ለውጥረት፣ ግጭትና ሞት ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡
 በሲዳማ ክልል ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ያለምንም ፈቃድ ክልሉ የመሆን ጥያቄያችንን ተግባራዊ እናደርጋለን ባሉ የክልል ተወላጆችና በመንግስት መካከል ተፈጥሮ በነበረው ውጥረትና ይህን ተከትሎ በተቀሰቀሰ የብሔር ግጭት ሳቢያ የበርካቶች ህይወት አልፏል፡፡
 በዛው ዓመት የሲዳማን የክልል እንሁን ጥያቄ ተከትሎ፣ በአዋሳ ከተማ ውስጥ በተቀቀሰ ግጭት በርካቶች ለሞት አደጋ ሲዳርጉ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስትና የግለሰቦች ንብረትና ሃብት ወድሟል። በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ተበትነዋል፡፡ የማታ ማታም ክልሉ በህዝበ ውሳኔ 10ኛው ክልል ሊሆን በቅቷል፡፡
ቀጣይ ባለተራ በደቡብ ህዝቦች ክልል ውስጥ ተዋቅሮ የኖረው የምዕራብ ኦሞ ቤንች ሸካ፣ የከፋ፣ የዳውሮና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ህዝቦች ሆኑ። በአካባቢው ለወራት ከዘለቀ ውዝግብና ውጥረት በኋላም መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ አስራ አንደኛ ክልል ሆኖ ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ድምፅ ሰጥተው የራሳቸውን ክልል በመስራት የደቡብ ምእራብ ክልል አራት ከተሞችን የክልሉ መቀመጫ በማድረግ ተዋቅሯል፡፡
የደቡብ ክልል ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄው፤ በዚህ ብቻ አላበቃም-ቀጥሏል፡፡ ክልል የመመስረት ጥያቄን አጥብቀው ከሚያነሱ የደቡብ ክልል አካባቢዎች መካከል የወላይታ ዞን አንዱ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረ ግርግር ሳቢያ በዞኑ አሁንም ውጥረቱ እንደነገሰ ነው፡፡
የጋሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫም ከዓመታት በፊት ለዞኑ ምክር ቤት ያቀረበው የክልል እንሁን ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅሬታውን አቅርቦ ምላሽ ባላገኘበትና የህዝቡ ጥያቄ ፍላጎት በተጨፈለቀበት ሁኔታ ክልሉን በሁለት ክልሎች ከፍሎ ለማዋቀር እየተደረገ ያለውን ሩጫ አጥብቄ እቃወማለሁ ብሏል፡፡
ከ3 ዓመታት በፊት የራሱን ክልል ለማቋቋም ለደቡብ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ ባለማግኘቱ ቅሬታውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በማቅረብ መልስ እየተጠባበቀ ባለበት ሁኔታ የህዝብን ፍላጎት ያላገናዘበና ህገ መንግስታዊ መብቱን የሚጨፈልቅ ተግባር ለመፈጸም የሚደረገውን ጥረት አጥብቀን እንቃወማለን ብሏል ፓርቲው፡፡
የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንብር አቶ ዳሮት ኮምባ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የጠየቁት ህገመንግስታዊ  ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነና ህዝብ ያልተስማማበትን ውሳኔ  በጫና  እንዲቀበል የሚገደድ ከሆነ፣ ወደ ቀጣይ ህጋዊ እርምጃዎቻችን መሄዳችን አይቀሬ ነው ብለዋል። ህዝብ ሳይመክርበት በአቋራጭ የሚደረጉ አካሄዶችን እንቃወማለን ሲሉም አክለዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የተካተተው የጉራጌ ህዝብ እራሱን በቻለ ክልል ለማዋቀር ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን ለጥያቄው ምላሽ ባለማግኘቱሰሞኑን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ ሰንብቷል፡፡
ከእነዚህ እንቅስቃሴዎቹ መካከልም  ባለፈው ሰኞ ነሀሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ያካሄደው የስራ ማቆም አድማ ተጠቃሽ ነው፡፡ ማን እንደጠራው በትክክል አልታወቀም በተባለው በዚሁ የስራ ማቆም አድማ፣ ከዳቦ ቤቶችና ከህክምና ተቋማት ውጭ በወልቂጤ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቋማት ዝግ ሆነው ውለዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የመንግስት አካላት በዞኑ ውስጥ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪውን ለማወያየት ጥሪ ቢያደርጉም፣ ነዋሪዎቹ ለመሰብሰብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የጉራጌ ዞንን በክላስተር ለማደራጀት በመንግስት ተይዞ የነበረው አቅጣጫ ህዝቡን የሚከፋፍልና ማንንቱን የሚያሳጣ ተግባር ነው በሚል ከዞኑ ነዋሪ ህዝብ ተቃውሞ ገጥሞታል። በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ከትናት በስቲያ ተሰብስቦ የነበረው የጉራጌ ዞን ምክር ቤትም ዞኑ ከአጎራባች ዞኖች ጋር በአንድ ክልል ስር እንዲደራጅ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ አድርጎታል- ከ97ቱ የምክር ቤት አባላት 52 የውሳኔ ሃሳቡን ተቃውመውታል፡፡
የጉራጌ ዞን ከከምባታ ጠምባሮ፣ሀድያ ሀላባ፣ስልጤና ጉራጌ ዞኖች እንዲሁም ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በአንድ ክልል ስር እንዲደራጁ የሚጠይቀውና  የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ርዕስቱ ይርዳው በተገኙበት፣ በዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ መሀማድ ጀማል የቀረበውን ሃሳብ የዞን ምክር ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። በሁለት ተከፍለው እንደ አዲስ ይደራጃሉ ከተባሉ አስራ አንድ ዞኖችና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ውሳኔውን ባለመቀበል ውድቅ ያደረገው የጉራጌ ዞን ም/ቤት ብቻ ሲሆን ሌሎቹ ሁሉም የዞን ምክር ቤቶችና አፈጉባኤዎችና የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ይህንኑ የፀደቁ ውሳኔዎቻቸውን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ለፌደሬሽን ምክር ቤት አስገብተዋል፡፡
ከሁለቱ አዲስ ክልሎች መካከል አንደኛውን ለመመስረት በምክር ቤቶቻቸው  ውሳኔ ያሳላፉት ዞኖች የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ጋሞ ጎፋ የደቡብ ኦሞና የኮንሶ ዞኖች ናቸው! የአማሮ፣ ባስኬቶ ቡርጂ፣ ደራሼና አሌ ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶችም ይህንኑ በጋራ የመደራጀት ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
ሁለተኛውን ክልል በጋራ ለመመስረት የሚያስችላቸውን ውሳኔ ያሳለፉትና በምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁት ደግሞ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጠምባሮ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ሲሆኑ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የክላስተር አደረጃጀቱን ባለመቀበል ብቸኛው የዞን ምክር ቤት ሆኗል፡፡
ይህ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔም በአካባቢው ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት  ሆኗል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የዞኑ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት፣ በአካባቢው ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር በሚሞክሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡ የጉራጌ ዞን የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪው  ሌተና ኮሎኔል ፈጠነ ፍስሃ ህብረተሰቡ ደስታውን በሰላማዊ መንገድ መግለፅ አለበት ብለዋል፡፡
ይህንኑ በደቡብ ክልል እየበረታ የመጣውን የክልልነት ጠያቄ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሠጡን የፖለቲካ ሳይንስ ምዑሩ ዶክተር ዮሴፍ ታረቀኝ እንደሚናገሩት፤ አገሪቱ አሁን ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ተጠያቂው ስርአቱ ነው፡፡ የፌደራሊዝም ስርአቱ በብሔር ማነንት ላይ ያተኮረ መሆኑ የችግሮች ሁሉ መሰረት ነው ያሉት ምዑሩ ብሔር ላይ ያተኮረ ክልል ሲዋቀር “ባለቤት”ና “መጤ” የሚሉ ስሜቶችን በመፍጠር አስከ አሁን ያላየነውን ችግርና መፈናቀል  ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡
“ይህ የእኛ ክልል ነው፤ ከዚህ ለቃችሁ ውጡ” በሚል ምክንያት፣ በአገሪቱ የሚታየው ውጥንቅጥ የተፈጠረው በዚሁ በብሔር አደረጃት ሳቢያ ነው፡፡ እናም አዳዲስ የሚቋቋሙት ክልሎቸም በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች እንዲገለሉና ለአደጋ እንዲጋለጡ በማድረግ፣ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላሉ ብለዋል ዶ/ር ዮሴፍ፡፡
አሁን በተጀመረው የመልሶ ማዋቀር ሂደት የጉራጌ ዞን ምክር ፣አዲስ ክልል የሚመሰርቱ ከሆነ፣  የደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ ክልል ህልውና ያከትማል፡፡


Read 6348 times