Saturday, 13 August 2022 00:00

ኢዜማ በአዲስ አበባ የሚስተዋሉ የአስተዳደር መደበላለቅ ችግሮችን እያጠና መሆኑን ገለፀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በአዲስ አበባ የሚስተዋሉ የአስተዳደር መደበላለቅ ችግሮችን በባለሙያዎች እያስጠና መሆኑን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ የአዲስ አበባ  ከተማ  አስተዳደርና  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ወሰን ለማካለል የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን መረዳቱን ጠቁሞ፣ ማካለል ያለበቂ የህዝብ ተሳትፎ መፈጸም እንደሌለበት አሳስቧል።
“ህዝብ የአስተዳደር ውሳኔን የመቀበል ግዴታ የሚኖርበት እንደ ዜጋ በሂደቱ ላይ የመሳተፍና  የማወቅ መብቱ በአግባቡ ሲከበርለት ብቻ ነው” ያለው የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ “በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መሃከል ያሉ የወሰን ችግሮችን ለመፍታት የአስተዳደር ወሰን ማካለሉ ጠቃሚ መሆኑ ባይካድም፣ ውሳኔዎቹን ማስተግበር የሚቻለው፣ ዜጎችን አሳትፎ፣ የሂደቱ ባለቤት በማድረግ እንጂ፣ በሃይል ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሊታወቅ ይገባል” ብሏል።
“በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መሃከል ስላለው የወሰን ማካለል ጉዳይም ሆነ በየቦታው የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች በቀጣይ በሚካሄደው ሃገራዊ የምክክር መድረክ ይፈታል” የሚል እሳቤ እንዳለው የጠቆመው ፓርቲው፤ መንግስት በአንጻሩ ሃገሪቱ ያለችበትን ከፍተኛ ችግር ታሳቢ ያላደረጉ እንደ ክላስተርና የአስተዳደር ማካለል አይነት  ውሳኔዎች መስተዋላቸው ተገቢ አይደለም ሲል ነቅፏል።
እንዲህ አይነት የህዝብ ተሳትፎን ያላማከለ፣ በቁንጽል እሳቤዎች ላይ የተንጠለጠለና ጊዜውን ያልጠበቀ አካሄድ ከፍተኛ ስህተት በመሆኑም፣  በፍጥነት ሊታረምና ሊስተካከል እንደሚገባም አስስቧል-።
“በየአካባቢው የሚኖረው ህዝብ፤ የመንግስትን ውሳኔዎች የመቀበል ግዴታ የሚኖርበት፣ እንደ ዜጋ በሂደቱ ላይ የመሳተፍና የማወቅ መብቱ ሲከበርለት ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል- ፓርቲው።
በአዲስ አበባ እየተስተዋሉ ያሉ የአስተዳደር መደበላለቅ ችግሮችን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ሰብስቦ በጥናት የሚለይ ቡድን በማሰማራት ቀደም ብሎ ስራዎችን እንደጀመረ የጠቆመው ኢዜማ፤ ጥናቱ ሲጠናቀቅም ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

Read 6569 times