Saturday, 13 October 2012 14:14

“የንጉሥ ዳዮኒስየስ ፍርድ”

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ
Rate this item
(4 votes)

የባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን የመጀመሪያ ቴአትር
“ሚስስ ሐቺንግስ ጠጉራችንን በመቀስ ቆራርጣ እንደሮማውያን ትሪቡናል ሻሽ አሰረችልን፤ አቡጀዲ ገዝታ እንደ ግሪክ ኦራተሮች አስደገደገችን፡፡ ሲርበን ዳቦና ሻይ እያቀረበችልን እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ልምምዱን ቀጠልን፡፡ ጃንሆይ በአሥራ አንድ ሠዓት ግድም ደረሱ፡፡ አስቀድሜ ያዘጋጀሁትን አጭር መግለጫ እንዳነብ ሚስስ ሐቺንግስ ስለጠየቀችኝ ወጥቼ አነበብኩ፡፡ ቴአትራችንንም ጀመርን፤ ከመካከላችን አንዱ ልጅ ቃለ ተውኔቱ ቢጠፋበትም እንደምንም አድርገን ተወጣነው፡፡ በመጨረሻም በጣም የሞቀ ጭብጨባ ስለተሰማ በጣም ደነገጥን፡፡ ዲሬክተሩ አስፈቀደና ወደ ጃንሆይ አቀረበኝ፤ “ይህ ተማሪ እና ባለቤቱ ናቸው ቴአትሩን ያዘጋጁት” አላቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም “በርታ” አሉኝ፡፡ ሸለሙኝም፡፡ ትምህርት ቤቱንም ሁሉ ሸለሙ”

ፀጋዬ ገብረ መድህን የተወለደው በአምቦ ከተማ ደቡባዊ ምዕራብ ራስጌ ከምትገኝ ቦዳ ደረባ ከተባለች ቀበሌ ውስጥ ሲሆን ጊዜው ነሐሴ 1928 ዓ.ም ነበር፡፡ ፀጋዬ የስዕለት ልጅ ነው - እናቱ ወይዘሮ ፈለቀች ዳኜ የቦዳ አቦን ደብርን ተማጽነው የተገኘ፡፡ ዘመኑ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ዋዜማ እንደመሆኑ አባቱ አቶ ገብረ መድህን ሮባ ጠላትን ለመፋለም ንጉሠ ነገሥቱን ተከትለው የማይጨው ዘመቻ ላይ ናቸው፡፡ ጠላት አገሩን ከወረረ ወዲያ የጣሊያን ባንዳዎች የዘማቹን የአቶ ገብረ መድኃንን ቤት ስላቃጠሉት፣ ወይዘሮ ፈለቀችና ልጃቸው አስካለ ገብረ መድኅን ህጻኑን በአገልግል አዝለው ለመሰደድ ተገደዱ፡፡ 
ገና በአራስነት ለጋ እድሜው የስደትን እንግልት የቀመሰው ፀጋዬ፤ በኋለኛው ዘመኑ የልጅነቱን ህይወት ሲዘክር፤ “የህጻን አፌን የፈታሁበት ልሣን ኦሮሚፋ ነው፡፡ የእናቴ ወንድሞች መንዞች፣ የካህን ቤቶች፣ ቀሳውስቶች ነበሩና የግዕዝ ግሥ ገና ሁለት ዓመት ሳይሞላኝ በጨቅላነቴ ያስገጥሙኝ ነበረ፡፡ “አእመረ - አወቀ ማለት ጀመርኩ፡፡ በኦሮሚፋ አፍ መፍቻ ቋንቋ ላይ የግዕዝ ግሥ ተዳበለ” ሲል ተናግሮ ነበር፡፡
ፀጋዬ ማታ ማታ ፊደል በመቁጠር፣ የሃይማኖትና የቃል ትምህርት በቃል በመድገም በቤት ውስጥ የጀመረው ትምህርት፤ ወደ ቄስ ትምህርት የተሸጋገረው ገና የሶስት ዓመት ከመንፈቅ ልጅ ሳለ ነበር፡፡ ስድስት አመት እስኪሞላው ድረስም ዳዊት ደግሟል፣ ዜማ አጥንቷል፤ ቅኔ ቆጠራም “ሞከርኩ” ብሏል፡፡
ፀጋዬ ከአካባቢው ጋር የነበረው ልምምድ የተጀመረው ደግሞ ቀን ቀን በእረኝነት ከጓደኞቹ ጋር በየወንዙ፣ በየሜዳውና በየሾላው የሚያውቁትን የአበው ተረት ሽለላና ወግ በመቀባበል፤ ከዚያም ከጥጆችና ከግልገሎች ጋር በጋጣና በጉረኖ በማገልገል፤ አልፎ አልፎም ታላላቆቹ አውድማ ጥበቃ ደጅ ሲያድሩ አብሮ በማደር እና ጥቃቅን አራዊትን ሲያድኑም በመከተል የባላገር የትግል ሕይወትን አጣጥሟል፡፡ ስድስት ዓመት ሲሞላውም አባቱ ዘመናዊውን ትምህርት እንዲከታተል አምቦ ከተማ ከሚገኘው የማዕረገ ሕይወት ዘቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡
በማዕረገ ሕይወት ቀ.ኃ.ሥ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት እንግሊዛውያን መምህራን፣ በአገራቸው ቋንቋ የተጻፉ የሕጻናት ድራማዎችን ወደ አማርኛ እያስተረጐሙ በየተርሙ እና በዓመቱ መጨረሻ ተማሪዎቻቸው እንዲተውኑ ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነበር የፀጋዬ የወደፊት ሕይወት ጥሪ የሆነው ኪነ ጥበብ አመርቂ ምልክት ማሳየት የጀመረው፡፡ በኋላኛው የሕይወት ዘመኑ ፀጋዬ ይህንን የጥበብ ትውውቅ ሲናገር “በዘጠኝ አመቴ አራተኛ ክፍል ሆኜ የመጀመሪያ ቴአትሬን በመምህር ኃብተ ወልድ ኩርፋ የሂሳብ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ውስጥ ለክፍል ጓደኞቼ አቀረብኩ” ብሎ ነበር፡፡
ይህ የጥበብ ቅምምስ በፀጋዬ ውስጥ የተፀነሰውን ጥበብ አጉልቶ ለማውጣት ምክንያት ስለሆነ ግጥሞችንና ድራማዎችን እየደረሰ ለክፍሉ ተማሪዎች ሲያቀርብ፣ በመምህራኑ ዘንድ የታወቀ ሆነ፡፡ ችሎታው የክፍሉን ድንበር አልፎ በትምህርት ቤቱ መድረክ ላይ ለተጋባዥ ንጉሣዊ ቤተሰቦች፣ ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች፣ ለመምህራንና ለተማሪዎች ቀርቦ “ወጣቱ ደራሲ” የተሰኘ ቅጽል እና ሽልማት ያስገኘለት የአስራ ሶስት ዓመት ታዳጊ ሳለና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን ሥራውን ወደ አደባባይ ያወጣለትን ልዩ አጋጣሚ ፀጋዬ ገብረ መድህን በአንድ ወቅት እንዲህ አስታውሶት ነበር፤ “ጃንሆይ አምቦን ሊጐበኙ መጡ ማለትን ስሰማ ከሁለት ጓደኞቼ ጋር መከርኩና በአንድ ሌሊት “የንጉሥ ዳዮኒስየስ ፍርድ” (The Judgement of Dionysius) የተባለ የግማሽ ሠዓት የእንግሊዝኛ ቴአትር አጥንተን አደርን፡፡ ጧት ለዲሬክተራችን ለሚስተር ሐቺንግስ እና ባለቤቱ ያጠናነውን በቃላችንን ወረድንላቸው፡፡ ‘ለምን አጠናችሁት’? ብለው ሲጠይቁን ‘ለጃንሆይ ልናሳይ’ ብለን ስንመልስላቸው ተገርመው ባለቤቱ ለተጨማሪ ልምምድ ወደ ትምህርት ቤቱ አዳራሽ ወሰደችን፤ ዲክሬተሩ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ ትምህርት ቤቱን እንዲጐበኙለት መጥሪያ ወረቀት ይዞ ወደ አገረ ገዢው ቢሮ ሄደ”
“ሚስስ ሐቺንግስ ጠጉራችንን በመቀስ ቆራርጣ እንደሮማውያን ትሪቡናል ሻሽ አሰረችልን፤ አቡጀዲ ገዝታ እንደ ግሪክ ኦራተሮች አስደገደገችን፡፡ ሲርበን ዳቦና ሻይ እያቀረበችልን እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ልምምዱን ቀጠልን፡፡ ጃንሆይ በአሥራ አንድ ሠዓት ግድም ደረሱ፡፡ አስቀድሜ ያዘጋጀሁትን አጭር መግለጫ እንዳነብ ሚስስ ሐቺንግስ ስለጠየቀችኝ ወጥቼ አነበብኩ፡፡ ቴአትራችንንም ጀመርን፤ ከመካከላችን አንዱ ልጅ ቃለ ተውኔቱ ቢጠፋበትም እንደምንም አድርገን ተወጣነው፡፡ በመጨረሻም በጣም የሞቀ ጭብጨባ ስለተሰማ በጣም ደነገጥን፡፡ ዲሬክተሩ አስፈቀደና ወደ ጃንሆይ አቀረበኝ፤ “ይህ ተማሪ እና ባለቤቱ ናቸው ቴአትሩን ያዘጋጁት” አላቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም “በርታ” አሉኝ፡፡ ሸለሙኝም፡፡ ትምህርት ቤቱንም ሁሉ ሸለሙ” ሲል ወደ ቴአትር ዓለም አንደርድሮ ያስገባውን አጋጣሚ አውስቷል፡፡
===========================================
“ሚስስ ሐቺንግስ ጠጉራችንን በመቀስ ቆራርጣ እንደሮማውያን ትሪቡናል ሻሽ አሰረችልን፤ አቡጀዲ ገዝታ እንደ ግሪክ ኦራተሮች አስደገደገችን፡፡ ሲርበን ዳቦና ሻይ እያቀረበችልን እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ልምምዱን ቀጠልን፡፡ ጃንሆይ በአሥራ አንድ ሠዓት ግድም ደረሱ፡፡ አስቀድሜ ያዘጋጀሁትን አጭር መግለጫ እንዳነብ ሚስስ ሐቺንግስ ስለጠየቀችኝ ወጥቼ አነበብኩ፡፡ ቴአትራችንንም ጀመርን፤ ከመካከላችን አንዱ ልጅ ቃለ ተውኔቱ ቢጠፋበትም እንደምንም አድርገን ተወጣነው፡፡ በመጨረሻም በጣም የሞቀ ጭብጨባ ስለተሰማ በጣም ደነገጥን፡፡ ዲሬክተሩ አስፈቀደና ወደ ጃንሆይ አቀረበኝ፤ “ይህ ተማሪ እና ባለቤቱ ናቸው ቴአትሩን ያዘጋጁት” አላቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም “በርታ” አሉኝ፡፡ ሸለሙኝም፡፡ ትምህርት ቤቱንም ሁሉ ሸለሙ”
==============================================
መጋቢት 27 ቀን 1942 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ “ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት እና ግርማዊት እቴጌ ማዕረገ ሕይወት ዘቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤትን በጐበኙ ጊዜ የታየ ቴአትር” በሚል ርዕስ ሰፊ ሀተታ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ጋዜጣው በዚሁ ሀተታው ግርማዊና ግርማዊት እንዲሁም ልዑላን ልዑላት ንጉሣዊ ቤተሰብ ሳይቀሩ ቴአትሩን ምክንያት በማድረግ መጥተው በመጐብኘታቸው ለትምህርት ቤቱ ከፍ ያለ ክብር መሆኑን ጠቅሶ፣ ቴአትሩ “በእንግሊዝኛ የተሰራ የቆየ የጥንታዊ ግሪክ ታሪክ ሲሆን ንጉሥ ዳዮኒስስ ስለሚባል ንጉሥ ፍርድ የተዘጋጀ ነበር” ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን በዘገባው “የንጉሥ ዳዮኒስየስ ፍርድ” የተሰኘውን ቴአትር ዋና ታሪክ ዘርዝሮ አውጥቶታል፡፡ ፓዚያስ የተባለ ሰው በፈፀመው ወንጀል ተከስሶ ንጉሥ ዳዮኒስየስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይከራከርና የሞት ፍርድ ይፈረድበታል፡፡ ከፍርዱ በኋላ ፓዚያስ “ሞትን አልፈራም፤ ነገር ግን ከመሞቴ በፊት ወላጆቼን እንድሰናበት ይፈቀድልኝ” ሲል ንጉሡን ይለምናል፡፡ ንጉሡም ቤተሰቦቹን እንዲሰናበት ፈቃድ ሊሠጠው ያስብና የፓዚያስ ቤተሰቦች ያሉበትን አገር ርቀት አስታውሶ ፈቃድ ይከለክለዋል፡፡
በዚህ ጊዜ ዳመን የሚባል የፓዚያስ ወንድም ወደ ንጉሡ ቀርቦ “እኔ ፓዚያስን አምነዋለሁ፤ ቤተሰቦቻችንን እንዲሰናበት ፈቅደህለት በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ያልተመለሰ እንደሆነ በእሱ ቦታ እኔን ግደለኝ” ሲል ንጉሡን ይማፀናል፡፡ ንጉሡም ዳመን በወንድሙ ላይ ያለው የእምነት ጥንካሬና ፍቅር እያስገረመው ፓዚያስ እንዲሄድ ይፈቅድለታል፡፡ ነገር ግን ዳመንን ፓዚያስ ሳይመለስ የቀረ እንደሆነ መገደሉ እንደማይቀር ያስጠነቅቀዋል፡፡
በቴአትሩ ሁለተኛ ክፍል የሚታየው ንጉሥ ዳዮኒስየስ ከፍርድ ቤቱ ዳመንን አቁሞ “ይኸውልህ ያልሁህ ደረሰ፤ ወንድምህ ፓዚያስ የመመለሻው ቀን ሊያልፍ ነው” እያለ ሲያስፈራራው ነው፡፡ ዳመን ግን በወንድሙ ላይ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ ሳይገባው “ፓዚያስ አይቀርም፡፡ ይመጣል፤ የዘገየውም አንድ ያልታሰበ ነገር አጋጥሞት ይሆናል” በማለት ለንጉሡ ምላሽ ከመስጠቱ ፓዚያስ እያለከለከ መጥቶ ከመካከላቸው ይቆማል፡፡
ዳመን ግን ቅር እያለው ወዳጁን “ወንድሜ ፓዚየስ ሆይ፤ ለመሞት ብለህ እየተጣደፍክ እዚህ ድረስ ስለመጣህ አዝናለሁ!” ይለዋል፡፡ ንጉሥ ዳዮኒስየስ በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል ያለው ፍቅር ብርታት አንዱ ከአንዱ እስከ መሞት ድረስ እንደሚደርስ ተመልክቶ ልቡ ይነካና ዳመንንና ፓዚያስን በነጻ እንዲሄዱ ሲፈቅድላቸው መጋረጃ ተዘግቶ የቴአትሩ ፍጻሜ ይሆናል፡፡
ፀጋዬ “የንጉሥ ዳዮኒስየስ ፍርድ” የተሰኘውን ጽሑፍ የወሰደው በጊዜው ከሚማሩበት የእንግሊዝኛ መማሪያ መጽሐፋቸው ምንባብ ላይ ሲሆን ግማሽ ሠዓት የሚፈጅ ቴአትር እንዲሆን ጽሑፉን እንደገና አዘጋጅቶታል ማለት ነው፡፡ ይህንን ቴአትር በጣም በአጭር ጊዜ ያስጠናቸው ሁለቱ ጓደኞቹ መላኩ ዘለቀ እና ደሬሳ ካባ የሚባሉ እኩዮቹ ነበሩ፡፡ ቴአትሩን ያቀረቡት ሶስቱ ታዳጊዎች እንደመሆናቸው የንጉሥ ዳዮኒስየስን፣ የዳመንን እና የፓዚያስን ገፀ ባህሪ ለሶስት ተከፋፍለው ተጫውተውታል፡፡
በዚህ ቀደምት ሥራው የተጀመረው የፀጋዬ ቴአትር ጥበብ ሥጦታ አብሮት እያደገ ሄዶ እስከ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ዘልቋል፡፡ በንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ሆኖ “የደም አዝመራ” የተባለ የሙሉ ጊዜ ቴአትሩን በቀድሞው ማዘጋጃ ቤት ከክፍል ጓደኖቹ ጋር ለሕዝብ ሲያሳይ ፀጋዬ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነበር፡፡ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ ደግሞ “የእሾህ አክሊል” የተሰኘ ቴአትሩን በንግድ ሥራ ትምህርት ቤት አዳራሽ እና በጊዜው ገና አዲስ በነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር (አሁን ብሔራዊ ቴአትር) በማቅረብ የታላላቅ ሥራዎቹን መሠረት ጣለ፡፡ እነዚህ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ አልፈው ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ የቀረቡ ሁለት ሥራዎቹን ፀጋዬ ሲጽፍና ሲያዘጋጅ እድሜው 20 ዓመት እንኳን አልሞላም ነበር፡፡
ጋሼ ፀጋዬ የጥበብን አክሊል በልጅነቱ መቀዳጀቱ ክብርንና ሞገስን አስገኝቶለት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ እና ሥነ ጥበብ ዕድገትና መስፋፋት ላበረከተው ገንቢና በጐ አስተዋጽኦ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የ1959 ዓ.ም ተሸላሚ ሆኖ ሲመረጥ አሁንም ገና የ29 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ እስካሁን ድረስም ይህንን ሽልማት ከተቀበሉት መካከል በዕድሜ ትንሹ ጋሼ ፀጋዬ ገብረ መድህን ነው፡፡ ፀጋዬ በኢትዮጵያ የቴአትር ድርሰትና ዝግጅት ታሪከ ውስጥ ስሙ ሲዘከር የሚኖረው በጻፋቸው፤ ውብ አድርጐ በተረጐማቸው እና ባዘጋጀቸው አንፀባራቂ ታላላቅ ቴአትሮቹ ብቻ ሳይሆን በልጅነቱ ከቴአትር ጥበብ ጋር ተወዳጅቶ አብሮ ያደገ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡

 

br /

br /

Read 2266 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 14:53