Saturday, 06 August 2022 11:39

የስነተዋልዶ ጤና በአዲስ አበባ

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  “የስነተዋልዶ ጤና ላይ ምን እየተሰራ ይገኛል” በማለት ወደ አዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ እንዲሁም ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል አምርተናል። በተጨማሪም በመኖሪያ ቤት፣ ት/ቤት እና የንግድ ተቋማት ያገኘናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ልምዳቸውን አካፍለውናል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቤሮ የሴቶች ማብቃት እና ተጠቃሚነት ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ስፍራሽ አልማው እንደተናገሩት ቢሮው በዋነኝነት እየሰራ የሚገኘው ስለ ስነተዋልዶ ጤና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ነው። “በያዝነው አመት በአዲስ አበባ ከተማ የስነተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ለ90ሺ ሰዎች ተደራሽ ሆኗል” ብለዋል ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተሯ። ግንዛቤ ከሚሰጥባቸው ጉዳዮች መካከል ስለ ጡት እና ማህጸን ካንሰር፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ አባላዘር እና ፌስቱላ በሽታ እንዲሁም የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሽ ነው። በዚህም በከተማዋ የሚገኙት 11 ክፍለከተማዎች እና 122 ወረዳዎች የተካተቱበት ነው።
“እናት ጤና ስትሆን ነው ትውልድ ጤና የሚሆነው” በማለት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሴቶች ተሳትፎ ማብቃት እና ተጠቃሚነት ቡድን መሪ አቶ ደፋር አድነው በክፍለከተማው ለእናቶች ጤና የተሰጠውን ትኩረት ገልጸዋል። መስተዳድሩ ግንዛቤው [ስልጠና] ሲሰጥ ሰልጣኞችን የሚመርጥበት መስፈርት እንደየ ርእሰ ጉዳዩ ይለያያል። ነገር ግን እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ ሴቶችን ብቻ እንደሚያካትት ወ/ሮ ስፍራሽ አልማው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ መስረት አንዲት ሴት ወይም ወንድ ለትዳር ዝግጁ ናቸው ተብሎ ትዳር እንዲመሰርቱ ፍቃድ የሚያገኙት እድሜያቸው 18 አመት ለሆነ ሰዎች ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ልማድ የተለመደው ልጆችን በተለይም ሴትን በለጋ እድሜ መዳር ጎጂ ተብሎ እየቀረ ቢሆንም ሙሉበሙሉ ያልተቀረፈ ጉዳይ ነው። የተባበሩት መንግስታት ህጻናት መርጃ ድርጅት [unicef] ከሀገሪቱ [ኢትዮጵያ] መንግስት አገኘሁ ባለው መረጃ መሰረት እኤአ ከ2021 አሁን እስካለንበት 2022 በተለይም በድርቅ በተጎዱ አከባቢዎች ሴቶች እድሜያቸው ለአቅመ ሄዋን ሳይደርስ ትዳር እንዲይዙ ይገደዳሉ። ይህም ሴት ልጆችን ለጋብቻ መስጠት የቤተሰቡ አንዱ ችግር መፍቻ መንገድ ተደርጎ እየተወሰደ በመሆኑ ቁጥሩ እንዲጨምር አድርጎታል ይላል የዩኒሰፍ መረጃ።
እኛም በታዳጊዎች ላይ እየተከሰተ የሚገኘውን ችግር እና በአንድ ጾታ ላይ ብቻ የሚሰራ ስራ ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ታሳቢ በማድረግ “ታዳጊ ሴት እና ወንድ ልጆችን እንዲሁም ከ18 አመት በላይ ለሆኑ ወንዶች በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ እንደ ቢሮ ምን እየተሰራ ይገኛል” ስንል ጥያቄ አቀረብንላቸው።  
ወ/ሮ ስፍራሽ እና አቶ ደፋር እንደገለጹት ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ ብቻ ነው ወንዶች የስልጠናው ተሳታፊ እየተደረጉ የሚገኙት። እናም የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት በጾታዊ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ሁለቱንም ጾታዎች ሊያካትት በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ወንዶችን ተሳታፊ ለማድረግ “እንደ የቤት ስራ እንወስደዋለን” ብለዋል ወ/ሮ ስፍራሽ አልማው ።
በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የወጣቶች እና ስነተዋልዶ ባለሙያ ሲስተር መታሰቢያ ከ10 እስከ 24 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ታዳጊ እና ወጣቶች ላይ እየሰሩ ይገኛሉ። ሆስፒታሉ በታዳጊ እና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የሱስ ተጠቂ የሆኑ፣ ያልተፈለገ እርግዝና ላጋጠማቸው እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ምክር ፈልገው ለሚሄዱ ወጣቶች የማማከር አገልግሎት ይሰጣል። እንዲሁም ስለ አባላዘር በሽታ ወይም ኤች አይ ቪ ኤድስ ግንዛቤ ይሰጣል።
በሆስፒታሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ፣ የቤተሰብ ምጣኔ [የወሊድ መከላከያ] እና ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ታዳጊዎች ወይም ወጣቶች አስፈላጊውን አገልግሎት እንደሚያገኙ ነው ሲስተር መታሰቢያ የተናገሩት። በተጨማሪም ወደ ት/ቤቶች በመሄድ የውይይት፣ የማማከር እና የግንዛቤ ስራ ይሰራል።
ታዳጊዎች እና ወጣቶች ከወላጆቻቸው ጋር በስነተዋልዶ ጉዳዮች በግልጽነት ከመወያየት ይልቅ ከጓደኛ ጋር መነጋገር ይመርጣሉ ብለዋል ሲስተር መታሰቢያ። ለዚህም ታዳጊዎች ወደሚ ገኙበት በመሄድ ስለአቻ ግፊት እና መሰል ጉዳዮች ተገቢውን ትምህርት በመስጠት እንዲሁም በግልጽነት ሀሳባቸውን እንዲገልጹ በማድረግ ከቤተሰባቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ለማሻ ሻል እየተሰራ ይገኛል።
በተቋም ደረጃ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በቤተሰብ ውስጥ ስለ ስነተዋልዶ የሚደረገው ውይይት ምን ይመስላል ስንል ወደ መኖሪያ ቤት፣ ት/ቤት እና የንግድ ተቋማት ጎራ ብለናል።
ቤተልሄም ድንቁ ትባላለች የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ናት። ከእናቷ ጋር አንዳንድ ሀሳቦች ላይ ከመነጋገር ባለፈ “በስነተዋልዶ ጤና ላይ እንደ ቤተሰብ የሚደረግ ውይይት የለም” ብላለች። ይህም ታላቅ እህቷ በድብቅ የፍቅር ግንኙነት እንድትጀምር ብሎም ጸንሳ ከቤተሰቦቿ እውቅና ውጪ ከቤት እንድትወጣ ምክንያት ሆኗታል።
በተመሳሳይ በቤተሰብ ውስጥ ስለጾታዊ ግንኙነት ሆነ መሰል ጉዳዮች ምንም አይነት ውይይት አለመኖሩን የሚናገረው በሽያጭ ስራ ላይ የተሰማራው ጸጋዬ ደጀኔ ነው። ጸጋዬ ለዚህም እንደምክንያት ያስቀመጠው “ይሄን የምናወራበት እድል አላገኘንም ወይም ማውራት ጥቅም የለውም ብዬ ስላሰብኩ ይሆናል” የሚል ነው።
ከቤተልሄም እና ጸጋዬ ሀሳብ በተቃራኒ በቤተሰብ ውስጥ በሙሉ ነጻነት እንዳደገች የምትናገረው ሄለን ክፍሌ የጸጉር ባለሙያ ስትሆን የ9 አመት ልጅ አላት። ሄለን ከአስሪዎቹ እድሜዋ ጀምሮ በተለይ ከታላቅ እህቷ ጋር ተፈጥሯዊ ስለሆነው የወርአበባ ጨምሮ ስለ ሌሎች ጾታዊ [የስነተ ዋልዶ] ጉዳዮች መነጋገሯ በጣም ጥቅም እንዳለው ተናግራለች። “ልጄ እኔ ባደኩበት መንገድ እንዲያድግ ነው የምፈልገው” በማለት በአጽንኦት ተናግራለች።
“እኔ ባደኩበት አስተዳደግ ልጄ እንዲያድግ አልፈልግም” ያለችው ደግሞ የ4 አመት ልጅ እናት የሆነችው መቅደስ ወንድወሰን ናት። መቅደስ ከቤተሰቧ ጋር ስለ ስነተዋልዶ ማውራት የሚያ ሳፍር ነገር ስለሚመመስላቸው በፍጹም አውርተውበት እንደማያውቁ ተናግራለች። ይህን ቃለመጠይቅ በሰጠችበት ወቅት “ስለጉዳዩ ለማውራት እውቅት የለኝም” በማለት ፍራቻዋን ነግራናለች።
ስለ ስነተዋልዶ ጉዳዮች የመነጋገር ፍራቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተቀባበለ እንደመጣ የተናገሩት ወ/ሮ ገነት አበበ ሲሆኑ የ61 አመት አዛውንት፣ የ6 ልጆች እናት እና የ3 ልጆች አያት ናቸው። እንደሳቸው አባባል ማፈር እና መፍራት ሰዎች ማወቅ የሚገባቸውን እንዳያውቁ አድርጓቸዋል። በዚህ ችግር የእሳቸው ቤተሰብም ተካፋይ ሆኗል።
“መፍራትን በማስወገድ በእራስ መተማመንን የማዳበሪያ እና በእቅድ ለመንቀሳቀስ አንዱ መንገድ ስለ ጾታዊ ጉዳይ መወያየት ነው” በማለት ከእናቱ፣ ከወንድሞቹ እና እህቶቹ ጋር እንደሚነጋገር የተናገረው ተቻለው ንጉሴ [ኢ/ር] ነው። ተቻለው ስለጾታዊ ጉዳዮች በግልጽነት እየተነጋገረ በማደጉ የእራሱን ቤተሰብ ለመመስረት በእራስ መተማመኑን እንደጨመረለት ተናግሯል።  
የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል እንዲሁም የአዲስ አበባ መስተዳድር የሚሰጡት ግንዛቤ ከላይ የጠቀስናቸው እና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የታለመ ነው። ከሚሰጠው ግንዛቤ በተጨማሪ የአ.አ መስተዳድር ከተለያዩ የግብረሰናይ ተቋማት ጋር በመተባበር ነጻ የህክምና ምርመራ አገልግሎት ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ ለ18ሺ 6መቶ ሰዎች መሰጠቱ ተጠቃሽ ነው።
ከዚህ አልፎም ህክምና ለማድረግ አቅም የሌላቸውን ሰዎች ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያመቻቻል። ነገር ግን የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ከባህል እና ሀይማኖት ጋር ማያያዝ ለስራው እንቅፋት መሆኑን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሴቶች ተሳትፎ ማብቃት እና ተጠቃሚነት ቡድን መሪ አቶ ደፋር አድነው ጠቁመዋል። ስለሆነም ህብረተሰቡ ስለ ስነተዋልዶ ጤና ተገቢውን ግንዛቤ በመውሰድ ተጠቃሚ እንዲሆን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።  

Read 12151 times