Saturday, 23 July 2022 14:59

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በወልቃይት ጉዳይ ላይ ከህዝብ ጋር መከሩ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

    • “የወልቃይትና ራያ ማንነት ጉዳይ የክልሉ መንግስት የማይቀየር አቋም ነው”
      • “ወልቃይትና ራያ መሬቱም የአማራ፤ ህዝቡም አማራ ነው” ብለዋል
             
            የወልቃይትና ራያ ማንነት ጉዳይ በምንም ሁኔታ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑንና በዚህ ጉዳይ ላይ የክልሉ መንግስት አቋም የፀና መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፍለ ገለፁ።
ሰሞኑን በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ውስጥ ከነዋሪው ጋር ሲመክሩ የሰነበቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፍለ እንደተናገሩት የአማራ ህዝብ በተለያዩ አካባቢዎች እያደረሰበት ያለው የግፍ ጭፍጨፋ የክልሉን መንግስትም እንደሚሰማው ጠቁመው፤ “ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት የምንችለው” ከህዝባችን ጋር በጥምረት ስንሰራ ነው” ብለዋል።
“የአማራው ሞት ቢያመንም መፍትሄው ጊዜያዊ ጩኸት ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ መስራት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የወልቃይትና ራያ ማንነት ጉዳይን በተመለከተ ከነዋሪዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ርዕሰ መስተዳድሩ ሲመልሱ፤ የወልቃይትና ራያ ማንነት ጉዳይ የክልሉ መንግስት የማይቀየር ወጥ አቋም ነው፤ እነዚህን ቦታዎች ለማንም አሳልፈን አንሰጥም፤ ማለታቸውን የአማራ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
የአማራ ህዝብና የክልሉ መንግስት ሰላም ፈላጊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሰላም ፈላጊዎች ብንሆንም የጠላትን ወረራ ለመመከት ግን ሁሌም ዝግጁዎች ነን። የጠላትን ወረራ ለመመከት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ ነን ብለዋል፡፤ ከደሴ ነዋሪ ህዝብ ጋር ሲመክሩ የሰነበቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል፤ በክልሉ በህውሃት ታጣቂ ሃይሎች የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችለውን መርሃ-ግብር አስጀምረዋል።
በክልሉ በህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በተፈጸመ ጥቃት ከአንድ ሺ 145 በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ5.9 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት መድረሱን ቀደም ሲል የቱደረገ ጥናት ማረጋገጡ ተጠቁሟል።
መንግስት ህብረተሰቡንና ተቋማትን በማስተባበር የወደሙትን ትምህር ቤቶች በተሻለ ደረጃና ጥራት እንደሚሰራም ተገልጿል።

Read 11897 times