Saturday, 23 July 2022 14:15

“ቶሎ የተያዘ የጡት ካንሰር ይድናል”

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ከ40 እስከ 60 በመቶ የካንሰር በሽታ መነሻ የአመጋገብ ችግር ነው” ምንጭ/ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ተመራማሪ] እና አሰልጣኝ ዶ/ር ዳዊት መንግስቱ ካንሰር፡- ካንሰር ማለት በአንድ የሰውነት ክፍል ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት[sell] ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ ተባዝተው ወደ ሌላ የሰውነት
ክፍል ሲሰራጩ ነው። የህዋሳት መሞት እና በሌላ አዲስ ህዋስ መተካት እንዲሁም መባዛት ተፈጥሯዊ ሲሆን የካንሰር በሽታ መነሻ የሆኑት የእነዚህ ህዋሳት ሂደት ግን ከዚህ የተጻረረ ነው። አስፈላጊ ያልሆኑት ህዋሳት ናቸው የሚባዙት። በአለም አቀፍ ደረጃ ለሞት ከሚያደርሱ በሽታዎች ውስጥ የሚመደበው የካንሰር በሽታ እ.ኤ.አ 2021 የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት አለም ላይ 10 ሚሊዮን ሰዎች በካንሰር ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል። በአለም
አቀፍ ከ5 ሰዎች 1 ሰው በህይወት ዘመኑ በካንሰር የመያዝ እድል አለው።
    በቀዳሚነት እየተስፋፋ የሚገኘው የካንሰር በሽታ አይነት፡-
በአለም አቀፍ ደረጃ የካንሰር በሽታ ከሚያጠቃቸው ሰዎች መካከል 12 በመቶ በጡት ካንሰር ነው። እንደ የአለም የጤና ድርጅት ጥቆማ እ.ኤ.አ በ2021 የጡት ካንሰር በሽታ 2.26 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቂ አድርጓል። በዚህም በአለማችን ከካንሰር የበሽታ አይነቶች ቀዳሚውን ቦታ ይዟል። እንዲሁም ከፍተኛ የሞት መጠን በማስመዝገብ ከሳንባ፥ ከአንጀት፥ ከጉበት እና ከጨጓራ የካንሰር በሽታዎች በመቀጠል የጡት ካንሰር የ685ሺህ ሰዎችን ህይወት በመንጠቅ በ5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በኢትዮጵያ ከመላው የካንሰር ታማሚዎች ውስጥ 34በመቶ በጡት ካንሰር የተጠቁ ናቸው። የጡት ካንሰር ማለት
በጡት ህብረህዋሳት ውስጥ የህዋሳት ቁጥር በማያስፈልግ መጠን እና ሁኔታ መራባት ነው። ካንሰር የሚከሰተው ጡት አከባቢ ባለ ህዋስ ላይ በሚወጣ እጢ አማካኝነት ሲሆን በአብዛኛው በሴቶች እንዲሁም አልፎአልፎ በወንዶች ላይ የሚስተዋል ነው።
የጡት ካንሰር መንስኤዎች፡-
ሀ. አመጋገብ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ ለጡት ካንሰር ብቻ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ የአብዛኛው የካንሰር አይነቶች ቀዳሚ መነሻ ምክንያት ነው። “ከ40 እስከ 60 በመቶ የካንሰር በሽታ መነሻ የአመጋገብ ችግር ነው” በማለት የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ተመራማሪ እና አሰልጣኝ ዶ/ር ዳዊት መንግስቱ
ተናግረዋል። እንደሳቸው ንግግር በዋናነት እንደ መንስኤ የሚጠቀሰው የምግብ አይነት የእንስሳት ተዋጽኦ ነው። ከዚህም ምሳሌ ያደረጉት ስጋ’ን አዘውትሮ መመገብን ነው።
ለ. የሰውነት ሁኔታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እጥረት እና ከአቅም በላይ ውፍረት።
ሐ. የአልኮል መጠጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው መጠጦች መጠጣት።
መ. በዘር በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር ታማሚ መ ኖር ለ ህመሙ ተ ጋላጭ ያ ደርጋል። ከእናት፣ ከእህት፣ ከአባት እና ወንድም የመውረስ ዕድል ይኖራል፡፡
ሠ. ከወለዱ በኋላ ጡት አለማጥባት፡፡
ረ. ከ12 ዓመት እድሜ በፊት የወር አበባ መምጣት እና ዘግይቶ ከ55 ዓመት እድሜ በኋላ የወር አበባ መቆም ሴቶችን በሆርሞኖች ረዘም ላለ ጊዜ ያጋልጣሉ፡፡ ይህም በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ሸ. እድሜ፡- የጡት ካንሰር በየትኛውም እድሜ ሊከሰት እንደሚችል የታወቀ ሲሆን እድሜ በጨመረ ቁጥር ግን ይበልጥ ይከሰታል።
ቀ. የጡት ካንሰር እና የማህጸን ካንሰር ተጠቂዎች፡- ከዚህ በፊት በጡት ካንሰር የተያዙ ወይም ካንሰር ያልሆኑ የጡት በሽታዎች ያጋጠማቸው ሴቶች ለሁለተኛ ጊዜ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ እንዲሁም የማህጸን ካንሰር በሽታ ተጠቂዎች ለጡት ካንሰር ሊጋለጡ ይችላሉ።
በ. የመጀመሪያ እርግዝና ከ30 ዓመት እድሜ በኋላ ከሆነ እና ሙሉ ጊዜ (9 ወር) ሳይጨርሱ መውለድ የጡት ካንሰርን የመያዝ ዕድል ሊኖረው ይችላል።
እነዚህ መንስኤዎች ሲኖሩ የጡት ካንሰር አለብዎት ማለት አይደለም ነገር ግን ወደ ሐኪም በመሄድ እንዲያረጋግጡ ይመከራል፡፡
የጡት ካንሰር ምልክቶች፡-
1. በወር አበባ ኡደት ጊዜ በጡት ላይ ወይም አከባቢ እንዲሁም በብብት አከባቢ እብጠት መኖር
2. የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ መጨማደድ እና መቅላት
3. የጡት ቀለም መቀየር
4. ቆዳ ላይ መበሳሳት
5. በሁለቱ ጡቶች መሀከል የመጠን ልዩነት
6. ከጡት ውስጥ የሚወጣ ደም የተቀላቀለበት ወይም ንጹህ ፈሳሽ
የምርመራ አይነቶች፡-
-  በእጅ መፈተሽ በቤት ውስጥ እራስንከመፈተሽ ባለፈ የህክምና ባለሙያዎች ጡት ላይ እብጠት መኖሩን ይፈትሻሉ።
-  አልትራሳውንድ በፍተሻው ወቅት ምልክት ወይም ጥርጣሬ በማለሙያዎቹ ከተገኘ በአልትራሳውንድ መሳሪያ ይታያል።
-  ሞሞግራም እንደ ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ ገለጻ በጨረር የሚደረገው ምርመራ ከተደጋገመ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል እድሜያቸው ከ40 አመት በላይ ለሆኑ ሴቶች በወር 1 ጊዜ በሞሞግራም [ጨረር] እንዲታዩ ይደረጋል።
የጡት ካንሰር በሽታ ደረጃዎች
የጡት ካንሰር እንደሌሎች የካንሰር ዓይነቶች በክብደት ደረጃው ሲለካ 4 ደረጃዎች አሉት፡፡ ከደረጃ 1-3 ያለ ካንሰር ማለት በመጀመሪያ ደረጃ ያለ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ያልተሰራጨና መታከም የሚችል የካንሰር ደረጃ ነው፡፡ ደረጃ 4 የምንለው ደግሞ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የተሰራጨ ካንሰር ማለት ነው፡፡ ከጡት አልፎ ሊዛመት ከሚችልባቸው ቦታዎች አጥንት እና ጉበት ይጠቀሳሉ።= በጡት ካንሰር በሽታ የተጠቃ ሰው የመዳን እድል- በካንሰሩ መያዛቸው የተረጋገጠላቸው ሰዎች ወደ ሕክምና በፍጥነት ማምራት ይኖርባቸዋል። በተለያዩ ህክምና ዘዴዎች በመጠቀም በጡት ካንሰር የተጠቃ ሰው
ከበሽታው ሙሉበሙሉ እንዲድን ጥረት ይደረጋል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ደረጃ 1 እና 2 ላይ ህክምና ያገኙ ታካሚዎች የመዳን እድላቸው ይጨምራል። የፒንክ ሎተስ ኢትዮጵያ የጡት ካንሰር ድጋፍ አድራጊ ቡድን ወይም ሚሮን ካንሰር ሰፖርት ፋውንዴሽን መስራች ወ/ሮ ሜሮን ከበደ በጡት ካንሰር በሽታ ተይዘው ከዳኑ ሰዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። “ቶሎ የተያዘ የጡት ካንሰር ይድናል” በሚል ዘመቻ የስነልቦና እና ሌሎች የህክምና
ድጋፎች በማድረግ ላይ ይገኛሉ ወ/ሮ ሜሮን ከበደ። ህክናውን በተመለከተ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት፤ ኬሞቴራፒ፣ ሆርሞናል ቴራፒ እና ታርጌትድ ቴራፒ (HER2)፤ የጨረር ህክምና (Radiotherapy) የመሳሰሉት ናቸው፡፡
የጡት ካንሰር አስቀድሞ መከላከል፡-
እንደ አጠቃላይ ካንሰር አስጊ በሽታ ይሁን እንጂ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ተመራማሪ እና አሰልጣኝ ዶ/ር ዳዊት መንግስቱ እንደሚናገሩት የጡት እና ሌሎች የካንሰር አይነቶች ጨምሮ 80በመቶ የሚሆነውን የካንሰር በሽታ አስቀድሞ መከላከል ይቻላል። ለዚህም ዋነኛው መፍትሄ ነው ተብሎ በዶ/ር ዳዊት
የተጠቀሰው የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የበሽታ የመከላከል አቅም ማሳደግ ነው። እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ጭንቀትን ማስወገድ የካንሰር በሽታን ለመከላከል ይረዳል። ዶ/ር ረድኤት ንጉሴ እንደሚናገሩት በሽታው ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተሉ አስቀድሞ አንዲት ሴት በቤቷ ሆና የጡቷን ጤንነት መመርመር ቀዳሚው አማራጭ ነው። ይህም በወር 1 ጊዜ መስታወት ፊት በመቆም እራስን የሚፈተሽበት ሂደት ነው። በወንዶች ላይ የሚከሰት የጡት ካንሰር ምልክቶች በቀላሉ ስለሚታይ እንደ ሴቶች በወር 1ጊዜ በቤት ውስጥ መፈተሽ አያስፈልግም ብለዋል ዶ/ር ረድኤት። በተጨ ማሪም የህክምና ተቋም በመሄድ መመርመር ይገባል።
Read 12599 times