Print this page
Saturday, 16 July 2022 18:06

ለከርሞ የሚራብ ዘንድሮ እህል- ተራ ያንዣብባል!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ደራሲ ከበደ ሚካኤል በ”ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ” የሚከተለውን ትርክት አኑረውልናል። ጥንት የጻፉት ለዛሬ አብነት አለውና ጠቀስነው።
ርዕሱ፡- “እጅግም ስለት ይቀዳል አፎት
      እጅግም ብልሃት ያደርሳል ከሞት” ይላል። በአጭሩ ታሪኩ እነሆ፡-
ከዕለታት አንድ ቀን፣ ዕድሜያቸውን ሙሉ መጽሐፍ በማንበብና፣ ጥበብን በመመርመር የሚኖሩ ሶስት ሰዎች ነበሩ። ሥራ ለመለመንና ደጅ ለመጥናት ወደ ቤተ-መንግስት ሄዱ። የዘመናቸው ንጉስ ጥበብ እንደሚወድ አሳምረው ያውቃሉ። እየተጫወቱ መንገድ እንደጀመሩ እነሱ ወደሚሄዱበት ከተማ የሚሄድ አንድ ሌላ መንገደኛ አግኝቷቸው አብሯቸው ይጓዝ ጀመረ። እሱ ብዙም የተማረ አልነበረም። ሆኖም ከነሱ የበለጠ የተፈጥሮ አስተዋይነት ነበረው።
ሦስቱ ሰዎች የጥበብን ነገር አንስተው እየተከራከሩና ወደፊት የሚያገኙትን ክብር እየተጫወቱ ሲሄዱ ካንድ ጫካ ውስጥ ደረሱ። እዚያ ቦታ ከብዙ ጊዜ በፊት የሞተ አንድ አንበሳ አገኙ። አጥንቱ በያለበት ተበታትኗል። ከሦስቱ አዋቂዎች አንደኛው፡-
“እንግዲህ የዕውቀታችን ልክ የሚታወቀው አሁን ነው። እነሆ ይህ ተበታትኖ የምናየው የአንበሳ አጥንት ነው። እኔ ጥቂት ቃል ደግሜ፣ ይህ አጥንት ሁሉ ተሰብስቦ ቀድሞ እንደነበረ በየቦታው ገብቶ እንዲገጣጠም አደርገዋለሁ” አለ።
ሁለቱ ባልንጀሮቹ፡- “እስቲ በል አድርግ እንይህ” አሉት።
እሱም እንዳለው ድግምቱን ደግሞ የአንበሳውን አጥንት ሁሉ በየቦታው ገብቶ እንዲገጣጠም አደረገው።
ሁለተኛው አዋቂ ይሄንን ባየ ጊዜ፤ “እኔ ደግሞ፣ ስጋውን መልሼ፤ ደሙን ሞልቼ ቆዳውን አለብሰዋለሁ” ብሎ ድግምቱን ደገመና እንደተናገረው አደረገ።
 ያ ብዙ ትምህርት የሌለው አራተኛው መንገደኛ፣ የአንበሳው አጥንት እንደተገጣጠመና ሥጋውን ደሙንና ቆዳውን አግኝቶ አካላቱ እንደሞላለት በዓይኑ ባየ ጊዜ፣ የነገሩ አካሄድ አላምርህ ስላለው፤ በአቅራቢያው ግራ ቀኙን ተመልክቶ አንድ ዛፍ መኖሩን አስተዋለና ልቡ ረጋ።
ሦስተኛው አዋቂ ተነሳና፤ “እናንተ ይሄንን ብታደርጉ እኔ ደግሞ የሕይወት ትንፋሽ የሚሰጥ ድግምት አውቃለሁ” ብሎ መድገም ሲጀምር፤ አራተኛው መንገደኛ፤
“ወንድሞቼ ሆይ! ይህ አያያዛችሁ ከቶ አላማረኝም። እናንተም ዕውቀታችሁን ብቻ እንጂ ይህ የምታስነሱት አውሬ አንበሳ መሆኑን ዘንግታችሁታል መሰለኝ። ነፍስ ዘርቶ የተነሳ እንደሆነ ከያዝነው በትር በቀር የምንከላከልበት ሌላ የበቃ መሳሪያ በእጃችን ስለሌለ ሁላችንንም ያበላሸናልና ተው ይቅር” ብሎ ቢያሳስባቸው፣ ያ መጀመሪያ ያንበሳውን አጥንት የገጣጠመ አዋቂ፣ ከት ብሎ ሳቀና፤ “አዬ  የኛ ጅል ደንቆሮ፣ እኛ የምንሰራውን ጥበብ እየተመለከትህ መደነቅ አነሰህና ምን ጥልቅ አርጎህ በማታውቀው ሙያ ገብተህ ምክር ልትሰጠን ደፈርህ” ብሎ  ዘለፈው። ለአንበሳው ሥጋ ደምና ቆዳ የመለሰለትም ሁለተኛው አዋቂ፤ “ምንስ አስር ደንቆሮ ብትሆን ከሞት ያስነሳነው አውሬ መልሶ እኛኑ ይበላናል ብለህ ማሰብህ ከጅልም ጅል ነህ!” ብሎ ሳቀበት።
“እንግዲያውስ ለእኔ ለደንቆሮው ፍቀዱልኝና እዚያ እዛፍ ላይ እስክወጣ ድረስ ጊዜ ስጡኝ” ብሎ  ሸሽቶ ከዛፉ ላይ ሆኖ መጨረሻቸውን ይመለከት ጀመር።
ሦስተኛው አዋቂ፡-
“ከጓደኞቼ አንሼ አልቀርም” ብሎ ድግምቱን ደግሞ ሲጨርስ፣ አንበሳው ነብስ ዘርቶ ተነስቶ፣ በተራበ አንጀቱ ዘልሎ አጠገቡ የነበረውን ነብስ የዘራለትን ሰው መጀመሪያ በላው። ቀጥሎ ሥጋ ደምና ቆዳ የሰጠውን ሰው ደገመው። ከዚህ በኋላ ራቡ ታገስ ሲልለት አጥንቱን የገጠመለትን ሰው ገድሎ ሬሳውን ጎትቶ ወደ ዋሻው ይዞት ሄደ።
***
“ደንቆሮ የተባለውን ሰው ድንቁርናው አዳነው። ሦስቱን ጥበበኞች ግን የሰሩት የጥበብ ሥራ አጠፋቸው። ማንኛውም ነገር በመጠኑ ሲሆን መልካም ነው። ከመጠን ሲያልፍ ግን ይልቁንም ፉክክር ሲጨመርበት፤ ሌላው ይቅርና ያቺ መልካሚቱ ጥበብ እንኳን ትጎዳለች፤ ከጥፋትም ታደርሳለች።”
መጽሐፍ ማንበብና ጥበብን መመርመር ታላቅ ጸጋ ነው። ዕውቀት የዚህ ፍሬ ነው። እውቀትን ወደ ተግባር ስንመነዝር ትርጓሜው ሕይወት ይሆናል። ወጣቶቻችን ይህን ሊገነዘቡ ያሻል። ከሁሉም በላይ ግን መሪዎች!!
መሪዎቻችን ህዝብን የመምራት ሃላፊነት ተቀብለዋልና፣ ሰላምን የማስከበርና ጦርነትን የመግታት የአንበሳው ድርሻ እነሱው እጅ ላይ ይወድቃል። ስለዚህ በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በማህበራዊውም ጉዳይ ላይ ሳያሰልሱ፣ ነጋ ጠባ መጨነቅ ግዴታቸው ይሆናል። በእርግጥ ለራሳቸው ህልውናም ሲሉ ነው! ወንበር ያለ ፖለቲካ ጥንካሬ፣ ፖለቲካም ያለ ኢኮኖሚ መረጋጋት ስር የለውም። ማህበራዊ ምስቅልቅል የዚህ ነጸብራቅ ነው።
የሒትለር አማካሪና የጀርመን ፕሮፓጋንዳ ዲሬክተር የነበረው ጎብልስ፤ “አንድን ውሸት ደጋግሞ በመናገር እውነት ለማድረግ ይቻላል” የሚለው ንድፈ-ሀሳቡ፣ ዛሬ መኖር የለበትም- ነፍሶበታል (Obsolete ሆኗል እንዲል ፈረንጅ)፡፡ “እውነት ቦት ጫማዋን ሳታጠልቅ እውሸት አለምን ዞሮ ይጨርሳል”፤ የሚለውን ብሂል አገር አውቆታልና ነው። የአመራሮችና የሹማምንት ውሸት እድሜ የለውም! ቢያንስ “ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም” የሚለውን ተረት አለመዘንጋት ብልህነት ነው፤ እንላቸዋለን።
መጪው ጊዜ የከፋ እንዳይሆን ዛሬን ማስተካከልና ማመቻቸት ይበጃል። ዳር ዳሩን መዞር ትተን ወደ ጉዳዩ መግባት፣ ወደ ወሳኙ ለውጥ ያሸጋግረናል ብለን እንገምታለን። የተሸራረፈ ለውጥም አያዛልቀንም። ነገን በቅጡ ማስተዋል ከብዙ ችግር ያድነናል።
ዝናብ የሚመጣ ከሆነ መጠለያ ማመቻቸት፣ ድርቅ ሊከሰት ይችላል ከተባልን አስቀድመን ከእልቂት የሚያድነንን ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው። ጦርነት እንኳ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ከተጠረጠረ መዘጋጀት ያባት ነው። አለበለዚያ “ለከርሞ የሚራብ ዘንድሮ እህል-ተራ ያንዣብባል” የሚባለው ተረት ዓይነት እንሆናለን።
ከዚህ ይሰውረን! ሁሉም ነገር እንደ ቤንዚንና ናፍጣ ዋጋ ጭማሪ በየቀኑ እያሳቀቀን፣ በጥይት ሰውነታቸው የተበሳሳ ህጻናት የምናይበት አሰቃቂ ሁኔታና ኢ-ሰብዓዊ ትዕይንት ውስጥ መግባት፣ አንድም ከድጡ ወደ ማጡ ነው፣ አንድም ደግሞ “ኦ ሰላም! በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ!” የሚለውን ጥንተ-ንባባችንን የሚያስታውሰንን ትዝብት በመሪር ሐዘን ማሰብ ነው! በዚህ ላይ በየፖለቲካና ብሄር ድርጅቶቹ የሚታየው መንታ ገጽታ፣ ዛሬም እንደ ትላንት በቅራኔ፣ በውዝግብና በመተላለቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ ነገራችንን ሁሉ እጅጉን የእውር- የድንብር ያስኬደዋልና “ያገር ያለህ?!” ያሰኘናል። ከዚህ ቁጣም ይሰውረን!! ቀና አዕምሮና ቀና ሰብዕና ያለው ዜጋ ሁሉ፣ ሁኔታው የዕለት ሰርክ መሆኑን አውቆና ነግ-በእኔ ብሎ ቢያስብበት፤ ለሁሉም መልካም ነው።

Read 11724 times
Administrator

Latest from Administrator