Saturday, 16 July 2022 17:57

ከኮንዶሚኒየሙ እጣ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት ፍርድ ቤት ቀረቡ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  • የማይመለከታቸው 172 ሺ ሰዎች በዕጣው ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል
   • የሶፍትዌሩ ብቃት ከንቲባዋ ባሉበት መረጋገጡን ባለሙያዎቹ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል
   • ፍ/ቤቱ መዝገቡን ለመመርመር ለቀጣይ ሰኞ ቀጠሮ ይዟል
               
         ከ14ኛው ዙር የ20 80 እና ከ3ኛው ዙር የ40/60 የአዲስ አበባ ከተማ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ ያልቆጠቡና በወቅቱ ያልተመዘገቡ ሰዎች በህገወጥ መንገድ በእጣው  እንዲካተቱ ተደርገዋል የሚል ቅሬታ በፈጠረው የኮንዶሚኒየም እጣ ጋር  በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ የስራ ሃላፊዎችና የሶፍትዌር ባለሙያዎች ትናንት ፍ/ቤት ቀረቡ፡፡ ከዚሁ ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉትን የአዲስ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሀፍቱን ያለመከሰስ መብት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ትናንት አንስቷል፡፡
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት እነዚሁ ተጠርጣሪዎች፡- የቤቶች ልማት ዳታ ቤዝ ቡድን መሪ ስመኘው አባተ፣ የቴክኒክ ሙያ ስልጠና አይሲቲ ቢሮ ም/ቢሮ  ኃላፊ አቶ አብርሃም ሴርሞሌ፤ የቤቶች  የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ  ባለሙያሚኪያስ  ቶሌራ፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አይሲቲ ሃላፊ አቶ ኩምሳ ቶላና የሶፍትዌር ባለሙያዎች፡- ሃብታሙ ከበደ፣ ዮሴፍ ሙላት፣ጌታቸው በሪሁን እና ቃሲም ከድር የተሰኙ ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት 172 ሺህ በኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ላይ ያልተመዘገቡ፣ ያልቆጠቡ ግለሰቦችን በዕጣው ውስጥ በዳታ ቤዝ በማካተት፣ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ አድርገዋል ሲል የፌደራል ፖሊስ  ወንጀል ምርመራ ለችሎት አስረድቷል፡፡
ፖሊስ ለችሎቱ ባቀረበው የክስ መነሻ፣ ለዕጣው 79 ሺህ በተገቢው መንገድ የቆጠቡ ግለሰቦች የተካተቱ ሲሆን ቀሪዎቹ  172 ሺህ ያልተመዘገቡና ያልቆጠቡ ሰዎች በዳታ ቤዙ እንዲካተቱ መደረጋቸውን ከባንኩ በቀረበው ሲስተም መረጋገጡን አመልክቷል፡፡ ሂሳባቸውን የዘጉና ገንዘባቸውን ወጪ አድርገው የወሰዱ ሰዎች ሁሉ እንዲካተቱ መደረጉንም ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ “ከሰው ንኪኪ የፀዳ” ነው የተባለው ሶፍትዌር፣  ከሰው ንክኪ ያልጸዳ እንደነበረም አመልክቷል፡፡
ፖሊስ ቀሪ ምርመራዎችን ለማካሄድና የምስክር ቃል ለመቀበል 14 ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠውም ጠይቋል፡፡
በችሎቱ የቀረቡት ተጠርጣሪ የሶፍትዌር  ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ “ሶፍትዌሩ በኢኖቬሽን ሚኒስቴር እንዲፈተሽ ተደርጎ ከንቲባዋ በተገኙበት ህዳር 1 ቀን 2014 ተፈትሾ ብቁ መሆኑንና ዳታ ቤዙም ምንም እንደሌለው ተረጋግጧል፡፡: ስለዚህም እኛ ስለቁጠባ አያገባንም፤ ስራችን ሶፍትዌር ማልማት ብቻ ነው፡፡
በዕጣ አወጣጥ ወቅት ሶፍትዌር ታይቶ ዳታ ቤዙ ምንም እንደሌለው ተረጋጦ ሀክ እንዲደረግ እንኳን ኢንተርኔት አጥፍተን ነው የገባነው ስለዚህም በወንጀሉ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የለንም ብለዋል፡፡ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ፍ/ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለፊታችን ሰኞ ሀምሌ 11 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡



Read 11837 times