Print this page
Saturday, 16 July 2022 17:45

የገቢ ግብር ክፍያዎችን በቴሌብር መፈጸም ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የዲጂታልም ሎተሪም ሊጀመር ነው

             ኢትዮ ቴሌኮም፤ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብር በቴሌብር መክፈል የሚያስችላቸውን አሰራር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ጋር  ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን  የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሆነው፣ የግብር ክፍያቸውን መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።
በዚህ ተግባራዊ በተደረገው የግብር ክፍያ ስርዓት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት ግብራቸውን የሚከፍሉ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች፣ ያለምንም እንግልትና ውጣ ውረድ በወቅቱ ግብራቸውን እንዲከፍሉ፣ ለከፈሉት የአገልግሎት ክፍያ ማስረጃው በቅርብ እንዲኖራቸው፣ ግብር ለመክፈል የግብር መክፈያ ጣቢያ በአካል ሲሄዱ የሚደርሰውን የገንዘብና የጊዜ ብክነት እንዲሁም፣ የትራንስፖርትና ሰነዶችን ኮፒ ለማድረግ የሚያወጡትን ወጪ እንደሚያስቀር ታውቋል፡፡
 “ግብር ከፋዮች በየትኛውም ቦታና ሰዓት በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር *127# በመጠቀም ግብራቸውን በወቅቱ ለመክፈል ያስችላቸዋል” ብሏል- ኢትዮ ቴሌኮም።
በዚህም የግብር ክፍያ ስርዓት ከ300 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የጠቆመው ኩባንያው፤ ግብር ከፋዮች በሞባይል ስልካቸው ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በ7075 በአጭር የጽሁፍ መልእክት የሚደርሳቸውን የክፍያ ማዘዣ ቁጥርን በመጠቀም ክፍያቸውን ሲፈጽሙ፤ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ከ7075 እንዲሁም ከ127 የክፍያ ማረጋገጫ መልዕክት ይደርሳቸዋል ብሏል።
ደንበኞች ለቴሌብር አገልግሎት ያልተመዘገቡ ከሆነ መመዝገብና አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የተጠቆመ ሲሆን በዚህም መሰረት ደንበኞች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከላት እንዲሁም የቴሌብር ህጋዊ ወኪሎች በአካል በመሄድ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ ገንዘብ ተቀማጭ በማድረግ የግብር ክፍያውን በቀላሉ በቴሌብር መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።
በተጨማሪም የባንክ አካውንት ያላቸው ደንበኞች ከቴሌብር ጋር ትስስር ባደረጉ ባንኮች ማለትም አዋሽ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ብርሃን ባንክ፣ ህብረት ባንክ፣ እናት ባንክ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ አባይ ባንክ፣ ዳሽን ባንክ፣ ኦሮሚያ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ እና ንብ ባንክ አማካኝነት ከባንክ አካውንታቸው ወደ ቴሌብር አካውንታቸው ገንዘብ በማስተላለፍ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል- ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው።
የቴሌብር አካውንት ያላቸው ነገር ግን የባንክ አካውንት የሌላቸው ግብር ከፋዮች ደግሞ ምንም አይነት የባንክ አካውንት ሳያስፈልጋቸው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ዳሽን ባንክ፣ እናት ባንክ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ ወጋገን ባንን እና ንብ ባንክ ቅርንጫፎች በአካል በመሄድ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም እና ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የዲጂታል ሎተሪ በቴሌ ብር እና በ60ና አጭር የፅሁፍ መልዕክት ለመጀመር ከትላንት በስቲያ ስምምት ፈፅመዋል፡፡
የብሔረዊ ሎተሪ አስተዳደር የዲጂታል ሎተሪ መጀመሩ ከዚህ በፊት ለህትመትና ሌሎች ተያያዥ ያላቸው ሥራዎች ያወጣው የነበረውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስና ለደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን ያስችለዋል ተብሏል፡፡


Read 11799 times
Administrator

Latest from Administrator