Saturday, 16 July 2022 17:40

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በጦርነቱ2.6 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶብኛል አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት  ሳቢያ 2.6 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት አስታወቀ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጌአለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት  ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከህዝብ ከተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያዎችን በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት፤ ኮርፖሬሽኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል፡፡
“በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ሳቢያ በንብረት ብቻ ወደ 200 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት ወድሞብናል ያሉት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ፤ ጦርነቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመስፋፋቱ  ኮርፖሬሽኑ ለተጨማሪ  ከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል ብለዋል፡፡ እነዚህ ሲደመሩም በጦርነቱ ሳቢያ ኮርፖሬሽኑ የደረሰበትን ኪሳራ ወደ 2.6 ቢሊዮን ብር ከፍ ያደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳዳር በበኩሉ፤ በተለያዩ የአገርቱ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ ከ81 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ከ60 በላይ ፕሮጀክቶች ስራ መቆሙን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ የአስተዳደሩ  ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ተገኝ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንዳመለከቱት፤ የፀጥታ ችግሮቹ ፕሮጀክቶቹን ከማስቆምና በድርጅቱ ላይ ኪሳራ ከማድረስ ባለፈ የአስተዳደሩ ሰራተኞችን ህይወት አጥፍቷል ብለዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ አካባቢ አራት የድርጅቱ ሰራተኞች በሽፍቶች መገደላቸውንም በዚሁ ማብራሪያቸው ላይ ተናግረዋል፡፡ የሰራተኞቹን አስከሬን እንኳን ለማውጣት ከፍተኛ ችግር ገጥሞን ነበር ያሉት  ኃላፊው፤ ሠራተኞቻችን ስራቸውን የሚሰሩት እየሞቱ ነው ሲሉ ለአባላቱ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢዎቹ ያለው የፀጥታ ችግር ስራቸውን ለመስራት  ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን የተቋማቱ ኃላፊዎችን ለምክር ቤቱ ገልፀዋል፡፡

Read 1000 times