Tuesday, 12 July 2022 00:00

በአሜሪካ የስደተኞችን ችግር የሚታደገው ተቋም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 “በዋናነት የአዕምሮ በሽታ ላይ ነው የምንሠራው”

          ሠናይት አድማሱ ትባላለች። ነዋሪነቷ በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ከተማ ነው። ቀድሞ በሞዴሊንግ ሙያ ትሰራ እንደነበር ትናገራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን ሃገር ከሌሎች ጋር የመሠረተችውን የበጎ አድራጎት ድርጅት እየመራች ትገኛለች፡፡ “አፍሪካን ኮሚውኒቲ ፐብሊክ ኸልዝ ኳሊዥን” ይሰኛል ድርጅቱ። የተለያዩ ችግሮች ለሚያጋጥማቸው ስደተኛ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን ድጋፍ እንደሚያደርግ ትገልጻለች፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ወገኖች በአሜሪካ እየገጠሟቸው ስላሉ ችግሮችና ድርጅታቸው ስለሚያደርጋቸው ድጋፎች ኢትዮጵያ በመጣችበት ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-

            በአሜሪካን ሃገር የምታስተዳድሪውን ድርጅት በተመለከተ በቅድሚያ ብታስተዋውቂን?
ድርጅቱ “አፍሪካን ኮሚውኒቲ ፐብሊክ ኸልዝ ኳሊዥን” ይባላል። የአፍሪካ ማህበረሰቦች ጤና ጥምረት እንደማለት ነው። ከተቋሙ መስራቾች አንዷ ነኝ። በድርጅታችን በኩል የምናደርገው በዋናነት ሰዎችን የመደገፍና የማነጽ ተግባር ነው።  በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አፍሪካውያንን በማህበራዊ ጉዳዮች መደገፍ (መርዳት) ነው፤ ዋና ተግባራችን። በዋናነት ደግሞ የአዕምሮ በሽታ ላይ ነው የምንሠራው። እንደሚታወቀው የአዕምሮ በሽታ በማህበረሰባችን ዝቅ ተደርጎ የሚታይ ግን አደገኛ በሽታ ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች በዚህ በሽታ ሲያዙ ከእምነትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በማያያዝ፣ ወደ ህክምና ተቋማት የመሄዱ ጉዳይ ደካማ ነው። በአሜሪካም ያሉ ወገኖቻችን  በተመሳሳይ መልኩ ነው የአዕምሮ ጤና ላይ ያላቸው ግንዛቤ፡፡ በዋናነት ድርጅታችን ይህን የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍና በዚህ ህመም የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አፍሪካውያንን ለመርዳት የተቋቋመ ነው።
መቼ ነው የተቋቋመው?
እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው። አሁን 11 ዓመት ሆኖታል። በእነዚህ 11 ዓመታት ውስጥ በዋናነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በተለያዩ መንገዶች ስንሰራ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከበርካታ የአፍሪካ ሃገራት ወደ አሜሪካ የመጡ አፍሪካውያንን በየባህላቸውና በየቋንቋቸው ስናስተምር ቆይተናል። በተጨማሪም ለአእምሮ ህመም ለተዳረጉ ወገኖቻችን የስነ-ልቦና ህክምና እንዲሁም መድሃኒቶችንም ስንሰጥ ቆይተናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከኢምግሬሽን ጋር ተያይዞ ሰዎችን ችግር ሲገጥማቸው እናማክራቸዋለን፤ መፍትሄ እንዲያገኙም እናደርጋለን። ብዙ ሰው ደግሞ ከዚህ አገልግሎት ማጣት ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ጭንቀቶች የተነሳ ለአእምሮ ህመም የመጋለጥ ሁኔታ አለ። ይህን ችግር ለመፍታት ከፌደራል መንግስቱ ፈቃድ አግኝተን የኢምግሬሽን አገልግሎት በቋንቋቸው እንሰጣቸዋለን። የመኖሪያ ፈቃድ፣ የስራ ፈቃድ ማግኘት የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ እናግዛቸዋለን። የቤት ችግር፣ የህክምና ችግር ሲያጋጥማቸውም፣ በአብዛኛው የሃገሩን ቋንቋና ባህል እንዲሁም መብታቸውን ካለማወቅ ችግሩ ስለሚፈጠር ቀርበን ድጋፍ እናደርግላቸዋለን። በአጠቃላይ በአሜሪካን ሃገር ኢትዮጵያውያንን  ጨምሮ ለአፍሪካውያን ወገኖቻችን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እናማክራለን፤ ድጋፍ እናደርጋለን፤ ጉዳያቸውንም በበጎ ፈቃድ እናስፈጽማለን።
እንዲህ አይነት ተግባር የሚያከናውነው የእናንተ ድርጅት ብቻ ነው?
ሌሎችም አሉ። የጥቁር መብት ተከራካሪ ድርጅቶች አለ። እኛ ግን በዋናነት እርዳታና ድጋፍ ላይ እናተኩራለን።
 በአብዛኛው በአሜሪካን አገር በስደት የሚኖሩ አፍሪካውያን የአዕምሮ ችግር የሚገጥማቸው ከምን የተነሳ ነው?
ሳይንሳዊ ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ በአሜሪካን ሃገር ከ5 ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ህመም ይኖረዋል። ያ ማለት እንግዲህ መጠነ ሰፊ የሆነ የአዕምሮ ታማሚ በየደረጃው አለ ማለት ነው። የአዕምሮ ህመም የሚጀምረው ምናልባትም ከትንሽ ጭንቀት ሊሆን ይችላል። ደረጃውና መጠኑ ወይም የጊዜው መርዘም እንደየሰው ይለያያል።
በተለይ አሜሪካ  ያሉ ኢትዮጵያውያን በምን ምክንያት ነው የአዕምሮ ህመም ተጠቂ የሚሆኑት?
በአብዛኛው ምክንያቶቹ ማህበራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ኑሮ በአሜሪካ ሃገር ቤት ካለው አንጻር ትንሽ ከበድ ይላል።  የመስራት አጋጣሚው ሰፊ ቢሆንም፣ በውስጡ ሲታለፍ ግን ትንሽ ይከብዳል፡፡ በሌላ በኩል፤ ብቸኝነት ከቤተሰብ መራቅ እንዲሁም ከቤተሰብ የሚጠበቅብንን ጉዳይ ማሰላሰል ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ ቤተሰብ የሚጠብቅብንን ጉዳይ ከማሟላት ጋር በተያያዘ የኛ ማህበረሰብ ሁኔታ ከሌላው በጣም ይለያል። በጣም የሚያስጨንቅ ጉዳይ ነው። በአንጻሩ ለሌሎች የቤተሰብ ጉዳይ ከራስ ፍላጎት መሟላት ቀጥሎ የሚመጣ ነው የሚሆነው። በኛ ማህረሰብ ግን ከራስ በፊት  የቤተሰብ ጉዳይ ነው የሚቀድመው። ይህ እንግዲህ ከአስተዳደጋችን የመጣ ነው ማለት ይቻላል። ለቤተሰባችን ማድረግ ያለብንን ሳናደርግ ስንቀር ጭንቀቱ ይጀምራል፤ ራስን መውቀስ፣ የበታችነት ስሜት መፈጠር፣ በዚያ ላይ የኑሮ ጫናው ተጨማምረው ዋነኛው የአዕምሮ ህመም ምክንያት ሆነው ይታያሉ።
ሌላው ከጋብቻ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ችግሮች አሉ። በአሜሪካ በአብዛኛው ባለትዳሮች መሃል በገቢ ሁኔታ ጭቅጭቆች ይኖራሉ። የፋይናንስ ችግር ሌላው የጭንቀት መንስኤ ሲሆን በዚህ ምክንያት የትዳር መፍረስ ሁኔታም የአዕምሮ ህመም መንስኤ ሲሆን እንመለከታለን። በሌላ በኩል፤ ከኢምግሬሽን አንጻር የመኖሪያ ፈቃድ ካለመመቻቸት ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ጭንቀት ይኖራል። የእፅ ተጠቃሚነት፣ ህጋዊ ያልሆኑ ሥራዎች ላይ መሰማራት፤ ከማይታወቁ  ሰዎች ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት ጋብቻ መፈጸምና ኋላ የሚደርስባቸውን ችግር ያለመቋቋም ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። በተለይ ለሴቶች ማሳሰብ የምፈልገው፤ በኢንተርኔት ጋብቻ መፈጸሙ ምናልባት፣ አጋጣሚው ጥሩ ሊሆን ይችል ይሆናል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ  ሽወዳዎች ስላሉት፣ አለመተዋወቁ ሰፊ  ስለሆነ አብዛኞቹ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ሲጋለጡ አይተናል። ሴቶቹን ከዚህ ከወሰዷቸው በኋላ ድንገት ጥለዋቸው የመጥፋት፣ ልጅ ከወለዱ በኋላ ትተዋቸው የመሄድ፣ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳያገኙ በማድረግ የማንገላታት ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። እውነት ለመናገር በዚህ ሁኔታ ከእነ ልጆቻቸው መንገድ ላይ ተጥለው ያሉ በርካቶች ያጋጥሙናል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እኛም አግኝተን የምንረዳቸው።
እንዲህ ያሉትን ወገኖች ምንድን ነው የምትረዷቸው?
ከጎዳና አንስተን ወደ መጠለያ ገብተው እንዲረዱ እናደርጋለን፤ ጠበቃ ፈልገን መብታቸው በህግ  እንዲከበር እንጥራለን፤  ከገቡበት ችግር እንዲወጡ  ድጋፍ እናደርጋለን።
በጉዲፈቻ የተወሰዱ ልጆችስ ችግር ሲገጥማቸው እርዳታችሁን ያገኛሉ?
የብዙዎቹ የጉዲፈቻ ልጆች ችግር የሚጀምረው እዚህ ሃገር ቤት እያሉ ነው። በተለይ ጾታዊ ጥቃቶች የሚጀምሩት እዚሁ ማቆያ ውስጥ  እያሉ ነው የሚሆነው።  ብዙዎቹ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የተለያዩ ጥቃቶች ይፈጸምባቸው የነበረው ከእዚሁ ጀምሮ በመሆኑ የአዕምሮ ችግራቸው በጣም ስር የሰደደ ነው የሚሆነው። ብዙዎቹ ታዳጊዎች በገንዘብ እንደተሸጡ ይሰማቸዋል። ወደ አሜሪካ በማደጎ የሚያመጧቸው ቤተሰቦች ሁኔታም ለልጆቹ ቀጣይ ህይወት ወሳኝነት አለው። ጤናማ ቤተሰብ ያላጋጠማቸው ከጾታዊ ጥቃት ጀምሮ ለተለያዩ የስነ-ልቦና ችግሮች የሚዳርጉ ጥቃቶች ይፈጸምባቸዋል። ጥቂት የማይባሉት የብቸኝነት ስሜት፣ የማንነት ቀውስ፣ እንዲሁም ከባህልና ከሃገር ውጭ የመኖር ሁኔታው ጭንቀት ፈጥሮባቸው ለከፋ ችግር የሚጋለጡ አሉ። በእነዚህ ተደራራቢ ጭንቀቶች የተነሳ ራሳቸውን ያጠፉ ልጆችም እናውቃለን። በሌላ በኩል ደግሞ አሳዳጊዎቻቸውን ጥለው ጠፍተው የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ልጆች አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ጠንካራ ሆነው ሁሉንም ችግር ተቋቁመው፣ ራሳቸውን አሸንፈው ሲኖሩም እንመለከታለን። አንዳንድ አሳዳጊዎች ደግሞ ከኛ ጋር እንዲገናኙ፣ የሃገራቸውን ባህልና ለዛ እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ነገር ግን ያን ያህል ውጤታማ አይደለም። ብዙዎች ግን ህይወታቸው የተበላሸ ነው። ሱሰኝነት፣ መጠጥ፣ የጎዳና ተዳዳሪነት ሁኔታዎች በእነዚህ ልጆች ላይ ይስተዋላል። የሚገርመው ግን ከእነዚህ ልጆች አብዛኞቹ ለአዕምሮ መረበሽ የሚዳርጓቸው ወይም የዳረጓቸው ጥቃቶች የጀመሩት እዚሁ ሃገር ቤት ሆኖ ነው የሚገኘው።
ለችግር የተዳረጉ ሰዎችን እንዴት ነው የምታገኟቸው?
የእኛ ተቋም በደንብ የሚታወቅና በመንግስት የሚደገፍ ነው።  በየመረጃ ቋቶች ስማችን አድራሻችን አለ።  ይደወልልናል፣ በቤተ ክርስቲያናት፣ በሙስሊም ቤተ እምነቶች በኩልም እናገኛቸዋለን።
እርዳታ ካደረጋችሁላቸው በኋላስ በምን መልኩ ነው ህይወታቸውን የሚቀጥሉት?
በአብዛኛው ወደ መደበኛ ኑሮ እንዲመለሱ እናግዛቸዋለን። ከስነልቦና ድጋፍ ጀምሮ የሥራ እድሎችን ማፈላለግ የመሳሰሉ ድጋፎች እናደርጋለን። በዋናነት ግን ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራዎችን እንሰራለን፡፡ በዚያ ሃገር ሲኖሩ የሚገባቸው ህጋዊ መብቶች በሙሉ እንዲከበሩላቸው ጥረት እናደርጋለን።


Read 8615 times