Sunday, 10 July 2022 19:22

“ዘውድ የጫነ ጭንቅላት አበሳው ብዙ ነው!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   “ወርቅ የተጫነች አህያ ስትገባበት የማይፈርስ ግንብ የለም” ሼክስፔር

             “ወርቅ የተጫነች አህያ ስትገባበት የማይፈርስ ግንብ የለም” የሚሉት እንግሊዞች ናቸው። ሀብታሙን፣ መናጢ ደሃውንና ቤሳ ቤስቲን የሌለውን ነጭ ደሀም አንቱ የተባለ ባለፀጋ የሚያደርገው፣ ሀብት ነው፡፡ ብር ነው፡፡ ወርቅ ነው!
አዳም ስሚዝ የተባለው ስኮትላንዳዊ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ፤ የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን የለውም (Human wants are unlimited) ይላል፡፡ እንግሊዛዊው የኢኮኖሚክስ ሊቅ ዴቪድ ሪካርዶም (1772-1823) ከአዳም ስሚዝ ጋር በመሆን ያንኑ ንድፈ ሀሳብ ሲያቀነቅን ነበር፡፡
በታሪክ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ (ጀምሮ) አገርና አገር አህጉርና አህጉር፣ክፍለ ዓለምና ነፍሰ-ዓለም  ጦርነት ሲያነሳ፣ሲፋጭና ሲጋጭ የኖረውና እሚኖረው በዚሁ በሀብት ክፍፍል ምክንያት ነው፡፡ በዚሁ ሳቢያም ህይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረት ወድሟል፡፡ ሥልጣኔ እንዳልነበር ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ አገራችንም የዚህ ዕውነታ አካል  ተጋሪ ናት፡፡ በተደጋጋሚ ጎረቤቶቿ ከቅርብ፣ ኃያላን ነገስታት ከሩቁ ወረዋታል፡፡ ወግተዋታል፡፡ እሷም ከመመከት አልቦዘነችም፡፡ አንዳንዶቹንም ምሳቸውን ሰጥታ፣ ውርደት አከናንባ መሸኘቷ ታሪክ የዘገበውና ዘመን የከተበው ሐቅ ነው፡፡
“ጠላት ከኛ ነጥቆ፣ትርፍ አገኛለሁ ሲል
እኛስ ከራሳችን፣ እንደምን እናጉድል!”
--እያለ ዳር ድንበሩን አላስነካም! ነፃነቱን አላስደፈረም፡፡
የገዢና ተገዢ ሥርዓት ሁሌም ያለ፣ የነበረና የሚኖር ነው፡፡ በመንግስታት ደረጃ በፓርቲዎች ውስጥ፣ በድርጅቶች ውስጥ፣ በቡድኖች ውስጥ ይከሰታል፡፡ ሁሉም ዘንድ አለቃና ምንዝር አለ፡፡ ሁሉም ዘንድ ውሎ አድሮ በአቋም ልዩነት ምክንያት መለያየት፣ አንጃ መፈጠሩ፣ ነገር ሲከርርም ጦር መማዘዙና መጋደሉ፤ የታየ  የተመሰከረ  ታሪክ ነው፡፡
በኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) “ክሊክ” እና “አንጃ” ተባብሎ ተከፋፍሏል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ  ሶሻሊስት ንቅናቄ “ሀቀኞች”  እና “ቀኝ መንገደኞች”  በሚል ወገን ለይቶ ተፋልሟል፡፡ ይሔው የሁለቱ አንጋፋ ድርጅቶች ፍልሚያ በባህር ማዶም “ኢዙና” እና “ኢዙዌ” በመሰኘት አይታረቄ ቅራኔ ውስጥ ተዘፍቆ ነበር፡፡ የ”ኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት” (ኢማሌድኃ) የተባለውም የአምስት ድርጅቶች ኃብረት ከፍተኛ ሽኩቻዎችን አስተናግዷል፡፡ ተስፈንጣሪ ቡድኖችን ፈጥሯል፡፡ በትግራይ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ከወያኔና ከዚያ ውጪ ተመሥርተዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ድርጅትና የኦሮሞ አንድነት ድርጅት እላይ የጠቀስነው  ታሪካዊ    ሂደት ውስጥ ያለ ነው፡፡
የፈረንሳይ አብዮት ተልዕኮዎች “እኩልነት ወንድማማችነትና  ነፃነት” የሚሉ ነበሩ። “የሽብርና የደም መፋሰስ” (reign of terror) በሚል አከተመ፡፡ እንደ ሀገራችን “ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር፣ ነፃ እርምጃ” የመሰለ አሰቃቂ ውጣ ውረድ እዛም ታልፏል፡፡ በሩሲያ “ቮልሼቪክ” እና “ሜንሼቪክ”፤ ተባልተዋል፡፡ ቻይናም የቻይናን ኮሙኒስት ፓርቲ እና የ”ጋንግ ኦፍ ፎርን” ፍጭትና አባዜ ተቀብላለች፡፡ ምኑ ቅጡ፡፡ “የእስከዛሬው የህብረተሰብ ታሪክ የመደብ ትግል ታሪክ ነው” አለ ማርክስ፡፡ የዛሬውም ታሪክ  ያው ነው፡፡ የእኛም ታሪክ ይኼው ነው!
በዚህኛው ዘመንም በኢትዮጵያ ለወሬ ነጋሪ ሳናስቀር አጥፍተናቸዋል የተባሉ ተቃዋሚዎች  የፈሉበት፣ አፈር ልሰው፣ ትብያ ምሰው፤ የተነሱ/ ድርጅቶች የማያባራውን ጦርነት በር እንዳዲስ የሚያንኳኩበት፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው “ሞት  ሳይሞቱት ነው የሚለመድ” ማለት እጅግ የተለመደበት፤ ስደትና መፈናቀል፣ ረሃብና ድርቅ የዕለት-ሠርክ ቋንቋ የሆነበት፣ “የሸንቁጤ ጊዜን” እንድንጠቅስ የተገደድንበት ጊዜ ነው፡፡ መንግስት ደግሞ “ጠላትን ድባቅ መትተናል”፣ “ወረራን መክተናል“፣ “የውስጥ ቦርቧሪዎችን መንጥረናል“፣ “የኮንትሮባንድ መሳሪያ ይዘናል”፣ “ኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ዓይነተኛ እርምጃ ወስደናል”፣ “ገበያውን ለማረጋጋት ማሻሻያ እያደረግን ነው”፣ “ጥናት እየተካሄደ ነው፣ ሌላም አጥኚ ቡድን ይቋቋማል” ማለቱን ቲቪና ሬዲዮው እየነገረን ነው፡፡ ለእኛ አብዛኛው ሁኔታ አስጊ ነው፡፡ ካርታ የሚጫወቱ ሰዎች “ዲካርቴ ገብቻለሁ” የሚሉትን ይመስላል፡፡ ከዚህ ይሰውረን፡፡ አለበለዚያ “ዘውድ የጫነ ጭንቅላት አበሳው ብዙ ነው!” (Uneasy lies the head that wears the crown-- እንዲል ሼክስፔር፡፡)

Read 10711 times