Friday, 08 July 2022 00:00

የወለጋውን ጭፍጨፋ የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ ህይወት ቀጠፈ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በሸዋ ሮቢት ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች አደባባይ የወጡት በወለጋ ከ300 በላይ የአማራ ተወላጆች በጅምላ መገደላቸውን ለማውገዝና የወረዳውን የአብን ፓርቲ ቅርንጫፍ ሃላፊን  እስር በመቃወም ነበር። በወቅቱ የፀጥታ ሃይሎች የተቃውሞ ሰልፉን ለመበተን ሞክረው ነበር፤ አንዳንድ ሰልፍ ተሳታፊዎችንም በቁጥጥር ስር አውለዋል።
በነጋታው አርብ የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞ ሰልፉን አደራጅተዋል ብለው የጠረጠሯቸውን የወረዳውን አብን ፓርቲ ቅርንጫፍ ሃላፊን ጨምሮ ተማሪዎችንና ግለሰቦችን በየቤቱ  እየዞሩ ለቅመው ማሰራቸውን የዓይን እማኞች ለአማርኛው ዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።
እስሩን ተከትሎ ታዲያ የዚያኑ ዕለት ተማሪዎችና ከተማዋ ነዋሪዎች  ወደ ፖሊስ ጣቢያው ያመራሉ። በሥፍራው ከደረሱ በኋላም በጸጥታ ሃይሎችና ነዋሪዎቹ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት  ወደ ግጭት ተለወጠ። በወቅቱ በተከፈተው ተኩስ ቁጥራቸው ያልታወቀ ዜጎች ህይወት መጥፋቱን፣ በርካቶችም ለጉዳት መዳረጋቸውን የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል። “ቁጥሩን በትክክል ባላውቀውም ዜጎች ሞተዋል፤ ጉዳት ደርሷል፤ ሰዎች ታስረዋል” ብለዋል አንድ የከተማዋ ነዋሪ።
“በቀጣዮቹ 3 ቀናት የሸዋሮቢት ከተማ ባልተለመደ ጸጥታ ተውጣ ቆይታለች፣ የንግድ ቤቶች ዝግ ነበሩ፤ አብዛኞቹ ነዋሪዎች በፍራቻ ከቤታቸው አልወጡም” ሲል አክሏል-ነዋሪው።
ዶቸ ቬሌ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በጸጥታ ሃይሎችና የእስረኞችን መለቀቅ ጠየቁ። በነዋሪዎች መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት እስከ 12 የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል።
አሳዛኙን ክስተት ተከትሎ የከተማዋ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፤ በተፈጠረው ግጭት በጠፋው የሰው ህይወትና በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልፆ፤ ከተማዋን ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ከወረዳና የፀጥታ ሃይሎች እንዲሁም ከሽማግሌዎች ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። በከተማዋ የታወጀው ኮማንድ ፖስትም ላልተወሰነ ጊዜ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ በመግለጫው ተመልክቷል።
በተመሳሳይ በዚያው ሳምንት ጎንደር ዩኒቨርስቲ አደባባይ ወጥተው የወለጋውን የአማራ ተወላጆች ጅምላ ግድያ ያወገዙ ሲሆን በአንጻሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ሰልፍ  በጸጥታ ሃይሎች ተበትኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ በፓርላማ ተገኝተው በወለጋው አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋና በበጀት ዙሪያ ከም/ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያም ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር።
“እንኳንስ ንፁሃን ዜጎች በግፍ ተጨፍጭፈው ለሌላም ጉዳይ ሰልፍ ይወጣል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ግድያው ስሜታዊ የሚያደርግ ቢሆንም ሰላማዊ ሰልፉ ሰላማዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ያለጥበቃ የሚደረግ ሰላማዊ ሰልፍ ህይወት ሊጠፋበት ይችላል” ብለዋል- ጠ/ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ።

Read 9982 times