Saturday, 02 July 2022 18:17

“የራበው ዜጋ ጎረቤቱን ይበላል” ሙሴ ሸሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ


            እየተባባሰ በመጣው የዋጋ ንረት፣ የገንዘብ መግዛት አቅም መዳከምና የአቅርቦት እጥረት ምክንያት የከተሞች ውስጥ ረሐብ ሊከሰት እንደሚችል እየተተነበየ ነው። ከመንግስት የምንጠብቀው መፍትሔ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከእኛስ ምን ይጠበቃል? በሚለው ዙርያ ሐሳብ ማንሸራሸር አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ?! የጋለው ኢኮኖሚያችን እስኪረጋጋ፣ የቁሳቁስ፣ የምግብ ነክና የአላቂ ቁሳቁስ አጠቃቀም ስርዓትና ባሕላችን ሊፈተሽና ሊታደስ አይገባውም ትላላችሁ?! ጥያቄ አለኝ?! የታሸገ ውኃ ቅንጦት ቢመስልም፣ እንደ ቀላል አስረጅ ምሳሌ ላንሳውና፣ ወደ መሰረታዊ ጥያቄዬ ልገባ?!
ዛሬ ላይ 17 ብር በሚያወጣ የላስቲክ ኮዳ፣ 1ብር የማያወጣ ውኃ ገዝተን ውኃውን ጠጥተን፣ አስራ ሰባት ብር የሚያወጣ የወኃ ማሸጊያ፣ ያውም በዶላር የተገዛ በየመንገዱ ላይ የምንጥልበት ሃገር፣ ከኢትዮጵያ ውጭ የት ይገኛል ትላላችሁ?! ነዳጅ ተወዶ እያለ ቀኑን ሙሉ መንገድ በዚህ ደረጃ የሚጨናነቅበት መንስኤስ?! የመብራትና የወኃ አጠቃቀማችንስ ምን ይመስላል?! ከወቅታዊ ፍላጎታችን በላይ በመሸመት ስለምንፈጥረው እጥረትና የዋጋ ንረትን አስበን እናውቃለን?!  የምንጠቀማቸውን አላቂ እቃዎች፣ ምግብና ምግብ ነክ ነገሮችስ ከብክነት የጸዱ ናቸው?!  ወዘተ ....
ማንም ሰው በገንዘቡ የማዘዝ ሙሉ ስልጣን አለው። ነገር ግን ገንዘብ ስላለው ብቻ የሌሎችን ጥቅም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሚጎዳ ተግባር ላይ መሰማራት ከ”ሞራልም” ሆነ ከኢኮኖሚያዊ ምክንያታዊነት ጋራ እጅግ የተራራቀ ተግባር ነው።  ገንዘቡ የሚወጣው ከግለሰቦች ኪስ ቢሆንም ሁሉም ዓይነት ሀብት የሌላውን ዜጋ ሕይወት ለመለወጥ ጠቃሚ ተግባር ላይ መዋል የሚችል ኦፖርቹኒቲ ኮስት ያለው መሆኑ ስንቶቻችን ላይ ያቃጭልብናል?!
ተወደደም ተጠላ በሰው አዕምሮ ውስጥ ካለው እውቀት፣ ክህሎትና ጉልበት ውጭ ሁሉም ተፈጥሯዊ ሐብትና ሐብት መፍጠርያ ቁሶች፣ የውጭ ምንዛሪን ጨምሮ የቀሪውን ማህበረሰብ ሕይወት ለማሻሻል የሚያስፈልጉ የጋራ ሐብት መሆናቸው ተሰምቶን ያውቃል ወይ? ግብርና ቫት በመሰወር፣ አቅርቦት ደብቆ ዋጋ በማናርና በወገን ደምና አጥንት ያልተገባ ሐብት በማፍራት እስከ መቼ መዝለቅ የሚቻል ይመስለናል?!
ተገልጋዮችስ አቅም ስላለን ብቻ በዘፈቀደ ከኢኮኖሚያዊ ምክንያታዊ ተጠቃሚነት (Rational Consumer) ውጭ የምናባክነውና የምናድፋፋው ሐብት ወደ ማያባራ የዋጋ ንረትና አዙሪት በመውሰድ፣ በሂደት ሁላችንንም  ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ሊዘፍቀን እንደሚችል ምን ያህሎቻችን እንረዳለን?! የራበው ዜጋ መሪውን ይበላል የሚለው ብሒል፤ የራበው ዜጋ ጎረቤቱን ይበላል በሚለው ሊተካ እንደሚችልስ ምን ያህል አስበንበት እናውቃለን?!
እንደ አንድ ምክንያታዊ ኢኮኖሚያዊ ፍጡር (Rational Consumer) እንደዚህ ባሉ የቸልተኝነት ተግባሮች በቀጠልን ቁጥር በተለይ ደግሞ አስጨናቂ እጥረት (Chronic Shortage) የዋጋ ንረት በሚያባብስበት ሁኔታ ላይ እያለን ግሽበቱ እንዳይባባስ፣ ኢኮኖሚያችን ከመስመር እንዳይወጣና መኖር ወገናችን ላይ ፈተና ሆኖ እንዳይቀጥል ወጭን በመቆጠብ፣ ብክነትን በመከላከል ትርፍን ምክንያታዊ በማድረግና ምርታማነትን በማሳደግ እየደገፍነው ነው ወይስ በዘፈቀደ እየኖርን፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሩን እያባባስንና የሀገሪቱንና የወገናችንን የመግዛት አቅም እያዳከምነው ነው? ጥያቄ አለኝ፡፡  
ጤናማ የግብይት ስርዓት ከመፍጠር አኳያስ እለት በእለት እየናረ ለሚሄደው የዋጋ  ንረት እየዳረገን ካለው ስሜታዊ ግምታዊነት  (Speculation) እየታቀብን ከመጠን በላይ የጋለው ኢኮኖሚያችን እንዲበርድ፣ የግላችንን ኃላፊነት በምን ያህል ደረጃ እየተወጣን ነው?!  ገንዘብ ስላለን ብቻ ለአበደ ግብይትና ለጦዘ ገበያ  የተጠየቅነው ብር በመክፈል ተባባሪ መሆናችን በኢኮኖሚው ላይ ምን ያህል ውጥረት እየፈጠረ እንደሆነ እንረዳለን?!  
ጥያቄ አለኝ?! አዎ መንግስት ኢኮኖሚውን እየመራ ባለበት መንገድ ላይ መሰረታዊ ጥያቄ አለን፡፡ መንግስት ላይ የምንደረድረው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኛስ ለችግሩ መባባስ ምን ያህል እያዋጠን እንደሆነ እራሳችንን እንጠይቃለን?!



Read 2337 times