Saturday, 02 July 2022 17:42

የዓለም ቱጃር ደራሲያንና ጸሐፍት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከጥንት አንስቶ እስከዛሬ የፕላኔታችን ደራሲያንና ጸሐፍት ስማቸው በአብዛኛው የሚነሳውና የሚወሳው ከድህነትና ከጉስቁልና  ጋር ተያይዞ ነው። የህይወት ታሪካቸው እንደሚጠቁመው፤ አብዛኞቹ የሥነጽሁፍ ሰዎች ይህችን ምድር የተሰናበቱት በችግር ተቆራምደውና መከራቸውን በልተው ነው፡፡
ከድርሰት ሥራቸው ገንዘብ አግኝተው እንኳንስ ጥሪት ሊቋጥሩ ቀርቶ ረሃባቸውንም ያስታገሱ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ “ደራሲያን ባለጸጋ ከሚሆኑ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል” የተባለ እስኪመስል ድረስ ከሃብት ጋር በእጅጉ የተራራቁ ነበሩ - ለረዥም ዘመናት፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ በሰለጠኑትና በበለጸጉት አገራት የደራሲያንና ጸሐፍት ታሪክ እየተለወጠ መጥቷል። ዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቱጃር ደራሲያንን እያፈራች ነው - ያውም ከ1ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ያላቸው!  ከዚህ በታች ጥቂት የዓለማችንን እጅግ ባለጸጋ ደራሲያንና ጸሐፍትን እናስተዋውቃችኋለን - እግረመንገድ መጪው ዘመን ለታዳጊ አገራት ደራሲያንም በብሩህ ተስፋ የታጀበ  መሆኑንም ለማንጸባረቅ ጭምር! ለዚህ ታዲያ የንባብ ባህልና የህትመት ኢንዱስትሪው ላይ ተግቶ መሥራትን ይፈልጋል፡፡
***
 ጄፍሬይ አርቸር
እንግሊዛዊ ደራሲና የቀድሞ ፖለቲከኛ ነው። አርቸር  ወደ ደራሲነት ሙያው ከመግባቱ በፊት የፓርላማ  አባል ነበር። ሃብቱን ያካበተው በድርሰት ሥራው ነው። መጻሕፍቱ በመላው ዓለም 330 ሚሊዮን ገደማ ቅጂዎች ተሸጠውለታል። የጄፍሬይ አርቸር የተጣራ ሃብት ከጁን 2022 ዓ.ም ጀምሮ 195 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ  ይገመታል፡፡
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-  
Only Time will Tell
The Sins of the Father

ጆን ግሪሻም
በዓለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅናን የተቀዳጀ አሜሪካዊ ደራሲ ነው። ግሪሻም የህግ ባለሙያ ሳለ በሚሲሲፒ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገልግሏል። ከጁን 2022 ዓ.ም ጀምሮ የጆን ግሪሻም የተጣራ ሃብት 220 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ ይገመታል፡፡
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-
 A Time to Kill
Sparring Partners

ባርባራ ቴይለር ብራድፎርድ
መጻሕፍቷን በሚሊዮኖች ቅጂዎች በመቸብቸብ የምትታወቅ እንግሊዛዊት ደራሲ ናት - ባርባራ ቴይለር ብራድፎርድ። የብራድፎርድ መጻሕፍቶች በ90 አገራት ከ80  ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች ተሸጠዋል። ከጁን 2022 ዓ.ም ወዲህ የባርባራ ቴይለር ብራድፎርድ የተጣራ ሃብት 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ  ይገመታል።
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-  
Emma’s Secret
A Woman of Substance
ዳኒኤላ ስቲል
ዳኒኤላ ስቲል በህይወት ያለች ምርጥ- ተሸያጭ አሜሪካዊት ደራሲ ስትሆን ከ800 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ መጻህፍቶቿ ተሸጠውላታል። የዳንኤላ ስቲል የተጣራ ሃብት 310 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው ተብሎ ይገመታል።
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-
Invisible
Beautiful

ኖራ ሮበርትስ
አሜሪካዊቷ ደራሲ ኖራ ሮበርትስ ከ200 በላይ የፍቅር ልብወለዶችን ያሳተመች ሲሆን ከፍተኛ የመጻህፍት ሽያጭ አስመዝግባለች። ሮበርት  የስነ-ጽሁፍ ሥዋን የጀመረችው በ70ዎቹ መጨረሻ ሲሆን  በ1985 እ.ኤ.አ ካሳተመችው “Playing the odds” ከተሰኘው መጽሐፍዋ አንስቶ ከፍተኛ ሽያጭ ማስመዝገቧን ገፍታበታለች። የኖራ ሮበርትስ የተጣራ ሃብት 390 ሚሊዮን ዶላር ነው ተብሎ ይገመታል።
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-
Legacy
Nightwork

ስቲፈን ኪንግ
ስቲፈን ኪንግ አድናቆት የተቸረው ዘመነኛ የአጓጊ፣ አስተኔ፣ አስፈሪና ሳይንስ ልብወለድ ሥራዎች ደራሲ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የባችለር ድግሪ ያለው ሲሆን በዓለም ላይ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ ደራሲያን አንዱ ነው። ብዙዎቹ መጻህፍቱ በቴሌቪዥን ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ “IT” እና “The Shining” ይጠቀሳሉ፡፡ የስቲፈን ኪንግ የተጣራ ሃብት 400 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-
The Shining
The Stand

ጄምስ ፓተርሰን
ልብ አንጠልጣይና በስሜት የሚያጥለቀልቁ ረዥም ልብወለዶችን የሚጽፍ አሜሪካዊ ደራሲ ነው፡፡ ፓተርሰን በፍጥነት የሚቸበቸቡ መጻህፍትን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የጄምስ ፓተርሰን የተጣራ ሃብት 560 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-
22 Seconds
Along came a Spider

ጄ.ኬ. ሮውሊንግ
እንግሊዛዊቷ ደራሲ ጄ.ኬ ሮውሊንግ የዓለማችን ሁለተኛዋ ቱጃር ደራሲ ናት፡፡ በገቢ ረገድ ከፍተኛ ስኬት በተቀዳጀው በሃሪ ፖተር ፈጣሪነቷ የበለጠ ትታወቃለች፡፡ ሃሪ ፖተር ከፍተኛ ገቢ ያስመዘገበ የምንጊዜም ተከታታይ ፊልም ነው፡፡ የጄ.ኬ. ሮውሊንግ የተጣራ ሃብት 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-
Harry Potter and the Philosopher’s Stone
The Ickabog

ኤሊዛቤት ባዲንተር
ፈረንሳዊት ፈላስፋ፣ ደራሲና የታሪክ ምሁር ናት። ባዲንተር በፌሚኒዝምና ሴቶች  በህብረተሰብ ውስጥ ያላቸውን ሚና በተመለከተ በከተበቻቸው ፍልስፍናዊ ጽሁፎች የበለጠ ትታወቃለች። ማርያና የተሰኘ መጽሄት እ.ኤ.አ በ2010 “የፈረንሳይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሁር” በሚል መርጧታል።
የኤሊዛቤት ባዲንተር የተጣራ ሃብት 1.3 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሎ የሚገመት ሲሆን ይህም የዓለማችን የምንጊዜም ቢሊዬነር  ደራሲ ያደርጋታል።
ተጠቃሽ ሥራዎች፡-  
Mother Love: Myth and Reality

ሌሎች ቱጃር ደራሲያን
ሱዛን ኮሊንስ (አሜሪካዊት ደራሲ) - 80 ሚ.ዶላር
ጃኔት ኢቫኖቪች (አሜሪካዊት ደራሲ)- 80 ሚ. ዶላር
ዲፓክ ቾፕራ (ህንዳዊ-አሜሪካዊ ደራሲ) - 80 ሚ. ዶላር
ጃክ ሂጊንስ (የሰሜን አየርላንድ ደራሲ) - 86 ሚ. ዶላር
ክሪስቶፈር ሊትል (መቀመጫውን ለንደን ያደረገ የሥነጽሁፍ ኤጀንት) - 86 ሚ. ዶላር
ፓውል ማክኬና  (እንግሊዛዊ ፀሃፊ)- 100 ሚ. ዶላር
ስቴፌኒ ሜዬር (አሜሪካዊት ደራሲ)- 125 ሚ.ዶላር
ዲን ኩንትዝ (አሜሪካዊ ደራሲ)- 145 ሚ.ዶላር
ዴቪድ ኦዬዴፖ (ናይጄሪያዊ ሰባኪ፤ የክርስትያን ደራሲ)- 150 ሚ.ዶላር
ዳን ብራውን (አሜሪካዊ ደራሲ) -178 ሚ. ዶላር

Read 2507 times