Saturday, 18 June 2022 20:44

አታንጋጥ ሩጥ! ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ››ን እንዳነበብኩት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 "--በእግዚአብሄር፣ በእምነት፣ በረሃብ፣ በስንፍና፣ በስደት፣ በሥራ፣ በባህል፣በመስዋዕትነት እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ››፤ ከዚህ መውጣት የምንችለው ሁለንተናችንን ለስራ ስናስገዛ፤ ስራን ስናከብር፤ ስንፍናችንን ወዲያ አሽቀንጥረን ስንጥል፤ ወደ ጥንቱ ማንነታችን ስንመለስ፤ (የትኛው ጥንት እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም)፣ ከውጪ የተጫነብንን ሸክም ስናራግፍ ነው ይለናል፡፡ --"
                  በዮናስ ታረቀኝ


            መነሻዬ ንባቤ ነው፡፡
በሰዎች ላይ የሚደርስ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሸ ስደት፣ ጦርነት፣ በሽታ፣ ረሃብ፣ ስቃይ መከራ …  እምነትን መፈተሹ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ነው። ስለምን እግዚአብሔር ይህ እንዲሆን ይፈቅዳል? የሚል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ341- 270 የኖረው ግሪካዊ ፈላስፋ ኤፒከረስ እንዲህ የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር፡-
‹‹እግዚአብሔር ክፉውን ማስወገድ ይፈልጋል ግን አይችልም እንበል፤ እንዲያ ከሆነ ሁሉን ቻይ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይችላል ግን አይፈልግም ካልን፤ ክፉ ነው ማለት ነው፡፡ አይፈልግምም አይችልምም ከተባለ፤ ደካማም ክፉም ነው ማለት ነውና ስለምን እግዚአብሔር ብለን እንጠራዋለን። ይፈልጋልም ይችላልም ካልን ደግሞ ስለምን ስቃያችንን አያስወግድም?››  
የእኛ ዘመን ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› የሚለውም ይህንኑ ነው፡፡
‹‹ለአዳምና ሔዋን ስህተት
ሳይጠራ የመጣ፣
ለእኛ መከራ ግን
ጆሮውን ሳያዘነብል ቀረ፡፡›› ገጽ 34
በ1775 ዓ.ም በፖርቹጋል ሊዝበን የተከሰተውና ብዙ የሰውና የንብረት ውድመት ያስከተለው የመሬት መንቀጥቀጥ በዘመኑ የነበሩ ፈላስፎች፣ ደራሲያንና የስነ መለኮት ልሂቃን፤ በተለይ ጀርመናዊው ፈላስፋ ጎትፍሪድ ዊልኸልም ላይብኒዝ በ1710 ዓ.ም ባሳተመው ‹‹Essay Theodizze“ ስራው ላይ ያሰፈረውን ‹‹የቴዎዲስ ቲዎሪ›› እንዲሞግቱ አደረጋቸው። ፈጣሪ እንዴት ዝም ይላል? በማለት። በዚህ ቲዎሪው ላይ ላይብኒዝ፤ እግዚአብሔር ቅን እና መልካም እንደሆነና የሰዎች ነጻ ፈቃድ የክፋት መነሻ እንደሆነ፤ የክፋት መኖር የፈጣሪን ህልውና ጥርጣሬ ላይ ሊጥል እንደማይችል፤ አሁን ያለችው ዓለም ሊኖሩ ከሚችሉ ዓለማት ሁሉ ይበልጥ የተሻለችው እንደሆነች አስፍሮ ነበር፡፡ እነ ቮልቴር፣ ዣን ዣክ ሩሶ እና ኢማኑኤል ካንት ‹‹የቴዎዴስ ክርክር›› የሚል ስያሜ በተሰጠው መድረክ የሰላ ክርክር አድርገዋል፡፡ በተለይ ቮልቴር ‹‹Candide l‘optimisme›› በሚል ርዕስ የጻፈው ሳታየር ስራው የላይብኒዝን ፍልስፍና የተቸበት ነው የሚል ትንተና ተሰርቶበታል፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን የተለያዩ ጸሐፍት ከሚያዩትና ከሚሰሙት ሰቆቃ የተነሳ በስራዎቻቸው ፈጣሪ ከወዴት ነው ያለው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የእነ ሃይንሪሽ ፎን ክላይስት ‹‹የመሬት መንቀጥቀጥ በቺሊ›› አጭር ልቦለድ አንዱ ነው፡፡ በእኛም ሀገር በተለይ በስነ ግጥሙ እንዲህ አይነት ሃሳቦች መንሸራሸራቸው የተለመደ ነው፡፡
‹‹ቀና ብዬ ሳየው ሰማዩ ቀለለኝ፣
አንተንም ሰፈራ ወሰዱህ መሰለኝ፡፡›› አይነት።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በጀርመን ‹‹ድህረ ጦርነት ሥነ ጽሑፍ›› ወይም ደግሞ ‹‹የፍርስራሸ ስር ሥነ ጽሑፍ›› የተሰኘ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ በ1947 ዓ.ም ቮልፍዲትሪሽ ሽኑረ የተባለ ደራሲ ቡድን 47 በሚባል ለሚታወቀው የደራሲያን ቡድን ‹‹ቀብሩ›› የሚለውን አጭር ልቦለዱን አንብቦ ነበር፡፡ ለህትመት የበቃው በኋላ ነው፡፡ በዚህ አጭር ልቦለድ ጊዜው የጦርነት መሆኑን አሳይቶ አንድ ባልና ሚስት ማን እንዳመጣው ያልታወቀ ስለ አንድ ቀብር የሚያሳስብ የጽሑፍ መልዕክት ይደርሳቸዋል፡፡ እንዲህ የሚል፡-
‹‹በማንም ያልተወደደ፣ በማንም ያልተጠላው፤ በሰማያዊ ትዕግስት ለረዥም ጊዜ ከስቃዩ ጋር ሲታገል የቆየው እግዚአብሔር ዛሬ በሞት ተለይቷል፡፡›› ይላል፡፡ በዚህ መሰረት ባልየው በእግዚአብሔር ቀብር ላይ ለመታደም ይሄዳል። ባለቤቱን ጨምሮ ማንም ሰው ጉዳዩን ከቁብ አልቆጠረውም፡፡ ፍታት ለማድረግ የተገኘው ቄስ እንኳን ሬሳውን አይተው ማንነቱን አላወቁትም፡፡ ስለ ሞቱም በዜና አልተነገረም፡፡ ‹‹ዛሬ››፣‹‹ነገ›› እና ‹‹ወደፊት›› በሚሉ ጋዜጦች ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ የተዘገበ አንዳች ነገር የለም፡፡
‹‹የተጠላው እንዳልተጠላም›› እንዲህ ያለ ነው፡፡ ተጠልቶ እንዳልተጠላ የሆነው ከህዝቡ አንጻር ልመናውን ጆሮ ዳባ ያለው እግዚአብሔር፤ ከእግዚአብሔር አንጻር ደግሞ የእሱን እጅ ብቻ የሚጠብቀው ህዝቡ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹አእምሮውና አካሉ በልምሻ እንደተመታ ልጅ እንዲሁ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ የዘላለም ሞግዚት ሆኗል (ገጽ 7)፡፡ እንዳለው፡፡
‹‹ጥረህ ግረህ ብላ›› የሚለውን ቃል እንደ እርግማንነቱ ተፀይፈን፣ ‹‹…ለነፍሳችሁ በምትበሉት፣ ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ቁራዎችን ተመልከቱ አይዘሩም አያጭዱም፣ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም። እግዚአብሔር ይመግባቸዋል። እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ?›› የሚለውን ነቅሰን በመያዛችን ምድር ሲኦል ሆናብናለች ነው የሚለን።
አንጋጠን በመኖራችን በ“ደስታ መንደር“ የደረሰን ረሃብ፣ እርዛትና ሰው እስከመብላት የተደረሰበትን ታሪክ እያጣቀሰ፣ በነውራችን በሰቆቃ እንድንሰቃይና እንድናፍር ያደርገናል። እሱ ላይ ብቻ አትንጠላጠሉ በማለት፡፡ ወላጅ ወፌ ቆመች ከማለት ጀምሮ፣ እንዲመገብ፣ ልብሱን እንዲለብስ ወዘተ በማድረግ ልጁ እራሱን እንዲችል እንደሚጥር ሁሉ፤ በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል እንዲሁ መሆን እንዳለበት (ገጽ 5) ይነግረናል፡፡ ‹‹በእምነት ስም ወደ ሰማይ የምትወረውሯት ስንፍና በራሳችሁ ላይ መዓት ሆና ትወርዳለች (ገጽ 69) በማለትም ሰቀቀናችንን ያበዛዋል፡፡
‹‹ከበደልነው፣ የተበደልነው፣
ካጠፋነው የተጠፋብን
‹ሰውን ሰው ሲበላው
እዚያ
ፈጣሪያችሁ ነበር፣
ደስም ብሎታል (ገጽ 95)››
ይለንና ይህ የደረሰበት ህዝብ፣ እንዴት የተከደነበትን አይገነጥልም፣ እንዴት ከዚህ ሁሉ በኋላ በተስፋ ይጸልያል? በማለት አናታችንን የሚበሳ ጥያቄ ያቀርብልናል፡፡
‹‹እግዚአብሔር ሊያተርፍባችሁ እውቀቱንና ጊዜውን እንዳፈሰሰባችሁ ዘነጋችሁትን?›› (ገጽ 102) ብሎ እያሳሰበ፤ የደስታ መንደሯ እናት ራሱን ከረሃብ ለመታደግ የተሰደደ ልጇን በፈጣሪ እውቀት ተመርታ ተርቦ ያበላችው፣ ተጠምቶ ያጠጣችው ሽፍታ፣ ውለታዋን ቆጥሮ ሲያድንላት ያሳየናል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔርን በማያውቁ ግብጻውያን የተመረተ እህል፣ እስራኤላዊያንን እንደታደገ፣ የአራጣ አበዳሪው ገንዘብ የ“አይን አንባ“ ህዝብን ከረሃብ ሲታደግ ያመለክተናል (ገጽ 78)፡፡  
እኛ ኢትዮጵያውያን ረሃብ እየተመላለሰ አንጀታችንን ይልስዋል፤ ላለመራብ ብለን ግን ስንሰራ አንታይም፡፡ በሰላም እጦት ህይወታችን በየጊዜው ምስቅልቅል ይላል፣ ሰላም እንዲኖረን ከወሬ ባለፈ ስንሰራ አንገኝም፡፡ ፍቅር ፍቅር እንላለን ፍቅር እንዲኖር ግን መሰራት ያለበትን አንሰራም። አንዳችም ነገር ያለስራ እንደማይሆን፣ ስራ ብቻ እንደሚያኮራ፣ መብትን፣ ነጻነትን እንደሚያጎናጽፍ፤ ከማንጋጠጥ ቁልቁል እራሳችንን፣ እጆቻችንን፣ መሬታችንን መመልከት እንደሚገባ ማስታወስ የ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› ዋና ጭብጥ ነው፡፡
እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት? በምትል አነስተኛ መጽሐፋቸው፣ ‹እግዚአብሔርና እኛ› በሚል ርዕስ ስር የጻፉትን አስታወስኩ፣
‹‹… እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንዲያደርግልን እንፈልጋለን፡፡ የሚቻል ቢሆንማ እሱው አርሶ፣ እሱው ዘርቶ፣ እሱው አርሞ፣ እሱው አጭዶ፣ እሱው ወቅቶ፣ እሱው አበጥሮ፣ እሱው ፈጭቶ፣ እሱው አብኩቶ፣ እሱው ጋግሮ፣ እሱው ቢያጎርስን ደስ ይለን ነበር፡፡…›› ይላሉ፡፡
ለመሆኑ ለማያባራው የድረስልን ጩኸታችን ፈጣሪ፣ ‹‹ለምለም ምድር፣ ህሊና፣ ጉልበት ሰጠኋችሁ ምን አድርግ ነው የምትሉኝ?›› ቢለን መልስ አለን? እንደውም በኢትዮጵያ ጉዳይ ፈጣሪ ግራ የተጋባ፣ የተጨነቀም ይመስለኛል፡፡
ገጽ 6 ላይ ዶክተር አሮን እንዲህ ሲል ይነበባል፡- ‹‹አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ወጣ ብሎ ግድብ ሰራን። ሰው ይራባል፡፡ ከግድቡ ጠልቆ ግን አያርስም። ለምን? ስንል የኢትዮጵያ አምላክ ከሰማይ ባልሰጠው ላመረትን ይቆጣል፣ በረከት ይነሳናል አሉ፡፡››
ቮልፍጋንግ ብሮሸርት በ26 ዓመቱ የተቀጨ፣ በዚህ አጭር ዕድሜው በርካታ ስራዎችን ጀባ ያለ፣ በጀርመን ‹‹ድህረ ጦርነት ስነ ጽሑፍ›› ስማቸው ገኖ ከሚነሱት ደራሲያን መካከል የሚመደብ ነው። ‹‹Draussen vor der Tür - ደጃፉ ላይ›› የሚል አንድ ትያትር ጽፏል፡፡ በአንዱ ክፍል እንዲህ ያለ ምልልስ አለው፡
‹‹ሽማግሌ፣- ልጆቼን፣ ወይኔ ልጆቼን፣ ወይኔ ልጆቼ
ቀብር አስፈጻሚ፣- ምን ሆንክ፣ ለምን ታለቅሳለህ ሽማግሌው?
ሽማግሌ፣- መለወጥ ስለማልችል፣ መለወጥ ስለማልችል! ወይኔ!
ቀብር አስፈጻሚ፣- አዝናለሁ መለወጥ አለመቻል ደስ የሚል ነገር ባይሆንም፤ ባሏ ጥሏት  
እንደሄደ ሙሽራ የሚያነፋርቅ ጉዳይ ግን አይደለም፡፡
ሽማግሌ፣- ልጆቼን፣ ወይኔ ልጆቼን፣ ወይኔ ልጆቼ!
ቀብር አስፈጻሚ፣- ለመሆኑ ማን ትባላለህ?
ሽማግሌ፣- እግዜር ነኝ፣ ማንም የማያምነኝ እግዜር፡፡
ቀብር አስፈጻሚ፣- ምን ያስለቅስሃል ታዲያ፣
ሽማግሌ፣- መለወጥ ስለማልችል፣ እርስ በእርስ ይታኮሳሉ፣ ይለቃቀሳሉ፣ ይደፋፈቃሉ ይገዳደላሉ። ዛሬ በመቶ፣ ነገ በመቶ ሺህ፡፡ እኔስ? እኔ ደግሞ ምንም ማድረግ፣ ምንም መለወጥ አልችልም።
ቀብር አስፈጻሚ፣- ያሳዝናል፣
ሽማግሌው! በጣም! ሆኖም ግን በአንተ የሚያምን ማንም የለም፡፡ ይኸው ነው፡፡
ሽማግሌ፣- ያሳዝናል፣ ማንም እምነቱን ሊጥልበት ያልቻለ እግዜር ነኝ፡፡ መለወጥ ደግሞ አልችልም፡፡ ያሳዝናል መለወጥ አልችልም፡፡››   
ምንም እንኳን ለማንጋጠጣችን ሰበብ አንዱ ስንፍና እንደሆነ ቢታመንም፣ በመሪዎች መበደል፣ የአስተዳደር እጦት፣ የፍትህ መዛባት በአጠቃላይ የምድር ላይ ተስፋ ተሟጦ ማለቅ ትንሹንም ትልቁንም፣ የሚረባውንም የማይረባውንም ጉዳይ ወደ ፈጣሪ ለማመልከት እንድንታትር ሳያደርገን አልቀረም፡፡
‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› ከሁሉም በላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ፈጣሪን የተረዳንበትን መንገድ በቅጡ መፈተሽ እንዳለብን የሚያሳስብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር ሰው አጣች ይለናል፡፡
በቤተ መጻሕፍት ሙያ ላይ ሁልጊዜ የሚባል አንድ ነገር አለ፡፡ ‹‹መጻሕፍት ከሞሉትና የቤተ መጻሕፍት ባለሙያ ከሌለው ቤተ መጻሕፍት ይልቅ፤ ሞያተኛ ያለው መጻሕፍት አልባ ቤተ መጻሕፍት ይሻላል፡፡›› የሚል፡፡ ባለሙያው እንዴትም ብሎ መጽሐፉን ያመጣዋል ስለሚባል። ለነገሩ ይህ አባባል ለሁሉም የሞያ ዘርፍ የሚሰራ ነው፡፡ ለሀገርም ጭምር፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን›› ሲል በአካባቢው ያለ ድምጽ እረጭ አለ፡፡ ‹‹ሀገር ይዘው ህዝብ ይፈልጋሉ። እንደ እስራኤሎች ህዝብ ይዘው ሀገር ቢፈልጉ እንዴት ደግ ነበር፡፡ (ገጽ122) በማለት ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› በቁስላችን እንጨት ይሰድዳል፡፡ ሰው ካለ፣ ሀገር ትሰራለች፡፡
በእግዚአብሄር፣ በእምነት፣ በረሃብ፣ በስንፍና፣ በስደት፣ በሥራ፣ በባህል፣ በመስዋዕትነት እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ››፤ ከዚህ መውጣት የምንችለው ሁለንተናችንን ለስራ ስናስገዛ፤ ስራን ስናከብር፤ ስንፍናችንን ወዲያ አሽቀንጥረን ስንጥል፤ ወደ ጥንቱ ማንነታችን ስንመለስ፤ (የትኛው ጥንት እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም)፣ ከውጪ የተጫነብንን ሸክም ስናራግፍ ነው ይለናል፡፡
‹‹በነቢያቶቻቸው ፋንታ ነቢያቶቻችንን
በመምህሮቻቸው ፋንታ መምህሮቻችንን
በመሲሀቸው ፋንታ መሲሀችንን መተካት (ገጽ 88)፡፡
ለዚህ ደግሞ የስራዎቻችን ባሪያዎች እንሁን፤ ስለራሳችን ራሳችንን የምናስገዛ፣ የራሳችን ባሪያ እንሁን፣ ጀግንነታችን ደም በማፍሰስ ሳይሆን በስራ ይገለፅ በማለት ይመክራል፡፡ ይህንኑ ለማጽናትም እውር የሚያበራው (የረድ ሰርዌን)፣ አልአዛርን (ታለን) ከሞት ያስነሳው፣ እራሱም በሶስተኛው ቀን ከሞት የተነሳው በመሲህ የተመሰለው መምህር ከአረገ በኋላ ተመልሶ መጥቶ፣ ያለው መንግስተ ሰማያት ሳይሆን፣ መንግስተ ምድር እንደሆነ ጌታዬና ባሌ ለምትለው ዐይነ ስውር ሴት፤ ነባሩ ተስፋቸው በአዲስ ተስፋ መተካቱን ሲነግራት እናነባለን፡፡
‹‹ሂጂ ንገሪያቸው፡፡
ተስፋ ያደረጉት ቦታ ደርሼ ተመለስሁ፡፡
ማንም ምንም የለም ነበር፡፡ እንግዲህ ተስፋችሁ ምድር ላይ ናት፡፡ መሬትን በስራ ሙጥኝ በሉ (ገጽ 164)፡፡›› በማለት፡፡
ሐዋርያቱም ህዝቡ የመምህራቸውን ስብከት መቀበሉን እንዲህ ብለው መሰከሩ፣
‹‹ህዝቦች በቀደድክላቸው ቦይ ፈሰሱ
ምድር ላትችልህ እንደተፋችህ፣
ሰማየ ሰማያት እንደተጎበኙልህ፣
አሉ፣
ተቀበሉ፣
እርስ በእርሳቸውም ተማማሉ (ገጽ 186)፡፡
በ‹‹መዝሙረ ዳዊት›› ቅርጽ የቀረበልን ይህ መጽሐፍ አምልኳችንን እንድንፈትሽ፣ ችግሮቻችንን ለመላመድ ከመጣደፍ ይልቅ መፍትሄ እንድናበጅ፣ በጸሎታችንም የዕለት እንጀራችንን እንዲሰጠን ብቻ ከመለመን የዕለት እንጀራችንን ለመጋገር እንድንበረታ፤ በህይወት ግብ ግብ ውስጥ ረዳት ፍለጋ ሸቅብ ከማማተር የተሰጠንን እና ያለንን እንድንጠቀም ያመላከተ ሲሆን፤ በተለይ እጅና እግራችንን አጣጥፈን ‹‹Miracle Money - ሚራክል መኒ›› ኪሳችን፣ ቦርሳችን እና አካውንታችን ውስጥ እንዲገባ ለምንጠባበቅ ለእኛ፤ ወቅቱን ያገናዘበ ሥራ ነው፡፡
አለማየሁ ገላጋይ  እንደወትሮው ሁሉ በ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላም›› ምናባዊና እውናዊ ሕይወትን ደበላልቆብናል፡፡
መደምደሚያዬም ንባቤ ነው፡


Read 671 times