Saturday, 18 June 2022 20:39

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በልጅነቷ በጋዜጠኝነት ፍቅር የወደቀችው ብዙ

            በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ካኖሩት መካከል አንዷ ናት፡፡ በተለይ ከ1962-1983  ለ21 አመታት በሚድያው ዘርፍ ናኝታበታለች፡፡ መነን መጽሄት ላይ ሰርታለች። አዲስ ዘመንም ቤቷ ነበር፡፡ ብዙ ወንድም አገኘሁ አለሙ ለአመታት መኖርያዋን በካናዳ ያደረገች ሲሆን ከ 3 ወር በፊት ሀገር ቤት መጥታለች፡፡ ወዳጃችን ሮማን ተገኝ፣ ስለ እሷ  መጻፍ እንዳለበት ነግራን፣ ብዙን ለማግኘት ጉዞ ወደ ካዛንቺስ ሆነ፡፡ እናም ብዙ አወጋን፡፡ አማረ ደገፋውና እዝራ እጅጉ ብዙን እንደሚከተለው ተርከዋታል፡፡
      ዘጠኝ ጊዜ ዳዊትን ደግማለች
በ1948 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ሰንጋ ተራ በተባለ ሰፈር፣ የቀኝ አዝማች ወንድምአገኘሁ ዓለሙና  የወይዘሮ አረጋሽ ደስታ ቤት ውስጥ ሦስተኛ ልጅ ሆና ተከሰተች፦ ብዙ ወንድምአገኘሁ ዓለሙ። ወግ አጥባቂ የነበሩት አባቷ፣ ለጸሎት ያህል ዳዊትን ከደገምሽ በቂ ነው ብለው ለዘመናዊ ትምህርት ሳይሆን ለትዳር ሊያጯት ሲሰናዱ ታዝባቸዋለች። ትዝብቷን በልጅ አእምሮዋ ቀምራ ከዳዊት በኋላ የሚጠብቃትን  ትዳር ፍራቻ ዘጠኝ ጊዜ ዳዊትን ደግማለች። ከትምህርት ማዕቀብ የተጣለባት ብዙ ወንድማገኘሁ፣ በሰፈሯ የሚያልፉ ተማሪዎችን ማየት እያንገበገባት ወድቀው የምታገኛቸውን ጋዜጦችና ወንድሟ የሚያቀብላትን መጽሐፍት ማንበብ ተያያዘች። በዚሁ መጽሐፍ አቀባይ ወንድሟ ትግል አባቷ ተሸንፈው፣ በማየት ብቻ ስትቀናባቸው የነበሩ ተማሪዎችን ተቀላቅላ፣ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተገኘች።
ጽሁፏ እንዲወጣ ብር ይዛ ሄደች
እስከ 8ኛ ክፍል በዚያ ከቆየች በኋላ አባሀና ጅማ (በኋላ ጆን ኤፍ ኬኔዲ የተባለው) ትምህርት ቤት ለ9ኛ ክፍል ትምህርቷ አቀናች። በዚያ በሳምንት አንድ ቀን ከሰንደቅ ዓላማ ስነስርዓት ቀጥሎ “ሰዎች ምን ይሉናል?” በሚል ርዕስ ተማሪዎች ፊት ዝግጅት በማቅረብ የጋዜጠኝነት ጉዞዋን ሀ ብላ ጀመረች። ቀጥላ የጋዜጠኝነት ፍቅሯ እየገፋት የራሷን ጽሑፍ አዘጋጅታ ወደ ‹‹ድምፅ›› ጋዜጣ አቀናች። የልጅነት የዋህ ልቧ ጋዜጠኛ ለመሆን ክፍያ ያስፈልገዋል ብሎ ነግሯት፣ ከጽሑፏ ጋር ከወንድሟ  ያስላከችውን ገንዘብ  ይዛ ከአቶ ከበደ አኒሳ ፊት ቆመች። የወቅቱ የ"ድምፅ" ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ከበደ አኒሳ፣ የልጅነት የዋህ ልቧንና ይዛ የመጣችውን ጽሑፍ በአባታዊ ፍቅር ተቀበሏት። በማግስቱ ጽሑፏን ጋዜጣው ላይ አወጡላትና በራሳቸው ክፍያ በየዕለቱ የጋዜጣዋን አንድ ኮፒ ትምህርት ቤት ድረስ እንዲደርሳት አደረጉ።
በጽሑፏ በርትታ በበዓሉ ግርማ ጠያቂነት ለ”መነን” መጽሔትም መፃፍ ጀመረች። ጽሑፎቿ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ስለሚያነሱ ብዙዎች ማን እንደሆነች ለማወቅ ጓጉተው እንደነበር ታስታውሳለች። 11ኛ ክፍል ስትደርስ በ"ድምፅ" ጋዜጣ የሴቶች አምድ አዘጋጅ ሆና ከጽሑፍ አበርካችነት ወደ ቋሚ ተቀጣሪነት አደገች። ወዲያው "ድምፅ" ጋዜጣ ስትዘጋ ብዙ ወንድማገኘሁ በ182 ብር ደሞዝ ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዛወረች። የአስራዎቹ እድሜዋን እንኳ ሳትጨርስ ለአራት ዓመታት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አገለገለች። እዚያው አዲስ ዘመን እያለች ለፖሊስና እርምጃው ጋዜጣም ትፅፍ ነበር። ይህ የአፍላነት እድሜዋ ድፍረትን ሰጥቷት ብዙ ጽፋለች፤ ከጎምቱዎቹ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተገፋፍታለች።
ገና በለጋነቷ የወደቁ ጋዜጦችን ስታነብ ደጋግማ እንደሱ በሆንኩ ያለችው ጳውሎስ ኞኞን፣ “አዳር በንፋስ ስልክ ሲነጋ ላምበረት” ብሎ በመፃፉ ሞግታ “አንድ ለሊት በመሸታ ቤት” ብላ ፅፋለች፤ በጽሑፏ በሽቀው ሊደበድቧት የመጡ ባለዱላዎችን በብርሃኑ ዘሪሁን ትከሻ ተከልላ አልፋለች፤ ለጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን ትችት አይኗን ሳትሰብር አይበገሬ መሆኗን አሳይታለች፡፡
የ"መነን" ኗ ብዙ ወንድምአገኘሁ


ብዙ ወንድምአገኘሁ በመነን መጽሄት ትሰራ በነበረበት ጊዜ ምናልባት 20 አመት ቢሞላት ነው፡፡ በጊዜው ማለትም በመጋቢት 1965 የዚህ መጽሄት ተጠባባቂ አዘጋጅ አዛርያ ኪሮስ ነበር፡፡ ስራ አስኪያጅ ደግሞ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር  ነበር፡፡ ያኔ ብዙ ወንድምአገኘሁ በመዝገብ ስሟ እና በብእር ስሟ በርካታ ጽሁፎችን ታበረክት ነበር፡፡ በጊዜው ብዙ ከጻፈችው ፊቸር ጽሁፍ ውስጥ ‹‹የከርታታዋ ኑሮ›› የሚለው ይገኝበታል። የሴተኛ አዳሪዎችን ህይወት የዳሰሰችበት ሲሆን  ቀለል ባለ  መንገድ የተጻፈና ጠንካራ ማህበራዊ ጉዳይን በወጉ ያቀረበ ነው፡፡
ብዙ በመነን  ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ላይ የሴቶች አምድን በጥንቃቄ ታዘጋጅ ነበር፡፡ በ1962 ዓ.ም ከእነ አቶ ከበደ አኒሳ ጋር ገና በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ላይ ሳለች ሰርታለች። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሴት ጋዜጠኞች ታሪክ ከሁለተኛዋ አንጋፋ ጋዜጠኛ  ወይዘሮ እሌኒ ፈጠነ ጋር የመስራት እድል ገጥሟታል። ብዙ ከሰሞኑ እንዳጫወተችን፤ ወይዘሮ እሌኒ ሙያቸውን የሚወዱ ጠንካራ ሴት ነበሩ፡፡ ከእርሳቸው ቆራጥ መሆንን ተምሬአለሁ ስትል ብዙ ምስክርነት ሰጥታለች፡፡
ብዙ ወንድምአገኘሁ በኢቲቪ
ብዙ  በ1968 ዓ.ም ወደ ቴሌቪዥን ተሻገረችና ረዥሙን  የጋዜጠኝነት ህይወቷን በዚያው አሳለፈች። “ከማጀት እስከ አደባባይ” በሚል ርዕስ በበርካታ የሀገራችን ክፍሎች እየዞረች ብዙ ዝግጅቶችን ሰራች። ወደ አርሲ ዘልቃ በርካታ ሚስቶች ስለሚያገቡት አባወራ የሰራችው ፕሮግራም ከተማን አስትቶ ወደ ክፍለ ሀገር ልቧን እንዳሸፈተው ትናገራለች። ከትራንስፖርትና ከካሜራ እጥረት ጋር እየታገለች ኢትዮጵያን አካላለች፤ እግሯ በርካታ የሀገራችንን ክፍሎች መርገጡን ለማስረዳት፤ “አፄ ምኒልክ በሁለት ግዛቶች ብቻ ነው የሚበልጡኝ” ትላለች።
ከአፍላ እድሜዋ አራት አስርታትን ብትርቅም ዛሬም በወኔ “ባህሪዬ ነው መሰል ማንንም አልፈራም” ትላለች። ይሄ ድፍረቷ አይነኬ የተባሉ ርዕሶችን እያነሳች ከሚኒስትሮች ጋር ጭምር አጋጭቷታል። ለዚህ ማሳያ ሲስተር እማዋይሽ ገሪማን ቃለ-መጠይቅ አድርጋ በሰራችው ስራ የወቅቱ የጤና ሚኒስትርን አበሳጭቶ በወታደር ተከባ እንደነበር ታስታውሳለች። በዚህ ሁሉ ትጋትና ድፍረት በቴሌቭዥን መስኮት በርካታ ዝግጅቶችን ለተመልካቾቿ በማድረስ  ኢትዮጵያን ስታስተዋውቅ ቆይታ በ1983 ዓ.ም መንግስት ሲለወጥ እንቅፋት ገጠማት። ደህንነት ነሽ ተብላ ታገደች፤ ጉዳዩዋ ሲጣራ ከሳሾቿ ማስረጃ ማቅረብ ቢያቅታቸውም፤ ደህንነት አለመሆኗን ለማስረዳት ብትጥርም፣ ያለ ፍርድ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምትወደው ሙያዋ ተገለለች። በኋላ ላይ እንድትመለስ ብትጠየቅም አሻፈረኝ አለች። ጥቂት ጊዜያትን በኢትዮጵያ ከቆየች በኋላ ወደ እስራኤል፣ ከዚያም ወደ ካናዳ አቅንታ የስደት ኑሮዋን ተያያዘች።
(ከተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን)

________________________________________________

                  ንጉሥ ሲጨንቀው!

የአንዲት ደሃ ሀገር፣ ዜጎቿ በሙሉ
መሄጃ ቢያሳጡት፣ ‘ተራብን’ እያሉ
ምስኪን ንጉሣቸው፣ እንዲህ ጸለየ አሉ፡-
‘’እባክህ አምላኬ!
የተራበ ሕዝቤን፣ ሲያሻህ በነጠላ
ካሰኘህ በጅምላ፣
ከፊቴ አርቅና፣ ባሕር ክተትልኝ
ከሐይቅ ጣልልኝ፡፡
ከዚያማ!
ያልቻሉት ሲሰምጡ፤
የቻሉት ለማምሻ፣ ዓሣ ይዘው ይውጡ!
(በረከት በላይነህ፤ "የመንፈስ ከፍታ")

___________________________________________________


                      በኢትዮጵያ ተጓዥ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ብዙ ሊነገርለት የሚገባው ባለሙ


             ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ከ10 አመት በፊት ህይወቱ ያለፈ፣ ለ34 አመታት በኢትዮጵያ የቴአትር ሙያ ላይ በትጋት  ሲሰራ የቆየ ባለሙያ ነው፡፡  ሳላይሽ የቴአትር ኢንተርፕራይዝን  ከ29 ዓመት በፊት መስርቶ  "ሸፍጥ፣ ሰቀቀን፣ ፍትህ፣ ቃልኪዳን  እና እናት; የተሰኙ ቴአትሮችን ለእይታ ያበቃ በሳል ባለሙያ ነው፡፡ ይህ ባለሙያ ብዙ የለፋ ግን ጥቂት ያልተነገረለት፤ ብዙ ሊጻፍለት ሲገባ ግን  ብዙ ያልታወቀ ታላቅ ሰው ነው፡፡
ጥላሁን ጉግሳ አለሙ በ1941 ዓ.ም ተወለደ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በንጉስ ሚካኤል 1ኛ ደረጃ ተማሪ ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን  ደግሞ  በደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ በንግድ ስራ ትምህርትም ዲፕሎማውን ተቀብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር  ዲፕሎማ ተቀብሏል፡፡ ከ1961-1963 የትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደር ረዳት፤ በጤና ጥበቃ  የሪከርድና ማህደር አገልግሎት ኃላፊ በመሆን ሀገሩን አገልግሏል፡፡ ከ1967-1969 በባህል ሚኒስቴር የማሰልጠኛ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ሰርቷል፡፡ በሀገር ፍቅር ቴአትርም  ለ2 አመታት በአስተዳዳሪነት  አገልግሏል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን በመዝለቅም፣  የአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ በመሆን ሀገራዊ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ ከ1975-1978 ደግሞ በባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር የአስተዳደርና ፋይናንስ  መምሪያ ኃላፊ በመሆን  አገልግሎአል፡፡ ለ7 አመታት በባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር፣  የስነ-ጥበባት መምሪያ ኃላፊ ሆኖ  በንቃት ማገልገሉን አብረውት የሰሩ ይመሰክራሉ፡፡


ደራሲና አዘጋጅ ጥላሁን  በ1985 ዓ.ም ምናልባትም በሀገራችን የመጀመርያ ሊባል የሚችለውን  የቴአትር ኢንተርፕራይዝ፣ ሳላይሽ  የስነ-ጥበባትና ማስታወቂያ  ድርጅትን መሰረተ። በዚህም በርካታ ወጣት የቴአትር አፍቃርያንን ወደ ሙያው ዘልቀው እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ይህ ለሀገራችን ቴአትር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል የተባለለት ባለሙያ፤ ከ1972-1980 ባሉት ጊዜያት በምስራቅ ጀርመን፣ በሶቭየት ህብረት፣ በምዕራብ ጀርመን፣ በፈረንሳይ፣ በቡልጋርያና  በቻይና በርካታ ሴሚናርና ጥናታዊ ጉብኝቶችን ተካፍሏል፡፡ ይህም የበርካታ ሀገራትን የስራ ተሞክሮ ለማወቅ አግዞታል፡፡
ደራሲ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ  ‹‹ትዝብት.›› የተሰኘው ቴአትሩን በ1979 ዓ.ም የዛሬ 35 አመት ደርሶ ያዘጋጀ ሲሆን የታየውም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ነበር፡፡ በወቅቱ ይህ ስራው እጅግ ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ ለአንድ አመት ተኩል መድረክ ላይ በቆየበት ጊዜ ከ40 ሺህ በላይ ተመልካች በአድናቆት ተመልክቶታል፡፡ የመድረኩ ፀዳል ወጋየሁ ንጋቱ  በመሪ ተዋናይነት ድንቅ ክህሎቱን ያሳየበት ቴአትር ነበር፡፡ "ትዝብት" በታየ በ3 ዓመቱ ደግሞ  ‹‹ጽናት›› የተሰኘው በጥላሁን ጉግሳ አለሙ ደራሲነትና አዘጋጅነት የተሰራው ቴአትር፣ በሀገር ፍቅር መድረክ ለዕይታ ቀረበ፡፡ ወደ ክልል ከተሞችም ወጥቶ ከ100,000 ሰው በላይ የተመለከተው ድንቅ ቴአትር ነው፡፡
ጥላሁን ጉግሳ ከመንግስት የስራ ኃላፊነቱ ለቅቆ በ1984 ሳላይሽ የቴአትር ኢንተርፕራይዝን ሲመሰርት በቅድሚያ ለመድረክ ያበቃው ቴአትር  ‹‹ሸፍጥ›› የተሰኘውን ነበር፡፡ ‹‹ሸፍጥ›› በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትርና በራስ ቴአትር ከ20ሺህ ህዝብ በላይ ተመልክቶታል፡፡ በ1986 ዓ.ም መስፍን ጌታቸው የጻፈውና ጥላሁን ጉግሳ ለመድረክ እንዲሆን አድርጎ ያዘጋጀው ‹‹ሰቀቀን›› ቴአትር ከተመልካች አእምሮ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ይህን ቴአትር በጠቅላላ  90ሺህ ህዝብ ተመልክቶታል፡፡ ሳላይሽ የቲያትርና የፊልም ጥበብ ኢንተርፕራይዝ “ፍትህን በ1989 ዓ.ም ሲያዘጋጅ”፤ ደራሲና አዘጋጅ፦ ጥላሁን ጉግሳ አለሙ፣ ተዋንያን፦ ፍቅርተ ጌታሁን፣ ሰለሞን ሀጎስ፣ ገሊላ መኮንን፣ አበበ ደምሴና  ሌሎችም የተወኑበት ድንቅ ቴአትር ነበር ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋከልቲ  ለ7 ወራት የታየው ‹‹ፍትህ››፤ በሌሎች ክልሎችም እየተዘዋወረ የታየ ሲሆን ከ85,000 በላይ ህዝብ ተመልክቶታል፡፡
በ1992 ዓ.ም በደራሲ አብርሀም አማረ የተደረሰውና ጥላሁን ጉግሳ አለሙ ያዘጋጀው ሌላው ተወዳጅ ቴአትር ‹‹ቃልኪዳን›› ነው።  ይህን ቴአትር በጠቅላላ 72ሺህ ህዝብ ተመልክቶታል፡፡ በአመቱ በ1993 ዓ.ም ለመድረክ እይታ የበቃው ቴአትር ደግሞ  ፍጹም ንጉሴ የደረሰውና ጥላሁን ጉግሳ ያዘጋጀው ‹‹እናት››  ቴአትር ነው፡፡ ይህ ቴአትር በቤተሰብ አኗኗር ላይ ትኩረቱን ያደረገ፣  የሀገር መሰረት ቤተሰብ ነው የሚለውን ጭብጥ የሚያንጸባርቅ ሥራ ነው፡፡    
የጥበብ ባለሙያው  ጥላሁን ጉግሳ አለሙ በህይወቱ ደስታን ከሚሰጠው ነገር ቀዳሚው ቴአትርን ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህን ውስጣዊ ስሜቱንም ለማርካት ለአመታት ታላቅ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ ወጣቶች  የድርሰት ችሎታቸውን እንዲያወጡ እድል በመስጠት ሃላፊነቱን  በሚገባ ተወጥቷል፡፡ ጋሽ ጥላሁን አቅማቸውን  እንዲያወጡ ከረዳቸው የቴአትር ባለሙያዎች መካከል ዶክተር ሱራፌል ወንድሙ ፤ ተዋናይ ተመስገን  አፈወርቅ ፤ አሁን በህይወት የሌለው መስፍን ጌታቸው ይገኙበታል፡፡ ቴአትርን በክፍለ ሀገር እየዞሩ በማሳየት ፈር ቀዳጅ የሆነው የጥላሁን ድርጅት ሳላይሽ፤ በርካታ የክፍለ-ሀገር የቴአትር አፍቃርያንን ስሜት ያረካ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
(ከተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን)

Read 944 times