Saturday, 18 June 2022 20:28

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “አለማየሁ ገላጋይ አይመቸኝም!”


           (ማስታወሻ-ይህንን ፅሁፍ ስታነቡ ወገቧን ይዛ ለነገር ያቆበቆበች ወይዘሮን እያሰባችሁ ቢሆን ይመረጣል)
ሰሞኑን በአዲሱ የአለማየሁ ገላጋይ መፅሀፍ ዙሪያ ትችት፣ሂስ የሚል የዳቦ ስም እየተሰጣቸው በየቦታው የሚለጠፉ ፖስቶችን እየተመለከትኩ ስገረም ነበር የሰነበትኩት። እውን ይሄ ሁላ አንባቢ እስከዛሬ ድረስ ነበረ? ይሄ ሁላ ሀያሲ? ይሄ ሁላ ተች እስከዛሬ የት ነበር? እንዲህ የበዛ የሥነፅሁፍ ተቆርቋሪ አለን? ብቻ ተደመምኩ።
ትንሽ ስቆይ ግን በራልኝ። ሀያሲ ተች ያልኳቸው ሰዎች ጠበቆች ሆነው አገኘኋቸው። የስነፅሁፍ ተቆርቋሪ ያልኳቸው ስነፅሁፍ የሚቆረቁራቸው፤በተቃራኒው ለሀይማኖታቸው (ፈጣሪያቸው) የሚቆረቆሩ ሆነው አገኘኋቸው። (እስካሁን ድረስ አንድም ስነፅሁፋዊ ሂስ አላጋጠመኝም።) አሀ! ገባኝ። ለማረጋገጥ ትችትን በለጠፉ ፖስቶቹ ፕሮፋይል አንገቴን ብቅ አድርጌ ሰለልኳቸው። ቅልጥ ያሉ አማኞች ናቸው። በለጋ እድሜያቸው ከወላጆቻቸው እንከን የለሽ እምነትን የወረሱ...የነሱ መንገድ እውነተኛ፤ እንቅፋት የሌለው አድርገው የሚያምኑ፣ ከነሱ ተቃራኒ ሀሳብ ያለው ደሞ ሰይጣን የሚጋልበው፣ እርኩስ፣ በገደል ላይ የሚራመድ መስሎ የሚታያቸው ብፁአን ናቸው...ረጋ ብለው እየተንሳፈፉ ወደ ገነት በር እየገቡ የሚመስላቸው። ከነሱ ተቃራኒ ሀሳብ የያዘውን ሰው ወግረው፣ አሸማቀው የገነትን VIP ቦታ ያገኙ የሚመስላቸው ናቸው።
የአሌክስን ሙሉ መፅሐፍ በሶቅራጥስ አንድ አባባል ልቀንብብላችሁ፤ “ለአማልክት ህዝቡ የሚሰግደው ስለሚያምን ሳይሆን ማሰብ ስለማይችል ነው!”
ይሄኔ VIP ትኬት ያስጎመጃቸው ሰዎች አሌክስ ላይ ጓ አሉ። አንዳንዶቹ ንዴታቸውን ዋጥ አድርገው፤ የአንባቢ ፌስ ማስክ አጥልቀው፣ረጋ ብለው “ይሄኛውን የአሌክስ መፅሐፍ አልወደድኩትም።” ወይም “ይሄኛው መፅሐፉ ከሌሎቹ ወርዶብኛል።” ሲሉ ሰምታችኋል መቼም። ለምን ወረደባችሁ? የቋንቋ አጠቃቀሙ ነው? የገፀ ባህሪ አሳሳሉ ነው? ሴራው ነው? ታሪኩ ነው? ምኑ ነው ያልተመቻችሁ ስትላቸው አፋቸውን ከቦታው ላይ ታጣዋለህ። በቃ ያልተመቻቸው አንድ ነገር ነው፤ ለዘመናት ተከናንበውት የነበረውን አቧራ የጠገበ ድሪቶ አንስቶ በማራገፉ ነው!!! “ይሄ አቧራ የጠገበ ድሪቶ በሽታ እያመጣ ነው። እናንተ ከበሽታው ጋር ተላምዳችሁ ከጊዜ ብዛት ጭራሽ መድሀኒት እየመሰላችሁ ነው!!” በቃ ይህችን ብቻ ነው ያለው።
አንዳንዶቹ በግልፅ ጅማታቸው ተገታትሮ ወባ እንደያዘው ሰው እየተንቀጠቀጡ፡- “የዚህ ሰውዬ አላማ ምንድነው?” -”ከፈጣሪ ጋር ከሀይማኖት ጋር ችግሩ ምንድነው?” (ከዛ ባላንስ ለማድረግ) “ከባህላችን፣ ከእሴታችን ጋር ችግሩ ምንድነው?” ብለው እንጥላቸው እስከሚታይ ጮኹ። እኔማ ሂደው ሂደው እንደ ዘመኑ ራስ አልባ ሰዎች “አለማየሁ ገላጋይ 666 ነው!!...የሴክሬት ሶሳይቲ አባል ነው..ስውር ተልዕኮ አለው” እያሉ ይተነትናሉ ብዬ ብጠብቅ ማግኘት አልቻልኩም። (አብይ ይልማ ራሱ ፈዟል። ደህና የዩቲዩብ መሸቀያ አግኝቶ)
ብቻ አንዳንዱ አንብቦ እያጣቀሰ እሪ አለ። ሌሎች ደፋሮች ደሞ “መፅሀፉን አላነበብኩትም ግን...” ብለው ትችት ወረወሩ። ሼልፌ ላይ ሌማቴ ላይ አሉ። ከጭፍን አማኞች የሚጠበቅ ነው።
ሶቅራጥስ ከላይ የፃፍኩትን ነገር በማለቱ የግሪክ ገዥዎች ተቆጡ። የማይነካ ነካ፣ ወጣቱን አሸፈተ፤ አካኪ ዘራፍ ብለው እንዲገደል ወሰኑ። ይኸኔ ሶቅራጥስ ምን አለ? “የወጣቶችን ልብ አልበከልኩም። የእኔ ስራ እውነትን መፈለግ ብቻ ነው። እኔን የምትከሱኝ ጥፋተኛ ሆኜ ሳይሆን የእናንተን አላዋቂነት በመግለጤ ነው። የእናንተን አላዋቂነት የገለጥኩት ደሞ ስለምጠላችሁ ሳይሆነ ከፍ ላደርጋችሁ ስላሰብኩ ነው። አንድ እውነት ግን አለ። ሰው ሳያስብ ከሚኖር እያሰበ ቢሞት ይሻለዋል።”
ምናለ አሌክስ ይችን የሶቅራጥስ ንግግር፣ ቃል በቃል በዛ መድረክ ላይ ቢናገራት ብዬ አሰብኩ።
(ከዚህ ሁሉ ነገር በፊት ግን)
አለማየሁ ገላጋይ አይመቸኝም!! ነበር በፊት። ድህነት ከመፅሐፎቹ ጋር ሁሌ የሚያፋቅርበት መንገድ። ሰፈሮቹ፣ሰዎቹ፣ቤቶቹ ጉራንጉሩ፣ የምር አንዳንድ የሱን መፅሐፍ ሳነብ አፍንጫዬን ሁላ እይዛለሁ። ካሁን ካሁን እጣቢ ተደፋብኝ እያልኩ እየተሳቀቅኩ ነበር፣ ካንድ ገፅ ወደ ሌላ ገፅ የማልፈው። በዚህ መፅሐፍ ግን ወደድኩት። ደፋር ደራሲ ይመቸኛላ።
((እንግዲህ አካሄዴ ገብቷችኋል፤ሀያሲ ነኝ ባዮቹን እየሄስኳቸው ነው። ጠበቃ ነን ባዮቹን እየሞገትኳቸው ነው። ህፃናቶቹንም እየኮረኮምኩ ነው።))
የመጀመሪያ ስህተታቸው ፈጣሪ፤ ሀይማኖት፤ ባህል...መነካት የለባቸውም ብለው ማሰባቸው ነው።
ሁለተኛውና ዋናው ስህተታቸው ግን እኛ የምንራመድበት መንገድ ብቻ ነው ትክክለኛና እንቅፋት የሌለበት ብለው መደምደማቸው ነው። ሌላው የሚጓዝበት መንገድ ገደል ነው። ድምዳሜ በራሱ በእውቀት ክሳት የሚፈጠር ነገር ነው። ከነሱ ተቃራኒ ሀሳብ ያለው ሰው እርኩስ፣ ሰይጣን የሚጋልበው መስሎ ስለሚታያቸው። በተቃራኒው ሌላ አስተሳሰብ ያለው ቡድን እንዳለ ይረሳሉ። ሀይማኖተኞች የሚራመዱበት ጎዳና የድንቁርና፤ የቂላቂል፤ የባርነት መንገድ ነው ብለው የሚያምኑ፤ ህዝቡን ነፃ ማውጣት የሚሹ... ካለማሰብ ወደ ማሰብ፤ ካለማወቅ ወደ ማወቅ መምራት የሚሹ እንደነ አሌክስ አይነት ሰዎች መኖራቸውን ይዘነጋሉ። ለነሱ ተቃራኒ ሀሳብ የያዘ ሰው ጦርና መትረየስ ይዞ ከተጋፈጣቸው ሰው በላይ ጠላታቸው ነው።
ይህ የሆነው ደሞ አይምሮን ክፍት ካለማድረግ። ከተለያየ አቅጣጫ ለሚመጡ ሀሳቦች ካለመጋለጥ ነው። በልጅነታቸው ወላጅ ያስታቀፋቸውን አስተሳሰብ እሹሩሩ እያሉ፤ሳይቀጡ አሳድገው ማጎልመሳቸው ነው። የራሳቸውን አስተሳሰብ አምጠው፤ወልደው ማጎልመስ ስለማይፈልጉ ነው። ለዚህ ነው የራሱን ሀሳብ ወልዶ ካሳደገ አባት ጋር ሲገናኙ ጋጣው እንደጠፋበት በሬ የሚደነብሩት። ስለዚህ የአእምሮ መስኮቶቻችሁን ከፋፍቷቸው። ብርሀን ከየአቅጣጫው ይስረግ። በአንድ በኩል ብቻ የሚገባ ብርሀን አይምሮን ከማክሰል ውጭ ፋይዳ የለውም።
“የእውቀት መጀመሪያ አለማወቅን ማወቅ ነው!” እንዲል ሶቅራጥስ።
፨ ኪሮቤል ሮሪሳ የተባለ አንድ የበራለት ኤቲስት ልክ እንደናንተ ሰዎች፤ “ለምን ፈጣሪን ትናገራለህ?-ሀይማኖታችንን ለምን ትተቻለህ? ባህሌን-ሀብሌን..እባክህ አታውራ! ዝም በል; ሲሉ የሰጠው አረቄ የሆነች ፅሁፍ ልጋብዛችሁ።
ሰዎችን ወደ አንተ ሀይማኖት እየሳብክ ከሰይጣን መንገድ መመለስ ያንተ ወንጌል ነው።
“ትውልድን እያዳንኩ ነው” ብለህ ታስባለህ።
“ትውልድን እያዳንኩ” ነው ብዬ አስባለሁ።
የኔ መንገድ ወይስ ያንተ የጥፋት መንገድ የሚለውን ጥያቄ ማንም ሊያረጋግጠው አይችልም። ስለዚህ ሁለታችንም እኩል ነን። አንተም አጥምደህ የኔን ሰዎች ትነጥቀኛለህ። እኔም አጥምጄ ያንተን ሰዎች እነጥቅሀለሁ። ያ ያለ ነው። ተመሳሳይ ስራ እየሰራን ነው። ነገር ግን አንተ እፍርታም ነህ። ከሀይማኖትህ በወረስከው የውድመትና የስግብግብነት ትምህርት ተጠቅመህ እኔ እንድጠፋ ትመኛለህ። አንተ ብቻ ያለ ከልካይ እንድትኖር ትፈልጋለህ። ስራዬን እንዳልሰራ “ከሀይማኖት ውጡ” የሚለውን ወንጌል እንዳላዳርስ “ሀይማኖቴን ነካህ” ብለህ ትከሰኛለህ። እኔ ግን “አስተሳሰቤን ነካህ” ብዬህ አላውቅም። የኔ የማምንበትና የምሰብከውን አስተሳሰቤን እንደ ሀይማኖት እየው። ያንተ የመስበክ መብት ለኔም ይሰራል። ልዩነቱ የምንሰብከው ፍሬ ነገር ነው። ልብ ካለህ ሳትነጫነጭ የያዝከውን እውነት ይዘህ ብቻ ኑር።
የምታመልከው ውሸትና ሌብነት እንደሆነ ሲጋለጥብህ አስሬ “ዝም በል” እያልክ ሰውን አታፍን። “ዝም በል” የሚለው ትዕዛዝ የስብከትህ አንድ አካል እስካልሆነ ድረስ አትጠቀመው። ፀረ-ሀይማኖታዊ የሆነ ወንጌል ለአለም ይዳረስ ዘንድ አትከልክለኝ።
(Swipe Januda)Read 665 times