Saturday, 18 June 2022 20:00

የ"አዋጭ" ጉዞ - ከቁጠባና ብድር እስከ ግዙፍ ባንክ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በተለምዶ  ሰባ ደረጃ በሚባለው አካባቢ ተወልደው ፈረንሳይ ለጋሲዮን በተሰኘው ሰፈር ነው ያደጉት፡፡ የወታደር ልጅ እንደሆኑ የሚገልፁት እንግዳችን፤ ገና የ4 ዓመት ህፃን እያሉ አባታቸው በመሞታቸው በጠንካራ እናት እጅ እንዳደጉ በኩራት ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከጅማ ዩኒቨርስቲ ያገኙ ሲሆን በውጭ ሀገርም የመማር እድል ገጥሟቸዋል፡፡ እንግዳችን አቶ ዘሪሁን ሸለመ፤ የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ በቅርቡ 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ያከበረው አዋጭ፤ በአሁኑ ወቅት ከ3 ቢሊዮን  ብር በላይ ሀብትና ከ75 ሺህ በላይ አባላትን አፍርቷል፡፡ ለመሆኑ አዋጭ ከምን ተነስቶ ምን ደረሰ? የስኬቱ ምስጢርስ ምንድን ነው? የጠንሳሹ ታሪክ ምን ይመስላል? ለእነዚህ ጥያቄዎች የተሟላ መልስ ለማግኘት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከአቶ ዘሪሁን ሸለመ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡                “አዋጭ” የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበርን ከመመስረትዎ በፊት ምን ይሰሩ ነበር?
አባቴ በልጅነቴ በመሞቱ እናቴ ብቻዋን ነው ያሳደገችኝ፡፡ በዚህ ምክንያት እናቴንም ራሴንም ለማገዝ የቀን ሥራም እየሰራሁ፣ ችቦ እየሸጥኩ፣ መፅሔትም እያዞርኩ ነው ያደግሁት። ተምሬ ከተመረቅኩ በኋላ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት (NGO) ውስጥ ከማህበራዊ አገልግሎት ባለሙያነት እስከ ፕሮጀክት አስተባባሪነት ሰርቻለሁ፡፡ እዛ እየሰራሁ በ1996 ዓ.ም ትዳር መሰረትኩ፡፡ ትዳር መስርቼ ለሁለት ዓመት ቴሌቪዥን ለቤቴ መግዛት አልቻልኩም ነበር። እኔም ባለቤቴም ቤት ገብተን መፋጠጥ ሆነ፡፡ ሩጫም ሆነ እግር ኳስ ወይም ሌላ ለየት ያለ ነገር ሲኖር ሆቴል እየሄድኩኝ ነበር የማየው፡፡ በ1997 ዓ.ም በሀገራችን ያ ሁሉ ነገር ሲከሰት እኔ ጫንጮ ነበርኩኝ፤ አዲስ ሆቴል የሚባል ቦታ እየሄድኩ ነበር ቴሌቪዥን የማየው፡፡ እንግዲህ አስቢው ቴሌቪዥን ብርቅ የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ እናም እኔ እናቶች ገቢ ማስገኛ ስራ ላይ እሰራ ስለነበር ኑሮአቸውና ቤታቸው ሲቀየር እያየሁ፣ እኔ ግን ቤቴ ውስጥ ቴሌቪዥን አልነበረኝም፡፡ እኛ ገንዘብ እንዲቆጥቡ ገቢ እንዲያገኙ የምናግዛቸው እናቶች ከእኛ ቀድመው ተቀይረዋል፡፡
ነገሩ ተረት ተረት ይመስላል አይደል፡፡ ግን‘ኮ 1996 ቅርብ ነው---
እውነት ነው፤ ተረት ይመስላል፡፡ ግን የኖርኩትን ነው የምነግርሽ፡፡ ከዚያ ይሄ ሀሳብ ሲመጣልኝ አዋጭን መሰረትኩ፡፡
ምን ዓይነት ሀሳብ መጣልዎት?
ምን መሰለሽ… እኔ እዚያ እርዳታ ላይ ሰዎችን እያደራጀሁ ስሰራ፣ እነዛ እናቶች 5 እና 10 ብር እየቆጠቡ 10 ሺህ ብር ይበደራሉ፡፡ እኛ ደሃ የምንላቸው እናቶች የኢኮኖሚ ደሃ ነበሩ እንጂ የአስተሳሰብ ደሃ አልነበሩም፡፡ አየሽ ደሃ ስንል መጠንቀቅ አለብን፡፡ የኢኮኖሚ ደሃ አለ፤ እንደገና የአዕምሮ ደሃ አለ፡፡ እኛ ስልጠናና ገንዘብ ሰጥተናቸው ሲቀየሩ እያየሁ ነው፡፡ በየቤታቸው ስንሄድ ቴሌቪዥን አለ፣ቤታቸው ቆንጆ ነው፡፡ እነሱ 5 እና 10 ሺህ ብር እየተበደሩ ነበር፡፡ እኔ ያኔ 4 ሺ700 ብር ነበር ደሞዜ፤ የታሸገ 5 ሺህ  ብር አይቼ አላውቅም፡፡ ጠቅለል ሳደርገው እነዚህ እናቶች 5 እና 10 ብር ቆጥበው ህይወታቸውን ከቀየሩ እኔ ለምንድን ነው የማልቆጥበው ብዬ፣ በ1999 ዓ.ም እናቶች 5 እና 10 ብር እንዲቆጥቡ አድርጌ፣ 41 አባላት በ15ሺ600 ብር አዋጭን መሰረትኩኝ። የዛን ጊዜ የብዙዎቹ ችግር ምን መሰለሽ? ቴሌቪዥን፣ ፍሪጅ፣ ስቶቭ፣ ፈረሱላ በርበሬ ነበር፡፡ እኔ እሱን እያመጣሁ ሰው ወለድ ስለሚፈራ እኔ እሱን ዋናው ላይ ደምሬና እኩል አካፍዬ፣ መስጠት ጀመርኩኝ። ያን ጊዜ ወለድ ያለው አይመስላቸውም፡፡ ረጅም ጊዜም ስለሆነ ሰው ይወስዳል፡፡ ኢትዮጵያዊ ብድር ይፈራል፣ ብድር አይወድም:: ከእምነትም ከምንም አንጻር ማለቴ ነው፡፡ አለመክፈል ነው እንጂ ነውር፤ መበደር ነውር አይደለም፡፡ አሁን እኛ ህዝቡን ያስተማርነው ይህንን ነው። እንዲበደር ከዛ እንዲከፍል ማድረግ ጀመርን፡፡
እርስዎስ ቴሌቪዥን ገዙ?
አዎ ገዛሁ፡፡ “ናፍትሮን” የሚባል አዲስ ብራንድ ቴሌቪዥን በ1ሺ 400 ብር ገዛሁ፡፡ ያን ጊዜ ሶኒ 2ሺ400 ብር ነው፤ ናፍትሮን 1 ሺህ 400 ብር ነበር፡፡ 21 ኢንች ማለት ነው፡፡ ያቺ ቲቪ ከነፎቶዋ አሁንም አለች፡፡ ከዚያ በኋላ አምስት ሺህ፣ አስር ሺህ፣ ሃምሣ ሺህ፣ መቶ ሺህ ብር ድረስ ማበደር ጀመርን፡፡ እኔም እስከ 2003 ዓ.ም ለአራት ዓመት ያለ ደሞዝ ሊቀ መንበር ሆኜ በነጻ  ነው የሰራሁት። እርዳታ ድርጅቱ ውስጥ በሚከፈለኝ ደሞዝ ብቻ ማለቴ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም ታዲያ  የመጀመሪያው የአዋጭ ሰራተኛ ሆኜ በ1 ሺህ 500 ብር ደሞዝ ተቀጠርኩ፡፡ በወቅቱ አዋጭ በደህና ብር ሰራተኛ የመቅጠር አቅም ስላልነበረው ከምሰራበት የእርዳታ ድርጅት 4ሺ700 ብር ደሞዜን ትቼ ነው በ1 ሺህ 500 ብር የተቀጠርኩት፡፡ በላሜራ በተሰራ ቆርቆሮ ቤት፣ ሰው ገብቶ የሚዘጋው ጠባብ ቢሮ ውስጥ ነው አዋጭን የጀመርኩት፡፡ አሁን ይህን የተንጣለለ መኖሪያ ቤት የሚመስል ቢሮ አትመልከቺ፡፡ ዘሪሁን ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚለው ከባድ ነው፡፡ የአሁኑ ቢሮዬ እንደምታይው የተንጣለለ ነው፤ባዝ ሩም አለው፤ ቴራስ አለው፤ በጎን አዳራሽ አለው፤ መኖሪያ ቤት ይመስላል። ማታ ከዚህ የምወጣው ለልጆቼና ባለቤቴ ስል ብቻ ነው፡፡ ብቻ በ1 ሺህ 500 ደሞዝ ጀመርኩ። በየመስሪያ ቤቱ እየሄድኩ ቁጠባ የሌላቸውን ለማስገባት ስዞር ጫማዬ ተበስቶ ሶል በ30 ብር ሁሉ ቀይሬ አውቃለሁ፤ ታዲያ ሶሉ ስራመድ ቋ ቋ ቋ እያለ እያሳቀቀኝ ነበር የምሄደው። አንዳንድ ቢሮ ስሄድ ደግሞ ቢሮ ከመግባቴ በፊት መንገድ ላይ ቁጭ ብዬ፣ጫማዬን አውልቄና ካልሲዬን አናፍሼ ነበር የምገባው፡፡ ስለ እውነት ነው የምነግረሽ፣ ከመሳቀቄ የተነሳ ሰው ቢሮ ስገባ ጫማ ይሸት ይሆን  እንዴ ብዬ ነው ይህን የማደርገው። ምክንያቱም ብዙውን መንገድ በእግሬ ነበር የምጓዘው፤ በፀሀይ ማለት ነው፡፡ ያ ሁሉ አለፈ፡፡
እኔ ስሰራ በታማኝነት ነው የምሰራው። አልሰርቅም፡፡ ስርቆት ቆሻሻ ነው፤ እፀየፈዋለሁ። እኔ እስከማውቀው ድረስ ሰርቄ አላውቅም። ሰውም በስርቆትና በቆሸሸ ነገር ይከሰኛል ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም አሰራሬ ንጹህና ግልፅ ነው፡፡ በዚህ በኩል ደረቴን ነፍቼ ነው የምናገረው። እኔ የራሴን ስራ እሰራለሁ፡፡ ፋይናንሱን ለፋይናንስ ሌላውንም ለሚመለከተው ነው የምተወው፡፡ ይሄ እንድናድግ አድርጎናል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ላይ ከ75 ሺህ በላይ አባላትና  ከ3 ቢ.ብር በላይ ሀብት አለን፡፡ ከ30 ሺህ ሰው በላይ የስራ ዕድል ፈጥረናል፣ ለ12 ሺህ አባላት ወደ 3.5 ቢ. ብር ብድር ሰጥተናል፡፡ እያንዳንዱ ሰው 3 ሰው ቢጠቅም፣ 54 ሺህ ሰው ተጠቃሚ ሆኗል ማለት ነው፡፡
እርስዎ ያደጉበት የፈረንሳይ መንደር በእርስዎ ምክንያት ዕድገትና ለውጥ እንዳመጣ ሰምቼ ነበር። እስኪ ስለሱ ይንገሩኝ?
እውነት ነው፡፡ ያደግኩበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን ብትመጪ ከአንድ ቤተሰብ አምስትና ስድስቱ የአዋጭ አባላት ናቸው፡፡ በዚህ አካባቢ የነበሩት የጭቃ ቤቶች በሙሉ ወደ ብሎኬት ተቀይረዋል። ይሄ እንግዲህ በመቆጠብ መቀየር እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ ሰዎች ሲቆጥቡ አይሰደዱም፤ ሞራላቸው የተጠበቀና ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ሰው ቤቱን ሸጦ ሲሄድና ከቀዬው ሲርቅ ሞራሉም መንፈሱም ይጎዳል፡፡ እኛ ግን እየቆጠቡና እየተበደሩ ዘመናዊ አኗኗር እንዲኖሩ፣ ግቢያቸው ውስጥ ባለ ቦታ ላይ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ፣ ኑሯቸው እንዲለወጥ ማድረግ ችለናል፡፡
ይህ እንግዲህ የራሴን ህይወት ከመለወጥ አልፌ የአካባቢዬን ህዝብ መለወጥ ችያለሁ ማለት ነው፡፡ በዚህ ደስ ይለኛል፡፡ ሌላው እዚህ ከተማ ውስጥ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ከ2 ሺህ በላይ ሜትር ታክሲዎች ከአዋጭ ተበድረው ገዝተው እየሰሩ የሚገኙ ናቸው፡፡ ራይድ የምትጠቀሚ ከሆነ አብዛኞቹ ከአዋጭ ተበድረው ገዝተው እየሰሩ መሆናቸውን ይነግሩሻል፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር እንግዲህ መነሻው ችግር ነው፤ ህብረት ሥራ የሚመሰረተው ከችግር ነው፡፡
ችግር ነው ፈጠራን (ኢኖቬሽንን) የሚያመጣው ይባል የለ?
አዎ ትክክል ነው፡፡ በተናጠል ልንወጣ ያልቻልነውን ችግር በመተባበር በአሁኑ ቋንቋ በመደመር እንዴት እንፍታው ነው ጉዳዩ። በነገራችን ላይ እኔ “መደመር” መፅሐፍን ካነበብኩ በኋላ ለእኔ አዲስ አይደለም ነው ያልኩት፡፡ ምክንያቱም ህብረት ሥራ የሰዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ከ15 ዓመት በፊት ተግብረነው ውጤታማ ሆነናል፡፡ እውቀትንና አቅምን አስተባብረን ነው ችግርን የፈታነው፡፡ አሁን ላይ አዋጭ ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ ትልቅ ኮኦፕሬቲቭ ነው፡፡
ቀድሞ ቅያሬ ጫማ አልነበረዎትም፣ ትዳር መስርተው ለሁለት ዓመት ቴሌቪዥን መግዛት አልቻሉም ነበር፣ ስለ ቁጠባና ብድር ለሰዎች ግንዛቤና እውቀት ለመስጠት ከቦታ ቦታ በእግርዎ በጠራራ ፀሀይ ይጓዙ ነበር፣ ይሄ ሁሉ አልፎ አሁን ያለውን ስኬት ሲመለከቱት ምን ይሰማዎታል?
አሁን በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡ ምክንያቱም ይሄ ቢዝነስ ሳይሆን አገልግሎት ነው፡፡ እናም ደግሞ እኔ ሰዎችን አስተባብሬ በእኔ ምክንያት ይሄ ሁሉ አባል ማለትም ከ75 ሺህ ሰው በላይ አባላት ማፍራትና ከ 3 ቢ. ብር በላይ ቁጠባ ማሰባሰብ ቀላል አይደለም፡፡  ከመንግስትም ሆነ ከሌላ ወገን 10 ብር  ሳትወስጂ፣ ህዝብን አስተባብረሽ ይህን ያህል ቁጠባ በማሰባሰብ ረገድ በኢትዮጵያ አዋጭን የሚያህል የለም፡፡ በዚህም  በእጅጉ ደስ ይለኛል፡፡ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡
ለመሆኑ "አዋጭ" የሚለውን ስያሜ ከየት አመጣችሁት ?
 ምን መሰለሽ… እኛ ተሰብስብን ያመጣሁትን ሀሳብ ሳቀርብላቸው ከመካከላችን አንድ ትልቅ ሰውዬ ነበሩ፡፡ እናም ሀሳቡን ሳቀርብ “ይሄማ አዋጭ ሀሳብ ነው” አሉ፡፡ በዚያው “አዋጭ” እንበለው ተባለና ጸደቀ፡፡ ስያሜውን ያገኘው ከአባላት በአንዱ ሰው ነው ማለቴ ነው፤ ሀሳቡ ያዋጣል ለማለት ነው። እውነትም አዋጥቶናል። ከድህነት ወጥተንበታል፡፡ እኔ አዋጭ ባይኖር አሁን የምታይኝ ዘሪሁንን አልሆንም ነበር። እንኳን ቤት ሊኖረን፣ እንኳን መኪና ሊኖረን፣ እንኳ ይህንን ሁሉ ሰው ለመቀየር ልንበቃ ቀርቶ ምስኪኖች ነበር የምንሆነው፡፡ አሁንኮ  አዋጭ 211 ቅጥር ሰራተኞችን ይዟል፡፡ ይህን ሁሉ ሰራተኛ መቅጠር ብቻ አይደለም፤ ጥሩ ደመወዝ ከፋዮችም ነን፡፡ በዓመት 36 ሚ. ብር ለሰራተኛ ደሞዝ  እንከፍላለን። በወር እስከ 50 እና 60 ሺህ ብር ደመወዝ የምንከፍላቸው ሰራተኞች አሉን፡፡ ይህ ማለት በዓመት ከ7-8 ሚ. ብር የስራ ግብር ለመንግስት እንከፍላለን። ከገቢ ግብር ግን ነፃ ነን። በሌላ በኩል ጥሩ ዲቪደንድም እንከፍላለን። ባለፈው ለአባላት በሼር 30 በመቶ የትርፍ ክፍያ ከፍለናል፡፡ በዓመት እስከ 600 ሺህ ብር ትርፍ ያገኘ አለ። ባለፈው የበጀት ዓመትም 102 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝተናል። ስለዚህ ለእያንዳንዱ አባል  በአንድ ሼር 30 ፐርሰንት ከፍለናል፡፡ ይሔ ማለት አንዳንድ ባንኮች ከሚከፍሉት ትርፍም የተሻለ ያደርገናል ማለት ነው፡፡ በዚህና በመሰል ስኬቶች ጉዞውን የቀጠለው አዋጭ፤ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ነው፡፡ የእኛ ከሌላው የሚለየው ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ ነው። እንግዲህ ህብረት ስራ ማህበር በሀገራችን ከ50 ዓመት በፊት ነው የተመሰረተው፡፡ አብዛኞቹ ግን ተቋማትን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መንገዶች ባለስልጣን አለው፣ድሮ መብራት ሀይል የሚባለው  አለው፤ ቴሌ አለው፡፡ እነዚህ ሁሉ የክሬዲት ዩኒየን አላቸው፡፡ እነሱ ማለት ነን እኛ፡፡ ነገር ግን እኛ ማህበረሰብ አቀፍ ነን። ከዘር፣ ከፖለቲካ፣ ከሀይማኖት ወገንተኝነት የፀዳ፤ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በእኩል የሚያገለግል ኢትዮጵያዊ ተቋም ነው፤ አዋጭ፡፡
አንድ ሰው የክፍለ ሀገር መታወቂያ ኖሮት አዲስ አበባ ውስጥ ሼር መግዛት፣ አባል መሆንና የብድር አገልግሎት ማግኘት ይችላል?
በፊት የስራ ክልላችን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ነበር፡፡ አሁን ግን በሀዋሳም፣ በአዳማም፣ በቢሾፍቱም፣ በጫንጮም ከፍተናል። በቅርቡም በባህርዳርና አምቦ እንከፍታለን፡፡ በቀጣይ ደግሞ በደብረ ብርሃን፣ በጅማ፣ በወሊሶ፣ በቤንች ማጂና በሌሎችም ከተሞች እንከፍታለን፡፡ የአቅም ውስንነት ካልያዘን በስተቀር  በሁሉም ክልሎች የህዝብ ጥያቄና ፍላጎት እስካለ ድረስ እንከፍታለን። ይህም ሰው በየአካባቢው አገልግሎቱን እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አንድ ሰው የየትኛውም ክልል መታወቂያ ይኑረው፣ነዋሪነቱ አዲስ አበባ ከሆነ የአዋጭ አባል መሆን ይችላል፡፡ አሁን የስራ ክልላችን በመላው ኢትዮጵያ ስለሆነ፣ የግድ የአዲስ አበባ መታወቂያ አንጠይቅም፡፡
የ15ኛ ዓመት የምስረታ በዓላችሁን አስመልክታችሁ በሰጣችሁት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አዋጭ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ በተመሳሳይ ተቋማትና  ማህበራት ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ስለመሆኑና በአፍሪካ የህብረት ስራ ማህበራት ህብረትም ላይም የሀላፊነት ተሳትፎ እንዳላችሁ ጠቁማችሁ ነበር፡፡ እስኪ በዚህ ላይ ማብራሪያ  ይስጡን፡፡ አይያዘውም በዚህ የህብረት ስራ ማህበር በኩል የሌላው ዓለም ተሞክሮ ምን ይመስላል የሚለውን በመጠኑ ያስቃኙን…?
እንዳልሽው አዋጭ ከኢትዮጵያም አልፎ “አኮስካ” በሚባለው ተባባሪ አባል ነን፡፡ አሁን ደግሞ በኢንተርናሽናል ኮኦፕሬቲቭ አፍሪካ፣ የአፍሪካ የቦርድ አባል ሆነናል፡፡ ምክንያቱም አዋጭ የኢንተርናሽል ኮኦፕሬቲቭ አሊያንስ (የአለም አቀፍ የህብረት ሥራ ቃልኪዳን)  አባልም ነን፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር አባል አልነበረችም፤ እኛም ቁጭት ነበረን። እኛ የመጀመሪያዎቹ  አባል ሆነናል፡፡ ይህ ድርጅት ከ100 በላይ አገራትን በአባልነት የያዘ ነው፡፡ አሁን ላይ እነ ኦሮሚያ ህብረት  ሥራ ባንክና ኦሮሚያ  ኮፊ ዩኒን አባል ሆነዋል፡፡ የአፍሪካው ደግሞ የቦርድ አባል ሆነናል። ይህን የቦርድ አባልነት ያገኘነው በትልቅ ድምጽ ተመርጠን ነው፡፤ እንደ ሀገርም ኮኦፕሬቲቭን እያስጠራን ነው ማለት ነው፡፡
ስለ ሌላው ዓለም ተሞክሮና የእኛ አገር በዘርፉ ስላለችበት ደረጃ ወዳነሳሽው ጥያቄ ስመለስ፣ እኔ ለምሳሌ በነበረኝ አጋጣሚ ለትምህርት ወደ ውጪ ሄጄ በነበረበት ወቅት ኔዘርላንድ ውስጥ የተለያዩ ኮኦፕሬቲቮችን አይቻለሁ፡፡ በተለይ “ራቦ ባንክ” የተሰኘው ባንክ ልክ እንደ አዋጭ ሆኖ ከ80 ዓመት በፊት ህብረት ሥራ ማህበር ሆኖ የተመሰረተ ነበር። አሁን በጣም ግዙፍ ባንክ ሲሆን በመላው ዓለም በ60 ሃገራት ላይ ይሰራል። እጅግ ትልቅ ባንክ ነው፡፡ እኛም ነገ አዋጭን ወደ ትልቅ ባንክ መቀየር ሳይሆን፣ ራሱን የቻለ ባንክ እንመሰርታለን። እንደሚታወቀው በ300 ሚ. ብር አዋጭ ኢንሹራንስን መስርተናል። ቀደም ስንል በውስጥ ኢንሹራንስ ነበረን፡፡ ለምሳሌ ተበዳሪ ሲሞትብን ቤቱን ወይም ንብረቱን አንይዝም፤ የቆጠበውንም ጭምር ለቤተሰቡ ነው የምንሰጠው፡፡ በኮቪድ ጊዜ ለምሳሌ ወደ 24 ተበዳሪ አባላት ሞተውብናል። አንድ ሰው 400 ሺህ ብር ለመበደር 100 ሺህ ብር መቆጠብ አለበት። ያ ሰው ሲሞት ሙሉ በሙሉ እዳውን ሰርዘን የቆጠበውን 100 ሺህ ብር ለቤተሰቡ እንሰጣለን። እንዲህ የሚያደርግ ተቋም የለም። እዳ ይሰረዛል። የቆጠበው ለቤተሰቡ ይሰጣል። ቤተሰቡም ትንሽ እፎይታ ያገኛል። በህይወት ያለ ሰው ነው የሚጠየቀው። ለምን መሰለሽ… ተበድሬ ብሞት ለቤተሰብ እዳ አወርሳለሁ እያለ፣ መበደር እየፈራ ህይወቱ ሳይሻሻል ይቀራል። ሰው ብድርን መፍራት የለበትም። የሆነ ሆኖ ከብሄራዊ ባንክ በተሰጠን ፈቃድ ሁሉንም አይነት ኢንሹራንስ የሚያካትት አዋጭ ኢንሹራንስን መስርተናል። ሼሩን ለአባላቶቻችን ሸጠን እንደገና ሌላ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን አመቻችተንላቸዋል። እዚህ ጋ ኢንሹራንስ አላቸው፤ የትርፍ ተካፋይም ናቸው።
አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበርን ወደ ባንክ የማትቀይሩበትና አዲስ ባንክ ለብቻው ለመክፈት የፈለጋችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?
በጣም ጥሩ! ብዙዎቹም አዋጭ ባንክ ይሆናል ወይ ብለው ይጠይቁናል። ኮኦፕሬቲቩን ወደ ባንክ አንቀይረውም። ምክንያቱም እኛ የባንክ አገልግሎት ለማይጠቀመው - unbankable - ለሆነው ማህበረሰብ ነው የፈጠርነው። ባንክ ከሆነ አላማውን ይስታል፡፡ ይሄ ህብረት ሥራ ማህበር ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ አገልግሎት እንጂ ቢዝነስ አይደለም። ስለዚህ ይሄ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ወደ ባንክ አይቀየርም።
ነገር ግን ከእኛ  ተበድረው ያደጉ ሰዎች አዋጭ ከሚሰጠው ብድር በእጅጉ ያደገ ብድር ይፈልጋሉ። እኔ ለምሳሌ ከአዋጭ ገንዘብ ቁጠባና ብድር ተበድሬ ተበድሬ አቅሜን ጨርሻለሁ። ከፍ ያለ ብድር ያስፈልገኛል። ለምሳሌ እኛ አሁን የምናበድረው ትልቁ  ብር 2 ሚሊዮን ነው። እኔ የምፈልገው 10 ሚሊዮን ብር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አዲሱ ባንክ ይህን ብድር ይሰጠኛል። አዋጭ ውስጥ እየተበደሩ አድገው ትልልቅ ብድር ለሚፈልጉ አዲስ በምንመሰርተው ባንክ ብድር እናመቻችላቸዋለን ማለት ነው። እንዲህ እንዲህ እያልን የአንዱን ተቋም ሚና  በአንዱ ሳናጠፋ ራሳቸውን ችለው እንደየ ባህሪያቸው እንዲሄዱ ነው የምናደርገው። አሁን አንዳንዶቹ ወደ ባንክ አደጉ ሲባል ብዙም ስሜት አይሰጠኝም። ምክንያቱም እታች ላለው ሰው የሚሰጡትን አገልግሎት አቋርጠውና ዓላማውን ቀይረው ነው ባንክ የሚሆኑት የሚል እምነት አለኝ።
አዋጭ የገንዘብ ብድርና ቁጠባን የመሰረቱ ናቸው አዋጭ ኢንሹራንስንም የመሰረቱት። ሼር የሚገዙትም የአዋጭ ገንዘብ ቁጠባና ብድር አባላት ናቸው። እነዚህ አባላት በአዋጭ ፋውንዴሽንም ውስጥ ተሳትፎ አላቸው፡፡ አዋጭ ባንክ ሲመሰረትም መስራቾቹ ይሆናሉ። አክሲዮን በቅድሚያ የሚገዙትም እነዚሁ አባላት ናቸው። ይሄ የሆነ የተሳሰረ የአንድ ቤተሰብ አባል የሚያስመስል ሂደት አለው። እስኪ በዚህ ላይ ትንሽ እንቆይ…
ታንክ ዩ! ጥሩ ሀሳብ ነው ያነሳሽው። ትልቁ ህብረት ሥራ የሚመሰረተው ችግርን ለመፍታት እንጂ ችግርን ለማምጣት አይደለም። ቅድም ተበዳሪ ሲሞት እዳው ሙሉ ለሙሉ ተሰርዞ የቆጠበው ለቤተሰብ የሚሰጠውም ለዚህ ነው። ለምሳሌ ዕድር ስናቋቁም የሞተን ሰው ለመቅበር ነው አላማው። የቤተሰብ ማህበርም ሲመሰረት በደስታ በሃዘን  ጊዜ ለመደጋገፍ ነው። እኔም አዋጭን ስመሰርት ትርፍ ለማግኘት ወይም ለራሴ እንዲህ አድርጌ እጠቀማለሁ የሚል ስሌት ውስጥ ገብቼ አይደለም። እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸውን ሰዎች አሰባስቤ፣ ይህን የጋራ ችግር በጋራ ለመፍታት ነው። ሰው እስከሰራ ድረስ የተበደረውን መክፈል ይችላል። “አይ ስሞት እዳ ለቤተሰብ አላወርስም” ብሎ እንዳይፈራ፣ ሲበደር 1 ፐርሰንት ለኢንሹራንስ እየተቆረጠ ይቀመጣል። ከሞተ ዕዳውን ሰርዘን ያስቀመጠውን ለቤተሰቡ ስንሰጥለት ደስተኛ ይሆናል። እንዳልሽው ከስር ተነስተን አብረን አድገናል። ሁላችንም ተሰብስበን የምንሰራው የሚጠቅመንን ነው። ወለዳችንም በጣም አነስተኛ ነው። እንደፈለግን አንጭንም። መክፈል ይችላል ወይ የሚለውን ከግምት እናስገባለን፡፡ ወጪያችንን ከሸፈነ፣ የቢሮ ኪራይና የሰራተኛ ደሞዝ ከቻለ ሌላ ብዙ መታሰብ የለበትም። ተቋሙ እንዲቀጥል ትንሽ ትርፍ ብቻ ነው የምንጠብቀው።  ይህ ሲሆን አባላት በሙሉ በአንድ ገበታ እንደሚበላ አንድ ቤተሰብ ናቸው። ከህብረት ስራ ማህበሩ ወደ ኢንሹራንሱ፣ ከኢንሹራሱ ደግሞ ወደ ባንኩ እያደጉ፣ ኢኮኖሚያቸው እያደገ፣ የስራ ዕድል እየፈጠሩ፣ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚቀጥሉ ቤተሰቦች ናቸው፤ የአዋጭ አባላት። ይህ እንዲፈጠር ቅንነትና ታማኝነት ያስፈልጋል። ፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ይጠይቃል። እነዚህን ነገሮች ይዘን ነው ለእድገትና ለለውጥ የበቃነው። የፈለገ እውቀት፣ የፈለገ ልፋት ቢፈስ ቅንነት፣ ታማኝነትና ጨዋነት ካልታከለበት የትኛውም ስራ ውጤት አይኖረውም። እኛ በጨዋነት ያደግን ነን። ስልጣኔው ብዙ ነገራችንን እየቀማን ነው። አሁን ሌብነት እንደ ስልጣኔ እየታየ ነው፤ ይገርመኛል። የሆነ ሆኖ ወደ ቀደመ መተዛዘናችን መተባበራችን፤ ወደ ጨዋነትና ታማኝነታችን ካልመጣን እንጠፋለን። እኔ የሰራሁት ለሌላውም መትረፍ፤ ተጋግዞ ተደጋግፎ ችግርን መፍታት የጥንት አያቶች አባትና እናት ሲሰሩት የኖሩት ነገር እንጂ አዲስ አይደለም። “እናትህን በምን ትክሳታለህ?” ብትይኝ እሷ እንድሆንላት ባሳደገችኝ መንገድ መሄዴ ነው፤ ይሄ ነው እሷን የሚክሳት፡፡ “ልጄ ሌባ ነው ተብሎ ከሚመጣ ሬሳው ይምጣ” የምትል ቆራጥና ጀግና እናት ናት ያሳደገችኝ። ሌብነት ውሸት ጸያፍ ነው ትለን ነበር፤ ቃል በቃል፡፡ ስለዚህ  እነዚህን ጸያፍ ነገሮች ተጸይፌ ነው የኖርኩት። ወደፊትም የምቀጥለው እንደዚሁ ነው።
ወደ ሪል እስቴት የመግባት ሀሳብ እንዳለዎት ሰምቼ ነበር…
ገብቻለሁ። “ዘሚ” ፒኤልሲ የሚባል ሪል እስቴት አለኝ። አንዱ የሀገራችን ችግር ቤት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው አልሚዎችን 70/30 አድርጋችሁ 30ውን ለማህበረሰቡ ስጡ ብለው ነበር። እኔ ደግሞ ሌላ ሀሳብ አመጣሁ፤ 30/30 አድርጌ አርባውን ለፐብሊኩ ለምን አልሰጥም የሚል።
እስኪ ያብራሩልን?
ለምሳሌ 1 ሺህ ቤት ብገነባ 30ው ለአዋጭ አባላት፣ 30ው ለመንግስት፣ 40ው ደግሞ ለዘሚ ይሆንና በዚያ ሽያጭ ወጪውን ይሸፍናል። መንግስትም መሬት ያቀርባል ማለት ነው። ይሄ ትልቅ ስትራቴጂ ነው። ምክንያቱም በመንግስት በኩል ያሉት ቤት ያገኛሉ። አዋጭ ፋይናንስ ያደርጋል። ዘሚ ሪል እስቴት ይገነባል ማለት ነው። ለምሳሌ የአዋጭ አባላት የረጅም ጊዜ ብድር ይሰጣቸውና የቤት ባለቤት ይሆናሉ። ይህንን ስትራቴጂ ለመንግስት ለማቅረብ መንገዶችን እየፈለግን፣ እኛም እንደ ሙከራ ፕሮጀክት ባለ 13 ፎቅ ህንጻ እየገነባን ነው፤ ሀያት አካባቢ ነው። 10ኛ ፎቅ ላይ ደርሰናል። አዋጭ ደግሞ የገንዘብ ሀብት ብቻ አይደለም ያለው፤ ከፍተኛ የሰው ሃብትም አለው። ብዙ ኢንጂነሮች አርክቴክቶች አሰባስቤና ዕውቀትና ሃብትን አጣምሬ ነው እየሰራሁ ያለሁት፡፡ መንግስትም ይህንን ጉዳይ ቢያስብበት ይጠቀማል ብዬ አምናለሁ። ዕድሉን ከሰጡንና ለ1ሺህ ቤት መስሪያ ቦታ ከሰጡን ቃላችንን ጠብቀን መስራት እንችላለን። ምክንያቱም እኛ ፋይናንስ አለን። ባንክ ብቻ ብታይም ዲፖዚት ያስቀመጥነው ከ700 ሚ. ብር በላይ አለን። መንግስት መሬት አለው። ይህን አቀናጅተን ብንሰራ በቤት እጦት የሚሰቃየውን ህዝብ እንታደገዋለን። ይህን በ5  ዓመት ጊዜ ገደብ በየዓመቱ 700 ሚ. ብር ባስቀምጥ፣ በ5 ዓመት ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ይኖራል ማለት ነው። እና ይህን ብር በባንክ አስቀምጠን ዲፕሪሼት እንዲያደርግ ሳይሆን ወደ ካፒታል እንዲቀየር እንፈልጋለን። እኛ በአዋጭ ኢንሹራንስ፣ በፋውንዴሽኑ ሰርተን አሳይተናል። አያቅተንም። እኛ ለአባላት ቤት መስራት እንፈልጋለን። ይህን የሚገነባ ታማኝ ተቋም ያስፈልጋል ብዬ ነው ዘሚን የመሰረትኩት። ዘሚ ቤት ይገነባል፣ አዋጭ ፋይናንስ ያደርጋል። መንግስት መሬት ያቀርባል። ይሄ ትልቅ አጋጣሚ ነው። ችግሩ ምን መሰለሽ? ሀሳብ ያላቸው ሰዎችና ባለስልጣናቱ አይገናኙም፤ ድልድዩም የለም። ለምሳሌ እኔ አዋጭን መስርቻለሁ። ለብዙዎች የስራ እድል ፈጥረናል፣ ማህበራዊ ሃላፊነታችንን እየተወጣን ነው፣ ወደ ኢንሹራንስ ገብተናል። ቀስ በቀስ ባንክ እንመሰርታለን፤ ግን ፋይናንስ እያለን በኪራይ ቢሮ ነው የምንኖረው። 1 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ለቢሮ ግንባታ ከጠየቅን ረጅም ጊዜ ሆኖናል፡፡ እስካሁን ምንም መልስ የለም፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ቅር ያሰኙኛል። በተረፈ በስራዬ፣ እኔን አምነው ተሰብስበው አዋጭን እዚህ ባደረሱ አባላት፣ በቢሮው ሰራተኞችና በአጠቃላይ በአዋጭ ስኬት ደስተኛ ነኝ። 15ኛ ዓመታችንንም ዘንድሮ ያከበርነው እጅግ በስኬት ታጅበን ነው። ለዚህ ሁሉ ፈጣሪ ይመስገን። ወደፊትም እንቀጥላለን።

Read 2287 times