Print this page
Saturday, 18 June 2022 17:45

ይድረስ ለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

ክፍል 3:-

መፍትሄው ሚድሮክን የሚመራ ቦርድ ማቋቋም ነው

              ውድ አንባብያን! ባለፉት ሁለት ሳምንታት በወጡት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ እትሞች ላይ በዚሁ ርእስ ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለት ጽሑፎች ለህትመት መብቃታቸው ይታወቃል። ለማስታወስ ያህል፤ ሳምንት በቀረበው ክፍል 2 በአቶ ጀማል ዘመን የተከናወኑ በጎ ጅምሮችን በማውሳት፤ መስዋእትነት ከፍለው ሚድሮክን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ በርካታ በከፍተኛና በመካከለኛ አደረጃ የሚገኙ የማኔጅመንት አባላት እና የበታች ሰራተኞች ላይ የደረሰውን በደል የሚያስገነዝብ ነበር፡፡
በዚህ በዛሬው በክፍል ሦስት ጽሁፍ በኢንቨስትመንቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት አለፍ አለፍ እያልን እናያለን፡፡ አሁን በአቶ ጀማል አህመድ ፊት አውራሪነት የሚመራው የሚድሮክ ሊደርሺፕ ጉዳት እያደረሰ ያለው በእኔና በሰራተኞች ላይ ብቻ አይደለም። የሚድሮክ ኢንቨስትመንትም እየተጎዳ ነው። አሁን ያለው የሚድሮክ አመራር እየወሰዳቸው ባለው የተሳሳቱ ግብታዊ እርምጃዎች ምክንያት በሚድሮክ ኩባንያዎች ላይ ጥፋት እየደረሰ በመሆኑ ይህንን በተመለከተ ህዝብም፣ መንግስትም፣ ባለ ሃብቱም ማወቅ አለባቸው ብየ ያሰባሰብኳቸውን መረጃዎች ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
በመጨረሻም፤ እንደ እኔ ያለ ለረጅም ዓመታት በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ባሉ ኩባንያዎችና በኮርፖሬት ሊደርሺፕ ደረጃ ጭምር የሰራ ሰው፣ ልዩ ልዩ ችግሮችን በመዘርዘር ብቻ ጽሁፉን ሊደመድም አይገባውም፡፡ በመሆኑም፤ ሚድሮክን እግር ተወርች ቀፍድደው የያዙት ዋና ዋና ችግሮች ምን ምን ናቸው? መፍትሄው ምንድነው? ክቡር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ የሚድሮክ ሊቀ መንበር እንደመሆንዎ (እንደ የበላይ አመራርነትዎ) እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ በእርስዎ በባለሃብቱ በኩል ምን ምን እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል?... ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ጽሁፌን እቋጫለሁ፡፡
ወደ ዛሬው ጽሁፌ ከማለፌ በፊት አንድ ነገር ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ ያለፉትን ሁለት ክፍል ጽሁፎች ያነበቡ አንዳንድ የሚድሮክ ሰራተኞች ከሰጡኝ አስተያየት ልጀምር፡፡ “አሁን ያነሳኸው በኩባንያ ደረጃ ያለ አግባብ የተባረሩ የማኔጅመንት አባላትን ነው፡፡ ነገር ግን በኮርፖሬት ደረጃ በአቶ ጀማል ቢሮ ይሰሩ የነበሩ በርካታዎችም ተባረዋል፡፡ ስለእነርሱም ብታካትት ጽሁፍህን የተሟላ ያደርገዋል” የሚል አስተያየት ደርሶኛል፡፡
ልክ ነው በኮርፖሬት ደረጃ በአቶ ጀማል ስሜታዊ፣ ይግባኝ የሌለው ውሳኔ የተባረሩ ሰዎች አሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት የንግድና አገልግሎት (የኮሜርስን) ዘርፍ እንዲመሩ በሼህ ሙሐመድ በራሳቸው ፊርማ ተሹመው የነበሩት ዶክተር በቀለ ቡላዶ ናቸው፡፡ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ ሰፊ ልምድ ያላቸው፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩ ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ ከዶ/ር በቀለ ጋር በቅርበት ሰርቻለሁ፡፡ በተለይም የኢንቨስትመንት ግሩፑን (የ35ቱን ኩባንያዎች) የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ፕላን በማዘጋጀቱ ሂደት የኮሚቴው ሰብሳቢ ስለነበሩ ከዶ/ር በቀለ ጋር በቅርበት ሰርቻለሁ፡፡ እርሳቸው በሌሉ ጊዜ እርሳቸውን ተክቼ ኮሚቴውን እንድመራ ውክልና ሰጥተውኝ ሰርተው አሰርተውኛል፡፡ ከእርሳቸው ጋር በመስራቴ ብዙ እውቀት ቀስሜያለሁ፡፡
ዶ/ር በቀለ የኮሜርስን ዘርፍ በመሩበት ወቅት በርካታ ለውጦችን አምጥተዋል፡፡ በተለይም ፈዞና ደንዝዞ የነበረውን ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት፤ ከተኛበት ቀስቅሰው፣ “ኩዊንስ እንደ ቤተሰብ…” የሚለውን ሞቶ አስይዘው፤ እንዲነቃነቅ ያደረጉት እርሳቸው ናቸው፡፡ 6 ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኩዊንስ በአዲስ አበባ 8 ቅርንጫፎችን በተጠኑ ቦታዎች እንዲከፍት አድርገዋል፡፡ በቀጣይም በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች ሁለት ሁለት የኩዊንስ ቅርንጫፎችን የመክፈትና በአጠቃላይ በአምስት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ 28 ቅርንጫፎችን ለመክፈት ሃሳብ ነበራቸው። ይህንንም በረቂቅ የስትራቴጂክ እቅዱ ውስጥ እንዲካተት አድርገዋል፡፡
በኪሳራ የሚታወቀው “TNA” የተባለ በአየር ትራንስፖርት የስራ መስክ የተሰማራ ኩባንያ ራሱን ከመቻል አልፎ አትራፊ እንዲሆን ጥረት አድርገዋል - ዶ/ር በቀለ፡፡ ሌሎችንም በርካታ ስራዎች ሰርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ አንዲት ትንሽ እንከን ባየ ቁጥር ሰውን በማባረር የተለከፈውና ሰራተኛን ማባረር መፍትሄ የሚመስለው አቶ ጀማል፤ ዶ/ር በቀለን ከነበሩበት ትልቅ ኃላፊነታቸው ለምኖና አስለምኖ ካመጣቸው በኋላ፤ ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ በሁለት መስመር ደብዳቤ (ውል የተዋዋለ ይመስል) “ውልህ ተቋርጧል” ብሎ አሰናበታቸው፡፡ በዚያው በኮርፖሬት ኦፊስ ተመድበው የነበሩት እነ ወ/ሮ ጥሩ ጣሹ፣ ጎልማሳው ኢንጅነር ዮሴፍ አጽብሃና የመሳሰሉት ድንቅ ባለሙያዎች ተገፍተው እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ ኃጢያታቸው ሌላ ሳይሆን ከዶ/ር አረጋ ይርዳው ጋር የሰሩ መሆናቸው ነው፡፡ ወደ ዛሬው የጽሁፌ ጭብጥ እናምራ…
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ላይ የደረሰ ጉዳት
ክቡር ሆይ!
ጽሁፌን የምጀምረው በአንድ እድሜ ጠገብ ተረት ነው፡፡ … በዱሮ ጊዜ፣ በአንድ የኢትዮጵያ አካባቢ አንድ የግራዝማች ማእረግ ያላቸው የመሬት ከበርቴ ነበሩ አሉ፡፡ ግራዝማች በርካታ በጎችና ፍየሎች ነበሯቸው፡፡ እነዚያንም በጎችና ፍየሎች የሚጠብቅ አንድ ጎበዝ እረኛ ነበራቸው። ግራዝማች የእረኛውን ጉብዝና አይተው አንድ ግልገል ይሰጡታል፡፡ ጎበዙ እረኛ በሽልማቱ ተደስቶ ጥበቃውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ግልገሏም ታድጋለች፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን በእረኛው አጠገብ የሚያልፍ አንድ ሰው፤ “እነዚህ በጎችና ፍየሎች የማን ናቸው?” ብሎ እረኛውን ይጠይቀዋል፡፡ እረኛውም ዘና ብሎ፣ በኩራት መንፈስ “የእኔና የግራዝማች ናቸው” አለው ይባላል፡፡ ይህንን አባባል ለምን እንዳነሳሁት ወደ ኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡ በቅድሚያ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ላይ የታዩ ጉድለቶችን እንይ…
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ላይ በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ ችግሮቹ በቶሎ ካልተፈቱ ያንዣበቡ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ከፍተኛ ስጋት አድሮብኛል፡፡ ስጋቴን ያባባሰው የሚድሮክን ሚስጥሮች የሚያውቁ “Memory of MIDROC” ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች ከየኩባንያው መባረራቸው ነው፡፡ ነባር ሰራተኞች ሲባረሩ ተገቢው የርክክብ ስርዓት ስለማይፈጸም የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይነት እንዳይኖራቸውና የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዳይሰፍን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ለረጅም ጊዜ በፍርድ ቤት እየተንከባለሉ ያሉ ጉዳዮች በክትትል ማነስ ፋይላቸው ሊዘጋ ይችላል። በመንግስት መስሪያ ቤቶች በእንጥልጥል ላይ ያሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ባለቤት አጥተው ይሰናከላሉ፡፡ የሀብት ኢንቬንተሪ ስላልተደረገ በየሽርንቁላው ያሉ የሚድሮክ ሀብቶች አስታዋሽ አጥተው ባክነው ይቀራሉ፡፡ ይህንን አባባሌን በምሳሌዎች እያጣቀስኩ ላቅርበው፡፡
ቢሮክራሲው ቀጣይነት በማጣቱ በክትትል ማነስ በህገወጦች የተወረሩ የሚድሮክ መሬቶች በርካታ ናቸው፡፡ በሀዋሳ ከተማ መናኸሪያ ክፍለ ከተማ አላቲዮን ሆስፒታል አጠገብ የዋንዛ ፈርኒሺንግስ ኢንዱስትሪ ኃ. የተ. የግል ማህበር ይዞታ የሆነ 1,920 ካሬ ሜትር ካርታ ያለው መሬት በባለቤትነት መንፈስ የሚከታተል ሰው ባለመኖሩ በግለሰቦች ተወስዶ ዛሬ ህንጻ እየተገነባበት መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ይህንን መሬት እኔ ራሴ ስከታተለው የነበረ፣ አላለማችሁትም በሚል መንፈስ ጉዳዩ በከተማው ከንቲባ የሚታወቅ ነበር፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የኤልፎራ ይዞታና ንብረት ከነበረ ወደ 30 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ህገወጥ ካርታ ወጥቶበት በግለሰቦች ተወስዷል፡፡ ከአዳማ ከተማ ወደ ወንጂ በሚወስደው መንገድ ላይ ኩሪፍቱ የእንስሳት ማቆያ አጠገብ የነበረው “አብዱሶመድ” የተባለ እርሻ በወጣቶች ከተወሰደ 4 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን ጉዳዩ በአዳማ መዘጋጃ ቤት ክርክር ላይ ነበር፡፡
በኤልፎራ ስም ከመንግስት ላይ የተገዛው 8 ድርጅቶችን ከነይዞታቸውና ከ60 ሺህ ሄክታር መሬት ጋር ቢሆንም፤ ኩባንያው ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ እስከ አሁን ድረስ የተረከበው መሬት ግን ከ9 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ኤልፎራ በሶማሌ ክልል የገዛውን ይዞታ ማንም አይቶት አያውቅም። በአፋር ክልል በአሊደጌና በሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ መሬቶች በኤልፎራ እጅ አይደሉም። በጎንደር ከተማ አዘዞ አቅራቢያ ተመሳሳይ የመሬት ቅሚያ ተደርጓል፡፡ በሞጆ ከተማ ያለው የእንስሳት ማቆያ የነበረ መሬት በከተማው ማዘጋጃ ቤት ክርክር ተነስቶበት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ቆቃ በሚገኘው የጂቱ እርሻ ላይ ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ በቦረና ዞን፣ በሊበን ወረዳ በሚገኘው የሚድሮክ - ኤልፎራ ይዞታ በሆነው ካርታ ያለው 1,057 ሄክታር መሬት ላይ ሰዎች በህገወጥ መንገድ ገብተው የሰፈሩበት መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ (ይህ መሬት 4 ሺህ ሄክታር ነበር። 1,057 ሄክታር የቀረው 3 ሺህ ሄክታር መሬት በአካባቢው ህብረተሰብ በሰፈራ ተወስዶ ነው) ይህም ሊሆን የቻለው ጉዳዩን በባለቤትነት መንፈስ የሚከታተል፣ ጉዳዩን ጠንቅቆ የሚያውቅ ኃላፊ ባለመኖሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እነዚህ ሁሉ የመሬት ቅሚያዎች የተካሄዱት ጉዳዩን ይከታተሉ የነበሩ ሰዎች በመነሳታቸው ነው፡፡
ክቡር ሆይ!
ሌላው በኢንቨስትመንቱ ላይ የደረሰ ጉዳት ብዬ የማቀርበው ከአሰራር ግድፈት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም በሸገር ዳቦ፣ በሳዑዲ ስታርና ሌሎች ከግዢና ከጨረታ ጋር የተያያዙ ጥቅል ምሳሌዎችን አነሳለሁ፡፡ ከከሸፉ ፕሮጄክቶች ልጀምር፡፡
ትናንትን እያሰብን ሂሳብ እናወራርድ ከተባለ በአቶ ጀማል አመራር የከሸፉ ፕሮጄክቶች ብዙ ናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አቶ ጀማል ይመራቸው በነበሩ ፕሮጄክቶች በሚወስዳቸው ያልተጠኑና ከህግ አንጻር ያልታዩ እርምጃዎች ምክንያት አንዳንድ ፕሮጄክቶች ወይ መክነዋል አሊያም ቁሞ-ቀር ሆነዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ባክኗል፡፡
በርግጥ የሳዑዲ ስታር ፕሮጄክት በአቶ ጀማል የተጀመረ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ጀማል ፕሮጄክቱን ከተረከበ በኋላ ምን ምን እርምጃዎችን በመውሰድ ፕሮጄክቱን ለማዳን ሞከረ? የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ፣ ሰውን በማብቃት ማሰራት ሳይሆን ሰውን በማባረር ስራ የሰራ የሚመስለው አቶ ጀማል፤ ሳዑዲ ስታርን እንደተረከበ ከወሰዳቸው እርምጃዎች ቀዳሚው ተግባር ሰውን ማባረር ነበር፡፡ የፕሮጄክቱን እውነታዎች የሚያውቁ ሰዎች ሲባረሩ ደግሞ ስለ ፕሮጄክቱ ግንዛቤ በሌላቸው ሰዎች ህግና ስርዓትን ያልተከተሉ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው የሳዑዲ ስታር ፕሮጄክት የገጠመውን ውድቀት ለማካካስ ከቀረጥ ነፃ የገባን ትራክተርና ማሽነሪ በማከራየት ገቢ ለማግኘት የተወሰደው ህገወጥ እርምጃ ነው፡፡
ባለሙያዎች እንደነገሩኝ ከሆነ ጋምቤላ አካባቢ ያለን መሬት ማረስ የሚቻለው ከ120 - 150 የፈረስ ጉልበት ባለው ትራክተር ነው፡፡ ነገር ግን ለሳዑዲ ስታር እርሻ ያለ ምንም ጥናት 90 የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮችን የገዛው ማን ነው? እነዚህን ከቀረጥ ነፃ የገቡ የሳዑዲ ስታር ትራክተሮችንና መሽነሪዎችን ያለ አግባብ በማከራየት ገንዘብ በመሰብሰብ በገቢዎች ሚኒስቴር ተከሶ ድርጅቱን 248 ሚሊዮን ብር እዳ ውስጥ የከተተ ማን ነው? ይህንን ጉዳይ አሁንም የመንግስት ኃላፊዎችን በማሳሳት እንደገና ሌላ ስህተት ለመስራት የገንዘብ ሚኒስትሩ ቢሮ ጧት ማታ የሚመላለሰው ማን ነው? እንደዚያም ሆኖ ተሰርቶ ጋምቤላ ክልል በሚገኘው የሳዑዲ ስታር እርሻ ላይ በሺዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት ላይ የተዘራን ሩዝ ወፍ ያስበላው ማን ነው? ይህንን ሁሉ መዘበራረቅ የፈጠረ ሰው ተጨማሪ ኃላፊነት ሊሰጠው ይገባል?
የሸገር ዳቦን ፕሮጄክት ጉዳይ እናንሳ፡፡ የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የተወራለትንም ያህል ባይሆን ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ህብረተሰብ እየሰጠው ያለው አገልግሎት በበጎነት የሚወሳ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ፕሮጄክት በሸፍጥ የተሞላ፣ ለመክሸፍ የተቃረበ ፕሮጄክት ሆኖ ይታየኛል፡፡ በኃላፊነት ላይ በነበርኩበት ወቅት በቀን 1.5 ሚሊዮን ዳቦ ለማቅረብ ቃል በተገባው መሰረት ለህዝቡ ተገቢ አገልግሎት ባለመቅረቡ ከተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ይቀርቡልኝ ነበር፡፡ ጥያቄው ሲበዛ የዘርፉን ኃላፊ ጠየቅኳቸው፡፡ ኃላፊው ችግሮቹንም፣ እየተሰራ ያለውንም፣ በመንግስት ሊደረግ የሚገባውንም እገዛ፣ በዝርዝር ነገሩኝ፡፡
ሸገር ዳቦ ፋብሪካ በቀን 1.5 ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም እንዳለው ይታወቃል፡፡ ታዲያ በዚያ ወቅት (በየካቲት 2013 ዓ.ም) በቀን ያመርት የነበረው ከ750 – 800 ሺህ ዳቦ መሆኑንና እስከዚያን ጊዜ ድረስ ፋብሪካው ወደ 71 ሚሊዮን ብር ገደማ መክሰሩን የዘርፉ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ነግረውኛል፡፡ እኔም ይህንኑ ለጋዜጠኞች መረጃ ሰጠሁ፡፡ የኩባንያውን ችግሮችም አስረዳሁ፡፡ መንግስት ሊያደርግልን የሚገባውንም እገዛ ተናገርኩ፡፡ ያኔ ለFM 107.8 የሰጠሁት መረጃ አንዲት ውሸት አልነበረበትም፡፡ ኩባንያዬንም በአግባቡ ተከላክያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
መልእክቱ በሚዲያ ከተላለፈ በኋላ አቶ ጀማል ማሳሰቢያ የያዘ ደብዳቤ ጻፈልኝ፡፡ ኩባንያዬን ከአሉባልታ መከላከል ስራዬ ነው፡፡ አቶ ጀማል ሊቀጣኝ የሚገባው ይህንን ባላደርግ ነበር፡፡ ደብዳቤው ከተጻፈብኝ በኋላ አንድ ከእኔ ጋር ተመጣጣኝ ኃላፊነት ላይ ከሚሰራ ሰው ጋር ስናወራ “… ደብዳቤ ሊጻፍብህ አይገባም ነበር፡፡ ያልከው የ71 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እውነት ነው… ነገር ግን ይሄ ኪሳራ በሌላ መንገድ ተካክሶ አሁን 3 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው የቀረው፡፡ እሱም በቅርቡ ይካካሳል…” አለኝ፡፡
“በምንድነው የሚካካሰው?” አልኩት፡፡
“ከመንግስት የተወሰደው ስንዴ ከተፈጨ በኋላ ግማሹ ዱቄት ዳቦ ይጋገራል፤ ግማሹ ዱቄት ለሌሎች እየተሸጠ ኪሳራው ይካካሳል” አለኝ፡፡
ሸገር በቀን 1.5 ሚሊዮን ዳቦ ማምረት ሲገባው በወቅቱ ከ750 – 800 ሺህ ዳቦ ያመርት የነበረው ለካ ዱቄቱ ስለሚሸጥ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ዱቄት በመሸጥ ኪሳራን ለመሸፈን የተደረገው ስህተትን በስህተት የማረም መንገድ ተገቢ ነው? የአዲስ አበባ አስተዳደር ስንዴውን ከቀረጥ ነጻ ለሚድሮክ የሚሰጠው ህዝብ በዳቦው እንዲደጎም ነው እንጂ ዱቄቱ እንዲሸጥ ነው እንዴ?
ክቡር ሆይ!
እዚህ ላይ አንድ ነገር ለማለት እወዳለሁ። የተባረርኩት ስለ ሸገር ዳቦ በሰጠሁት መረጃ ምክንያት ከሆነ  እንኳንም ተባረርኩ! ይህ ለህዝብ ከምከፍለው መስዋእትነት በጣም በጣም ትንሹ ነው፡፡ ከህዝብ ጋር ሆኜ ደብዳቤ ጽፈው ያባረሩኝን ግለሰብ በታሪክ ፊት እፋረዳቸዋለሁ!
በቅርብ ጊዜ የተከሰተ ሌላ ስህተት እንይ። የሐዋሳውን የቺፕስ ፋብሪካ ጉዳይ እናንሳ። በሀዋሳ ከተማ የነበረው የቺፕውድ ፋብሪካ “ራሱን አልቻለም፤ አትራፊ አይደለም፣…” ተብሎ ሰራተኛው ተበትኖ ፋብሪካው “ለቆርቆሮ ያሌው” ተበትኖ ተሸጠ፡፡ ያንን ፋብሪካ “በቆርቆሮ ያሌው” ስም የማን ጓደኛ እንደገዛውና በዚህ ፋብሪካ ምትክ “የቺፕስ ፋብሪካ ተብሎ የተተከለው አሮጌ ማሽን ነው” የሚሉት በሰራተኛው የሚነሱ ቅሬታዎች መጣራት ይገባቸዋል፡፡
አሁን ደግሞ ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እናንሳ… የሰራተኛ መታከሚያ ሆስፒታል ያለ ጨረታ ውል መፈጸምን በተመለከተ በቅድሚያ የምናነሳው ጉዳይ ነው፡፡ በሀገሪቱ የአሰሪና ሰራተኛ ህግ መሰረት ሚድሮክ ሰራተኞቹ ሲታመሙ የማሳከም ግዴታ አለበት፡፡ በዚህም መሰረት በዶ/ር አረጋ ይመሩ በነበሩ 26 ኩባንያዎች ለሚሰሩ ሰራተኞች መታከሚያ ክሊኒክ በዚያው በሚድሮክ መቻሬ ሜዳ ጊቢ ውስጥ ተቋቁሞ ነበር። ክሊኒኩ በሰው ኃይልም ሆነ በቁሳቁስ የተሟላ፣ በሆስፒታል ደረጃ ሊታይ የሚችል፣ ሰራተኛው ምንም ዓይነት ውጣ ውረድ ሳይደርስበት ለመታከም የሚያስችለው ነበር፡፡ ይኸው ክሊኒክ ከሰላም ሆስፒታል ጋር ተቆራኝቶ የላቀ አገልግሎት መስጠት ጀምሮም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ አቶ ጀማል እነ ዶ/ር አረጋ የገነቡትን በጎ ነገር ሁሉ በማፍረስ አሻራቸውን የማጥፋት የጥፋት መንገድን የሚከተሉ በመሆናቸው ሰራተኛው በራሱ ክሊኒክ እንዳይታከም አድርገዋል። ሚድሮክ የራሱን ክሊኒክ ዘግቶ ሰራተኛው በአንድ “የግል ሆስፒታል” እንዲታከም መደረጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ይህ የግል ሆስፒታል ከሚድሮክ 100 ሺህ ገደማ ሰራተኞች ህክምና በዓመት እስከ 2 ቢሊዮን ብር ሊያገኝ እንደሚችል ይገመታል፡፡
እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ዋነኛ ጥያቄ፤ ለመሆኑ ይህ የግል ሆስፒታል የሚድሮክ ሰራተኞችን እንዲያክም የተመረጠው በምን መስፈርት ነው? ኮንትራቱ አስፈላጊው የግዢ ሂደት ተጠብቆ የተፈጸመ ነው ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች በጥብቅ መታየት ይገባቸዋል፡፡ አናቱ ላይ የተበላሸ አካል ወደ ግርጌው ሲወረድ ብልሽቱ የከፋ ሊሆን ስለሚችል የሚድሮክ የኦዲት ቢሮ ይህንን ጉዳይ ቢፈትሸው፤ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡ የሰራተኛው ተወካይ የሆኑት የሚድሮክ ኩባንያዎች ሰራተኛ ማህበራትም ሰራተኛው በከፊል የሚከፍልበት በመሆኑ የሰራተኛውን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ በጉዳዩ ላይ ክትትል ሊያደርጉ ይገባል፡፡
የሙስና ትንሽ የለውም፡፡ የሚድሮክ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሚስታቸው ወንድም ከውጪ ሀገር ስለመጣ “አማቻቸው” ወደ ሀገሩ እስኪመለስ ድረስ የሚድሮክን ሸግዬ መኪና መስጠት ሙስና አይደለም ያለው ማን ነው? በመኪናው ላይ ከፍ ያለ ብልሽት የደረሰበት እንደነበርና ለአንድ ጋራዥ በርከት ያለ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ መኪናው መጠገኑ ይነገራል። ለመሆኑ ለጥገናው የተደረገውን ወጪስ የሸፈነው ማን ነው? የሚለውም ጥያቄ መታየት አለበት፡፡
ቢሮክራሲያዊ አሰራርን አለማወቅ ሌላው የሚድሮክ አመራር ችግር ነው፡፡ ይህም በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ አለመስራት ያመጣው ጣጣ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አቶ ጀማል የተ/ሃይማኖት ሰፈር ልጅ መሆኑን ደጋግሞ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡ አዎ! በርግጥም አቶ ጀማል የተ/ሃይማኖት፣ “የበርበሬ ተራ ልጅ” ነው፡፡ ከነጋዴ ቤተሰብ የተገኘው አቶ ጀማል፤ በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ለአጭር ጊዜ እንኳ ቢሆን ባለመስራቱ ቢሮክራሲያዊ አሰራርን የተከተለ፣ አስተዳደራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ አመራር ለመስጠት የተቸገረ መሆኑን በቅርበት አስተውያለሁ።
በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ያለፈ ሰው በደብዳቤዎች ላይ እንዴት አመራር እንደሚሰጥ፣ ሰራተኞችን በማስተዳደር ሂደት የቅጣት አወሳሰን ሂደትና ደረጃዎች ምን ምን እንደሆኑ፣ የሰራተኛ እድገትና ዝውውርን፣ ወዘተ. በተመለከተ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ይኖረዋል፡፡ ህግ አይጥስም፡፡ የሚድሮክ አመራር ቢሮክራሲያዊ አሰራርን ባለማገናዘብ በሚወስዳቸው ስሜታዊ እርምጃዎች ከሰራተኛ ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት ከሶም ይሁን ተከሶ ያሸነፋቸው አጋጣሚዎች እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡
አቶ ጀማል በሲኢኦ ደረጃ ያለ ከፍተኛ አመራር ስብሰባ እንዴት እንደሚመራ እንኳ የጠራ ግንዛቤ የሌለው በመሆኑ ዮኒ ማኛን በሪፈረንስነት እየጠቀሰ ስብሰባ ሲመራ ብዙ ጊዜ የምገባበት አጥቼ ተሸማቅቄያለሁ። አፍሬያለሁ፡፡ አቶ ጀማል የቀረበለትን ማስታወሻም ይሁን ደብዳቤ ጊዜ ወስዶ፣ በአግባቡ አንብቦና ተገንዝቦ መምራት ወይም መልስ መስጠት አያውቅበትም፡፡ በአንድ ወቅት ለእርሱ ምክትሎች በአድራሻ የጻፍኩትን ደብዳቤ እንዲያውቀው ግልባጭ ስልክለት የሰጠኝ ምላሽ በአስቂኝነቱ እስከ አሁን አስታውሰዋለሁ፡፡ ያ ግልባጭ ደብዳቤ እንዲያውቀው የተላከ እንጂ ምንም ዓይነት ውሳኔ የሚሰጥበት አልነበረም፡፡ እርሱ ግን “እንደዚህ ዓይነት ደብዳቤ ለሲኢኦ አይቀርብም…” ብሎ መራልኝ፡፡ በመንግስት ቢሮክራሲ ያለፈ ሰው ከበታች የስራ ክፍል ግልባጭ የተደረገ ደብዳቤም ይሁን ማስታወሻ ምን ትርጉም እንዳለው ስለሚያውቅ በፋይል እንዲቀመጥ ያደርጋል ወይም የክትትል ውጤት ይጠይቃል እንጂ እንደዚያ ዓይነት አመራር አይሰጥም፡፡
ክቡር ሆይ!
በጽሁፌ መግቢያ አካባቢ የግራዝማችን እረኛ ታሪክ ጽፌ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ ማለቴ ይታወሳል፡፡ ይህንን እድሜ ጠገብ ተረት መሰል እውነት ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አንዳንድ የሼህ ሙሐመድ ንብረት ያልሆኑ ኩባንያዎች በሚድሮክ ግሩፕ ውስጥ መግባታቸው ይታያል፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ እንደ ግራዝማች እረኛ “የእኔና የሼሁ…” የሚል ነገር እንዳይፈጥርና ነገ በፍርድ ቤት መካሰስን እንዳያስከትል ስጋት ስላደረብኝ ነው ይህንን ባልቴት ተረት መጥቀስ የፈለግኩት፡፡
ቀደም ሲል እንዳልኩት አሁን ያለው የሚድሮክ አመራር የራሱን ኢምፓየር ለመገንባት በማሰብ ኔትዎርክ ዘርግቶ የራሱን ሰዎች እያሰባሰበ ነው፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ በዶ/ር አረጋ እና በአቶ አብነት ዘመን የተቀጠሩ ሰዎችን አንድ በአንድ በማባረር እነማንን እያሰባሰበ እንደሆነ በገሃድ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሜቴክ እና የስኳር ኮርፖሬሽን ሰራተኞች የነበሩ ሰዎች በቁጥር በዛ ብለው ሚድሮክ ውስጥ ተቀጥረዋል፡፡ በርግጥ ቀደም ሲል በሜቴክ እና በስኳር ኮርፖሬሽን ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ሚድሮክ ውስጥ መስራት የለባቸውም የሚል ገልቱ አመለካከት የለኝም፡፡ በብዛት መጥተው በየኩባንያው መሰግሰጋቸው ግን ቀደም ሲል የነበራቸውን ኔትዎርክ ላለመቀጠላቸው ዋስትና የለም፡፡ እናም በሜቴክ እና በስኳር ኮርፖሬሽን የነበረው በሽታ ወደ ሚድሮክ እንዳይዛመት የብዙዎች ስጋት ሆኗል። ለሚድሮክ ጤንነት ሲባል በቅርብ ጊዜ የተደረገው የሰራተኛ ቅጥርና ስምሪት በጥንቃቄ ቢፈተሽ መልካም ነው እላለሁ፡፡
ምን ይደረግ? - ምክረ ሃሳብ
ክቡር ሆይ!
እኔ እርስዎን ለመምከር አልሞክርም። እውቀትም ልምድም እድሜም ከእኔ በላይ አስተምሮዎታል። ይሁን እንጂ አንዳንድ የተዘነጉ ነገሮችን ማስታወስ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። እንግሊዞች “ሁሉንም እንቁላሎችህን በአንድ ቅርጫት ውስጥ አታስቀምጥ” የሚል አባባል አዘውትረው ይጠቀማሉ፡፡ ትክክለኛ አባባል ይመስለኛል፡፡  
ዛሬ ሚድሮክ የሚመራው በአንድ ሲኢኦ ነው፡፡ የሚድሮክ የመወሰን ስልጣን ተሰብስቦ ለዚህ ግለሰብ እንደተሰጠ ይታያል፡፡ ይህ ግለሰብ አለቃ ሊኖረው ይችላል፡፡ የሚቆጣጠረው አካል ግን የለውም። በዚህም ምክንያት ግለሰቡ የራሱን ኢምፓየር በመገንባት አምባገነን እንዲሆን እድል በማግኘቱ በማኔጅመንቱ ላይ ይግባኝ የሌለው ውሳኔ በማሳለፍ አምባ ገነንነቱን፣ ማን አለብኝ ባይነቱን፣ ከህግ በላይ ነኝ ባይነቱን… በይፋ፣ በአደባባይ እያሳየ ነው። ሚድሮክን የሚመራ አንድ ግለሰብ ብቻ መሾም ማለት እንቁላሎቹን በአንድ ቅርጫት ማስቀመጥ ሆኖ ነው የታየኝ። ይሄ ደግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና ብዬ አስባለሁ፡፡
እንደኔ እንደኔ፡- ስልጣን፣ እውቀት፣ ሀብትና ቁንጅና የሚሸከማቸውን አቅም ያለው ሰው ይፈልጋሉ፡፡ አምባገነኖች የታሪክ አጋጣሚ የሰጣቸውን ስልጣን መሸከም አይችሉም። አምባገነኖች ፈሪዎች ስለሆኑ ለሰው ህይወት ደንታ የላቸውም፡፡ በሌላ በኩል የሊደርሺፕ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ ኮሽ ባለ ቁጥር ፓኒክ የሚያደርግ፣ የሚደናገጥና የሚርበተበት ፈሪ ሰው መሪ (ሊደር) ሊሆን እንደማይችል ያስተምራሉ፡፡ ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ፈሪ ሰው የሚወረውረውን አያውቅም፡፡ ማን ላይ እንደሚወረውርም ግድ የለውም፡፡ እንዲህ ያለ ባህሪ ያለው ሰው መሪ መሆን አይችልም፣ አይገባውም፡፡ አሁን ያለውን የሚድሮክ አመራር በዚህ መስፈርት መፈተሽ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
እዚህ ላይ ሚድሮክን ዘመን ተሻጋሪ ተቋም ለማድረግ ምን መደረግ አለበት? የሚል ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በክፍል 2 በቀረበው ጽሁፍ፣ አቶ ጀማል በማኔጅመንቱ ላይ እየወሰደ ባለው ይግባኝ የሌለው ፍርድ የተነሳ ለሰራተኛው፤ “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” እንዲሉ ሆኖበታል ማለቴ ይታወሳል። ሚድሮክ ማኔጅመንቱ ይግባኝ የሚልበት አሰራር ቢኖረው ኖሮ፣ እኔም ሆንኩ ሌሎች ተበዳዮች እምባችንን አፍስሰን ባልቀረን ነበር። እኔም ይህንን አቤቱታዬን በጋዜጣ ለባለሃብቱ ከማቀርብ ለዚሁ አካል ማቅረብ እችል ነበር፡፡ እንደኔ እንደኔ መፍትሄው “ሚድሮክን የሚመራ ቦርድ” ማቋቋም ነው። (ለቦርድ አባልነት ራሴን እጩ አድርጌ የማቀርብበትን ማመልከቻ በዚህ አጋጣሚ ለክቡርነትዎ አቀርባለሁ!) የሚድሮክ ሲኢኦም ተጠሪነቱ ለዚሁ ቦርድ ስለሚሆን በሲኢኦው በደል የደረሰበት የሚድሮክ ሰራተኛም ይሁን የማኔጅመንት አባል አቤቱታውን ለቦርዱ የማቅረብ እድል ይኖረዋል። ሲኢኦ ሆኖ የተሾመው ግለሰብ ተቆጣጣሪ እንዳለው ሲያውቅ ስራውን በህግና በስርዓት በመስራት የሚድሮክ የኢንዱስትሪ ሰላም የተረጋጋ እንዲሆን ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሚድሮክ በቦርድ በመመራቱ የሚገኘው ሌላው ትሩፋት፣ ሚድሮክ ዘመን ተሻጋሪ ዘላለማዊ ተቋም ለመሆን ያስችለዋል፡፡ አሁን ባለው አሰራር የሚድሮክ ሲኢኦ ሆነው የሚሾሙ ሰዎች ለረጅም ዓመታት ከመቆየታቸውም በላይ ቀደም ሲል የነበረን ማኔጅመንት በማፍረስና በማባረር የራሳቸውን ኔትዎርክ ዘርግተው የራሳቸውን ኢምፓየር ለመገንባት ላይ ታች ሲሉ ይስተዋሉ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ አዲስ ሲኢኦ በተሾመ ቁጥር የሚድሮክ የሰው ኃይል እየፈረሰ የሚገነባ የሚያደርገው በመሆኑ ተቋሙ ዘመን ተሻጋሪ እንዳይሆንና ዘላቂነት እንዳይኖረው ያደርገዋል፡፡
ክቡር ሆይ!
ሌላው ምክረ ሃሳብ በኢትዮጵያ ያለውን የሚድሮክን ሀብት ጊዜ ወስዶ ቆጠራ (ኢንቬንተሪ) ማድረግን ይመለከታል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረው ሼህ ሙሐመድ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከ80 በላይ ኩባንያዎች አሏቸው፡፡ በእነዚህ ኩባንያዎችም በአጠቃላይ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ቋሚ፣ ጊዜያዊና የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞች የሥራ እድል አግኝተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም የሰው ኃይል ሼህ ሙሐመድን ከመንግስት ቀጥሎ ብዙ የሥራ እድል የፈጠሩ ባለሃብት ያደርጋቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ እኔ በቅርብ ሆኜ እንዳስተዋልኩት በኢትዮጵያ ያለዎት ሀብት በመላ ሀገሪቱ፣ በሁሉም ክልሎች የሚገኝ ነው፡፡ እናም እንኳን አሁን የተሾሙት ቀደም ሲል ለረጅም ዓመታት ሚድሮክን የመሩትም ኃላፊዎች የሚድሮክን ንብረት ጠንቅቀው ያውቁታል ብዬ አላምንም። አንዳንዶቹ ኩባንያዎች ከአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን ጀምሮ የነበሩ ተቋማት በመሆናቸው ለዘመናት የተጠራቀመ ንብረት ክምችት በአግባቡ አለመመዝገቡንም አስተውያለሁ፡፡ በአግባቡ ባለመመዝገቡ ንብረት በየስፍራው ተበትኖ፣ አንዳንድ ቦታ ላይ አቧራ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀበት፣ ሳርና ቅጠል በቅሎበት ይገኛል፡፡ ለዝርፊያና ለስርቆትም የተጋለጠ ነው። በመሆኑም አዲስ የሚያቋቁሙት “ሚድሮክን የሚመራ ቦርድ” በቅድሚያ ማከናወን የሚገባው ስራ የንብረት ቆጠራ ማድረግ፣ ንብረቶችን መለየት፣ የሚሸጡትን መሸጥ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
የሚድሮክ ችግር የንብረቱ መዝረክረክና አለመመዝገብ ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች በሚድሮክ ኩባንያዎች ስም በየፍርድ ቤቱ የተከፈቱ ዶሴዎችም በውል የሚታወቁ መስሎ አይታየኝም። በመሆኑም የሚያቋቁሙት “ሚድሮክን የሚመራ ቦርድ” ሌላው ተግባሩ አንድ የህግ ክፍል አቋቁሞ በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮችን ዝርዝር በማውጣት ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሪፖርት እንዲያዘጋጅና በቀጣይም ክትትል ማድረግ መሆን አለበት፡፡
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ ኢንዱስትሪዎችና ዘመናዊ የንግድ ተቋማት ብቅ ብቅ ያሉት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ በአውሮፓ ከ100 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው በርካታ ፋብሪካዎችና የንግድ ተቋማት አሉ፡፡ ይህም ማለት የነዚያ ተቋማት መስራቾችና ባለቤቶች ዛሬ በህይወት ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ተቋማቱ ዛሬም አሉ፣ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ለምን ቢባል ባለቤቶቹ ኖሩም አልኖሩ ተቋማቱ የሚመሩበት ህግና ስርዓት ስላላቸው (ተዓምራዊ ሁኔታ ካልተከሰተ በስተቀር) ቀጣይነታቸው አያጠራጥርም፡፡ ሚድሮክ እንዲህ ያለውን የአውሮፓ ኩባንያዎች አደረጃጀትና አሰራር በመከተል ዘላለማዊ ተቋም እንዲሆን መስራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ሲኢኦ በተቀያየረ ቁጥር እየተጠረገ የሚወጣ ሰራተኛ መኖር የለበትም። እነዚህ ሰራተኞች ያሉበት ደረጃ ለመድረስ እንደ ሀገር የፈሰሰባቸው ሀብት እንዳለ ሆኖ ሚድሮክም ለሰራተኞቹ እውቀትና ልምድ ሀብትና ጊዜ አባክኖባቸዋል፡፡ እናም ሚድሮክን ለመምራት ለአጭር ጊዜ የሚሾሙ ሲኢኦዎች ሚድሮክ የተሰራበትን ድርና ማግ መበጣጠስ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ እንዲህ ያለ ድርጅቱን የሚጎዳ ስራ ሲሰሩ ዝም ሊባሉም አይገባም፡፡  
ክቡር ሆይ!
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በሚድሮክ ውስጥ ለረዥም ዓመታት የሰራ በመሆኑ ስለ ኩባንያዎቹ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ብዙ መረጃዎችም በእጁ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ስጋትን ከመግለጽ ውጪ ሁሉም መረጃ ለጋዜጣ የሚቀርብ ባለመሆኑ ከዚህ በላይ መሄድን አልመረጥኩም፡፡ በኔ እምነት ሚድሮክ ተራ የግል ኩባንያ አይደለም። የመንግስትም ሆነ የህዝብ ፍላጎቶች በሚድሮክ ውስጥ እንዳሉ አስባለሁ፡፡
ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የተነሳሁትም የሚድሮክንም ሆነ የአቶ ጀማልን ድክመት ለማጋለጥ ሳይሆን፤ ሁሉንም ነገር በይሉኝታ ይዘን በዝምታ ካለፍነው የለየለት አምባገነንነት ሊያቆጠቁጥና አለፍ ሲልም የራስን ኢምፓየር የመገንባቱ ሂደት ተጠናክሮ ስለሚቀጥል መንግስት በተቀየረ ቁጥር የሀገሪቱ ቢሮክራሲ እየተበተነ እንደሚሰራው ሁሉ የሚድሮክ ሲኢኦ በተቀየረ ቁጥር የሚባረር የማኔጅመነት አባል እንዳይኖር ችግሮች በጊዜ እንዲፈቱ ለማሳሰብ መሆኑ እንዲታወቅ እሻለሁ፡፡ አቶ ጀማል ከሌሎቹ የሚድሮክ ኃላፊዎች ድክመትና ውድቀት ትምህርት ወስደው ድክመቶቻቸውን “በዳግም ጥልቅ ተሐድሶ” ካላስተካከሉ ውጤቱ ለዓመታት የሰሩትን በጎ ነገር ሁሉ በዜሮ ማባዛት ብቻ ሳይሆን፣ በታሪክ ፊት ተጠያቂ መሆንም እንዳለም ልብ ሊሉት ይገባል፡፡
በመጨረሻም፤ ጽሑፌን የጀመርኩት የራሴን ጉዳይ በማንሳት ነበር፣ የምደመድመውም በራሴ ጉዳይ ይሆናል… በክፍል አንድ ጽሑፍ ላይ እንደገለጽኩት አቶ ጀማል በእኔ ላይ ለምን ጨከነ? ጥፋቴ ምንድነው? የሚለው ጥያቄ አእምሮዬን ወጥሮ ሲይዘኝ ለሽምግልና የላኳቸው ሰዎች የሰሙት ነገር ካለ ጠይቄያቸው የተለያየ መልስ ሰጥተውኛል። አንዳንዶቹ “አብዱራህማን በሸገር ዳቦ ጉዳይ ለጋዜጠኞች በሰጠው መረጃ ምክንያት አዳነች አቤቤ አባረው ብላኝ ነው” ማለቱን ነግረውኛል፡፡ ሌሎች ደግሞ “አብዱራህማን በፌስቡክ ገጹ ስለ አሜሪካ በጻፈው ጽሁፍ ምክንያት ከአሜሪካ ኤምባሲ ተደውሎ አባረው ተብዬ ነው” ማለቱን ነግረውኛል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በፌስቡክ ገጼ ስለ አንድ ሆስፒታል በጻፍኩት ጽሁፍ ምክንያት እንዳባረረኝ ነግረውኛል። ሌሎች ደግሞ “ወሓብያን የሚያወግዝ መጽሐፍ ተርጉመህ በማሳተምህ ጓደኞቹ እነ አቡበከር አህመድ አባር ብለውት ሊሆን ይችላል” ብለውኛል። ከህግም ከሞራልም አኳያ እነዚህ ምክንያቶች ከስራ እንድባረር ሊያደርጉኝ የሚችሉ አይደሉም። ከአቅምም ከችሎታም፣ ከስነ ምግባርም ከልምድም፣ ከውጤታማነትም ሆነ ከሌላም ከሌላም መስፈርቶች አኳያ፣ በዚህ ወቅት ከሚድሮክ አንድ ሰው ይባረር ቢባል በቅድሚያ መባረር ያለበት ማን እንደሆነ መገመት ሊቅነትን የሚጠይቅ ሆኖ አይታየኝም። ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ፡፡ እነ አቶ ጀማል መልስ ከጻፉ አሁን ያላካተትኳቸውን ቀሪ ሃሳቦች እና የመልስ መልስ ይዤ እመለሳለሁ፡፡
ምንጊዜም አክባሪዎ!
አብዱራህማን አህመዲን፤ (ኢሜይል፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) Or  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ
የኮሙኒኬሽንና ፕሮሞሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር (የነበርኩ)


Read 1416 times