Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 06 October 2012 15:13

በ”የንጋት ሹክሹክታዎች” ውስጥ የታጨቁ የነብስ መቃተቶች!!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

እንደ መግቢያ…
ፀሐይ ከወደ መውጫዋ አድማስ ስርቻ ተፈልቅቃ ለመታየት በፊታችን ስትፍጨረጨር፣ ሩብ ግማሽ እያለች ሙሉ እንደምትሆን ሁሉ፣ የንጋት ድምፅም ጎልቶ ከመሰማቱ በፊት ቀድሞ የሚደመጠው ሹክሹክታው ነው፡፡
ከዚያም ቀስ በቀስ ጎልብቶ ሙሉ ይሆንና ደምቆ ወደ ልቦና ጥልቀት ይዘልቃል፡፡ የህይወትን ተዓምራዊ ግርማ ሞገስ ይለብስና በሁለት እግሩ ቆሞ መሄድ ይጀምራል፡፡ …እንዳነገሱትም ይነግሳል፡፡
የንጋት ሹክሹክታዎች ውስጥ የተዘሩ የስንኝ ቋጠሮዎችም እንዲህ ናቸው፡፡ …እያደር ሙሉ ለመሆን የምትፍጨረጨር የወጣት ነብስ መቃተቶች… የፍለጋ ዳናዎች… እና የመሆን ያለመሆን መውደቅ መነሳቶች… የሚደመጡ፣ የሚዳሰሱ የአፍላ ብዕር ቀለም ንክሮች ናቸው፡፡ የስነ ግጥም ውበትና ደም ግባትዋ ሲመረመር ነውና የሚጎላው እስቲ አብረን እንዝለቅና እንፈትሻቸው፡፡
በእውቀቱ “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” በተሰኘ ሥራው ውስጥ እንደ መክፈቻ አድርጎ ያቀረበውን አገላለጽ በገጣሚ ተስፋዬ አየለ “የንጋት ሹክሹክታዎችም” ውስጥ ተንፀባርቆ እናገኘዋለን፡፡

ገጣሚ በእውቀቱ ሥዩም፡- 
“ግጥም የህያው ስሜቶች ምስክርነት እንደሆነ እናምናለን፤ ምናባዊ መገለጥ እንደሆነ እናምናለን፤ ለአያቶቻችን ከመለኮት ጋር የሚያገናኝ መሠላል፤ ለአባቶቻችን የአብዮትን ሠይፍ የሚስል ሞረድ፤ ለእኛ ፍለጋ/ኅሰሳ መሆኑን እናምናለን ያልተንዛዛ ለቅሶ ያልቆረፈደ እንደሆነም እናምናለን፡፡” …ብሎ እንዳሰፈረው ተስፋዬ አየለ ደግም ግጥምን በራሱ መንገድ ይፈታዋል፡፡ እንዲህ በማለት፡-
“ግጥም የነብስያ እውነቶች ውቅር፣ የጠሊቅ ህላዌ ሚስጥርና የነግ ህልማዊነት ግት ነው፡፡ …እምቅ የስሜቶች ገሞራ… የብርሃን ፍጥረት መሰረት ነው፡፡ …ብልጭታ ነው - ፍንጥቅታ፡፡
…የንጋት ጀንበር የዋህ ፈገግታ፡፡ …አሁን በግጥም ይቀደሳል… ዛሬ በግጥም ይወደሳል… እዚያ በግጥም ይዳሰሳል… ትላንት በግጥም ይታወሳል… ነገ በግጥም ይበረበራል ይፈተሻል፡፡ በግጥም ህይወት የበለጠና የላቀ ይታሰሳል፡፡” …በማለት፡፡
“…ንጋትና ንቃት ተባብረው በቀጠሯቸው መሰረት ቦታ የመቱ እለት ንጋት ላይ… ነብሴ በሹክሹክታ ከዘመረቻቸው ዝማሬዎች መካከል እንደ ሰበዝ መዝዤ፣ ዜማቸውን የጫጫራቸው ብዕር እንደ ነብሴ ባያስውባቸውም፣ ከብርሃናው ሁዳድ በተንኳቸው፡፡… እናም በንጋት መዳረሻ ሜዳ ላይ ተዘርሬ በኩለሌት ያማጥኳቸው የስንኝ ቋጠሮዎቼን እነሆ ብያለሁ፡፡” …ይለንና ወደ ውስጥ እንድንዘልቅ ይጋብዘናል፡፡
ገጣሚውና የነብስ መቃተቶቹ /ነብስያን መፈለግ/
የገጣሚ የተስፋዬ አየለ የንጋት ሹክሹክታዎች የግጥም መድብል ውስጥ በተደጋጋሚ የሚደመጠው ወይም እያሰለሰ ብቅ የሚለው ጉዳይ የነብስያ ጥሪ ነው፤ የውስጥ ፍላጐት የውስጥ ጭንቀት ውትወታ፡፡
ገጣሚውን ወይም እኔ ባይ ተራኪውን በውድቅት ሌሊት ቀስቅሰው እያስማጡ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል በንጋት ሹክሹክታዎች መልክ ነብስ የዘሩ ብዙ ነብሶችን ማግኘት ይችላል፤ በንጋት ሹክሹክታዎች፡፡ ገጣሚው ለህይወት ያለው አመለካከት ብሩህ ነው፡፡ ህይወትን ውብ አድርጐ ስሎ በዚህ ውበት ውስጥ የምትቃትተውን የወጣትነት እረፍት ያጣች ነፍስ ነው የሚፈልገው፡፡ ግድ የሚሰጠውም ፊት ለፊት የሚታየው ውጫዊው ውበት ሳይሆን ውስጣዊ ማንነታችን፤ እኛነታችን ነው ቁም - ነገሩ፡፡
ለዚም ማስረጃ ይሆን ዘንድ በመድበሉ ውስጥ በተካተቱት 125 ግጥሞች ውስጥ 35 ጊዜ መግቢያና መውጫው ላይ ስምንት ጊዜ በድምሩ 43 ያህል ነብስ፣ ነብሴ፣ ነብስሽ ነብስህና ነብሶቻችን የሚሉ ቃላት ይገኛሉ፡፡
ግጥሞቹ የዘመኑን ወጣት ማንነት ፍለጋ፣ ራስን መሆን እና እኔ ማነኝ፣ ከየት ተገኘሁ መዳረሻዬ ወይም መጨረሻዬ ወዴት ነው የሚሉ ሁልአቀፍ ጥያቄዎችን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡
ለእኔ ግጥሞቹን በወፍ በረር አንብቤ ያገኘሁት አንድና አንድ እውነት የገጣሚውን ምናልባትም የብዙዎቹን ወጣቶች የውስጥ መሻትና የነብስያ ጥያቄ ነው፤ ገጣሚው ከውጫዊ ግርግርና በገሃድ የፈጠጠ እውነት ይልቅ ጊዜ ሰጥቶ፣ ከቀን ብርሃን ይልቅ ጨለማንና ንጋትን መርጦ ውስጡን ነው ለማዳመጥ የሞከረው፡፡
ተስፋዬ ውስጡን /በሌላ አገላለጽ ነብሱን አዳምጦ/ እንደብዙዎቻችን የውስጡን ውትወታ አፍኖ አላስቀረውም፤ ከዚህ ይልቅ እስኪ የነብሴን ጥማት እዩልኝ፣ አንዳች ነገር ሹክ ካሏችሁ ልቀሟቸው፣ የማይናገሩ የማይኮረኩሩ የውሃ መልክ ከሆኑባችሁ ደግሞ እርገጡና እለፏቸው ነው ያለው በራሱ አንደበት፡፡
ገጣሚው እንዲህ ይበል እንጂ ግጥሞቹ ከነብስና መሻት ጋር የሰመረ ግንኙነት ያላቸው እስከሆኑ ድረስ በአንድም ይሁን በሌላ የእያንዳንዳችን ነብሶች መንካታቸው አልቀረም፡፡
“እስቲ የነገይቱ የኔይቱ” /ገጽ 9/ እና “አንድ እውነት ለሄዋን” /ገጽ 10/ የቀረቡ ግጥሞችን እንመልከታቸው፡፡…
የነገይቱ የኔይቱ
ከነብሴ ተራራ ማዶ ከወንዛወንዙ ተሻግራ
አለች የኔ’ምላት ሰው መቅደሴ በልቤ ከብራ፡፡
ሳይታወቀኝ በሷ ቅላፄ በድምፅዋ ዜማ እየዘመርኩ
ዘንግቼው የኔን ጎዳና በሷ መንገድ እያዘገምኩ፡፡
ሳቄን በሳቋ ሸምኜ የቃል ወጓን እያደመጥኩ
የውብ ህልሞቿን ቋጠሮ ለመፍታት ሁሌ እየጣጣርኩ
የምኖራት ሔዋን አለች በምስጢር የሰረገች ከልቤ
ቃሌ የማይዘነጋት ህያው የማትወርድ ከወትሮ ሀሳቤ፡፡
እስክትነጋልኝ በተስፋ ገመድ ተተብትቤ
በእምነት ሆኜ የምቆያት
የልቤን እሻት በፀሎት ፍቅሬን በክብር ‘ማኖርባት
ከነብሴ ተራራ ማዶ ከወንዛ ወንዙ ተሻግራ፣
አለች የኔይቱ ሔዋን ከምኞቴ ከርስ ተቀብራ፡፡
***
በዚህ ግጥም ውስጥ እኔ ባይ ተራኪው፤ በልቡ ጽላት ቀርፆ፣ በእሳት ሰረገላ ያኖራት ነገ ሊያገኛት የሚፈልጋት በነብሱ ሥጋጃ ላይ ተደላድላ የተቀመጠች፣ ጥላ ጥላዋን የሚከተላት በገሃድ ግን ያላገኛት፣ የምኞቱ ንግስት አንዲት ሄዋን አለች - በነብሱ ውስጥ ተሰንቅራ፡፡
እኔ ባይ ተራኪው፤ እሷን መስሎና አክሎ የሚኖራት የድብቅ ነብሱ ጥማት ከአድማስ አድማስ አስሶ ለነብሱ እሷን ጠብቅ ታገኛለህ፤ አለችልህ በማለት በልቡ ማህተም ውስጥ ያነገሳት ሄዋን አለች፡፡ ተስፋዬ በመግቢያዬ ላይ ብሩህ ነው ለማለት ያስደፈረኝ እንዲህ ያለው እምነቱ ነው፡፡
ሄዋን የልቡን ንግስት የህላዊውን ዘውድ ነገ እንደሚያገኛት ተስፋ አድርጓል ደግሞም በለስ ከቀናው ሊያገኛት ይችላላ ለምን ቢሉ ነፍስያው በንጋት ሹክ ብላዋለችና፡፡
ሁለተኛው ግጥም አንድ እውነት ለሄዋን ቀጥሎ ይነበባል፡፡

አንድ እውነት ለሔዋን
ተቀብታ ውበት አምሮባት ካልነገሰች ነብስሽ ባለም፣
ስጋሽ ካማረው በቀር እሚሮጥ ወዳንቺ የለም፡፡
በክፋት ደቼ ተቦክቶ በተሰራ እርጉም ቃሉ፣
ሰውነትሽን ማበሽቀጥ ነው እሚሻ ምድረ አዳም ሁሉ፡፡
የመደመጥ ስልጣን አንዴ ባንቺ ከታደለ ፈቅደሽው
አኝኮ ይተፋሻል ደርሶ አድሮ ሲውል ቀፈሽው፡፡
ምን ቢረዝም እድሜሽ ምን ቢመዘዝ እንደ ሀረግ፣
ታሪክሽ ካልሆነ በቀር ሴትነትሽ የለውም ማዕረግ፡፡
እና ሔዋኔ ሆይ!
ቁመሽ ከመስታወቱ ትይዩ
“አይኔ ያምራል” አትበይ “ከናፍሬ ይማርካል ወይ”
ይልቅ ራስሽ ፊት ቁሚና፣
“ምኗ ያምራል የነብሴ፣ ምኗስ ላይን ያስቀይማል ‘በይ፡፡
***
በዚህ ግጥም ውስጥ ገኖ የወጣው ጉዳይ ውበት ማለት ውስጣዊ እንጂ ውጫዊ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ እንደሚነገረውና እንደሚደመጠው የሃገራችን የውበት መገለጫ አብዛኛውን ጊዜ ማለቴ ነው ሃሳባዊ (ideal) ነው፡፡ ደራሲዎቻችንም በየድርሰቶቻቸው ስለ ውበት ደግመው ደጋግመው የሚዘምሩት ውበት/ቁንጅና ውጫዊውን ነው፤ ሴቷን ፀጉረ ዞማ አፍንጫዋ ሰልካካ/ስንደዶ የመሰለ፣ አይኗ የብር አሎሎ፤ ጥርሷ ሃጫ በረዶ/የጊደር ወተት የመሠለ፣ ከንፈሯ ጽጌሬዳ፣ አንገቷ መቃ፣ ሽንጧ የንብ አውራ የመሰለ፣ ዳሌዋ ኮራ ያለ፣ ጭኖቿ ሞላ ያሉ፣ ባትና ተረከዟ የተዋቡ፣ ቁመቷ መለሎ ወዘተ… እያሉ ነው ሃሳባዊ ውበት ሲያስነብቡን የኖሩት፡፡ ይህ የቁንጅና/የውበት መለኪያ በተመሳሳይ ለወንዶችም እንደሚሰራ ልብ ይሏል፡፡
እውን ግን ደራሲዎችን በድርሰቶቻቸው እንደሚስሏት /ሉት ሴት/ ወንድ በገሃዱ ዓለም አለ? ምላሹን ለእናንተ ነው የምተወው፡፡ በአንፃሩ ግን ፀጉሩ ከርደድ፣ ግንባሩ ከበድ፣ አይኑ ሰርጎድ፣ አፍንጫው ጎረድ፣ ከንፈሩ ከበድ፣ መልኩ ጠቆር፣ ያለ ቁመና ያለውን/ያላትን አዳምም ሆነ ሄዋን የውበት አክሊል አስደፍተው አላስነበቡንም፡፡ እናም በደራሲዎቻችን ተጽዕኖም ይሁን በማህበረሰብ የቆየ ልማድ፣ በየቤታችን ያልኖረውን እንድንኖር የተፈረደብን ነን፡፡ በተለይ ደራሲዎቻችን ይህንኑ ጉዳይ ነው ሲያቀነቅኑ የኖሩት፡፡
ተስፋዬ ግን ይህንን ሥር የሰደደና የተለመደ አስተሳሰብ በመቃወም፣ የለም ውበት ማለት አይን ጥርስና ከንፈር ፀጉር ዳሌ ባትና ተረከዝ አይደለም፤ ቁንጅና ወይም ውበት ማለት የእነዚህ የውጫዊ ገጽታዎች ድምር ብቻ አይደለም፤ ይልቅስ የእኛነታችን የማንነታችን በጥቅሉ የነብስያችን፤ ሰው የመሆናችን ውበት የት ላይ ነው ብለን እንፈልግ ነው የሚለን፡፡
ይኸው የውስጣዊ ውበት/የነብስያ ጉዳይ በመቆምና መሄድ /ገጽ 13/ ላይም ያነሳል…

መቆምና መሄድ
ሩቅ የመሰለ ነገር ሲጠጉት ደርሰው ይቀርባል
ያለቀሱበት ዓይን ስቆ ቀን ሲነጋ ያባብላል፡፡
እንዳይመስል የተወጠነ
እንዳይሆን የተከወነ
ሲታይ ተገልጦ እውነቱ
ውስጡ ነው የሰው ውበቱ፡፡…
እያለ ይቀጥላል፡፡ …ይህ ደጋግሞ የሚዘምረው እውነታ ነው፡፡ ተስፋዬ እንደስሙ ተስፈኛ ብዕረኛ ነው፡፡ መጭው ጊዜ ካሁኑ የተሻለ እንደሆነ ያምናል፡፡ እናም በተስፋ እንንቀሳቀስ ከመቆም መሄድ ይሻላል ይለናል፡፡ ለነገሩ ብሂሉም እንደዚሁ ነው፡፡ አትቁሙ፤ እሹ፤ ፈልጉ፤ ጣሩ ሲለን፣ ከተኛ ውሻ የተንቀሳቀሰ ውሻ ይሻላል፡፡ የተንቀሳቀሰ ውሻ ወይ ላፉ ሊጥ ለወገቡ ፍልጥ አያጣም በማለት፡፡
እናም ተስፋዬ እንደስሙ ተስፋን የሰነቀ መሆኑን ተስፋ አድርጐ፣ ነገም ሌላ ቀን ነው ምን ይዞ እንደሚመጣ አይታወቅም ሲለን፣ በዚሁ ግጥሙ በ”መቆምና መሄድ” ማለቴ ነው አጥብቆ ይወተውታል፡፡
ይኸው ተስፈኛ መሆን ወይም የተስፋ ጉዳይ በ”የትዝታ ተረት /ገጽ 14/ በሚለው ግጥሙ ላይም ይስተዋላል፡፡ እኔ ባይ ተራኪው ያሳለፈው ዘመን ዛሬ ተመልሶ የእድሜ ዘመኑ ሲሰላ በግንባር ቋጠሮው ልክ ቢሆንም አምርሮ አለማዘኑን የቋጠረው ግንባሩን እንጂ ልቡን /ውስጡን/ ነብሱን አለመሆኑን እንዲህ በማለት ነው የገለፀው፡፡

የትዝታ ቅሪት
እንደ ተቋጠረ የቀረ የግንባሬ ሽብሽብ መስመር
ትናንት ባንቺ ስከፋ ሀዘኔን ላሳይሽ ነበር፡፡
አንቺም አልፆምሽ ከእርሙ አልቀረለት ብግነት ቆሽቴ
ዛሬ መለየትን ሊያዜሙ አንደበትሽ አንደበቴ
ወይኔ!… እንደው በመቻል ሰበብ ቆጨኝ ያ ሁሉ ዘመን
ግንባሬን የቋጠርኩበት የቀበርኩበት ንዴቴን፡፡
ግና!… ትናንት ባንቺ ስከፋ ተደልዬ በገናገና
በነገ የተስፋ ስሌት፣
…የምኮራበት እውነት
እንዳንቺ ልቤን አይደለም
ግንባሬን ነው የቋጠርኩት፡፡
***
ገጣሚው ደጋግሞ የሚያነሳው ጉዳይ ራስን መሆን፣ ነብስያን ማድመጥ መሆኑን ለማስረገጥ ረቂቅ ማንነት በሚለው ግጥም ውስጥም መመልከት ይቻላል፡፡ የግጥሙ ዋና መልዕክትም ሰው የሚልህን አስትማ፣ ሰው ጎበዝ ነህ ወይም ፈሪ ነህ ቢልህ እንኳ ለእነሱ ብለህ እህ አትበል ይልቅስ እውነተኛውን የነብስያ ፍላጎትህን ፈጽም ነው የሚለው፡፡ (ገፅ 85)
ረቂቅ ማንነት
“ተናገር ባዩን” አትስማ “ዝም በል” ሲሉህም አትመን
በራስህ ቅላፄ ካልሆነ በሰው ዜማ አታቀንቅን፡፡
በገፉህ መጠን አትውደቅ “እህ' ባሉህ ልክም አታውራ
አዝነህ 'ሚያዝንልህን አስተዛዛኝ ወዳጅ አታፍራ፡፡…
እያለ ይቀጥላል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ተስፋዬ ስስ የገጣሚ ነብሱን ሰዎች አዝነው በእምባ ሲሸነቁሩበት፣ ህመማቸው ከውስጡ ዘልቆ ቁስላቸው ሲጠዘጥዘው፣ በስንኝ ቋጠሮ ውበት ሲያቃስትም እናገኘዋለን፡፡ እንዲህ በማለት እንዲበረቱ አብሮ ይታመማል፡-
ልባዊ እውነት
ለገጠመውና ለሚገጥመው ሁልጊዜ እሽሩሩን ከዘመረ
ድቃቂት የቆይታ እድሜ የለውም ሰው ባለም ምንም አልኖረ፡፡
ብርሃን መሀል ደምቆ ታይቶ በላቀ ፍካት ካልቆመ
የጽልመት ሳቁን ድል ነስቶ ከደስታው እልፍኝ ካልታደመ
አንዳች ታሪክ አይሆነውም ብቻ ውሎ ስላደረ…
ሳቁም ብርሃን የለውም በልቡ ሰቀቀን እየዘመረ፡፡…
እያለ ይቀጥላል፡፡ ተስፋዬ ተስፋ ያለው ብዕረኛ ነው፡፡ እኔ ለመነሻ ያህል ለስሜቱ ቅርብ የሆነውን እና በተስፋዬ ምናብ ሁነኛ ቦታ ያገኘውን የነብስያ ጉዳይ ብቻ አነሳሁ እንጂ “የንጋት ሹክሹክታዎች”ን ጠልቆ ለመረመራቸው ከነብስ ተኮር ይዘት በተጨማሪ፤ ሄዋን ተኮር፣ ህይወት ተኮር፣ ፍልስፍና ተኮርና ትዝብት ተኮር ግጥሞችን ማግኘት ይችላል፡፡ እነዚህን እያነሱ መተንተንና መፈከር የሥነ ፅሑፍ ተማሪዎችና ምሁራን ሥራ ይሆናል፡፡ ግጥሞቹ ለአንባቢ ግጥሞቹ በቀላል ቃላት የተፃፉ፣ ብዙ የማያስቸግሩ ስሜት ንክር ናቸው፡፡
እንደ ማሳረጊያ…
ሌላው ጉዳይ ደግሞ ገጣሚ ተስፋዬ አየለ፤ በውጣ ውረዱ ብዛት ባክኖ የትም ሳይቀር የትላንት መውደቅና መነሳቱን በዛሬ ብርታቱ ሽሮት መገኘቱ የደነቀው ፀሀፊ ተውኔት ገጣሚና ተዋናይ ጌትነት እንየው፤ በግጥም መድብሉ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝቶ ሲናገር ያሰመረበት እውነት ደንቆኛል፡፡ “ስለ ሀቅ ለመናገር በገጣሚው ጥንካሬ ቀንቼበታለሁ፡፡ የትኛውም ወጣት ፀሐፍት ይህን የመሰለ ጥንካሬ ካለው ምንም ሳይደናቀፍ ከህልሙ ጫፍ በግዜ ለመድረስ ይቻለዋል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አይነት ብርታት ማንንም የማበርታት፣ የማጀገን እና የሚለኩስ አቅም የመስጠት ሀይል አለውና ረቂቅ የባለ ራዕይ ስንቅ ነው፡፡” ሲል ነበር የተናገረው፡፡ እውነትም ገጣሚውን ጌትነት እንየው ከልቡ ተመልክቶታል ያሰኛል፡፡ ታድያ እኔም በዚህ ሀሳብ ለመስማማት አላመነታም፡፡ የአንድ ገጣሚ ወጉም ወዙም ፅናቱ ነው፡፡ ነብሳዊ ብርታቱ፡፡ የውበቱ ጥግ ድግም ቅኔው ነው፡፡ በቃላት አምጦ የሚወልደው የታመቀ ረቂቅ ጥንጥን ሀሳቡ ነው፡ የህይወትን ውበት የሚኩልበት ደማቅ ቀለሙ፣ ያልታየውን የሚያይበት አይኑ ያልገነተረ መንፈሱ ነው፡፡ እናም በነዚህ ሁሉ ቀለሞች ድምር ነው የገጣሚው ልዩ ጥንካሬ የሚታወቀው፣ መልኩ ለአይን የሚገለፀው፡፡ እኒህን ውበቶች ታድያ በተስፋዬ ግጥሞች ነብስ ውስጥ ደጋግመው ሲመላለሱ እናያቸዋለን፡፡ ምናልባትም በንጋት ሹክሹክታዎች ውስጥ የታጨቁት የነብስ መቃተቶች፣ ከልቦናው ሁዳድ ተለቅመው ወደ ወረቀት የተበተኑ የራሱ የገጣሚው ህመሞች ሊሆኑ እንደሚችሉ እንገምታለን፡፡ በየግጥሞቹ እንብርት ታትመው የመገኘታቸውን ሚስጥር ስንበረብር ይህ እውነት ጎልቶ ይታየናል፡፡ ያኔ ደግሞ ልክ እንደኔ በጌትነት እንየው ሀሳብ ለማመን አናመነታም፡፡ የገጣሚው ጥንካሬ ለሌሎችም ወጣት ፀሐፍት ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ እውነት ነው፡፡
በተረፈ ግን…
በንጋት ሹክሹክታዎች ውስጥ የታጨቁ የነብስያ መቃተቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሁላችን ህመም መሆናቸውን ለማወቅ በመድብሉ ከተካተቱ ግጥሞች እጅግ በጣም ጥቂቶቹን ማንበብ በቂ መሆኑን ልንገራችሁና ከንጋት ሹክሹክታዎች ውስጥ የየራሳችሁን ነብስያ እውነቶች እንድትፈትሹ ልተዋቸው፡፡ መልካም ፍለጋ… ሀሰሳችሁ በግኝት ይቋጭ፡፡ …ጥበብ ሁሌም በነብሳችን ውስጥ ትለምልም፡፡ በጥበብ እንኑር አሜን!!

 

Read 6076 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 15:17