Tuesday, 07 June 2022 07:12

የልደት ቀን ውሎዬ

Written by  ከእስክንድር ኃይሉ
Rate this item
(4 votes)

 ከእናቴ ጋር አንድ አልጋ ላይ ነው የምንተኛው፤ ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ከጎኔ የለችም፤ ስራ ሄዳለች ማለት ነው። ሶስት ሆነን ነው እዚህ ቤት የምንኖረው፤ እኔ፣ ወንድሜና እናቴ፡፡ ወንድሜ ሳሎኑን ቆርጦ፣ ለእራሱ መኝታ ቤት ሰርቷል፡፡ እኔና እናቴ፣ መኝታ ቤቱ መግባት አይፈቀድልንም፡፡
ሳሎን ስሄድ ጠረጴዛ ላይ አንድ ወረቀት አገኘሁ፡- ‹አንቺ እንቅልፋም፤ መልካም ልደት› የሚል፡፡ እንዴ! ዛሬ ልደቴ ነው ለካ፤ ረስቼው ነበር፤ ወይኔ 17 ሞላኝ፤ አረጀሁ! ከወረቀቱ ጎን አንድ ሞባይል ተቀምጧል፤ ወንድሜ ለልደቴ ትቶልኝ የሄደው ስጦታ መሆኑ ነው፡፡ አይ መስፍን፤ የልደቴን ቀን ረስቶ አያውቅም። ትንሽም ትሁን ትልቅ ለልደቴ የሆነች ስጦታ ይሰጠኛል፤ አባት በሌለበት፤ እናት ስራ ውላ ማታ በምትገባበት ቤት፤ ወንድሜ አባቴ ሆኗል፡፡ ታናሽ እህቱ ስለሆንኩም ባቅሙ ያሞላቅቀኛል፡፡
ሞባይሉ አዲስ አይደለም፡፡ ገረመኝ። ወንድሜ ስራ የለውም፤ ‹ቢዝነስ ሰርቼ› ምናምን ነው የሚለው፤ ውሎ የሚገባበት አይታወቅም። ቢዝነስ የሚለው ምን እንደሆነ እግዚአብሄር ይወቀው፤ ከዚህ በፊት ሁለት ግዜ በስርቆት ታስሮ ተፈቷል። እናቴ፤ ‹ጓደኞችህ ናቸው የሚያበላሹህ፤ ከእነሱ ጋር አትግጠም› ትለዋለች፤ እሱ ግን አይሰማትም፤ ህይወቱ ጓደኞቹ ናቸው፤ እነሱም የሱ ነገር አይሆንላቸውም፡፡ ውሎው፤ አንዳንዴም አዳሩ ከነሱ ጋር ነው። አንዳንዴ ጓደኞቹን በድብቅ ቤት አምጥቶ፤ እራት አብልቶ፣ መኝታ ቤቱ ያሳድራቸዋል። ለዚህ ነው ሁልግዜ የመኝታ ቤቱ በር የሚዘጋው፤ እናቴ እንዳታውቅ፡፡
እንደጠረጠርኩት ሞባይሉ የተሰረቀ ነው። አይ መስፍን፤ የዋህ ነው፤ በዛ ላይ ደግ። ግን አይገባኝም፤ ሞኝነት አይሉት ብልጥነት ሌብነት ምንም አይመስለውም። ህይወቱንም ሊያበላሽበት እንደሚችል ጠንቅቆ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ የሰረቀውን እቃ ሸጦ ገንዘቡን ለጓደኞቹ ወይም ለእኛ ነው የሚበትነው፡፡
እኔ ራሴ ስራ የለኝም፤ አስረኛ ክፍል ከጨረስኩ ሁለት አመት ሆኖኛል፡፡ ዌይተርነት እንኳን የሚቀጥረኝ አጣሁ፡፡ ጊዜዬን ለእናትና ለወንድሜ ምግብ በመስራት ነው የማሳልፈው፡፡ እንደ ቀልድ ባለሞያ ሆኜአለሁ፡፡ ቤት መዋሌ ግን መስፍንን በጣም ይረብሸዋል፤ ሆድ ይብሳታል እያለ ይጨነቃል፤ እኔን ለማባበል ከአቅሙ በላይ ነው የሚያደርግልኝ፡፡ ከጓደኞችዋ እንዳታንስ እያለ ውድ ቀሚስ፤ ሽቶ፤ ምን የማይገዛልኝ ነገር አለ፤ ዛሬ ደግሞ ውድ ሞባይል ሰጠኝ። ስልኩን በማግኘቴ ብደሰትም አመጣጡን ስለማውቅ ጨንቆኛል፡፡
የስራ ፈት ነገር ሞባይሉን ስነካካ፣ ውስጡ ያሉትን ፎቶዎች ማየት ጀመርኩ፡-  የስልኩ ባለቤት ወንድ እንደሆነ ገመትኩ፤ ከሆነች ሴት ጋር ተቃቅፈው ሲስቁ፤ (ገርልፍሬንዱ ወይ ሚስቱ መሆን አለባት) የተጀመሩ ህንጻዎች፤ (ኮንስትራክሽን ስራ ውስጥ ይሆናል) ከጓደኞቻቸው ጋር ሲዝናኑ፤ የልደቱ፤ የሰርጉ፤ አቤት  የፎቶው ብዛት፤ ያለው ማማሩ፡፡ ቤታቸው ያምራል፤ የሚሄዱበት መዝናኛ ልዩ ነው፡፡ ለአፍታ ከኛ ኑሮ ጋር አነጻጸርኩትና ከፍተኛ የሞራል ኪሳራ በራሴ ላይ አደረስኩ፡፡ ብቻ ሳይፈቀድልኝ የሰው ኑሮ በቅናት ተመልካች ሆንኩ፤ በፎቶዎቹ ተመሰጥኩ፡፡
ኪሊሊው! ኪሊሊው! ስልኩ ጠርቶ አስደነገጠኝ፤ ‹ፍቅሩ› ይላል - ሳላስበው አነሳሁት፡፡
«ሀሎ ሀብትሽ! እየጠበቅንህ እኮ ነው፤  ሽማግሌዎቹ ሁሉ መጥተዋል፤ መስከረምም መጥታለች፤ አንተ ብቻ ነህ የቀረኸው» አለ የተጨናነቀ ድምፅ፤ ፍቅሩን ጆሮው ላይ ዘጋሁበት፡፡
መልሶ ሲደውል አላነሳሁትም፡፡
‹ጋሽ መኮንን› ቀጥሎ ደወለ፤ አነሳሁት፤ ሸምገል ያለ ድምፅ፤ «ሀብታሙ ምን አይነት ጨዋታ ነው፤ አንተው ጠርተኸን፤ ትጠፋለህ? ሀሎ አትናገርም እንዴ? ስትተነፍስ እኮ ይሰማል» ትንፋሼን እንቅ አድርጌ ያዝኩት፤ «መታረቅ ካልፈለክ ተናገር፤ ለምን ግዜአችንን ታባክናለህ፤ የልጅ ጨዋታ አደረከው እኮ! መስከረምም በጣም አዝናብሃለች፤ ሀሎ! ሀሎ! አይሰማም?...» ጋሽ መኮንን ቁጡ ሠው ይመስላሉ፤ አላስጨረስኳቸውም፤ ስልኩን ዘጋሁት፡፡
የስልኩ ባለቤት ሀብታሙ እንደሆነ አወኩኝ። ሻይ ጣድኩና ቁጭ አልኩ፤ ትንሽ ቆይቶ እንደገና ኪሊሊሊ፤ ‹መስኪ› ይላል፤ ዛሬ መደበሪያ አገኘሁ፤ ስልኩን አነሳሁት፤
«ሀሎ ሀብታሙ! በሽማግሌ ካልሆነ ያልከው አንተው ነህ፤ እንታረቃለን ብዬ ተስፋ ነበረኝ፤ አሁን ግን ቆርጦልኛል.. ከእንግዲህ ወዲህ እኔና አንተ ፍርድ ቤት ነው የምንገናኘው፤ ምን ይዘጋሀል? አትናገርም እንዴ…አንተ! አንተን እኮ ነው! ይዝጋህ፤ እንዳዋረድከኝ ቆይ አሳይሀለሁ» ብላ ስልኩን ዘጋችው፡፡ እረረ! ይቺማ እሳት ነች፤ ይቺ ከሀብታሙ ጋር ተቃቅፋ ፎቶዋን ያየሁዋት መስከረም መሆን አለባት፡፡
ሞባይሉ ዝም ብሎ ይጮሃል፤ አላነሳሁትም። ምን አለ ቢተዉኝ።
ይሄ ሀብታሙ የሚባል ሠውዬ፤ ከሚስቱ ጋር ጠብ ላይ ናቸው ማለት ነው፤ ሽማግሌዎቹና ሚስቱን ቆልሏቸዋል፤ አቦ! ይመቸው፤ ይሄኔ አቃጥላዋለች! ዛሬ አሪፍ መደበሪያ ነው ያገኘሁት፤ ይሄማ ከኢቲቪ ድራማ ይበልጣል፤ ለእራሴ አሳቀኝ፡፡
መስከረም እንደገና ደወለች፡፡ እስኪ ላስጨርሳት፤ አነሳሁት።
ሲቃ የተሞላበት ለቅሶ ይሰማኛል፤ ‹እኔ… እኔ… ለአንተ ክፉ ነኝ… እንደዚህ የጨከንክብኝ….› መቀጠል አቃታት፤ ወሬ የለም ለቅሶ ብቻ ሆነ፤ ‹እ እ እ ማውራት አልቻልኩም፤ ልረጋጋና መልሼ..እደውላለሁ› በሲቃ እየተንሰቀሰቀች፤ ስልኩን ዘጋችው፡፡
ከአንጀትዋ ነው የምታለቅሰው፤ የእኔ መደበሪያ፤ ለእሷ የምር ነው፤ ሙዴ ተከሸከሸ፤ በሰው ህይወትማ እንደዚህ አልቀልድም፤ አይ አሁንስ ደግማ ከደወለች፤ ‹ስልኩ ተሰርቆ› ነው ብዬ እውነቱን እነግራታለሁ፤ የዛኔ ምናልባት ሀብታሙ ለምን ሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ እንዳልመጣ ይገባታል፤ እኔንም ለቀቅ ታደርገኛለች! እንዳለችው ትንሽ ቆይታ ደወለች፡-
«ሀብትሽ!» አለች ለስለስ ብላ፤ ኦ! እውነትም ተረጋግታለች፡፡
«ሀሎ..ስሚ የኔ እህት...» አቋረጠቺኝ
«እንዴ! ማነሽ አንቺ?› አለች በድንጋጤ
‹የእኔ ማንነት ምንም አይሰራልሽም..ዋናው ነገር..›  እንደገና አቁዋረጠችኝ
‹ካንቺ ጋር ሆኖ ነው የጠፋው፤ እኔን ለማዋረድ ነው በአንቺ በኩል የሚያናግረኝ፤ እኔ ላይ ያን ያህል ይጨክናል፤ ክፉ!› በሲቃ ታለቅስ ጀመር፡፡
ነገሩን ወዴት ወሰደችው፤ አስደነገጠቺኝ፤ መኮለታተፍ ጀመርኩ፡፡ «ስሚ..ሀሎ..አዳምጪኝ...ሀሎ ይሄውልሽ ነገሩ...»
ወዲያው ለቅሶው ወደ ንዴት ተቀየረ፡ «ወይ ጉድ! አጅሬ በፍቅር እፍ ብሎ ነዋ፤ ትንሽ እንኳን አያፍርም፤ ሽማግሌ ሰብስቦ ካንቺ ጋር ሲሞዳሞድ፤ እነሱን እንኳን አክብር በይው›
‹መስከረም…ቆይ ላስረዳሽ›
‹ስሜንም ታውቂዋለሽ? ሌላስ ምን ነግሮሻል ስለእኔ፤ ጨቅጫቃ ነች፤ ሀይለኛ ነች፤ ሌላስ ምን ብሎሻል?› እንደገና ወደ ለቅሶ ተቀየረ፡፡
‹ምንም አላለኝም፤ አረ አታልቅሺ!›
‹ለምን አላለቅስም ትዳሬ ሲፈርስ፤ እኔን ይተወኝ፤ ግን ልጁ ያለ አባት ሲያድግ አያሳዝነውም?
ፎቶዎቹ ውስጥ ልጅ አላየሁም፤ የምን ልጅ ነው የምታወራው ‹እንዴ! ልጅ አላችሁ እንዴ?› አልኩ በመገረም፡፡
‹ኦ! ማርገዜንም አልነገረሽም? እሱንማ አይነግርሽም፤ ስሚ የእኔ እህት፤ የሰው ትዳር እያፈረሽ እንደሆነ ይገባሻል፤ ትልቅ ሀጥያት ነው፤ እግዚአብሄር የእጅሽን ይስጥሽ!
‹እንደሱ አትበይ…ላስረዳሽ..› አቁዋረጠችኝ
‹አግቢው! …መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ» ጆሮዬ ላይ ድርግም፡፡
ትዳር አፍራሽ ሆኜ ቁጭ! ተረበሽኩ!
ሴትየዋ ነቅላለች፡፡ ትንሽ ትረጋጋና ደውዬ በጥሞና ጉዳዩን አስረዳታለሁ፡፡ እስከዚያ የቀዘቀዘውን ሻዬን ላሞቅ ተነሳሁ፡፡ ሻዬን አሙቄ ስጨርስ መስከረም ጋር ደወልኩላት፤ «የደወሉላቸው ደንበኛ ቴሌፎን ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም» ይላል፤ ደጋግሜ ሞከርኩ፤ መልዕክቱ ግን ያው ነው፤ ይበልጥ ተረበሽኩ!!
ሻዩን ፉት እያልኩ በሞባይሉ ውስጥ ያሉትን ፎቶዎች እንደገና ማየት ጀመርኩ፤ ቅድም ፎቶዎቹ መደበሪያ ነበሩ፤ ለእኔ ምንም ትርጉም የሌላቸው ዝም ብሎ የሰው ጥርቅሞች፡፡ አሁን ግን  ተመልሼ ሳያቸው፤ ከሀብታሙ ጋር ተቃቅፎ የተነሳው ምን አልባት አብሮ አደጉና የቅርብ ጓደኛው ሊሆን ይችላል፤ ፍቅሩን አሰብኩት፤ ከበዋቸው የተነሱት ሽማግሌ  የሚወድዋቸው፤ የሚያከብሩዋቸው አቶ መኮንን መስለው ታዩኝ፤ በማያቸው ፎቶዎች ግዜ ታየኝ፤ ፍቅር ታየኝ፤ ህይወት ታየኝ፤ ሀብታሙና መስከረም ግዘፍ ነስተው ታዩኝ፡፡ ሀብታሙ ሚስቱን የሚያይበት ሁኔታ ---- ምን ያህል እንደሚሳሳላት ነገረኝ። የመስከረም ሳቅ በፍቅር መስከርዋን ያሳብቃል፤ የሚያንገበግብ ፍቅር! ውስጤ ገቡ፤ ቀረብኳቸው፤ ሳላውቃቸው አወቅኳቸው፡፡
ብዙ ነገር ማሰብ ጀመርኩ፤ ይሄኔ የማይረባ ነገር ነው ያጋጫቸው፤ ደግሞ ልጅ ሊወልዱ ነው! አባቴ ድሮ ጥሎን የሄደው ትዝ አለኝ፤ ቤታችን ሲበተን፤ እኔና ወንድሜ ስናለቅስ ---- በትዝታ ባህር ሰመጥኩ። ይሄኔ በማይረባ ግጭት ይሆናል፤ ልክ እንደ ሀብታሙና መስከረም፡፡ ሀብታሙ ሽማግሌ የሰበሰበው መፋታት ባይፈልግ ነው፤ መስከረምም ስብሰባ የሄደችው የሆነ ተስፋ ቢኖራት ነው፤ እንዴት ያዝኑ! ባልታሰበ አጋጣሚ ትዳርን የሚያክል ትልቅ ነገር ተበለሻሸ፤ በእኔ ጥፋት! በጭንቀት ተወጣጠርኩ፤ በማያገባኝ? መጀመሪያውኑ ይሄን ጣጠኛ ሞባይል ባላነሳው እዚህ ፈተና ውስጥ ባልገባሁ፡፡
አይ አሁንስ በቃኝ! ስልኩን ድርግም አድርጌ አጠፋሁት፤
ከእዚህ ሀሳብ ለመላቀቅ ሽሮ ልስራ ብዬ ተነሳሁ፤ ግን መላቀቅ አቃተኝ፤ ሀብታሙ ስልኩ መጥፋቱን እንዴት ነው እስካሁን ያላወቀው? የራሱን ቁጥር ደውሎ አይሞክርም እንዴ? ወይ ቴሌ ሄዶ ለምን አላዘጋውም? ጭንቅላቴ ሊፈነዳ ነው፤ የሀሳብ ዶፍ ማቆም አቃተኝ፤ እሺ ቆይ ስልኩስ ይጥፋበት፤ ለምን ቀጠሮ ቦታ አልሄደም?
የሚዘገንን ሀሳብ መጣብኝ! የሀብታሙን ስልክ ለመውሰድ እነ መስፍን ደብድበውት ይሆን? የሆነ ቦታ ወድቆ ይሆን? ውይ አምላኬ ሞቶስ ቢሆን! ግን መስፍን ይሄን ያደርጋል? እሱ ተራ ኪስ አውላቂ እንጂ ሰው ደብድቦ አይሰርቅም፤ ለራሱ ደቃቃ፤ ግን ማን ያውቃል ሰይጣን አሳስቶት ከሆነስ? ይሄ ሁሉ ለእኔ የልደት ስጦታ ለመስጠት? እኔን ለማስደሰት--- እንደዚህ አይነት ወንጀል ድረስ ይሄዳል? እረረ! ያን ያህልማ የሞራል ኮምፓስ ሊጠፋበት አይችልም። በምንም አይነት! እራሴን ለደቂቃ አፅናናሁ! ግን አንድ ሀሳብ እየተመላለሰ ይመጣብኛል፤ ከጭንቅላቴ ላጠፋው ያልቻልኩት - ምን ቢፈጠር ነው ሀብታሙ እንደዚህ ደብዛው የጠፋው፤መልስ ያጣሁለት ጥያቄ፤ ፈራሁ፤ በጣም ፈራሁ፡፡
መንተክተክ የጀመረውን ሽሮ ከከሰሉ አውርጄ አስቀመጥኩት፤ አፐታይቴ ሞቷል፤ ሀይለኛ እራስ ምታት ያዘኝ፤ መቆም አቃተኝ፤ መኝታ ቤት ገብቼ ፊቴን በትራስ ሸፍኜ ጋደም አልኩ፤ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ፤ ቅዠት የሞላበት እንቅልፍ።
‹ይቅርታ የእኔ እህት ሞባይል አይተሻል?›
ብንን አልኩ፤ የሆነ ሰው ከጎኔ ቆሟል፤ በህልሜ ነው በእውኔ፤ ፈንጠር ብዬ ተቀመጥኩ፡፡
‹ይቅርታ አስደነገጥኩሽ፤ ሞባይል አይተሻል?
‹ማን ነህ አንተ? እዚህ ምን ትሰራለህ?›
‹ሀብታሙ እባላለሁ፤ ትላንት ማታ ከመስፍን ጋር መጥቼ እዚህ አድሬ ነው›
ከአልጋው ተፈንጥሬ ተነሳሁ፤
‹እዚህ እቤት ነው ያደርከው?› ለነገሩ መስፍን ሁልግዜ የመኝታ ቤት በሩን ስለሚዘጋ ሰው ይኑር አይኑር አይታወቅም፡፡
‹አዎ! የሆነ ነገር ከመስፍን ጋር ስንጫወት ሳላስበው ከአቅሜ በላይ ጠጣሁ፤ በቃ ጨርቅ ነው የሆንኩት፤ በዛ ላይ ሰዐቱ ሄደ፤ እንዴት አድርጌ ቤት ልሂድ፤ መስፍን እዚህ ባያመጣኝ፤ የሌባ መጫወቻ ሆኜ ነበር፤ ለመሆኑ የታለ?›
ሌባ? ጉድህን አታውቅ፡፡
‹መስፍን በጠዋት ነው የወጣው›
‹እንቅፍልፍ ጥሎኝ ነው እንጂ እኔ ራሴ ከባድ ቀጠሮ ነበረኝ› ሰዐቱን እያየ ‹ለመሆኑ ሞባይሌን አይተሻል፤ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጬው ነበር?›
ኪሴ የከተትኩትን ሞባይል አውጥቼ ሰጠሁት፡፡
‹መደወል አለብኝ› ብሎ ሳሎን ሄዶ ተቀመጠ፤ ተከትዬው ሄድኩኝ፡፡
ሀብታሙ ስልኩን መደወል እንደጀመረ እጁን ይዤ አስቆምኩት፡፡
‹ሀብታሙ ከመደወልህ በፊት የምነግርህ ነገር አለ…› ጠዋት የተፈጠረውን አንድ  ሳላስቀር ነገርኩት፤ በእኔ ምክንያት ለተባባሰው ችግር ይቅርታ ጠየኩት፡፡
‹ታናሽ እህቱ ነሽ አደል? ትዝታ? አትጨናነቂ ባለማወቅ ነው ያደረግሺው፤ መስፍን ስላንቺ ብዙ ነገር አጫውቶኛል!  ነጥብ ሳይመጣልሽ ቤት መቀመጥሽ ያሳዝነዋል፤ ትማረራለች እያለ ይሰጋል፤ እንደዚህ የሚያስብ ወንድም ብዙ አይገኝም፤ እድለኛ ነሽ፤ በጣም ነው የሚወድሽ፤
‹እኔም በጣም ነው የምወደው፤ አንዳንዴ ግን ለእራሱ ቢያስብ ደስ ይለኛል፤ የሚረባ ጫማ እንኳን የለውም፤ የመስፍንን ጓደኞች አብዛኞቹን አውቃቸዋለሁ፤ አንተን ግን አይቼህ አላውቅም›
‹መስፍንን ትላንት ማታ ነው መጠጥ ቤት የተዋወኩት፤ ብቻዬን መቀመጤን አይቶ፤ ጓደኞቹን ጥሎ እኔ ጋ መጥቶ ተቀመጠ፤ እንደተረበሽኩ ገብቶታል፤ ይታይሽ እንግዲህ፤ አላውቀው አያውቀኝ፤ ብሶቴን የሚሰማኝ አገኘሁ ብዬ የትዳሬን ነገር አጫወትኩት፤ መጠጡም አለ፤ በቃ ውስጤ ታምቆ የነበረውን ጭንቀቴን፤ ብሽቀቴን እንዳለ ተነፈስኩ፤ እንዴት እፎይ እንዳልኩ! ያን ሁሉ ብሶት አወረድኩበት፤ እስኪ ምን እዳ አለበት፤ ከጓደኞቹ ጋር መዝናናት ሲችል፤ እሱ ግን በጥሞና አዳመጠኝ፤ በወጣት አቅሙ መከረኝ፤ ተራዬን አዳመጥኩት፤ የልጅ አዋቂ፤ ወንድምሽ እንዴት የበሰለ ልጅ መሰለሽ፤ አባታችሁ እንዴት ጥሎአችሁ እንደጠፋ አጫወተኝ፤ የእኛን ቤት ታሪክ አትድገመው ብሎ መከረኝ፤ አይኔን ገለጠልኝ! ሳመነታ የነበረውን የትዳሬን ነገር ቁርጠኛ እንድሆን አደረገኝ፡፡ መስፍን በጣም ባለውለታዬ ነው! እግዚአብሄር መልአክ ነው የላከልኝ›
 እረ መስፍን፤ ‹መልአክ› ተባለ? ሳስበው ፈገግ አደረገኝ፡፡
‹እረ፤ ባለቤቴ ጋር ልደውል፤ እስካሁን መቼም አብዳለች›
ሽሮ ላሞቅ ወደ ውስጥ ገባሁ - በዛውም ብቻውን በነፃነት ያውራ፤ በስሜት ሲያወራ ይሰማኛል፤ ትኩስ ሽሮ አቅርቤለት ከክፍሉ ልወጣ ስል በእጁ እንድቀመጥ ምልክት ሰጥቶኝ ተቀመጥኩ፡፡
‹መስኪዬ፤ እኔና አንቺ ሽማግሌ አያስፈልገንም፤ ይቅር እንባባል፤ እሺ? ቤት ስመጣ እናወራለን? የእኔ ቆንጆ እወድሻለሁ›
‹እኔም እወድሀለሁ፤ የእኔ ጌታ፤ ቻው!› ስትለው በስልኩ ይሰማኛል፡፡ ስልኩን ዘጋው፡፡
‹ሰላም ነው?› አልኩ የቀረበውን ትሬ ወደ እሱ እየገፋሁ፡፡
‹ሰላም ነው፤ ሁሉን ነገር አስረድቼአታለሁ፤ አይዞሽ ታርቀናል፤ አታስቢ›
‹እንዴት ነው መስከረም፤ በእኔ አልተናደደችም?›
ሳቀ፡፡ ‹ያንቺ ነገርማ በጣም ነው ያሳቃት›
እፎይ፤ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡ ሀብታሙ ተርቦ ኖርዋል!
‹እንደውም ልታገኝሽ ትፈልጋለች›  አለ በጉርሻ መሀል ‹ብዙ ነገር ተናገርኳት፤ በአካል አግኝቼ ይቅርታ ልበላት ብላለች፤ አንድ ቀን ከመስፍን ጋር ቤት ወስጄ አስተዋውቃችኋለሁ›
ሆ! ሆ! እኔ ሆንኩ ይቅርታ የምባለው፡፡ ያቀረብኩትን ሽሮ ጥርግ አድርጎ በላ፡፡
‹ጨረስኩት እኮ! በጣም ይጣፍጣል›
‹የስራ ፈት ነገር፤ ምግብ ስሰራ ነው የምውለው፤ በሱ እንኳን አሪፍ ልሁን እንጂ› አልኩ እየሳቅኩ፡፡
‹ትዝታ፤ እስኪ አንድ ሀሳብ ላማክርሽ፤ አንድ ያስጀመርኩት ፎቅ አለ፤ 60 የቀን ሰራተኞች የሚሰሩበት፤ ለምን አንቺ ምሳ አታቀርቢላቸውም፤ እዛ አካባቢ በሚያገኙት ምግብ ብዙም ደስተኛ አይደሉም፤ ምን ይመስልሻል? ላንቺም ጥሩ ገቢ ነው፤ እኔ መነሻ እንዲሆንሽ ሁሉን ነገር አመቻችልሻለሁ፤ ምን ትያለሽ?›
ላምነው አልቻልኩም! ተገኝቶ ነው፤
‹መስፍንንም ንገሪው፤ እፈልገዋለሁ! ታማኝ ካቦ ያስፈልገኛል›
ማሰብ ጀመርኩ፤ ‹መስፍን ታማኝ?› ልስቅ አልኩና ተውኩት፤ እኔ ብሎ ሰው ገማች!
ሀብታሙ ሊሄድ ተነሳ፤ በሩ ጋር ሲደርስ ምልስ አለ፤ ‹ውይ ረስቼው! ዛሬ ልደትሽ ነው ለካ?›
ሲም ካርዱን አውጥቶ፤ ሞባይሉን ሰጠኝ! ‹መልካም ልደት!›
 የ17ኛ ዓመት የልደት ቀኔን እንደዚህ ነው ያሳለፍኩት!


Read 1216 times