Tuesday, 07 June 2022 07:10

አነስተኛ አምራቾች በአፍሪካ ገበያ እንዲጠቀሙ የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሃቅ መልቲሚድያ እና ፕሪሚየር ኢንቨስትመንት ኮንሰልትስ በመተባበር ጥራት ያላቸው ምርቶች ለሚያመርቱ 500 የኢትዮጵያ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ በአፍሪካና በመላው አለም ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ ከገበያና ከኢንቨስተሮች ጋር የሚያገናኝ የ5 አመት ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ።  
የፕሮጀክቱ ዋና አላማ ጥራት ያላቸው ምርቶችን የሚያመርቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች ኢትዮጵያ በቅርቡ ከተቀላቀለችው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እና ሌሎችም የገበያና የኢንቨስትመንት እድሎች በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ መሆኑን የፕሪሚየር ኢንቨስትመንት ኮንሰልትስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ክንፈገብርኤል ገልጸዋል።
ለዚህም አላማ መሳካት ሁለቱ የግል ድርጅቶች ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ መላኩ፤ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ጥራት ያላቸው ምርቶችን የሚያመርቱ 500 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተለይተው አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶቻቸውን የማስተዋወቅያ መተግበሪያዎች በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከነዚህም ለማስታወቂያ ከሚውሉት መተግበሪያዎች ውስጥ ዋነኛ የሆነው የህትመትና የዲጂታል ቅጂዎች የሚኖሩት ‘የ2022 የኢትዮጵያ ምርቶች ካታሎግ’ (Ethiopian Products Catalog 2022: Promising SMEs Looking for Market and Investors) ዝግጅት በመገባደድ ላይ መሆኑን ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ከተመረጡት 500 ጥቃቅንና አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል በቆዳ፤ በዘመናዊና ባህላዊ በአልባሳት፤ በእንጨት፤ በብረታብረት፤ በኮንስትራክሽን ግብዐቶች፤ በእደጥበብና ተዛማጅ ምርቶችን በማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ እንደሚገኙበት አቶ መላኩ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከሚገኙት በተጨማሪ በተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ጥራት ያላቸው ምርቶችን የሚያመርቱ ጥቃቅንና አነስተኛ አምራቾች ከ500ዎቹ ጋር እንደተካተቱ ለመረዳት ተችሏል።
ይህ ሃገራዊ ፋይዳው ትልቅ የሆነ ፕሮጀክት ምንም እንኳን በበሃቅ መልቲሚድያ እና በፕሪሚየር ኢንቨስትመንት ኮንሰልትስ ተነሳሽነት ቢጀመርም፤ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን አቅም ያላቸው የግል ተቋማትና የመንግስት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ መላኩ ጥሪ አቅርበዋል።

Read 1140 times