Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 06 October 2012 14:57

አኮቴት ስለሚገባት እንስት ጋዜጠኛ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ሀተታ ሀ…
የዚህ ፅሁፍ መነሻ እውነት ነው…. እውነት እንደመነሻ እንጂ ያላግባብ ምስጋና ለማቅረብ ታስቦ አይደለም፡፡ ለመተዋወቅና ዝምድና ለመፍጠርም አይደለም፡፡
ጉርሻ ቢጤ ነገር ለማግኘት ማሞካሸት የሚል እሳቤም አልያዘም፡፡ የብልጠት ምስጋና እንዲሆን ታስቦ የተደረገም አይደለም፡፡ በፍፁም፡፡ በእውነት እውቀት እንጂ በብልጣብልጥነት የኖረ… የሚቀጥል ሀገር አለ ብሎ ጸሐፊው አያምንም፡፡ በመሆኑም የብልጠት መወድስ አይደለም፡፡ እውነት ግን ምክንያት ነበር፡፡ የሰራ ስው ሊወደስ እና ሊመሰገን ይገባል፡፡ የሚል እውነት ነው፡፡ ቤቴ ከባልንጀሮቼ ጋር ቁጭ ብዬ የማወራው… የሚያስወራ ርዕሰ ጉዳይ ከብዙ ጊዜ በኋላ በማግኘቴ የልቤን የእውነት ምስጋና ለማቀበል ያህል ነው፡፡
ሀተታ ሁ…


ጠጠር በምታክል የህይወት ተሞክሮዬ ውስጥ የማይረሱ እና ሊዘነጉ የማይችሉ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ የእውነትም ነበሩ፡፡ታዲያ ለኔ ቀድሞ የሚመጣው ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሀንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” ብለው በሬዲዮ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ በሬዲዮ ሲተላለፍ ባላዳምጠውም በመፅሀፍ መልክ በመታተሙ ለማንበብ እድል አግኝቻለሁ፡፡ ንግግሩ የተደረገበት ዋና መንስኤም አፄ ሀይለስላሴ ገነተ ልዑል ቤተመንግስትን ለዩኒቨርስቲ መገልገያ እንዲውል በማድረጋቸው ነበር፡፡ ንግግር ተባለ እንጂ ታስቦ የተፃፈ የሊቅ መፅሀፍ ነው ለኔ፡፡ ሀገሬ እንዴት ያለች የሊቅ ሀገር እንደሆነች ከሚያስረግጡ የሬዲዮ ንግግሮች መካከል እንዱ ነው ማለት ይቻላል፡፡
መፅሀፉን ያላነበባችሁት ብታነቡት መልካም ፍሬን ታገኙበታላችሁ በማለት ወደ ሚቀጥለው ሀሳቤ ልሻገር፡፡
ከሰማኋቸው እና እውቀት እውቀት ከሚሸቱ የሬዲዮ ፕሮግራሞች መካከል ከዛሬ 13 ዓመት በፊት ገደማ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይቀርቡ የነበሩት የ “እሁድ ጥዋት” እና “ቅዳሜ ወጣቶች” ፕሮግራም የማይዘነጉኝ ናቸው፡፡ በአንዲት ትንሽ የገጠር መንደር…በሰፈሩ ብቸኛ በሆነችው… በመቀጥቀጥ ብዛት የቢራ ጠርሙስ በመሳሰሉ ባትሪዎች በምትንቀሳቀሰው ያላምሬ ሬዲዮ የሱማሌ፣ የትግራይ እና የደቡብ ወንድሜን የሕይወት ልምድ፣ ተሞክሮ ያሳውቀኝ እና እሩቅ ሀገር ስላለው ኢትዮጵያዊ ወንድሜ መንፈሳዊ ቅናት ይፈጥርብኝ የነበረው የቅዳሜ የወጣቶች ፕሮግራም ድንቅ ነበር፡፡ ፕሮግራሞቹ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ፣ ወጣትነትን በእጅጉ የሚገልፁ እና የሚያንፁም ነበሩ፡፡ ወይ ጉድ! … እኔም በዚች እድሜዬ ነበሩ ካልኩ የሆነ ቦታ የተቋረጠ እና የተረሳ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ችግር አለ እንደማለትም ያስኬዳል፡፡
ትምህርት ቤት ሰኞ ጠዋት በእረፍት ጊዜ ለ15 ደቂቃ የምንወያይበትን ዕርሰ ጉዳይ የሚሰጠን ሌላው የሬዲዮ ፕሮግራም “ከመጻህፍት ዓለም” ነበር፡፡ በሚጢጢ አንጎላችን ስለገፀባህሪ አሳሳል፣ ስለሰው ምንነት የተከራከረንበትን ጊዜ አልረሳውም፡፡ ቃል የተባል መጸሕፍ ሲተረክ ጥጉ ይልማ ከጸሀይ ይበልጣል ብዬ በመከራከሬ የቀመስኩት ቦክስ ምልክቱ ዛሬም አለ፡፡ በአጠቃላይ ግን ለዛ ያላቸው እና ማንነትን የሚቀርጹ ፕሮግራሞች ነበሩ፡፡ ነበሩ… ነበሩ… ብቻ፡፡
ሀተታ…..
“ከትላንት ዛሬ ይሻላል ነው ይበልጣል” የሚለውን ሀረግ ከየት እንዳነበብኩት አላስታውሰውም፡፡ ዛሬ… በኔ ጊዜ ግን አብዛኞዎቹ በሬዲዮ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ልደትን ለማክበር የተሰናዱ ይመስላሉ፡፡ በኔ ጊዜ ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች በአራዳ ቋንቋ ብገልፀው … ለ‘ኢንጆይ’ የተቋቋሙ ይመስለኛል፡፡ ድረ ገፅ ላይ የተፃፈ እንግሊዘኛን ወደ አማርኛ ገልብጦ ማንበቢያ ጣቢያም ይመስሉኛል፡፡ ያልተጣራ መረጃ እና መረጃን ብቻ ለማስተላለፍ የተቋቋሙም ይመስሉኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ የክልል ከተማ ላይ የተቋቋመ የሬዲዮ ጣቢያ ስለ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ መለፍለፍ ፋይዳው ለኔ አይገባኝም፡፡ እንዲገባኝም አልገደድም፡፡ ይልቁኑስ የአካባቢውን እውነታ፣ ውበት ማንነት እና በራስ የመኩራት ባህል፣ በአጠቃላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነት ተኮር ስለሆነ ነገር በሬዲዮ ማውራት ግን ለብዙ አርቆ
አሳቢዎች ይገባቸዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ግሎባላይዜሽን’ ከሚያመጣው ጣጣ አንዱ መዋዋጥ ነው፡፡ የሀገሬ የሬዲዮ ፕሮግራሞችም መነሻ አላማ መሆን የነበረበት ከዚህ መዋዋጥ የምንወጣበትን መንገድ በማመልከት፤ ጥርት ባለ ኢትዮጵያዊነት መኩራት ምን ማለት ነው የሚል ሀገራዊ አንድምታ ያለውን ሀሳብ ይዞ መቅረብ ነው፡ ነገር ግን ፕሮግራማቸው ቀድሞ ከተዋጠ ወጤቱ አስፈሪ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ የሚዲያ ተፅዕኖ ክብደትን ሳስብ መጭው ጊዜ ያስፈራኛል፡፡ የወገኛ ነገር ሆኖብኝ እንጂ የጽሁፌ አላማ ስለጣቢያዎች የፕሮግራም ይዘት ማውራት አልነበረም፡፡ ግን ደግሞ በሰከነ አእምሮ እንዲያስቡ ጠቁሞ ማለፍ ክፋቱ አይታየኝም፡፡
ሀተታ አ…
ቀደም ብዬ ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት የጽሑፌ መነሻ አላማ ስለ አንድ ብርቱ እንስት የሬድዮ ጋዜጠኛ አኮቴት ማቅረብ ነው፡፡ ብርቱ እንስት የሬዲዮ ጋዜጠኛ ብዬ መፃፍ ስጀምር፣ መዓዛ ብሩ የምትባል የሸገር በተለይ ደግሞ “የጨዋታ እንግዳ” አስተናጋጅ ጋዜጠኛ በአንባቢያን አእምሮ እንደምትከሰት እገምታለሁ፡፡ በኔ ጊዜ እየቀረቡ ካሉት የሬዲዮ ፕሮግራሞች በተለየ መልኩ ብርሀን ለመፈንጠቅ የምትታትር ጋዜጠኛ ነች፤ መዓዛ ብሩ፡፡ እውነት ነው፤ እኛ ወጣት ኢትዮጵያዊያን የሆነ ብርሀን በማጣት እና የባዕድ ሀገር ተብለጭላጭ ብርሃን መሳይን ነገር በመሻት ውቅያኖስ ላይ እንደተጣለ ኩበት እየዋለልን እንደሆንን እኔን እንደማስረጃ ማቅረብ ወይም የጎረቤቴን ልጅ መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ዛሬ ከአድዋ ጀግኖች ይልቅ ቬትናም ላይ ጦርነት ያወጁ የአሜሪካ ‘ጀግኖች’ በልጠውብን በጣም በታመምንበት ሰዓት፣ “የጨዋታ እንግዳ” የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም መኖሩ እውነትም ይህች ሀገር ብዙ ተቆርቋሪ ዜጋ እንዳሏት የሚያመላክት ነው፡፡
አኮቴቴ የጨበጣ እንዳይሆን ግን ምክንያቶቼን ለመጥቀስ ልሞክር፡፡ የአዋቂ እይታ ስም ከማውጣት ይነሳልና ከስሙ ልጀምር፤ “የጨዋታ እንግዳ” ጨዋታ ለአብዛኛዎቻችን እንግዳ ቃል አይደለም፡፡ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለ የህይወት ምግብ ነው፡፡ ልብ ካላችሁ ደግሞ ቤተሰቦቻችን “ልጆች ጨዋታ ላይ ነን” ካሉ ቁም ነገር እየሰሩ ነው፡፡ እከሌ እኮ ጨዋታ አዋቂ ነውም ይባላል፡፡ በትያትረኛ ስንመለከተው ደግሞ በቅድመ-ቅኝ ግዛት በአፍሪካ ለትያትር መኖር ወይም መፈጠር ጨዋታ አዋቂዎች እንደመነሻ ምክንያት ይታያሉ፡፡ ጨዋታ የሚለው ቃል አስደንቆን ሳንጨርስ እንግዳ ይከተላል፡፡ እኔን፣ አንተን፣ አንችን፣ እኛን ሊገልፅ የሚችል ቃል ነው፡፡ በኢትዮጵያዊታችን ከምንኮራባቸው እና የጋራ መገለጫዎቻችን ከሆኑት አንዱ እንግዳ ተቀብለን ማክበራችን ነው፡፡ እንደ “ጨዋታ እንግዳ” አይነቱ ቀላል እና ሳቢ አገላለፅ የስነጥበብ አንዱ መገለጫ እንደሆነም ብዙዎች አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ይበልጥ ደግሞ አብረሀም በእንግዳ ተቀባይነቱ ሶስቱ ስላሴዎችን እንዳስተናገደ ሁሉ፤ በጨዋታ እንግዳ የቀረቡ ብዙ አዋቂ፣ መርማሪ፣ አርቆ አሳቢ እና ሀገርኛ የሆኑ ዘመዶቼ መሆናቸውን ሳስብ እውነትም ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንድል ይስገድደኛል፡፡ ከስያሜው ወጣ ብዬ መዓዛ ብሩን በአደባባይ እንዳመሰግናት ስላደረጉኝ ብዙ ነገሮች ለማውራት ትህትና የበዛው ድፍረት በቂ ይመስለኛል፡፡ መዓዛ ብሩ አብዝታ የጋዜጠኛ ስነምግባርን የተላበሰች፣ ለበቃ የጋዜጠኝነት ሙያ የተፈጠረች ብቁ ጋዜጠኛ ነች፡፡ እንዴት?
ስለጋዜጠኝነት ስነምግባር ሲወራ ቀድሞ የሚመጣው ጋዜጠኛ እውነትን የመሻቱ ጉዳይ ነው፡፡ መዓዛ እንግዶቿን ስታጨዋውት የተረዳሁት ነገር ቢኖር ይሄ እና ይሄ ብቻ ነው፡፡ ሀቁን በራሷ እይታ ለመተንተን አትደፍርም፡፡ አንድ ጥያቄ ጠይቀው መልሱን እራሳቸው እንደሚመልሱት እና በእንግዳቸው ላይ ተፅኖ ለመፍጠር እንደሚታገሉ ጋዜጠኞች አይነት አይደለችም፡፡ ሀቁ እንዲወጣ ግን የበሰለ የቤት ስራዋን ሰርታ ትመጣለች፡፡ አንዳንዴ “እንግዶቿ ከየት ያገኘችው መረጃ ነው?” እስኪሉ ድረስ ጥናቷ እጅግ በጣም ጥልቀት አለው፡፡ እንደአብዛኛዎቹ ልደትህ መቼ ነው የሚከበረው? የምግብ የመጠጥ፣ እና የልብስ ምርጫህ ምን ይመስላል? ድመት አትወድም አሉ? ጀምስ ቦንድ የተባለው ፈረንጅ አብሮህ እንዲሰራ ጠይቆህ ነበር? የሚሉ አይነት ጥያቄዎች ከመዓዛ አንደበት አልሰማሁም፡፡ ይልቁንም እውነት… በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ሊገነባ የሚችል ሀቅ እንዲወጣ እሳቷን ትለኩሳለች፡፡ ለኔ መረጃ እውቀት የሚሆነው በዚሁ ረገድ ነው ብዬ እተማመናለሁ፡፡
መዓዛ ለምታነሳው ርዕሠ ጉዳይ እራሷን ከምንጩ ትነጥላለች፡፡ ከስሜታዊነት የፀዱ ጥያቄዎችን በማሰናዳትም ከሙያው የሚጠበቀውን ስነምግባር ትጠብቃለች፡፡ በመዓዛ “የጨዋታ እንግዳ” የምናውቀው አንድ እና አንድ ነገር መዓዛ ብሩ የምትባል ጋዜጠኛ እንግዳ ስትጠይቅ ብቻ፡፡ ጥያቄዎቿም ከራስ ስሜት የፀዱ ናቸው፡፡
ለአድማጭ ፍላጎት እና ስሜት ቅድሚያ የምትሰጥ ጋዜጠኛ ናት፡፡ ይህ አይነቱ ስነምግባር አፍሪካ ውስጥ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ፈታኝ እና የማይታሰብ ነው፡፡ መዓዛ ጥቁር እንግዳ ብላ ከጋበዘች፤ እንትና የሚባል ግለስብ፣ እነእንትና የሚባሉ ሰዎች ወይንም እንትን የሚባል መደብ ይከፋዋል የሚል የደካማ ምክንያት ተብትቦ ሲይዛት እስካሁን አልታዘብኩም፡፡ ጥያቄዎቿ የማንም ተፅዕኖ ሲያደበዝዘው አይታይም፡፡ የሀቁ ጠቀሜታ ለአድማጯ እስካመዘነ ድረስ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አትልም፡፡
የመዓዛ ብሩ ሂስ እና የመቻቻል መድረክ
ይህ እንድፅፍ ካስገደደኝ ሁነኛ የመዓዛ ጥንካሬ መገለጫዎች የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ይገኛል፡፡ የምንጠያየቅበትን፣ የምንተቻችበትን እና ካለፈው ተምረን የወደፊቱን የምንተነብይበትን መድረክ በማዘጋጀት መዓዛ ትልቅ ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች፡፡ የታሪክ ክፍተቶች በበጎ እንዲሞሉ ትተጋለች፡፡ የትውልድ ቀጣይነት እንዲኖር መመኘት ብቻ ሳይሆን እውን እንዲሆን ትሮጣለች፡፡ በተለይ ደግሞ በ “ጨዋታ እንግዳ” የቀረቡ እንግዶች የዘነጋናቸው ወይንም በተዳፈነ አስተሳሰብ ከሆነ መደብ ጋር መድበን ቂም የያዘንባቸው፤ ሀቁ ሲወጣ ግን በየቤታችን ይቅር ይበሉን ያልናቸው ሊቃውንት ናቸው፡፡ እናም እንደ ሲኤንኤኑ ላሪ ኪንግ እና የሀርድ ቶኩ ስቴቨን ጆን ሳካር፣ መዓዛም ምርቱ ከገለባው የሚለይበት፣ ምክንያታዊ ዳኝነት ገዥ ሀሳብ የሚሆንብት መድረክ ነው የ “ጨዋታ እንግዳ”ዋ ፡፡አቦ መዓዛ ይመችሽ!
ከዚህ በላይ ስለመዓዛ ብቁ የጋዜጠኝነት ተሰጥኦ ለመተንተን ሰፊ እና ጥልቅ የጋዜጠኝነት እውቀት ይፈልጋል፡ለማድነቅ ግን ክፍት አእምሮ፣ ተራማጅ አስተሳሰብ እና ስሜት በቂ ነው ባይ ነኝ፡፡ነገ ብዙ መዓዛዎች እንዲመጡ እና ሌላ መዓዛ እንድናሸት ሁሌም በርችልን፡፡ በስተመጨረሻ መዓዛ “የጨዋታ እንግዳ” ብላ ሰዎችን መጋበዟ አንድምታው ምን ይሆን?.... ሙያው ውስጥ ላሉ ባልንጀሮቿ ብዙ ብዙ ነው መልዕክቱ፡፡ መቸም ለብልህ ሁለቴ አይነግሩትም፡፡
ለኛ… በየትኛውም ቦታ ተሰማርተን ቀና ደፋ ለምንል ወጣቶች ደግሞ ቃሉ ሰፊ ነው፡፡ በ “ጨዋታ እንግዳ” ከቀረቡ ልሂቃን መካከል የአንዱን ሊቅ ንግግር ልውሰድና እኔ እንደሚመቸኝ አድርጌ ላቅርበው፡፡ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የመጀመሪያ፣ የማትቀየር እና ምርጫ የሌላት እጮኛው ኢትዮጵያ ናት፡፡
የዚችን ድንቅ እጮኛ ሁኔታ እና ያልተፈታ እውነት ለማወቅ መጠየቅ፣ ጠይቆም ደጉን ከክፉ መለየት፡፡ ምክንያቱም እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ መጠየቅ ይበልጣል፡፡ ከመጠየቅም ደግሞ እጅግ በጣም መጠየቅ ያዋጣል፡፡ እንደ ሀገርም እንደራስም ለመኖር ሳናስተውል “አብቅቶላቸዋል… ያዛውንት ቃል ምንተዳዬ” ብለን የዘነጋናቸውን ፣ በአካባቢያችን ያሉ አዛውንትን እየጠየቅን መቅረፅ፣ መሠነድ ክፍተታችንን ለመሙላት አማራጭ የሌለው ማለፊያ መንገድ ነው፡፡

Read 3393 times