Sunday, 05 June 2022 00:00

የዝንጆሮ ፈንጣጣ በ30 የአለማችን አገራት ከ550 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱ ተነግሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአለማቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የሚገኘው የዝንጆሮ ፈንጣጣ እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በ30 የአለማችን አገራት መገኘቱንና በድምሩ ከ550 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱን የአለም የጤና ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን፣ በ7 የአፍሪካ አገራት የተገኘው ቫይረሱ በአህጉሪቱ 1 ሺህ 400 ያህል ሰዎችን አጥቅቷል ተብሎ ይገመታል፡፡
በድርጅቱ የዝንጆሮ ፈንጣጣ በሽታ መከላከል የቴክኒክ ቡድን ሃላፊ የሆኑት ሮሳሙንድ ሊዊስን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፤ ቫይረሱ ከዚህ ቀደም ታይቶባቸው በማያውቃቸው በርካታ አገራት በብዛትና በፍጥነት መገኘት መጀመሩ ያልተለመደና አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ቫይረሱ በመላው አለም የሚገኝበት የስጋት ደረጃ መካከለኛ ተብሎ የሚነገር መሆኑንና በአሁኑ ደረጃ አለማቀፍ ወረርሽኝ ተብሎ የሚጠራበት ሁኔታ ላይ አለመሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፤ ምናልባትም ወደ አደገኛ ደረጃ ሊያድግ የሚችለው ወደ ህጻናት በስፋት የሚዛመት ከሆነ ነው ማለቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ የዝንጆሮ ፈንጣጣ ቫይረስ እንደገባባቸው የተረጋገጡ አገራት ላይቤሪያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ናይጀሪያ፣ ካሜሮን፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክና ሴራሊዮን መሆናቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ ከእነዚህ አገራት መካከልም በኮንጎ 9 በናይጀሪያ ደግሞ አንድ ሰው ለሞት መዳረጉን አመልክቷል፡፡


Read 5470 times