Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 06 October 2012 14:52

Q ጦር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ይሔ አካሄድ አፎቱ ሁለት ነው፡፡
አንድም በራሱ… አንድም በእኔ፡፡
***
የሁለቱም አይደለችም፡፡
መሬት ላይ እንደሚውድቁት ካርታዎች ዋጋ የላትም፡፡
ቀድማ ራሷን ዲካርድ ስታለች፡፡
***
ዙሩ ከሯል፡፡
አይኖች የሚጣሉት የሚነሱት ላይ ጦራቸውን ወድረዋል፡፡
እጆች ድል ለመምዘዝ አሠፍስፈዋል፤… አሁን አብይ ከዘጋ ሶስተኛው ስለሆነ… ይቦንሳቸዋል፡፡ አኪር እያፏጨች እየዘፈነችለት ነው፡፡ …/አንዳንዴ ይሔ ልጅ ካርታው ላይ ምልክት አድርጐበታል እንዴ/ ይላሉ… እኔ ደግም በተከታታይ አንዴም ሳልዘጋ ተበልቻለሁ፡፡ …በተከታታይ ቸክዬ ካልዘጋሁ… ከከተማ ውጭ አብሬአቸው አልሔድም፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልኩ ቁጭ ብዬ መውደቄ ነው፡፡
***


ከአለም ብርሃን ጀርባ ነፋሱ ከፈጣሪው ጋር ትግል የገጠመ ይመስል… አስቀያሚ ሽታና አቧራ እየቀላቀለ ይገማሸራል፡፡ በግ አራጆች አርደው የሚደፉት ፈርስና አንጀት ሽታው አፍንጫ ይሰነጥቃል፡፡
የግራዋው ጥቅጥቅ ደን ውስጥ… አብነትና ካሱ ወደል ድንጋይ ተንተርሰው… በጀርባቸው ፈልሰስ ብለው… ከእግዜር ለመከለል…
በአብነት ጠይም ሻርብ ፊታቸውን ከገዛ ሀፍረት ቡዳነት ጋርደው… በከንፈራቸው ዳንቴል ይሰራሉ… የካሱ ግራ እጅ በአንገቷ አልፎ ሁለት ሥራ እያከናወነ ይገኛል… እቅፍ አድርጐ በደረቷ ገብቶ ብሎን እንደሚፈታ መካኒክ የጡቶቿን ዳዶ (Nipple) በስሜት ያጠብቃል…
አብነት ቀስ እያለች መንሳፈፍ፣ ግራ እግሯን ከካሱ ጭኖች ስር ጥብቅ አርጋ ወተፈች… ፍንክንክ… ቅ.ብ.ጥ.ብ.ጥ… አለች፤ ከስር ልምላሜ የራቀው አፈር መልካም ነገር ድርቅ የሆነበት… ከላይ በመጠኑ ፈገግታ የተኳለች ፀሐይ ብቻ ናቸው የሚያዩዋቸው፡፡ ግራዋዎቹ በድን ናቸው፡፡ ጣዕማቸውም ሽታቸውም መራራ ነው… /ቅንነት እንደጐደለው ሰው/ የአብነት ግራ እጅ የካሱን የሱሪ አዝራሮች መነካካት ጀመረ… ከመሬት ከፍ… ከግራዋው… ዝቅ ማለት ጀመሩ፡፡
***
አፈሩ… ቦነነ፡፡
***
አካሉ በጣም ጨንቆታል… ፊቱ በሳማ የተለበለበ ሥሥ ገላ መስሏል፡፡ በተመስጦ ስለሚከታተል… አፉን ገርበብ አድርጐ ከፍቶታል፡፡
ሁለቱ የተነቀሉት የፊት ጥርሶቹ የራበው የህፃን ልጅ ሆድ ይመስላሉ… ጭንቅላቱ ትልቅ ስለሆነ… Kwasharkor የያዘው ነው የሚመስለው፡፡ (በጭቃ የተጠፈጠፈ አሻንጉሊት… ለዛውም ህፃናት የጠፈጠፉት)
***
ሁሉም የአብይን እጅ ይከታተላሉ… /እንኳን ካርታ ቀርቶ ከአፍ ውስጥ ምራቅ ይሠርቃል/ ግን ምኑ ውስጥ እንደሚከተው ማንም አያውቅም፡፡ ለእኔ ግን ሌሎች ከሚዘጉ እሱ ቢዘጋ ይሻለኛል… ምንም ይሁን ምን ይበጥስልኛል፡፡
***
አካሉ ከጭንቀቱ የተነሳ አቧራ ላይ የተርከፈከፈ ውኃ የፈጠረው ቅርፅ ፊቱ ላይ ይታይበታል… እየቆየ እየቆየ… የተጨመቀ የዳማከሴ ቅጠል ይመስል… ደሙ እየቀዘቀዘ መጣ… በየደቂቃዎች ይለያያል…
አብይ ቀና ብሎ ሲያየኝ ጠቀስኩት… Q ጦርን ትቶ ሳበ… ስምንት ልብ ነበረች… ጆከር ለመሬት ጥሎ ቦነስ ቦነሳቸው፡፡
አካሉ ካርታው እጁ ላይ እንዳለ… በጀርባው ወደቀ… ሰውነቱ በቸንካር ተገድግዶ ፀሐይ እንደጐበኘው የለፋ ቆዳ ተወጣጠረ… አፉ ደረቀ ደፈቀ… ልክ እንደተገነደሠ ግንዲላ በተቀመጠበት ግምስ ሲል… አቤላ ቀድማ አይታው ስለነበር… ግራ እጇን የሞት ሞቷን ሰደደችለት… እጇ ባይታደገው ኖሮ… የእነ ነፃነት የበሠበሠ የማድቤት ቆርቆሮ አንገቱን ይሸረክተው ነበር…፡፡ እየተንፈራገጠ አረፋ እየደፈቀ ሁሉም “ክብሪት… ክብሪት” እያለ ሲሯሯጥ… አብይ ዘጠና ሶስት ብር ቆጥሮ ኪሱ ከተተ…
አካሉ ሲጨናነቅ… ሁሌም ፈንግል እንደ በረታበት አውራ ዶሮ መፈንገሉ የተለመደ ነው፡፡ ብዙ ክብሪቶች ተተርኩሠው ጭሱን ምጐ… ረጅም ሠዓት እንደተኛ ሰው ብንን ብሎ ነቃ…! (ሁሌም የማይገባኝ አንድ ነገር አለ… እንዲህ ወድቆ ለሚንፈራገጥ ሰው ክብሪት ሲለኮስ ነው፤… እርቦትስ ቢሆን…? ወይ ሌላ ነገር… ላይክ… አጋንንት… ወይም ሌላ ሌላ ነገር… ብቻ ሌላም ሌላም እኛ የማናውቀው እግዜር የሚያውቀው … ልክ ተመራማሪዎች የሽበትን አሸባበት መንገዱን እንዳልደረሱበት… ወይም ደግሞ… የእናትን የጡት ወተት እነሱ እንዳልፈጠሩት… አይነት…) አብይ እቅፍ አደረገውና … ስድስት ብር በግራ እጁ አስጨብጦ ወደ ታች… ወደ አለም ብርሃን ሸኘው፡፡
ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ለመጫወት ሲሠየም... ይጨንቀናል… ሲበላ /ይጠብቃል/ ስለሚወድቅ… ሙዳችንን አብሮ ያንፈራፍረዋል፡፡
“እወድሃለሁ”
“አውቃለሁ”
“እንዴት ልታውቅ ቻልክ?”
አይኖቿን እያየ ሳያንኳኳ ወደ ውስጥ ያለ ከልካይ ጠለቀ… በረበራት… ባለ አራት ክፍል ልቧ ሁለት መደብ እንዳለው አየ… አንዱም ግን እሱን አላስቀመጠም…
“መልስልኝ እንጂ…?” አለችው በአይኗና በከንፈሯ ለማሽኮርመም እየጣረች…
“እ…” ባነነ፤ ቆሞ መተኛት… አቅፎ መናፈቅ… ልክ ሽሮ እየተመገቡ የመራብ ያህል ደነዘዘ… ተስገበገበ!፡፡
“ስለ… ስለምወድሽ እንደምትወጂኝ አውቃለሁ…” አላት… ሞኝ… ወንዝ ዳር ተተክሎ የደረቀ ቄጤማ…! ጨለማ ውስጥ ያቀመሠችውን ትርፍ ከንፈሯን እያሰበ ልቡን የሸና ጅል! ብልጠት ያልተሞላበት ስስ… ቀዳዳ… ሥልቻ…! እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልጥ መሆን ያልሞከረው ቀረፎ… አይጥ አድና ወደ ግልገሎቿ እንደምትበር ቀበሮ፣ ሳንቲም ሲያገኝ ይፈልጋታል… እሷ ነፋስ… እሱ ገለባ… እሱ ለሷ ምኑን እንደመረጠችለት አታውቅም… ደረቱ በፑሻፕና… ብረት በመግፋት ዳብሮ ጥሩ ቅርፅ አለው፣ መጀመሪያ አግኝታው ውራ ያደረገችው ብልጥ መሣይ ሞኝ ናት… አብነት፡፡ ጠዋት አግኝቶ አይን አይኗን እያየ ያላንዳች ወሬ በመዳበስ ብቻ ይመሽበታል፡፡
***
ከጥቂት መደናዘዝ በኋላ ካርታው ተፐውዞ ታደለ… የነጺ እናት “ስልክ” ብላ ጠራችኝ… ሠምቻለሁ ግን ለመጫወት ስለጓጓሁ… ዝም አልኳት… /ላሽ/ “አንተ ደማ… እየጠራሁህ አይደለም…!” ተቆጣች /ደማ ቅፅል ስሜ ነው… ማን እንዳወጣልኝ አላውቅም… እትዬ መስቀሌ ማር ማለት ነው ብለውኛል… ድንቄም! እኔን የመሰለ ያልታጠበ ቡሃቃ ፊት ማር ሲባል “ማነው” አልኳት ያልሠማሁ በመምሰል…
“እኔ… ምን አውቅልሃለሁ ማን እንደሆነች… ብለህ ብለህ… ለህፃን ልጅ ደውሉልኝ ማለት ጀመርክ?!” ሁሉም ሳቁብኝ… አብይ ጠቀሰኝ…
…ጥቅሻው ማፅናኛ ጠብደል ጉርሻ መሆኑ ነው፤ አብዬ የአብነትን ድምፅ ያውቀዋል… አምልጦት ከት ብሎ ሳቀ… “እመለሳለሁ” ብዬ ካርታዬን አስቀምጬ ተነሳሁ… ሁሉም እኩል በሉ የተባሉ ይመስል…
“አጠሪራ አድርገው እሺ…” ብለው አልጐመጐሙብኝ… ሸዋለም ቶሎ በል በሚል ግልምጫ አይሉት ቁጣ ገሸለጠችኝ… ቁጣዋ አይሰማም እንጂ ጠንካራ ወረቀት ሲቀደድ አይነት የሚያሰማውን ስሜት ይመስላል፤
ያን ጐርፍ የሰረሰረው የመሠለውን ምድር ቤት በሁለት እርምጃ ፉት ብዬ ቤቷ ግራ ክንፍ እጥፍ አልኩ…
“ሔሎ…”
“ምን መሆንህ ነው… የዚህን ያህል የምትጀነነው…! …ከጐንደር ነው እንዴ የምትመጣው?!…” ተቆጣች አይገልፀውም…
“አብሽዬ… ይቅርታ… ፀጉሬን እየታጠብኩ…”
“ሲበቅልም የዚህን ያህል አልቆየ እንኳን መታጠብ…!” ድጋሚ አምባረቀች… ላስተባብል ስል…
“ተወው ተወው ጀብ መሠልኩህ… በዚህ ሰዓት እደውላለሁ… እዛው ቦታ አንዣብ አላልኩህም!”
“እዛው ነበርኩ እኮ…” ውይ ቅሌት… ማለቴ እዛው ነበር ስታጠብ የነበረው…” ከት ብላ ሳቀች፤ ውሸት እንደማልወድና እንደማልችልበት ታውቃለች፡፡
“ለማንኛውም… ደደብ!…”
“ማን?” ድምጼ ከውኃም ቀጠነ… የሆነ ቦጭረቅ ያለ ድምጽ አሰማሁ…
“ደደብ!… እንዴት አይገባህም…? ያ… ደደብ ወንድሜ ነዋ!”
“እ…” ትንፋሼ የተመለሠውን ያህል ተበጣጠሠ… አብዬ ሥትስቅ ጠይም አደይ አበባ ትመስላለች /የእናቴን አይነት/ ስትቆጣ ግን ለዛዋ ይሟጠጣል… ሙሉ ፊቷ የኮሽም እሾህ ይመስላል … ምንም የሚስብ ነገር የላትም!
“ፍቃድ ሥለከለከለኝ … የተባባልንበት ቦታ አልሔድም!… ያቺ ተልባ አፍ ነግሬአት… ስትነግረው ቀረች… ለዛ ነው… በጣም ስለተበሳጨሁ ራስ ምታቴ ተነስቶብኛል እና ቅቤ ስለምቀባ ከቤት አልወጣም፤ እስቲ እኔን እያየ ኪሎ እንደሚጨምር አየዋለሁ…” ድጋሚ ክው አልኩ…፡፡ ቀጠሯችንን ከነገርኳት ቀን ጀምሮ ሁለት ቀን እንቅልፍ እምቢ ብሎኝ ነበር፤ እንትኗን ለመውሰድ መጽሐፍ አገላብጬ ያላገኘሁትን ምክር እናብዬ ነገሩን… በሶስተኛው ቀን የምደግምበትን ወጪ አብዬ እንደሚሠጠኝ ቃል ገብቶልኝ ነበር… ያ ሁሉ እቅድ… ያ ሁሉ ፕሮጀክት መና ቀረ…
የማንም አለመሆን ከባድ ነው!...
በተለይ ከራስ መራቅ…!
አርፎ አለማረፍ… ከህሊና መጋጨት… ከፈጣሪ መጣላት… በመንፈስ መታመም… ርቀው ላይርቁ መብረር… ሳይተኙ መባነን፣ መበርገግ… መንገድ ላይ ያገኙትን እየቀመሱ /ላይጥም/ መሔድ፤ በመኖር ውስጥ መጉደል… በመጉደል ውስጥ ማነስ… በማነስ ውስጥ አለመኖር… አለማለም… ብርሃንን ተስፋ አለማድረግ… መነሻን መርሳት… እሚደርሱበትን አለማወቅ… የሆነ ሰው ነኝ ብለው እያሉ… የማንም አለመሆን… የራስም!… ይሔ… ላመነ… ፈጣሪን በመፍራት ለሚኖር ሰው ከመክበድም በላይ ከባድ ነው፡፡
***
ስንት ህልም ቋጥሮ፣ ፈትቶ… የወንድነት ልኩን የሚያይበትን ቀጠሮ ወፏ ቀረችበት (ሴቷ)… ዛፉ ቅርንጫፉ ደረቀ… ውኃ የሌለው መሬት ፍሬ ያለው ዛፍ አይኖረውም… ወንዱ ወፍ አኮረፈ፡፡ ስልኩን ዘጋና ለምቦጩን ዠልጦ… ካርታው ጋር መጣ፡፡
***
ቆቅ፡፡ አብይ ቀና ብሎ አየኝ… ፊቱ የዘንጋዳ ሊጥ መስሏል፡፡ እኔ ደግሞ አመዳምነቴ ላይ ሌላ አመድ ተነስንሷል… ውስጤ የጠፋ እሳት ይመስል ጨሠ…፤ በልቤ ወንድሟን በምርጥ ብልግና ሰደብኩት… (እናቴ መሳደቤን ብታውቅ ታዝንብኝ ነበር) ሲያንሠው ነው፡፡ ሸዋለም… እዛው ዋሻ ውስጥ ሆና (ቁጣዋ ስለት ነበረው) “አንተ… ቆረቆራም… እኔ ያንተ ኦፕሬተር ልሁን… ና!… አናግራት… ቆይ…” እጇን ወደ ላይ ቀስራ… “ልጅህ ናት… ምንህ ናት?” የሷ መጮህ ሳያንሠኝ… ሁሉም ሳቁብኝ ድጋሚ፤ ከወንድሟ መከልከል በላይ ሳቃቸው አመመኝ፡፡ የሸዋለም ቁጣ… ጣት ውስጥ እንደ ተሠነቀረ ስንጥር ቆጠቆጠኝ… “ኧረ… ተጐረመሠልኛ…” አለች…
እግሬ የምድር ቤቱን ደረጃ ሳይረግጥ ካርታውን ፐወዙት… ይበልጥ ተበሳጨሁ… “አቤት” ትዕቢት ልቤን ነፋው!… ለመለሳለስ አልሞከርኩም… ይብስ ሽልጦውን እንደ ነጠቁት ህፃን ተጉረጠረጥኩ… ከሥልኩ ውስጥ ሥሜቷ ታወቀኝ… አብቲ ቱግ ሥትል… “አንተ ነህ… ሳታስጨርሠኝ ጆሮዬ ላይ የምትዘጋው?” ድምጿ እንደ ጅራፍ ጮኸ… ሁለት ነገር ተሠማኝ… እቺ ልጅ… እየወደደችኝ ነው?… ወይስ ስትፎግረኝ?…
“ምን ፅናት ኖሮኝ እንድሰማሽ ትፈልጊ ነበር…?” ፎቶ የተነሣን ቀን የሳመችኝ ትዝ አለኝ…” ልቤ ሞላ… ወጠር አለ፡፡
“እስቲ አስቢ… እማዬን ስንትና ስንት ነገር ፎግሬ … ያ … ጣውላ ራስ ወንድሜን … እግሩን ልሼ… ያስፈቀድኩትን ምርጥ አጋጣሚ ዝም ብለሽ… ‘ወንድሜን እምቢ አለኝ’ ትይኛለሽ…!?”
“እና ምን ማድረግ ነበረብኝ…! እስቲ ንገረኝ … ምን ማድረግ ነበረብኝ? ቁጣ … ንዴት … መብገን … መንተክተክ… ‘እውነት ምን ማድረግ ነበረባት … አበሻን ለመሠለች ለጋ ቅቤ … ፍቅር የሚበረታው ብልግናው ሲበዛ ነው የሚመስላት … በዚህ በዚህ ደግሞ … ካሱ ላባዋ እስኪርገፈገፍ … ያስደስታታል … አጥንቷ እስኪልም … ቀሚሷን ሳይሆን ገላዋን ቀዳለታለች፡፡
“አንቺ እውነት መሔድ ብትፈልጊ ኖሮ … ተወዉ በኔ መብት መወሠን አትችልም ብለሽ አትነግረውም?!”
“ተመልሼ የት ልገባ…?” አሮጊት ይመስል ተንጣጣችብኝ … “ስማ እዛ ቤት ልታሠራልኝ መሠለህ የምንሔደው…? … ወይስ ስንመለስ እናንተ ቤት ልኖር…?” አሸሞረች … ገባኝ … የእና ሶስት ክፍል ቤት ለእኛም እንዳማይበቃን ታውቃለች፡፡ ከርግብ ቤት ትንሽ ነው ከፍ የሚለው … ቀለም ስለተቀባ … ድምጿ ውስጥ የፉጉ ቃና ነበረው፡፡
“እና በቃ አትሔጂም…?” የእውነቱን አዝኖ ጠየቃት … ፊቱን ላየው አጭር የሀዘን ደብዳቤ ነው የሚመስለው፤
“አልተግባባን እንዴ…? አማርኛ እያወራን … ሌላ ጊዜ አመቻችተን እንሔዳለን … እ… እ… ናንተስ ምን ላይ ደረሳችሁ…?” መሔድ አለመሔዳቸውን ለማረጋገጥ የፈጠነችው ፍጥነት … ይሔን ሁሉ ተከትሎ ሀሳቡን ለመስማት የመቸኮሏን ጉጉት እንደቀዘቀዘ አጥሚት ጣዕም አልባ አደረጋት፡ …
“በቃ አብይም እኔም መሔዱን ትተነዋል … ማንም የሚሔድ አይመስለኝም” አፌን መረረኝ … የሁሉን ድምዳሜ ተናገርኩ… የተበላሸ ለውዝ የበላሁ መሠለኝ… እሷ ድምፅ ውስጥ ግን እ.እ.እ… የሚል ጉጉት የሚወልድ ፅንስ ያለ ይመስላል…
“ቻው እሺ …” ትንፋሿ እርካታ ነበረው … “እወድ…” ሳትጨርሰው ዘጋሁት … እሷም መልሴን ሳትሠማ ቀረች … ‘ምን ሆኜ ነው ግን ከዚች ልጅ ጋር ፍቅር የያዘኝ …’ ድምጿ ይጣፍጣል … ዐይኖቿ ከወንዝ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ ነው የሚመስሉት … መቀመጫዋ አርክቴክቶች ተሠብሥበው፣ ተጨንቀው፣ ተጠበው የሠሩት የማዕዘን ድንጋይ ይመስላል … “በምን ፍርጃ ነው እንዲህ እፍ ያለ ፍቅር ውስጥ የገባሁት …?” መልስ የሌለው መደመር … መቀነስ የሌለው የሒሳብ ሥሌት … ማባዛትስ …? ማካፈል ግን ትትላለች … እሷ … እ…፡፡
እንደቀልድ አሁን ጳጉሜ ሁለት አመት ይሞላናል…እኔ ለሷ በበረዶ ምጣድ ላይ የተጋገርኩ ቂጣ ነኝ…እሷ ለኔ ቃተኛ…ጣት ምታስልስ፡፡ ላጠና ደብተሬን ስዘረጋ ፊደሎቹ “ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ መሆኗን…ፊደል እየፃፉ ይነግሩኛል…ለድመት ማስቸገሯን ጭምር፡፡
የስልኩን እጀታ ዘግቼውም እጄ ላይ ነው…ሙዴ ዘጭ ብሎ የበጋ ጭቃ ላይ ተነከረ፡፡
***
አብነት…ክንፏ እንደገጠመላት የቤት ርግብ…ተር ተር ብላ ሳቀች…ቤቱ ውስጥ ማንም አለመኖሩ እሱ አንሄድም ካላት በላይ አዘለላት፤ ራቁትነት ተሠማት…ሰው ቢኖርማ ለመደወልም ባልሞከረች፣ መልሳ የስልኩን እጀታ አንስታ ከሱ ጋር ቁጥሮቹን መታች…ኩይሳ ስሜቷን ለመናድ…፡፡
***
እቺ…ጡት እንኳ በቅጡ ሳታበቅል እንዲህ ልቧ የስምንት ሴሰኛ ሴቶች ያህል አቅል ያሳጣት ልጅ…እየበረረች ካሱ ጉያ ትወተፋለች…ካሱ ደግሞ እንኳን ጉርሻ ጉረስ ተብሎ ቀምቶም ለመብላት የሚመለስ አይደለም…ስትበር ስትበር ትመጣና ዛፍ ሆኖ ይጠብቃታል…ለዛውም ጐጆ ያለው ዛፍ…ከብዙ ነገር ያሳርፋታል፡፡ ስክን ያደርጋታል…እንዳትታፈስ አድርጐ ያፈሳታል፡፡
***
ደረጃው ላይ በተሠነጠቀ የላስቲክ መዘፍዘፊያ ፓንትና ካልሲ የምታለቀልቀዋ ሸዋለም ቀና ብላ “ምን ሆንክ ደግሞ…?” አለችኝ፤ ለካ የታችኛው ለንጨጩ ደረቴ ላይ ተለጥፏል…“ምንም፡፡”
አልኳት ሳላያት…ድምጼ ራሱ እምክ እምክ ሸተተኝ… “ተዋት…ወሔነት የገጉ” ሳቀች ወይም ሳቀችብኝ…የዋህ ስለሆነች ሳቋ እንደ ጨጨብሳ ይጣፍጣል…ሁሌም ሸዋለም…ትተርታለች…”ደግነት ለራስ ነው…ነው…ወሔነት የገጉ” እውነት ነው…ደግ መሆንና ታማኝ መሆን ለራስ ነው…የሰው ልጅ ሌላኛውን ሰው ከመዋሸቱ በፊት የገዛ ህሊናውን ቀድሞ መግደል አለበት…
ተመልሼ ጨዋታው ጋር መጣሁ…ተሰየምኩ (ቆሞ ማየት እስኪያልቅ) ቅድም የአካሉ ጠረን የሸተተኝ መስሎኝ ነበር…ለካስ የራሴ ስራ ነው እንዲህ እንደሞተ የውሻ ቡችላ የሸተተኝ…ስለ ተበሳጨሁ…ሰውነቴ ግሏል…ካርታውን እያየሁ ባቦ ጋያ ከአብሻ ጋር ውሃ ውስጥ ተከለመኝ…እየተሯሯጥን…በነዛ በሚያማምሩ ሳሮች ላይ/ሳልከልማቸው በሀሳብ/ እያንከባለልኩ ሳንከባልላት…እየሳምኩ ስመጨምጫት..እጆቼን ያለ ከልካይ…አካላቷ ላይ ሳነግሳቸው…ከንፈሯ ላይ ዋሽንት ስነፋ…
እሷ እስክስታ ስትመታ…መታ…መታ…አለው ደስታ አይነት ነገር…
በተለይ እጆቼ ሁለቱ ጡቶቿ ላይ ያላንዳች ተቀናቃኝ፣ ታይቶ የማይተነተን ስእል ስስል…ታየኝና ታየኝ…ምን ዋጋ አለው…የፈሠሠ ቀጠሮ!፡፡
አንድ ቀን እማዬን…እንጀራ ሸጣ ስትመለስ…አድርጌ የማላውቀውን በድፍረት አስር ብር ጠየኳት…”ለምንህ?” ሳትለኝ አሮጌ ቦርሳዋን ከብብቷ አውጥታ ሁለት አምስት ብር አሻረችኝ (እማ ጠረኗ ይጣፍጣል…ልቅ እንደ ቤተመቅደስ እጣን) በስመአብ እፊቷ ዘፈንኩ…እማ ተገረመች…የጤና አልመስል እስኪላት…ሳቀች…ጥይምናዋ ላይ በአንድ አፍታ የጠዋት ፀሐይ ወጣች…አፋራም ፀሐይ…እማን እወዳታለሁ፤ ባየኋት ቁጥር በስስ ሥጋ የተበጀችው ልቤ ቅልጥ ትልብኛለች፤ እሳት ዳር እንደተጠጋ ቅቤ…ፊቷን በሙሉ ስሜ የቀረኝ የለም…ልብሴን ቀይሬ…ወጣሁ ያለወትሮዋ…”ቶሎ ተመለስ” አላለችም (ቅዳሜ ከሰዓት ነዋ) መጐርመሴ የገባት ስለመሰለኝ ገባኝና ገባኝ…እንደ ፌንጣ እየዘለልኩ ከጊቢ ወጥቼ አብሻ ጋር ደረስኩ…”ከንፈሯን ካቀመሰችኝ በኋላ በትኩስ ትንፋሽ…”ቲያትር እንግባ” አልኳት…ጥርስ በጥርስ ሆኜ፡፡ “አቦ ቲያትር አይመቸኝም” አለችኝ…እጇን እያወናጨፈች…(የእጇ አወነጫጨፍ ገደል ግባ አይነት ይመስላል) አልገባትም…ምርጥ ከሚባል ፊልም ቀሽም ቲያትር እንደሚበልጥ…ለሷ መዝናናት…ሲኒማ ኢትዮጵያ የቅንጣቢ ሥጋ ሳንድዊች በለስላሳ እየበሉ የህንድ ፊልም ማየት ነው…ቲያትር እንዳማረኝ ቀርቶ ሲኒማ ገባን…፡፡
ቆሜ እንደፈዘዝኩ አብይ አየኝ…
“ነቃ በላ” አለኝ…በእግሩ እግሬን እየመታ…ባነንኩ (ከገነት የተባረርኩ ነው የመሰለኝ…) “አብዬ can you lend me fifty birr?” የሆነ ቦታ ለመሄድ ፈለኩ…
“Anything special?” እያፌዘ መሰለኝ፤ መልስ አልሰጠሁትም…
“ጣጣ የለውም… ተረጋጋ… አትበሳጭ…” ሲያረጋጋኝ እርጋታው ድምፁ ውስጥ ነበር… “እንዲያውም ቅዳሜና እሁድን ሶደሬ ነው የምንሄደው!” ደንግጬ ተጠጋሁት…”የምርህን ነው?”
“ሙት…ከዚህ መጠጣችንን ፓንች አድርገን አምስታችንም እንሄዳለን” አለኝ…ትልቁን ጉዳይ እንደቀልድ…አምነዋለሁ…አብዬ ካለ አለ ነው…አርብ ላይ ቆሞ የቅዳሜና የእሁድን ውሎ መስማት የሆነ ያህል ይሆናል፡፡
አጠገቡ ቆሜ እንደህፃን ራሱን አሻሸሁት (ብስመው ራሱ ደስ ይለኝ ነበር)
አቤላ Q ጦርን ጣለች…ቅድምም ማነው ሲጥላት አታንሣ ብዬ ጠቅሴው ነበር…አሁንም ጭንቅላቱን በጣቴ ሳላስጠጣ ነካ አደረኩት…ቀጥሎ የሚጥለው ያስዘጋዋል…Q ጦርን ትቶ ሳበ…አራት ዳይመንድ ስቦ ኤኒ ገቢ ሆነ…ዞሮ ሲመጣ ዘጋ፡፡
***
እውነትን ይዤ ስደክም …ያን ጊዜ ሐይለኛ እሆናለሁ፡፡
ለዝሙት አልወድቅም፡፡ ለኔ ላልሆነ ነገርም አልንበረከክም፤
የኔ የሚሆነው እስኪሆን የሌላ ለመሆን አልሆንም፡፡
***
ጠዋት ነው፡፡
ፀሐይዋ እንደ ጐረምሳ ሙቀት እያፏጨች…ደረቷን ሳትሸፍን…ትስቃለች፡፡ ከ15 ቀበሌ ጠላ ገዝተን…ብርቱካንና ሙዝ፣ አናናስ፣ ተፈጭቶ ተጨምሮበታል፡፡ ካሜራችን ዝግጁ ሆኗል፤ እኔ፣ አብይ…አቤላ…ሲሳይ…ፍሬው…ሥራ ተከፋፍለን ተዘገጃጅተናል…መሄድ ብቻ…ልቤ አንድ ነገር አዘዘችኝ…እነ እትዬ ሱቅ ገባሁና አብነት ጋር ደወልኩ…ታላቅ እህቷ ስታነሳ እማወራው ጠፋኝ…”አ.ብ.ሻ.ን. ነበር” ስል ከወዲያ “የለችም በይ የለችም በይ” የሚል የራቀ የሚመስል የቀረበ የጥድፊያ ድምጽ ተሰማኝ…(የሆነ ነገር ወረረኝ) እህቷ በትህትና “መልዕክት ካለ… ወጥታለች” አለችኝ፤ ጨዋነቷን የአንደበቷ ለዛ ሹክ አለኝ…ምናለበት ከልቤ በወጣች ብዬ ተመኘሁ…ስልኩን ዘግቼ እዛው ቆምኩ…ጅል እኮ ነኝ…”እወድኋለሁ” ስትለኝ “አውቃለሁ” ያልኳት ቀን…”እንዴት ልታውቅ ቻልክ?” ያለችኝ ጊዜ…ነቄ መሆን ነበረብኝ…ሠራተኛ ሰፈር ጅል ማነው ቢባል እኔና እኔ ብቻ ነን…ቀድማ እየነገረችኝ…ያልሠማሁ…ሒድ ብላ ቅኔ እየተቀኘችልኝ ነቄ ያላልኩ…ገገማ ችኮ…ደግሞ አንጀቴን ስትበላ…እንደ እማዬ ጣቶቿን የራስ ቅሌ ፀጉር ውስጥ ወትፋ ትዳብሠኛለች…ያኔ ይሆን ልቤን ወስዳ የጣለችብኝ…?
ከአሁን በኋላ ሰው እወድሃለሁ ሲለኝ…”አውቃለሁ” አልልም…ከእማ በስተቀር፡፡ ግድ አለኝ እንዴ ባይወዱኝ! ለመሸወደ ለመሸወድ መወደድ ምን ፋይዳ አለው…በአንድ እጅ መዳፍ ሁለት ነገር መጨበጥ፡፡
ትዝታዋን ከህሊናዬ ለማስወጣት እፈልጋለሁ፡፡
ፍቅር ዘይትና ውሃ ሆኖበታል፡፡ ያልተዋሃደ…ግን ያልተለያዩ…ዘይቱ ውኃው ላይ ራቁቱን በደረቱ ተኝቷል፤ ውሃዋም …ራቁቷን ለዘይቱ ደረቷን ሰጥታዋለች፡፡…
እሱም እንደዛው ነው፡፡ ያልተደባለቀ…ግን ያልተለያየ…የስልክ ሃምሣ ሳንቲም ከፍሎ ከፍሬው ጐን ቆመ…መፍዘዙን ሲሳይ አይቶት ምን ሆነህ ነው ማለቱ ይብስ ማስቆዙም ስለመሰለው ዝም አለው፡፡
ልቡ እየዋለለበት ተቸገረ…ያለችውን እያመላለሰ ማመንዠግ ጀመረ…ካፌ ቁጭ ብለው…ከቦርሳዋ የኪስ ካላንደር አውጥታ እየቆጠረች ስታስብ…መላልሶ ታየው…”ለእኔ ገላዋን ከልክላ…ለሌላ…ይብላኝ ለራሷ…እኔስ የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም ነው…አሁን ብትሰጠኝ ምን ነበር? አያልቅባት” ያሰበውን አሰበ፤ መልሶ በልቡ…ልርሳው ካሉ ምን የማይረሱት ነገር አለ…ይሄን ሁሉ ፍሬው አጠገብ ቆሞ አምሠለሰለው…ፍሬውን ሲያየው ካለውም እጥረቱ ላይ ያጠረበት መሠለው…”እንጐ እንጐ…”የሚለው ድምጽ አነቃው…አቤላ ያመጣችውን አገልግል ሰጡትና ዳገቱን ተያያዙት፡
***
ሞቱ ለኃጥአ ጽዋግ፡፡
***
ሒደቱ ፈጣን ነው፡፡
ሃሳቡን እያላመጠ…ተሳፋሪውን በሳቃቸው እያሳቁም…እየበጠበጡም መድረሻቸው ደረሱ…የመጨረሻው ርካሽ አልጋ መንደር ወስጥ ተፈልጐ ተያዙ…ለሁለት ቀን ደስታ…ገላ የትስ ቢወድቅ..ምን ችግር አለው፡፡
***
ካሡ ልቡም ኪሱም ሞላ ሞላ ብሎ በሙሉነት የአብነትን ሞንዳላ ሰውነት አቅፎ እንደወጌሻ እያሻሸ ነፍሱን እስክስታ ያለማምዳል፤ ፊትለፊታቸው ያሉትን ሰዎች ከመጤፍም አልቆጠሯቸውም! ስብሃትን እቅፍ፣ እንቅ አድርጐ በከንፈሩ ከንፈሯ ላይ እሽክምክም እያለ ነው…አንድ ሁለቴ…የተጐነጨውን ቢራ በአፉ አፏ ውስጥ በአደራ ያስቀምጣል…
***
አገልግሉን ግማሹን አጣጥመው ተነሱ…ጠላው ባህሪውን ቀይሯል…ደማ አንድም ሳይጐነጭ …ሲሳይና ፍሬው ደገምገም አርገው በደንብ አጣጣሟት..የተከራዩት ጊቢ…የዝንቡ አበዛዝ…የንብ ማነብያ ጊቢ እንጂ…መደዳ የተደረደሩት ክፍሎች ማስቀየማቸው…ፅዳት የናፈቀው ወለል…ብቻ ሁሉም ለአይን ደስ አይልም፡፡ ዘጭ ካሉ ምን ክብር አለ፡፡
***
የነፍሷን መድኃኒት መልካም ግብር መሥራት ለምን ረሳች?
ኩነኔ መኖሩን አላውቅም ነበር ልትል እኮ ነው…!
ካህናትና መጻሕፍት…አልነበሩምን? ይላል እንዳንወድቅ የሚታገል ቅዱስ መንፈስ፡፡ የሀጥህ ሞቱ የከፋ ነው የመረረ…
***
“እኔ ቡና አምሮኛል…”
“እኮ አብረን መዝናኛ እንገባና ቢራም ቀመስመስ አድርገን…” ሁሉም ተስማሙ…ያ ድንክ ፍሬው ብብቱን እንደተኮረኮረ ህፃን…ሳይነኩት ይፈግጋል…እየሳቁ እየተተራረቡ ገቡ…
***
አብነት ሁለተኛ ቢራዋ ነው…ካሡ ቢራው ውስጥ ጐርደን ጅን አስጨምሮ ነው የሚጠጣው…ትንፋሿ ቀየር ሳቋ ሞቅ ማለት ጀመረ…እሱ የመጨረሻ ልጁን ጭኑ ላይ አድርጐ እንደሚያጫውት አባት ጭኖቹ ላይ አጋድሞ የዝቅዝቅ እያየ ያዋራታል…ከንፈሯን እየመጠጠ የታፕስ እንጆሪ አለ መስሎታል…
***

ሃፍራታም ናት (ሀጢያት ነው የሰራችው፡፡)

ለማንም ቀርቶ…ለራሷም አትሆን፡፡

ሐሳቤን ለውጫለሁ (ሐሳቡን)

መታመም አልፈልግም…መውደዴ ተለውጦ ፍቅር ወልዶ ነበር…

ሠርዧታለሁ ከልቤ (ከልቡ)
***
ወደውስጥ ሲገቡ የፊልም አክተር ይመስላሉ…ሁሉም ሰው የገዛ ራሱን ጨዋታ ነው የሚከታተለው…ከጥቂት ሰዎች በስተቀር የማንንም ትኩረት መሳብ አልቻሉም…ቆመው ስለላ አካሄዱ…ጥግ ብቸኛ የሆነ የአራት ሰው መቀመጫ አዩ…ወደዛው እየሄዱ ሳለ…አስተናጋጁ አንድ ወንበር እንዳልተጠበሠ አሳ አንጠልጥሎ ከኋላ ተከተላቸው…ልጅነት ጐጆውን የሠራበትን ፊታቸውን እየተመለከተ አጠናቸው…
ትከሻቸው ሰፋ…ከደማ በስተቀር ሁሉም ትንፋሻቸው መረር ብሏል፡፡ ጨዋነታቸው ጥቂትም ብትሆን አልተሸረፈችም፡፡ ደማ ተሽቀዳድሞ የወረደ ቡና ያለስኳር አዘዘ…አራቱ ተያዩ…አቤላ “ጣጣ የለውም” በሚል ቢራ ያላበው ለአራታቸውም አዘዘች…ጨዋታውን አጨሠችው፤ ደማ ታጥቦ ታጥኖ ስለመጣ፣ ማሠሪያ የሌለውን ጫማውን አወለቀ፤ ቀበቶውን አላላ…የፍሬው አይኖች እሚያርፉበት አጡ…
***
አብነት ቆማ ለካሱ አለመስከሯን ታሳየዋለች…መሀል ላይ ናት “መጣሁ የኔ ጌታ ሬስት ሩም ደርሼ” ከንፈሩን ስማው ሄደች፡፡
***
ቆመ…ልቡን ማመን አቃተው፣ አይኑን ሳይሆን፡፡ ሱሪው እንደወረደ ያወቀው አብይ ከፍ ሲያደርግለት ነው…ሁሉም አይዋት…ራሷ ናት አብነት! ፍሬው ካሱን ያውቀዋል ግን ከአብነት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ፈጽሞም አያውቅም…መሄድ ጀመረ …ለባዶ እግሩ ግድም አልነበረውም…ነጩ ካልሲ የመሬቱን ቅዝቃዜ አልነገረውም፡፡ ቀጥ ብሎ ካሱ ፊት ቆመ…
“አቤት…” ካሱ ለጠጥ ብሎ ተቀመጠ…ፊትለፊቱ የቆመው ማን እንደሆነ ፈጽሞ አላወቁም…እነአብይ በተመስጦ የሚሆነውን እያዩ ነው…አብይ እንደማይጣላ ያውቃል…ለዚህ ነው ያልተከተለው….
“አብነት ምንህ ናት?” ድምጹ ውስጥ መንበርከክ አለ…ትህትና፣ ፍቅር…ርህራሄ፡፡ ከጀርባ ሲሳሳሙ አይቷቸዋል…ግን አብነት ትሆናለች ብሎ መች ጠረጠረ…እሷማ እቤት ቅቤ ተቀብታ ተቀምጣለች፡፡
“ጓደኛዬ…ማለት ፍቅረኛዬ ናት…” ካሱ ርህራሄ የተሞላበትን ፊት እያየ ያልፈጠረበትን ትህትና አሳየ…
“አየህ…” ብሎ ከኋላ ኪሱ ቦርሳውን አወጣና ከአብነት ጋር ተቃቅፈው የተነሱትን ፎቶ አሳየው፡፡ “አየህ የሁለት አመት ውዴ ናት” እንባው መጣ፡፡ ካሱም ከኋላ ኪሱ ዋሌቱን አወጣና በቄንጥ ተቃቅፈው፣ ደረቱ ላይ ፈልሰስ ብላ ከጀርባው አዝሏት ብዙ ፎቶ አሳየው “ለእኔ ደግሞ የአምስት አመት ፍቅረኛዬ ናት…” ከዚህ ሌላ ምንም ሊለው አልቻለም…ከቀኝ አይኑስር ተነጥላ እየተንከባለለች የወረደችውን እንባውን ሲያይ አዘነ…
ካሱ አላለቅስም አይነት ጥርሱን ነከሠ፡፡
እነ አብይ የሚሆነውን በስስት እና በስጋት እያዩ ነው፡፡
“እና”
“ምን እና አለው ወንድሜ” ካሱ አንገቱን ቀበረ፡፡
አብነት እየፈነጠዘች ስትመጣ ካሱ አቀርቅሮ፣ ደማ ቆሞ…አፈራርቃ ተመለከተቻቸው፡፡
አያት፡፡
ፊቷን ከፊቱ መለሠች፡፡
ካሱም አያት፡፡
አላየችውም፡፡
ካሱ እጁ እየተንቀጠቀጠ ፎቶዎቹን ዘረገፋቸው…አብነት ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ ሸሸት አለች፡፡ እነ አብዬ ከተቀመጠበት ተነሱ…
***
የኃጥዕ ሞቱ የከፋ ነው፡፡
***
የሁለቱም አይደለችም፡፡ መሬት ላይ እንደሚወድቁት ካርታዎች ቀድማ ራሷን ደክርታለች፡፡ ማንም አያነሳትም፡፡
ሶስቱም ተያዩ፡፡
ዙሩ ከሯል፡፡

Read 8978 times

Latest from