Monday, 30 May 2022 00:00

ጆርጅ ቡሽን ለመግደል የተሸረበ ሴራ መክሸፉ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አሸባሪው ቡድን አይሲስ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ዳላስ ውስጥ ለመግደል ያቀነባበረውን ሴራ ማክሸፉንና የግድያው አቀነባባሪ ባለፈው ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ መታየት መጀመሩን የአገሪቱ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ አስታውቋል፡፡
አህመድ ሺባብ የተባለና ከ2020 አንስቶ ነዋሪነቱ በኦሃዮ የሆነ የ52 አመት ኢራቃዊ #አገሬን አፈራርሰዋል፤ በርካታ ወገኖቼን ለሞት ዳርገዋል፤ የእጃቸውን ማግኘት ይገባቸዋል; ባላቸው ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ላይ ግድያ ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበርና በተደረገበት ክትትል ባለፈው ህዳር ወር ዳላስ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ቢሮው ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ የጥገኝነት ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ግለሰቡ፣ ግድያውን ለመፈጸም የሚያግዙትን በቱርክ፣ ግብጽና ዴንማርክ የሚገኙ የአገሩ ልጆች ከመመልመልና የገዳይ ቡድን በማዋቀር በሜክሲኮ ድንበር በኩል በስውር ወደ አሜሪካ ለማስገባት ከማቀድ አንስቶ፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት ቪዲዮ እስከመቅረጽ ሴራ ሲሸርብ እንደቆየ የጠቆመው ዘገባው፤ የፖሊስ አባል መስሎ ግድያውን ለመፈጸም ሃሰተኛ የፖሊስ መታወቂያ አውጥቶ እንደነበርም ዘገባው አመልክቷል፡፡
አሜሪካን ከ2001 እስከ 2009 በፕሬዚዳንትነት የመሩት ሪፐብሊካኑ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ በእሳቸው የስልጣን ዘመን አሜሪካ ኢራቅን እንድትወር ውሳኔ በማስተላለፋቸውና አገሪቱን ለከፋ ውድመት በመዳረግ እንደሚተቹም ዘገባው አስታውሷል።

Read 3216 times