Monday, 30 May 2022 00:00

ከጉልበተኛ መንግሥት ወደ ጉልበተኛ ክልሎች ተሸጋገርን?

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

  ማስፈንጠሪያ
የአፋኙ የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት ወደ ዳር መገፋትን ተከትሎ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል፣ ተንታኞች በተለያየ አጽናፍ ይተረጉሙታል፡፡ አንዳንዶች ሀገራዊ ፈተናውን ከሚጠበቀው በላይ ያከበደው፤ የፖለቲካ ምህዳሩ ያለበቂ መጠበቂያ ወለል ብሎ መከፈቱ ነው፤ ይላሉ፡፡
የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣበት ሰሞን ይህንን ሐሳብ የሚያጠናክር ዘለግ ያለ ጽሑፍ  በፎረን ፖሊስ ድረገጽ ላይ ፕሮፌሰር ፍሎሪያ እና ወንድማገኝ የተባሉ ጸሐፊዎች አጋርተው ነበር፡፡ ጸሐፊዎቹ ህወሓት ዘግቶ የኖረው የመጫወቺያ ሜዳ ድንገት መከፈት የሚያመጣውን ጣጣ፣ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ጋር እያነጻጸሩ ነው ያቀረቡት፡፡
“የፖለቲካ ምህዳሩ በሚሰፋበት ጊዜ፣ በዘውግ ማንነት ላይ የተቀለሰው የፌዴራል ሥርዓት፣ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ቆስቋሽ ሁነቶችን መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ በለውጡ ሂደት፣ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት፣ ማንነት ተኮር ግጭቶች መከሰታቸው አይቀርም፡፡” ሲሉ ተንብየው ነበር፤ ጸሐፊዎቹ፡፡
በርግጥም ትንበያቸው ከሞላ ጎደል በውል እየተከሰተ እንደሆነ አስረጂ አያሻውም። ያለበቂ የተቋም ግንባታ ምህዳሩ ወለል ብሎ መከፈቱ፣ ይዞት የመጣው ዕዳ እንዳለ ይታወቃል። ጽንፈኝነት ልጓም አልባ ሆኖ ተከስቷል፡፡ ከማእከላዊው መንግሥት ውጭ ያሉ ኃይሎች ተጽእኖ መልኩን እየቀያየረ ሀገሪቱን ቅርቃር ውስጥ ጨምሯታል፡፡
የማእከላዊው መንግሥትን አቅም የሚፈታተኑ ኹነቶች
የኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት፣ ማእከላዊውን መንግሥት የሚያዳክም፣ በአንጻሩ የክልል መስተዳድሮችን እንዲያፈረጥም ሆኖ የተቀለሰ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ከፌዴራሊዝም ይልቅ ወደ ኮንፌደሬሽን የሚያዘነብል ቅርጽ ተላብሷል። ሕወሓት ይኸንን ፈተና ሲያልፍ የኖረው በፓርቲ ማእከላዊነት አሰራር ነበር፤ ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡
ታዋቂው የማካረሪ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር መሀመድ ማምዳኒ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ ከዘር-ማንነት አወቃቀር ተላቆ፤ አካባቢያዊ እውነታን መሠረት ባደረገ መርህ ካልተከለሰ፣ የዳር ኃይሎች ተጽእኗቸው በርትቶ ሀገሪቱን ለባሰ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል መዳረግ የሚያስችል ቁመናን በጊዜ ሂደት መላበሳቸው አይቀርም ብለው፤ ያስረግጣሉ።
እርግጥ ነው የብሔር ፖለቲካው ከክልላዊ አወቃቀር ጋር ተዳምሮ፣ የማእከላዊው መንግሥት ፈተናን ከልክ በላይ አክብዶታል። መሠረታዊ የሆነውን የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቁን ሃላፊነት እንኳን በቅጡ እንዳይወጣ ሳንካ ሆኖበታል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
አንድ መንግሥት ሉአላዊ ሥልጣን አለው የሚባለው፣ ሕግ የማውጣት የማስፈጸምና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ከጥያቄ ውስጥ የማይወድቅ ከሆነ ብቻ እንደሆነ፤ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡
ማንኛውንም የዳር ኃይል አደብ ለማስገዛት የሚያስችለውን አቅም ገና መላበስ እንዳልጀመረ፣ ሂስ አቅራቢዎች ይሞግታሉ። ለዚህም በአስረጂነት የሚያቀርቡት፣ ሰላምና ደህንነት በአግባቡ ማስጠበቅ የሚያስችል አደረጃጀት እስከ ታችኛው አስተዳደራዊ መዋቅር አለመውረዱን ነው፡፡
የዳር ኃይሎች እያባባሱት ያለው
የመብት ጥሰት
በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የዜጎችን መብት መጣስ ተጠቅልሎ የተያዘው በማእከላዊው መንግሥት ነበር፡፡ አሁን መልኩ ተለውጦ የክልልና ሌሎች የዳር ኃይሎች አቅም አበጅተው ተገዳዳሪ ሆነዋል፡፡ በየጊዜው እየተባባሰ ለመጣው የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ እነዚህን ኃይሎች ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ግን አመክንዮዋዊ አይደለም፡፡ የመንግሥት ዳተኝነት ዋንኛውን ድርሻ ይወስዳል የሚሉት የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ተወካይ አቶ ያሬድ ኃይለማሪያም ናቸው፡፡
እንደ ተወካዩ ገለጻ፤ #አንድ መንግሥት ሰብአዊ መብትን በተመለከተ ሦስት መሠረታዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ በቅድሚያ ራሱ ከመጣስ መቆጠብ ይኖርበታል፤ የዜጎች ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ አደጋ የሚጥሉ አካላትን፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መልኩ ይቀጣል፤ በማሳረጊያው መብቶቹ እንዲከበሩ ውጤታማ አሠራሮችን ይተገብራል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ሦስቱ የመንግሥት ሃላፊነቶች ከእነአካቴው ተዘንግተው ነበር። የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣ አካባቢ፣ ብዙ አበረታች ምልክቶች የተስተዋሉ ቢሆንም፤ ቀስ በቀስ ተስፋ እንደ ጉም በኖ፣ አሁን መንግሥት በዜጎች ላይ አፈና በማድረግ መሪ ተዋናይ ሆኗል።;
የዜጎችን ሰብአዊ መብት በመከላከል ረገድ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ተቋማት ያለባቸው ሸክም ከሚገመተው በላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተላበሱት ተቋማዊ ጥንካሬ፣ ሀገሪቱ እያስተናገደችው ካለው ዘርፈ ብዙ የመብት ጥሰት ጋር ሲነጻጸር፤ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በመሆኑም  ትልቁን የቤት ሥራ መወሰድ የሚገባው ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደሆነ የፖለቲካ ልሂቃን ያስገነዝባሉ፡፡
የማእከላዊው መንግሥት እና የክልል መንግሥታት የኃይል ሚዛን መዛነፍ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው ሥርዓተ-አልበኝነት ጉልህ ሚና እንዳለው እሙን ነው። ሀገሪቱ በመዋቅር-ወለድ ፈተናዎች  መናጧን ቀጥላለች። ሰሞኑን በአማራ ክልል እየተስተዋለ ያለው ከመስመር የወጣ የፖለቲካ ኹነት፣ ከሁሉም በላይ ትኩረትን የሚስብ ሆኗል፡፡  

የሰሞኑ የአማራ ክልል ዘመቻ እና አንድምታው  
የሀገሪቱን ሰብአዊ ቀውስ በማባባስ ረገድ ጉልህ ሚና ያለው አሸባሪው ህወሓት፤ አሁንም የትግራይ ሕዝብን እንደ ምርኮ ይዟል፡፡ ለቀጣይ ዙር ጦርነት አፋፍ ላይ መቆሙን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ያለ ግጭት መኖር የማይችለው ይህ የሽብር ቡድን፤ በቀጣይነት ለማእከላዊው መንግሥትም ሆነ ለሀገሪቱ፣ ሌላ የቤት ሥራ ይዞ ብቅ ማለቱ አይቀርም። የሽብር ኃይሉ በማያንሰራራበት ደረጃ ካልተመታ፤ በማንኛውም ሰዐት ለዳግም ወረራ መሰናዳቱ እንደማይቀር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ሰሞነኛ ምልክቶችም ወደዚያው የሚያመሩ ይመስላሉ::
ለህወሓት ወረራ በቅድሚያ ተጋላጭ የሆነው የአማራ ክልል፣ ባሳለፍነው ሳምንት ጠንከር ያለ መግለጫ በማውጣት ወደ እርምጃ መግባት ጀምሯል፡፡ ከሁሉም በላይ ትኩረት የሳበው፣ በህወሓት ዳግም ወረራ ወቅት ትልቅ ጀብዶ የሰሩት ብ/ጄ ተፈራ ማሞ፣ ከአዲስ አበባ ታፍነው መወሰዳቸው ነው፡፡ አንዳንዶች እርምጃውን የክልሎች የኃይል ሚዛን እያደገ ለመምጣቱ ዋቢ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ብልጽግና ከአዲስ አበባ ጋዜጠኞችን አፍኖ መወሰዱ የሚታወስ ነው፡፡ ከአንድ ጉልበተኛ መንግሥት ወደ ጉልበተኛ የክልል መስተዳደሮች እየተሸጋገርን ለመሆናችን እነዚህን ምልክቶች እንደማሳያ የሚወስዱ ታዛቢዎች በርካታ ናቸው፡፡
የጄነራሉ ወደ ባህርዳር መወሰድ ለብዙ የሴራ ንድፈ ሐሳብ ተጋላጭ ነው፡፡ የአማራ ብልጽግና በፋኖ ሽፋን ሥርዓት አልበኝነት እየፈጠሩ ያሉትን ጥገኛ ኃይሎች ለመምታት የሚያስችል የመፈራት ግርማ ሞገስ (fear factor) እየፈጠረ ነው፤ የሚሉ አሉ፡፡ ሌላው ድርጊቱን ህወሓት ለብቻው ጠቅልሎ የያዘውን አምባገነናዊ አገዛዝ፤ ክልሎች መከፋፈል ለመጀመራቸው እንደ ማሳያ የሚወስዱትም  አልታጡም፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ በፋኖ ስም ሥርዓት አልበኝነት የሚፈጥሩ የድል አጥቢያ አርበኞችን አድብ ማስገዛት፤ የክልል መስተዳደሩ ቀዳሚ ግብር እንደሆነ እሙን ነው፡፡ በአንድ ሀገር ሁለት መንግሥት ሊኖር አይችልም፡፡ በአማራ ካባ ለህወሓት ሥልታዊ ድጋፍ በሚያደርጉ ኃይሎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መወሰድ፤ በይደር የሚተው ሥራ አይደለም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን በድሮ ኢሕአዴግ እሳቤ የተቸነከሩት ካድሬዎች፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው፤ የንጹሃንን መብት እንዳይጥሱ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
መከርቸሚያ
ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ላይ ደርሳለች፡፡ በዚህ ጊዜ ሀገሪቱን በሁሉም ረገድ የከበባትን  ፈተና በጥበብ ማለፍ፤ ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት የሚጠበቅ ግዙፍ ኃላፊነት ነው፡፡
በአጠቃላይ ምህዳሩን ወለል አድርጎ ከፍቶ የብሔር ኃይሎች እንዳሻቸው እንዲፈነጩ መፍቀድ በሀገር ኅልውና ላይ እንደመቀለድ ይቆጠራል፡፡ ምህዳሩንም መዝጋት ሌላ አደጋ ይዞ ይመጣል፡፡ ተስፋ መቁረጡና አፈናው ስለሚጨምር ጽንፈኛ ኃይሎች እንደ ቤንዚን እያርከፈከፉ የሚያቀጣጥሉት አጀንዳ ያገኛሉ። ስለዚህ አማካዩ አዋጪ ነው፡፡ ምህዳሩን በተመጠነ መንገድ ገርበብ አድርጎ፤ ተዛማጅ የሆነውን የተቋም ግንባታን ማፋጠን ተገቢ መሆኑን የሚያስረግጡ ተንታኞች በርካታ ናቸው፡፡
ህወሓት እና የህወሓትን አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ላይ መንግሥት የሚቀዳጀው አንጸባራቂ ድል  ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው የዜጎች ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ቅንጦት የማይሆኑባት፣ ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀ፣ በምጣኔ ሐብት የተራመደች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ኹነኛ ሥራ እንደተሠራ የሚቆጠረው ይላሉ፤ የፖለቲካ ልሂቃን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከላይ በቀረበው ጽሁፍ የተንጸባረቀው አመለካከት ጸሃፊውን ብቻ የሚወክል እንደሆነ እንገልጻለን፡፡

Read 9267 times