Saturday, 06 October 2012 13:46

ግልጽ ምላሽለአቶ ፃድቃን ገ/ትንሳይ (ሌ/ጄኔራል)

Written by  ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት አንዱ
Rate this item
(9 votes)

ከዚህ ይልቅ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን በምልልሳቸው ላይ ያጎሏቸው ነገሮች ሁለት ናቸው። አንደኛው ከኤታማዦር ሹምነት ሲነሱ ስህተት እንደተሰራባቸው፣ ዋና ዋና ውጊያዎችን እንደመሩ በማስመሰል የተናገሩት አባባል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አቶ መለስ እንጂ እርሳቸው ስልጣን እንደማይወዱ ያወጉት የውሸት ክምር ነው።ዕለተ ቅዳሜ ተሲያት ላይ፡፡ ምናልባትም ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል ገደማ፡፡ ቀኑ የሳምንቱ መጨረሻ እንደመሆኑ መጠን፤ አራት ኪሎ የሚገኙ ካፌዎች ውስጥ ቁጭ ብዬ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የፈጠራቸውን የግል ጋዜጦችን ማገላበጥ ያዝኩ። እንዲህ ዓይነት የቆየ ልምድ አለኝ፡፡…እናም ከካፌዎቹ ውስጥ በአንዱ በረንዳ ላይ ተሰይሜያለሁ፡፡ …

ጋዜጣ አዟሪው እጄ ላይ አስቀምጧቸው ከሄደው ጋዜጦች መካከል የዕለቱ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በነሐሴ 26 ቀን 2004 ዓ.ም ዕትሙ፣ በፊት ለፊት ገጹ ላይ አንድ ቀደም ሲል የማውቃቸውን ግለሰብ ቃለ - ምልልስ መያዙን ተመለከትኩ፡፡ የቃለ - ምልልሱ ባለቤት አቶ ፃድቃን ገ/ትንሳይ (ሌ/ጄኔራል) ሲሆኑ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አስመልክቶ ሲናገሩ “መለስ ከሁላችንም የበለጠ ነበር” ይላሉ፡፡ የሰውዬው አባባል እያስገረመኝ አጠቃላይ ዘገባውን ለማንበብ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ፡፡…

ግና በመጀመሪያ ቃለ-ምልልሱን ላካሄደው ጋዜጣም ይሁን ለአንባቢዎቼ ግልፅ ይሆን ዘንድ በርዕሴ ላይ የቀድሞውን ኤታማዦር ሹም ለምን “አቶ” እንዳልኳቸው ጥቂት ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ይመስለኛል። በቅድሚያ በጋዜጣው ላይ “ጄኔራል” ተብለው የተጠቀሱበት አገላለፅ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ግለሰቡ በጡረታ የተሰናበቱ በመሆናቸው የወታደራዊ ማዕረጋቸው አጠራር የተለየ በመሆኑ ነው።

እርግጥ ማዕረጉ በቃል የሚጠራ ከሆነ “ጄኔራል” ማለቱ ብዙም ችግር የለውም። ይሁን እንጂ በፅሑፍ ከሆነ የግለሰቡ ትክክለኛ ማዕረግ በትክክል መፃፍ አለበት። ስለሆነም ጋዜጣው በጡረታ የተሰናበቱት አቶ ፃድቃን ገ/ትንሳይ ካለ በኋላ፣ በስተመጨረሻ በቅንፍ ውስጥ “ሌ/ጄኔራል” ብሎ ወይም በጡረታ የተሰናበቱት ሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ትንሳይ የሚል አገላለፅን መጠቀም እንደሚገባው ለመግለፅ እወዳለሁ። እኔም በርዕሴ ላይ ከሁለቱ አንዱን አገላለፅ የተጠቀምኩት ለዚሁ ነው።

አቶ ፃድቃን (ሌ/ጄ) በአቶ መለስ ህልፈተ-ህይወት የተሰማቸውን ሐዘን መግለፃቸው፣ እርሳቸውም ከልማቱ ተጠቃሚ በመሆናቸው በጄ ሊባል የሚችል ነው። እናም በእነዚህ ሃቆች ከተግባባን ዘንዳ፤ ወደ ፅሑፉ ምልከታዬ ላምራ።

በጋዜጣው ላይ የተመለከትኩት አጠቃላይ እውነትን ያዘለ ርዕስ በአንድ ወቅት የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩ ግለሰብን የሚመጥን አይደለም — እንዲህ ያለውን እማኝነት ማንኛውም ተራ ዜጋ ሲናገር ማዳመጥ የተለመደ ነውና፡፡ ይሁን እንጂ ጄኔራል መኮንኑ ከ11 ዓመታት ዝምታ በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊ “ከሁላችንም የበለጡ ነበሩ” ብለዋል። ታዲያ እዚህ ላይ ጄኔራል መኮንኑ ምን እያሉን ይሆን? ከአቶ መለስ በስተቀር ሌላው አመራር እንደ እኔ ነው እያሉን ይሆን እንዴ?...እርግጥ ለማለት የፈለጉት ይህ ከሆነ፤ ለጄኔራል መኮንኑ እውነቱን መንገር የሚያሻ ይመስለኛል።

አዎ! ሌላው አመራር በፍፁም እንደ እርሳቸው ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አመራሩ ከሀገራችን ህዝቦች ጋር ተሰልፎ በልማቱና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ሂደት እየመራና እያታገለ የሚገኝ በመሆኑ ነው። በዚህ ሂደትም ዕውቀቱ ዳብሯል፤ የአመራር ብቃቱንም አሳድጓል። እናም አሁን ያለው አመራር ከአቶ ፃድቃን (ሌ/ጄ) ጋር የሚገናኝበት አንዳችም የአመለካከት ይሁን የብቃት ተዛምዶ የለውም።

እርግጥ ታላቁ መሪያችን ባለ ራዕይ፣ ሁለንተናቸውን ለህዝብ አሳልፈው የሰጡ፣ በዓለም ላይ ብሩህ አዕምሮ ከታደሉ ጥቂት ግለሰቦች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ ይህ ከፍተኛ ብቃታቸውም ከትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምሮ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ጠቢብ እንዲሁም የወታደራዊ ሳይንስ ሊቅ እንዲሆኑ ያስቻላቸው መሆኑን ለጡረተኛው ሌ/ጄኔራል መንገር “ለቀባሪው የማርዳት” ያህል ነው፣ ጠንቅቀው ያውቁታልና፡፡ ግና የእርሳቸው ነገር “አውቆ የተኛን፣ ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉት በመሆኑ፤ በቃለ - ምልልሳቸው ላይ “እኔ፣ መለስና እገሌ እንዲህ አደረግን” ከማለት በዘለለ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን የአቶ መለስን “ልዩ ማንነት” ለማጉላት አልደፈሩም፡፡ ሊገልፁም አልፈለጉም።

ከዚህ ይልቅ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን በምልልሳቸው ላይ ያጎሏቸው ነገሮች ሁለት ናቸው። አንደኛው ከኤታማዦር ሹምነት ሲነሱ ስህተት እንደተሰራባቸው፣ ዋና ዋና ውጊያዎችን እንደመሩ በማስመሰል የተናገሩት አባባል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አቶ መለስ እንጂ እርሳቸው ስልጣን እንደማይወዱ ያወጉት የውሸት ክምር ነው። እስቲ ይህን ግርምት የሚያጭርን ጉዳይ ከአንባቢዎቼ ጋር አብረን እንየው።

በመጀመሪያ ደረጃ ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነው በሰሩባቸው 10 ዓመታት ውስጥ በኢትዮ -ኤርትራ ጦርነት ወቅት በነበረው ውጊያ “…ብዙዎቹን ውሳኔዎች ከእርሱ (ከመለስ) ጋር ነበር የወሰንናቸው፤ ግምገማ ላይ ግን ብቻዬን ነው እንድገመገም የተደረገው፡፡…” በማለት ያቀረቡት ሙግት አይሉት አላዋቂነት እጅግ ያገጠጠና ያፈጠጠ ውሸት መሆኑን ውድ አንባቢዎቼ እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡

ገና ለገና አቶ መለስ ዛሬ በህይወት የሉም በሚል እሳቤ፤ ያልሆነንና ያልተፈጠረን ጉዳይ ማውራት ትዝብት ላይ የሚጥል ከመሆኑም በላይ፤ ተዓማኒነትን የሚያሳጣ ነው፡፡ እናም አቶ ፃድቃን (ሌ/ጄ) በወቅቱ የሌለን ጉዳይ ከመሬት ተነስተው ማውጋታቸው ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፤ ከአንድ ነባር ታጋይ ለዚያውም “የደቡብ ሱዳን መንግስት የሠራዊት ትራንስፎርሜሽን ኃላፊ” ተብሎ ከተሰየመ ግለሰብ (ማን እንደሰየማቸው ባላውቅም) የሚጠበቅ አለመሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡

እናም በውጊያ ስህተት “ለብቻዬ ተገመገምኩ” በማለት ያቀረቡት ውሸት ተቀባይነት የለውም፡፡ በቅድሚያ የውጊያው ስህተት የእርስዎ ብቻ ተደርጎ አልተገመገመም፡፡ በወቅቱ ስህተቱ በአመራር ደረጃ ሲታይ የሁሉም ነው እንጂ፤የግለሰቦች ነው አልተባለም፡፡ ታዲያ እርስዎ ይህንን እውነታ እያወቁ “አቶ መለስን ላገኘው ፈልጌ ነበር፣ ያኔ በእኔ ላይ የተደረገው ነገር ትክክል አልነበረም” በማለት ሆን ብለው በውጊያው ስህተት ከኃላፊነትዎ የተነሱ ማስመሰልዎ ከቶ ምን የሚሉት ማደናገር ይሆን?...

ታዲያ እዚህ ላይ ለእርስዎም ይሁን ለአንባቢዎቼ አንድ ዕውነትን ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ። ውድ አቶ ፃድቃን (ሌ/ጄ) ሆይ! ለመሆኑ የሌ/ጄኔራልነት ማዕረግ መቼ እንደተሰጥዎ ያስታውሳሉ?-ከዘነጉት እኔ ላስታውስዎ- አዎ! ማዕረጉን ያገኙት ከፆረና እና ከዘመቻ ፀሐይ ግባት ውጊያዎች በኋላ ነው። ምናልባትም በመጋቢት ወር 1992 ዓ.ም ይመስለኛል። ይህ ወቅት ደግሞ እርስዎ ከሃላፊነትዎ እንዲነሱ ከተደረጉበት ጊዜ የወራቶች ዕድሜ ልዩነት ቢኖረው ነው። ታዲያ በወቅቱ እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮችም ተሹመዋል። እነዚህን አመራሮች የጠቆሟቸው ሌሎች ግለሰቦች ናቸው። እርስዎ ግን በቀጥታ የተጠቆሙት በአቶ መለስ አማካኝነት አይደለም እንዴ?- ታዲያ ይህን ዕውነታ እንዴት ሊዘነጉት ቻሉ?- ይህን ሃቅ ደብቀው በራስዎ የአመለካከት ለውጥ ሳቢያ በመሰናበትዎ አቶ መለስን “ላገኛቸው አልቻልኩም” የሚሉትስ ከቶ ለምን ይሆን? እናም ጓድ ፃድቃን ሆይ! በወቅቱ ‘ሹመት ያዳብር’ ተብለው ተሾሙ እንጂ ምንም አልተደረጉም። ስለሆነም እርስዎ “ለብቻዬ ተገመገምኩ” የሚሉት ተረት-ተረት ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ቅጥፈት መሆኑን አስረግጨ ልነግርዎት እፈልጋለሁ።

መቼም “አለባብሰው ቢያርሱ፣ በአረም ይመለሱ”  የሚለውን የሀገራችንን  አርሶ አደር ብሂል የሚዘነጉት አይመስለኝም፡፡ እናም እርስዎ ያለባበሱትን እውነት እኔ እንዲህ ፍርጥርጥ አድርጌ እነግርዎታለሁ፡፡ ማንኛውም በወቅቱ የነበረ ሰው በግልጽ እንደሚያውቀው፤ እርስዎ ከኤታማዦር ሹምነትዎ የተነሱት በወቅቱ የቦናፓርቲዝምን አደጋ አስመልክቶ የተፃፈውን መፅሐፍ ካነበቡ በኋላ ወገንተኝነትዎ ለአንጃው በመሆኑና የአንጃውን የኪራይ ሰብሳቢነት የዘቀጠ አስተሳሰብ በማራመድዎ ምክንያት ነው፡፡ ምናልባትም ይህ አባባሌ ለውድ አንባቢዎቼ ግልጽ ላይሆን ስለሚችል እርስዎ የነበሩበትን የአንጃውን አስተሳሰብ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ማስታወስ ይኖርብኛል፡፡

እንደሚታወቀው በ1994 ዓ.ም በኢህአዴግ ውስጥ ቀደም ሲል ሲንከባለሉ የመጡ ሁለት ተጻራሪ አመለካከቶች ተፈጥረው በድርጅቱ ላይ የመሰንጠቅ አደጋ አንዣቦ ነበር፡፡

ይኸውም በአንድ ወገን ድርጅቱንና ሀገሪቱን ከመበተን የሚያድን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ የወቅቱ ሌ/ጄኔራል ፃድቃንና ሌሎች ግብረ - አበሮቻቸው በደቀ - ሙዝሙርነት የተሰለፉበት  የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና የጠባብ ኃይሎች ስብስብ ነው፡፡ በወቅቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊው መስመር ድርጅቱንና ሀገሪቱን ከጥፋት ናዳ እንታደግ የሚል አጀንዳን ሲያራምድ፤ አንጃው ግን ከዚህ ተፃራሪ በሆነ መንገድ በመጓዝ “ከጥገኛ ባህሪዬ ጋር የሚለያየኝ ሞት ብቻ ነው!” የሚል አቋም በመያዝ ወደ ትክክለኛው የድርጅቱ መስመር ውስጥ እንዲገባ ቢለመን አሻፈረኝ ብሎ መድረክ ረግጦ በመውጣት ጸረ - ዴሞክራሲያዊነትን በይፋ አቀንቅኗል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ እነ በጡረታ የተሰናበቱት ሌ/ጄ ፃድቃን ያቀነቅኑት የነበረው የአንጃው አስተሳሰብ በበላይነት አሸንፎ ቢወጣ ኖሮ፤ ሀገራችን የኪራይ ሰብሳቢዎች፣ የትምክህተኞችና የጠባቦች ሰለባ ሆና መበታተኗ አይቀሬ ነበር፡፡ የዛሬው የህዳሴ ጉዞአችንም ሊታሰብ አይችልም ነበር። ግና ምስጋና ለልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መስመር ይግባውና የተሃድሶ መስመሩ አሸንፎ፣ ኢትዮጵያ ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ማማ ላይ መውጣት ችላለች፡፡ የአንጃው አርማጌዶናዊ አስከፊ እልቂት ከሽፎ፣ ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ ከህንድና ከቻይና ቀጥሎ ሦስተኛዋ የፈጣን ዕድገት ባለቤት ሆናለች፡፡ ህዝቡም ከልማቱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። አዎ! መሬት ላይ ያለው ጥሬ ሃቅ ይኸው ነው፡፡

እናም የቀድሞው ኤታማዦር ሹም፣ አንጃው ያራምደው በነበረው የጥፋት ተልዕኮ እምነታቸው ሳቢያ እንዲሁም ህገ-መንግስታዊ ክህደት በመፈፀማቸው ሀገሪቱ ወደ ብተና መግባት ስለሌለባት መነሳታቸውም ትክክልና ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው “በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ሳቢያ ለብቻዬ ተገመገምኩ” የሚለው አነጋገር “ፍየል ወዲህ፣ ቅዝምዝም ወዲያ” መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ እናንተዬ ማን ነበር “እውነት ብትቀጥንም አትበጠስም ያለው?” መቼም ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል ፃድቃን ሊሆኑ እንደማይችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አይመስልዎትም ጓድ?...

ሌላኛው እጅግ ያስገረመኝ ጉዳይ ደግሞ እርስዎ የጉናውን ጦርነት የመሩ አስመስለው ያቀረቡት “ኮሜዲ ድራማ” ነው፡፡ እስቲ ለጋዜጣው ያሉትን ላስታውስዎ - “…ዝም ብዬ ያለማቋረጥ እስቅ ነበር… ከዚያም እንደ ምንም ራሴን ተቆጣጥሬ ያገኘነውን ድል አጠር፣አጠር አድርጌ ስነግረው (ለመለስ) ደግሞ እርሱም በተራው ረጅም ሳቅ መሳቅ ጀመረ፡፡…” አሉን። ውድ ጡረተኛው ጄኔራል መኮንን ሆይ! ለመሆኑ ይህ አባባልዎ ከቶ ምን ማለት ይመስልዎታል?- እርግጥ መሳሳቁ ፣ ድል ማግኘቱ እሰየው የሚያሰኝ ነው። ግና ምን እያሉን ነው?...“ውጊያውን የመራሁት እኔ ነኝ”  ለማለት ነው?- ፍላጎትዎ ይኼ ከሆነ አሁንም እውነት የሚባለውን ውድ ዋጋ ያለውን ነገር እንደ ተላጠ የኤሌክትሪክ ሽቦ እየሸሹት ነው። ለምን ቢሉ፣ ውጊያውን የሚያውቅና በውጊያው ላይ የተሳተፈ ማንኛውም ታጋይ ስለሚያውቀው ነው።

ለነገሩ በወቅቱ እርስዎ ውጊያውን እንዲያስተባብሩ መመደብዎ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። በቦታው ላይም ነበሩ። ይህንን ማንም አይክድም። ግና ይህ ማለት በውጊያው ላይ ሌሎች አዛዦች አልነበሩም ማለት አይደለም። እነ አቶ መለስ የሚመሩት ማዕከላዊ ኮማንድ ወጊያውን ሲጀመር ጀምሮ አያውቀውም ማለትም አይደለም። ኮማንዱ ውጊያውን ሲጀመር ጀምሮ ያውቀዋል፤ ካለበት ቦታም ሆኖ ሃሳብ ይሰጥ ነበር። እናም እርስዎ የውጊያው አድራጊና ፈጣሪ አድርገው ራስዎን ማቅረብዎ የለየለት ውሸት ነው። ታዲያ እዚህ ላይ እኔ የሚያሰጋኝ አንድ ነገር አለ። ምን መሰልዎት… ‘የውጊያውን ዕቅድ እኔ አወጣሁት፣ በመጨረሻም ላይ እኔ አፀደቅኩት’ ብለው እንዳይናገሩ ነው።

እርስዎም ሆኑ በውጊያው ላይ የነበርን ፈጻሚዎች ጠንቅቀን እንደምንገነዘበው፤ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባለ ራዕዩ መሪያችን ወታደራዊ ዶክትሪንን፣ ፖሊሲን፣ ስትራቴጂንና ታክቲክን ከመንደፍ አልፈው፤ በእያንዳንዱ ጦርነት ወቅት እጃቸውን ሙሉ በሙሉ በማስገባት ሲያዋጉ እንደነበር ይዘነጉታል ብዬ አልገምትም፡፡ በቃለ - ምልልስዎ ላይ ግን በአንድ በኩል “ከተራ የድርጅት አባልነት አንስቶ እስከ ጦር ኃይሎች አዛዥነት አውቀዋለሁ” እያሉ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ “ውጊያውን የመራሁት እኔ ነኝ” ለማለት መፈልግዎ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነው፡፡ እርስዎ 11 ዓመት ሁሉ እምጥ ይግቡ ስምጥ ሳይታወቅ እንዲሁም ‘የት ናቸው?’ እየተባሉ፣ ዛሬ ካሉበት ቦታ ድንገት ብቅ ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ሳይደርቅ ሐሰትን መስካሪ ሆነው መገኘትዎ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፤ ያሳፍራልም፡፡

እስቲ ወደ ሌላው “እኔ እንዲህ አድርጌ” አባባልዎ ደግሞ ልውሰድዎ! የትጥቅ ትግሉ በድል እንደተጠናቀቀ አቶ መለስን ከለንደን ለመቀበል ወደ ቦሌ መሄድዎን ነግረውናል፡፡

ለጥቀውም እርስዎ ተፈሪ ባንቲ ቤት እንደነበሩና አቶ መለስ ሲመጡ “ለምን ቤተ- መንግስት አልገባችሁም?” እንዳሉዎት አውግተውናል፡፡ እርስዎ ሲመልሱም “ህዝቡ  ስልጣን ፈልገው ነው የመጡት እንዳይለን ብዬ ነው” እንዳሉም ገልጸውልን፣ በመጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይሄን ዓመት ሁሉ የተዋጋነው ታዲያ ምን ልናደርግ ነው?” እንዳሉዎትም ነገሩን፡፡… እኔ የምልዎት ተፈሪ ባንቲ ይኖሩበት የነበረው ቤት የባለስልጣን እንጂ የተራ ሰው ቤት አለመሆኑን አላወቁም ማለት ነው?...ተፈሪ ባንቲ ቤት ሲገቡስ እርስዎ ባለስልጣን አልነበሩም ማለት ነው?...አይ የእርሰዎ ነገር! መቼም ከሌሎች ታጋዮች ተሽቀዳድመው የባለስልጣን ቤት አለመያዝዎን እንዲሁም ስልጣን እንደማይፈልጉ ለማስመሰል ሲሉ ያወሩት ይህ ዲስኩር አፍዎን አዳልጥዎት እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ።…

ግና ምን እያሉን ይሆን?- እርግጥም እያሉን ያሉት ነገር አቶ መለስ ስልጣን ፈላጊ፣ እርስዎ ግን ባለ ይሉኝታ መሆንዎን ነው፡፡ “ድንቄም ይሉኝታ” አሉ - ጎረቤታችን እማማ ማርታ፡፡ ኧረ ለመሆኑ ከመቼ ጀምሮ ነው የአንጃው ቅሪቶች ይሉኝታ የሚያጠቃችሁ የሆናችሁት?- የአንጃው ቡድን የሚታወቀው ያለ አንዳች ይሉኝታና ሐፍረት የታገለለትን ድርጅት በመካድ እኮ ነው፡፡ አዎ ጡረተኛው ሌ/ጄኔራል ፃድቃን ሆይ! ይህንን ታፔላችሁን በአንዴ ነቅላችሁ መጣል የሚቻላችሁ አይመስለኝም፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን፤ አቶ መለስ አንዲትም ቀን ቢሆን ስለ ህዝባዊ ድርጅታዊ መስመርና ስለ ሀገር እንጂ ስለ ስልጣን አስበው አያውቁም፡፡ ታላቁ መሪያችን የህዝብ እንጂ የግል ስልጣን የላቸውም፤ ኖሯቸውም አያውቅም፡፡ እንዲያውም ስልጣንን በአቋራጭ የገቢ ምንጭ ማስገኛ እንዲሆን አልማችሁ ድርጅቱን ለመበተን የተነሳችሁት አንጃዎቹ እንጂ፤ የልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው ህዝባዊ መስመር መሪው አቶ መለስ አይደሉም፡፡ እርስዎ ግን ከፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባፈነገጠ መልኩ፤ የሀገራችን ህዝብ ሉዓላዊ ባለቤትነት መሆኑ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ሲገለጽ የኖረውንና ኋላ ላይም በህገ - መንግስቱ የተረጋገጠውን “ህዝባዊ ስልጣን” የታላቁ መሪያችን ፍላጎት እንደነበር አስመስለው ለማቅረብ ሞከሩ፡፡ አባባልዎ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉት ዓይነት በመሆኑ እጅግ ያሳፍራል፡፡ ህዝቡ ግን እውነታውን ጠንቅቆ ስለሚያውቀው የእርስዎን ዲስኩር ከቁብ የሚቆጥረው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ለአራት ጊዜያት ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በተግባራዊ ምርጫ በማረጋገጡ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ እስቲ እዚህ ላይ እንደ አንባቢ ለጄኔራል መኮንኑ ሶስት ጥያቄዎችን

ላንሳ።

1ኛ/ ለመሆኑ ላለፉት 11 ዓመታት አንድም ነገር ትንፍሽ ሳይሉ፤ ይህንን ወቅት ጠብቀው

መናገርን ለምን መረጡ?፣

2ኛ/ አቶ መለስን እንዴት ሊያገኟቸው አልቻሉም? — በቃለ-ምልልስዎ ላይ ልጅዎና የአቶ  መለስ ልጅ ጓደኛሞች እንደሆኑ ነግረውናል። አቶ መለስ ማረፋቸውን የሰሙትም

ከልጅዎ ነው። ታዲያ ይህን ያህል ቅርርብ ባላት ልጅዎ አማካኝነት ቢያንስ በደብዳቤ ለመገናኘት እየቻሉ ለምን እንደዚያ ለማድረግ አልፈለጉም?

3ኛ/  እውነት በጋዜጣው ላይ የሰነዘሯቸው ሃሳቦች በሙሉ የእርስዎ ናቸው ወይ?  እርግጥ አንዳዶቹ ሃሳቦች የእርስዎ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለመገመት አይከብድም። ሌሎቹ ግን የእርስዎ አይመስሉኝም።

ለምን ቢሉ፤ ሃሳቦቹ የኢትዮጵያን ህዝቦች ዕድገትን ፣ ልማትንና ሰላምን ማየት የማይሹ ቀጣሪዎችዎ የኒዮ-ሊበራል አቀንቃኞች በእርስዎ አፈ-ቀላጤነት አማካኝነት እንዲተላለፉ የላኳቸው መልዕክቶች ይመስሉኛል። ግን ጓድ ፃድቃን ምናለበት ይህን ህዝብ ብትተውት?፣ምናለበት በጀመረው የልማት ጎዳና እንዳይጓዝ ፊት ለፊቱ ላይ እየቆማችሁ እንቅፋት በመሆን ባታስቸግሩት?...ምናለበት ኪራይ ለመሰብሰብ አባዜያችሁ እንደ መሳሪያ ባትጠቀሙበት?...ለማንኛውም በቀጣዩ ፅሑፌ እስምንገናኝ ድረስ ቸር ያሰንብተን።

 

Read 4686 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 13:55