Saturday, 21 May 2022 12:07

ምኗን ነው የወደድኩት?

Written by  አድሃኖም ምትኩ
Rate this item
(2 votes)

       ፋብሪካ ውስጥ ነው የምሰራው ፤ ድህነት መላ ነገሬ ላይ  ምልክት አሳርፏል ፤ ከድህነቴና ከጉልበት ስራ  ማምለጫ ተስፋ ያደረኩት በማታ የምማረውን ትምህርት ነው። በእርግጥ እንደምማር ለማንም አልናገርም፤ የድል መንገድ ጅማሮ እንደዋዛ አይዘበዘብም የሚል መርህ አለኝ፡፡
 በትምህርቴ ተንጠላጥዬ አሳካዋለሁ ባልኩት ህልሜ ነው  የዛሬ ትንሽነቴ ያላኮሰመነኝ ፤ ህልሜ ተስፋ ሆኖኛል፡፡
ተስፋን የመሰለ የመኖር ጉጉትን የሚያንር ምን አለ ? ምንም!
በዚህ ጉስቁልና ውስጥ እየተመላለስኩ ፤ ስንት መሰረታዊ ፍላጎቴን ሳላሟላ ተንጠራርቼ በሶፊያ  ውበት እደመማለሁ።
ሰው ከኤዶም ገነት በመፈጠሩ ነፍሱ የተሻለ ነገር እንደሚመኝ፣  እኔ በሶፊያ  ሰብዕና መመሰጤና መማረኬ ምስክር ነው፡፡
 ሶፊያን እወዳታለሁ።
ሶፊያን ግን ምኗን ነው  የወደድኩት ?
ድምጿን ፦
ድምጿን ነው የምወድላት ስል ፍቅሯ አክንፎኝ እያሞኘኝ  ያስመስለኛል ፤ ነገር ግን ድምፅ ውስጥ የማይታይ ማንነትና  የማይገለፅ  ስሜት የለም።
የድምጿ ጥንካሬ እንደቦታው እና እንደሁኔታዋ ሽብርክ ሲል ታስደምመኛለች ፤ አንድ ቀንም ድምጿ ውስጥ በገንዘብና በትምህርት እበልጥሃለሁ የሚል ነገር ሰምቼ አላውቅም።
ሶፊያ ድምጿን ብቻ ሰምቼ ከማን ጋር እንደምታወራ  ይገባኛል ፤ ያልተገራ ድምፅ ውስጥ ያልበሰለ ማንነት ይወሸቃል ፤ የጎደፈ ማንነት በድምፅ ውስጥ ይታያል።
ሶፊያ የምሰራበት ፋብሪካ ውስጥ  የእኛ ዲፓርትመንት አለቃ ናት ፤ ስለምንወዳት እንሰማታለን፤ ማስቀየም አንፈልግም።
 የበፊት አለቃችን ማንነት እሷን እንድንረዳትና እንድናውቃት መንገድ ስለከፈተልን፣ ባናምንበት እንኳን ቅር ላለማሰኘት የማንሆነው የለም፤ ለገባው ከክፉ ይልቅ መልካም ሰው በፍቅሩ ሰውን የበለጠ ባርያ እንደሚያደርግ ሶፊያ ምስክር ናት።
ሶፊያን  እቀርባታለሁ ፤ ስንት ቀን ለክፉ ቀን ደርሳልኝ እረስታልኛለች ፤ ለራሴም ለሰውም ነግራ አላስታወሰችኝም፡፡ ደግ ማለት የዋለውን ውለታ የሚዘነጋ ነው ፤ ድምጿ ውስጥ #ዋልኩልህ; ድምጸት ኖሮ አያውቅም።ስንቴ ስህተቴን አለስልሳ ሳታጎላ አስተምራኝ አልፋለች ፤ ስልጡን ማለት አለማወቅህን ሆን ብሎ የማያጎላ፣ ስህተትህን የማያጮህ ነው።
በቃ ሶፊያን  እወዳታለሁ !
ከጉድፍ ላይ ውበት የማያስስ ፤ ጭንቅላቱን ድክመትና ስህተት በማሰስ የማያደክም ሰው የተባረከ ነው ፤ ሶፊያ  ስንት ቀን ሰው አይቶ ነገሮኝ ወይም አስተውሎት የማያውቀውን ውበቴን በምወደው ድምጿ  ነግራኛለች ፤ የራሱ የውበት  መመዘኛ ያለው ሌላው የሚሰፍርበት መስፈርያ የማያውከው የታደለ አይደል?
የምትወደውን ለመናገር ፣ የታያትን ለመመስከር የእኔ ሶፊያ ደጋፊና አጨብጫቢ አላስፈለጋትም ፤ ልበሙሉነቷ ብቻውን ለመቆም ምርኩዝ ሆኗታል።
ድምጿ ርህሩህ እንደሆነች ፤ እንደማትፈራ ፤ ሰው እንደምትወድ ፣ እንደደበራት ዋሽቶ አያቅም ፤ ድምጿና አድራጎቷ አይለያይም ።
ከአለቃዋና ከእኔ ጋር ስታወራ የምታወጣው ድምፅ አይራራቅም ፤ የሰው ማንነት ዋነኛ መለኪያ ከበታቹና ከበላዩ ጋር ሲሆን በሚሆነው ሁኔታ፤ በሚያደርገው  ድርጊት፤ በሚሰጠው አስተያየት ልዩነትና አንድነት ርቀት  ልክ ይመዘናል።  
ሶፊያን እወዳታለሁ ።
 ከሚወዱት ጋር በፍቅር መቆራኘት የወደዱትንም ማግኘት ግዴታ አይደለም ፤ ጤነኛ የሆነ  መውደድ ምቾት አለው ፤ የምንወደውን ሁሉ ካላገኘን ትግል ነው ምቾታችንን የሚሰልበው።



Read 1285 times