Saturday, 21 May 2022 11:37

“የምክክር ኮሚሽኑን የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሊዘውረው አይገባም”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የምክክር ኮሚሽኑ እንደቀድሞዎቹ ኮሚሽኖች እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል
          ሽምግልና ሲዋረድ፣ ነባሩ ባህላችንና እሴታችን ሲረገጥ ለምን ብሎ የጠየቀ የለም
          ለትውልዱ መበላሸት ትውልዱን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይደለም

           በአገራችን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ምክክር በመጪው ዓመት ህዳር ወር ላይ እንደሚጀመር ተገልጿል። በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንደተገለጸው፤ ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያጠናቀቀ ሲሆን በቀጣዮቹ የክረምት ወራት የዝግጅት ምዕራፎቹ ይጠናቀቃሉ ተብሏል፡፡ ለዚህ አገራዊ የምክክር መድረክ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብለው ከሚጠበቁ አካላት መካከል የእርቅና ሽምግልና ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና የጎሳ መሪዎች ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ አንጻር በአማራ ክልል የተቋቋመውና “የአማራ ህዝብ የሽምግልና ስርዓት ማህበር” የተሰኘው ተቋም መሥራችና ፕሬዚዳንት የሆኑትን ሊቀህሩያን  በላይ መኮንን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ አግኝታ፣ ስለ ማህበሩ አመሰራረትና ዓላማ እንዲሁም ስለ አገራዊ የምክክር  ኮሚሽኑ ተስፋና ተግዳሮቶች አነጋግራቸዋለች። እነሆ፡-



              ይህንን የሽምግልናና የእርቅ ስርዓት ማህበር ለማቋቋም መነሻ የሆናችሁ ነገር ምንድነው? ማህበሩስ የተቋቋመው መቼ ነው?
ማህበሩ የተቋቋመው በ2010 ዓ.ም ነው። ለማህበሩ መቋቋም መነሻ ምክንያት የሆነን ጉዳይ በአገራችን ለሽምግልናና ለእርቅ ይሰጥ የነበረው ክብርና ቦታ ሲጠፋ ማየታችን ነበር። እኔ ለምሳሌ ያደግሁት በገጠራማው የአገራችን ክፍል ነው። የሽምግልና ስርዓቱ ያለውን ቦታና ዋጋ በደንብ እያየሁ ነው ያደግሁት። የሽምግልና ስርዓቶች ለማህበራዊ ችግሮቻችን ምን ያህል ቁልፍ መፍትሄ እንደሆኑ አውቃለሁ። እንዳለመታደል ሆኖ ባለፍንባቸው 40 እና 50 ዓመታት (ሶሻሊዝምን ስርዓተ መንግስት አድርገን ከተቀበልን ጊዜ ጀምሮ ማለት  ይቻላል) ሽምግልና ተረገጠ፤ ትኩረት አጣ፤ ተረሳ፡፡ በእድሜ ገፋ ያለውን ሰው ሁሉ ከነበረው ዘውዳዊ ስርዓት ጋር በማያያዝ አድሃሪ፣ ፊውዳል ምናምን እየተባለ ተገፋ። ሽምግልና ተረገጠ። ትልልቅ ሰዎቻችን፣ ጥቁር ደም ያደርቃሉ የምንላቸው የተከበሩ አባቶቻችን ሁሉ በጮሌ ካድሬዎች በስነ-ልቦናም በአካልም እንዲደርቁ ተደረገ። የደርግ ስርዓት ወድቆ በኢህአዴግ ስርዓት ሲተካም፣ ሽምግልና የገጠመው የከፋ ነገር ነው። ይህ ሁኔታ በጣም ያሳዝነኝ ነበር። እናም በዚህ ዙሪያ ለመስራት ፍላጎት አደረብኝ። ሆኖም ሁኔታዎች ይህንን እንድናደርግ አይፈቅዱልንም ነበር። ያው እንደምታውቂው በ2010 ዓ.ም ያልታሰበ ለውጥ መጣ። ሁኔታዎች ሲለወጡ አየን፤ መናገርና መተንፈስ እንደሚቻል ተገነዘብን። ጊዜ ሳናጠፋ ይህንን የሽምግልናና የእርቅ ማህበር መሰረትን። ማህበሩ ከየትኛውም ፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ዘር ውጪ የሆነ የሽምግልናና የእርቅ ስርዓት ማህበር ነው። ስንጀምረው አቅምም ስላልነበረን፣ የባህርዳር ከተማና አካባቢው የአገር ሽምግልናና እርቅ ማህበር ብለን ነበር ያቋቋምነው፡፡ በሂደት ነው ክልላዊ ሆኖ እንዲቋቋምና በመላው አገሪቱ እንዲንቀሳቀስ ያደረግነው።
ማህበሩ ባለፉት 4 ዓመታት ያከናወናቸው ስራዎች ምንድናቸው?
የማህበሩ ቀዳሚ አላማው ትውልድን ማስተማር፣ ግንዛቤ መፍጠርና የተበላሸውን ማስተካከል ነው። ከነባሩ አገራዊ ባህላዊ እሴቶቻችን ያፈነገጠ ብዙ ትውልድ አለን። ማንነቱ የጠፋበት፣ በመጤ ባህሎች የተጠመደና በሱስና መሰል ችግሮች ውስጥ የተዘፈቀ ብዙ ትውልድ አለን። ይህንን ትውልድ የማዳንና የመመለስ ስራ እንሰራለን። ከአገር አቀፉ የሽምግልና መማክርት ጉባኤ ጋር በቅርበት የመስራት ዕድሉንም አግኝተናል። ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች  ላይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ለመፍጠርም እንሰራለን።
ማህበራችሁ ሲቋቋም በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር። እንዴት ነው በክልል ደረጃ እንዲቋቋምና ስራውን በስፋት እንዲያከናውን ልታደርጉ የቻላችሁት?
በተለያዩ አገራዊ የእርቅና የሽምግልና ጉባኤዎች ላይ እየተገኘን የአቅማችንን ያህል ተሳትፎ ስናደርግ ቆይተናል። ማህበራችንን በክልል ደረጃ ብናሳድግና ሌሎች አካላትንም ብናካትት ብዙ መስራት እንደምንችል አሰብንበትና ከማንኛውም ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ዘር ተኮር ጉዳዮች ነጻ የሆኑ፤ ለትውልድም፣ ለወገንም ለአገርም የሚያስቡ ሰዎችን ለመፈለግ ጥረታችንን ቀጠልን። በክልሉ 12ቱም ዞኖች ጥናት ጀመርን። ጥናት በምናደርግበትና ሰዎችን በምናፈላልግበት ጊዜ በተዘዋዋሪ መንገድ ነው ለመሄድ የሞከርነው። በመንግስት መዋቅር ውስጥ በቀጥታ መሄድ አልፈለግንም። እንደዛ ካደረግን አንዳንድ በሽምግልና ስም ለፖለቲካው ሲያጨበጭቡ የከረሙ ሰዎች ጣልቃ ሊገቡብን ይችላሉ። እናም በዩኒቨርስቲዎች በሃይማኖት ተቋማትና በአገር ሽማግሌዎች በኩል እየሄድን አሰባሰብንና 12 የዞን ተወካይ ሽማግሌዎችን ይዘን የሽምግልናና እርቅ ስርዓት ማህበሩን በ2012 ዓ.ም ወደ ክልል ደረጃ አሳደግነው። እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ትላልቅ የሰላምና የእርቅ ጉባዔዎች ላይ እየተገኘን የበኩላችንን ለማድረግ መሞከር የጀመርነው። ባሰባችሁበት ልክ እየሰራችሁ ነው ወይ? ብለሽ ከጠየቅሽኝ ግን፣ እየሰራን አይደለም። ትውልዱን ለመድረስ ገና ብዙ ይቀረናል። ነገር ግን በእስካሁኑ ስራችን ሽምግልና ዕውቅና እንዲያገኝ፣ መንግስትም ለሽምግልና እና ለእርቅና ሰላም ጆሮውን እንዲከፍት አድርገናል።
በአሁኑ ወቅት የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የጎሣ መሪዎች ያላቸው ተሰሚነት ምን ያህል ነው? ትውልዱ ለእነዚህ ወገኖች ያለውን ግምት እንዴት ያዩታል?
ሽምግልናን ለማዋረድና ቦታ እንዲያጣ ለማድረግ የተሰራው ስራ በአጭር ጊዜ የተሰራ አይደለም። ዓመታትን የወሰደ ስራ ተሰርቷል። ይህንን ሁኔታ ለመለወጥም ጊዜ ያስፈልጋል። እኔ በትውልዱም አልፈርድም። ያኔ በደርግ ዘመን የሽምግልና ስርዓቱ ሲረገጥ አንገቱን ቀና አድርጎ እውነቱን በድፍረት ለመናገር የሞከረ፣ ትውልዱ  ከነባሩ ባህልና እሴት ሲወጣ ለመገሰጽ የደፈረ የለም። በእርግጥ በትሩም ከባድ  ቢሆንም ማንም በድፍረት ለመናገር  የሞከረ አልነበረም። እራሴን ጨምሮ ማለት ነው። አሁን በትውልዱ እናመካኛለን። ትውልዱ ከስርዓት ወጥቷል እንላለን። እንዲወጣ በሩን የከፈትንለት ግን እኛ ነን። እኛ ጠንክረን ከሰራንና በትክክለኛው መንገድ ከመራነው ይመለሳል፡፡ የአገር ሽማግሌም የሃይማኖት አባትም ይሁን አባገዳም በትክክል እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነትን ይዘው ትውልዱን ካስተማሩ ትውልዱ የማይመለስበት ምክንያት የለም። እኛ ጋ ግን ችግር አለ። ትናንት ወደ ፖለቲካው ተጠግቶ በሽበቱና በሽምግልናው ሲነግድ የነበረ ብዙ አለ። በሃይማኖትም ጭምር። ከደርግ ወዲህ ያሉ ሥርዓቶች እኮ የአገር ሽማግሌውንም ሆነ የሃይማኖት መሪውን ለመጠቀም ያላደረጉት ጥረት የለም። የጥቅም ተካፋይ እያደረጉ ለአላማቸውና በጎ ለማንለው ተልዕኮአቸው ማስፈጸሚያነት ተጠቅመውበታል። ይህ ሁኔታ አሁንም የለም ለማለት አልደፈርም። እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም፣ እያንዳንዱ ሽማግሌና የጎሳ መሪ በራሱ ቁመና ላይ ሆኖ በትክክል ቢሰራ ትውልዱ በቀላሉ ይመከራል። ፌስቡክ አይደል በቀላሉ እየነዳው ያለው፡፡ እኛ የራሳችንን በጎ ተጽዕኖ ብንፈጥርበት ልንመልሰው እንችላለን። ትውልዱ እኮ ከእኛ በተሻለ ያውቃል። ዕውቀት ባይኖረውም መረጃ አለው። ለእውቀት አላነበበም። እኛም እንዲያነብ አላደረግነውም። ለመረጃ ግን እያነበበ ነው። መረጃ ከእኛ የተሻለ አለው። እናም ትውልዳችንን ለመመለስ ከዘረኝነት  ነጻ ሆነን፣ ሁላችንም በትክክል ካስተማርነው የማይመለስበት ምክንያት የለም። ሌላው፣ ለትውልዱ መበላሸት የሚታየኝ አደጋ ሥራ አጥነት ነው። ምን ያድርግ የሚበላው የሌለው፣ ሆድ የባሰው የከፋው ትውልድ እንዴት አገር፣ ማንነት፣ እምነት  ሊኖረው ይችላል? እናም ለትውልዱ መበላሸት ትውልዱን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ትክክል ነው ብዬ አላምንም።
በአገር አቀፍ ደረጃ በቅርቡ ይጀመራል ለተባለው አገራዊ የምክክር መድረክ ምን አስተዋጽኦ እያደረጋችሁ ነው?
እንደ እኛ አገር አይነት ማህበረሰብ ላላት አገር፣ ምክክር በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። መመካከር፣ መወያየት፣ ችግርን የጋራ አድርጎ የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ በጣም ያስፈልጋል፡፡ ማህበረሰባችን የየራሱ መገለጫ ቋንቋ ወግና ስርዓት ያለው ህዝብ ነው። እንዲህ ሰፊ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ ምክክር ያስፈልጋል። አስታራቂ፣ የሚያግባባ ያስፈልጋል። ይህ በአገራችን ጥንትም ያለ ጉዳይ ነው፤ መኳንንቱና መሳፍንቱም አማካሪ አላቸው። እረኛ ምን አለ ሲሉም ይጠይቃሉ። ይህም የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማወቅና ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ ነው።
አሁን መሃል ላይ ነው ሽምግልናውም ሁሉም ሲቀር መመካከሩም የቀረው። ሁሉም እኔ አውቃለሁ ባይ ሆነ። እናም እኛ ለመመካከር በጣም ዘግይተናል። አሁን ችግሩ አፍጦ ሲመጣብን ነው ለመመካከር የተነሳነው። የምክክር ኮሚሽኑ ብዙ ስራ ይጠብቀዋል። እንደ በፊቶቹ ኮሚሽኖች እንዳይሆን ሊጠነቀቅ ይገባል። የቀድሞዎቹ ኮሚሽኖች ምን የሰሩት ተጨባጭ ነገር አለ ብለን ስናይ ምንም የለም። አሁን ለምሳሌ በቅርቡ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተተካው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ወይም የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚሽን የሚባሉት ባሳለፍናቸው ዓመታት ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወት ይችሉ ነበር። እንደ አገር ትልቅ ፈተና ውስጥ የገባንበት ጊዜ ነበርና ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ያ ባለመሆኑ ትልቅ ዋጋ ተከፈለ። አሁንም የተቋቋመው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ትልቅ ድርሻ አለው። መቼም መንግስትን ሆኖ አይሰራም፤ ህዝብን ሆኖ፣ የህዝብን ትንፋሽ እያዳመጠ፣ በመንግስትና በህዝብ መካከል መደላድልና መሰላል ሆኖ ትልቅ ስራ መስራት መቻል  አለበት።
በኮሚሽኑ ውስጥ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ይኖራል ብለው ያስባሉ? ከዚህ  የምክክር ኮሚሽንስ ምን ይጠብቃሉ?
ይህ የብዙዎች ስጋት ነው። ፖለቲካው እጁን ያስገባበታል የሚል ስጋት አለ። ይህንን ነው ሁላችንም በየመድረኩ የምንናገረው። መንግስት ይህንን የምክክር ኮሚሽን ከማደራጀት ከማጠናከርና ሜዳውን ከማመቻቸት ውጪ እጁን ሊያስገባበት አይገባም። ይህ ክስ እስካሁን የተፈተንበት ጉዳይ ነው። ኮሚሽን ተብሎ ይቋቋማል፤ ከፖለቲካው ነጻ አይሆንም። እያንዳንዱ ወይ የብሔር ወይ የቋንቋ መለያውን ይዞ ይገባል፡፡ እናም ፈተናችን የበዛው በዚህ ምክንያት ነው። አሁን አደራ የተጣለባቸው ሰዎች አሉ። ታሪክ እንዲሰሩ ይፈለጋል። ከእነዚህ ሰዎች ብዙ እንጠብቃለን። በየአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮችን ማየት፣ ህብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ ማወያየት፣ የግጭት መንስኤዎች ላይ ጥናት ማድረግና  የመፍትሄ ስራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል። ሸክማቸው ከባድ እንደሆነ ይሰማኛል። የህዝቡ ጥያቄ ህገ-መንግስት እስከማሻሻል የሚደርስ ነው። የህዝቡን ሁለንተናዊ ሃሳብና ስሜት በሚደግፍ መልኩ ህገ-መንግስትን እስከማሻሻል ድረስ የሚዘልቅ ከፍተኛ ሃላፊነትን የሚጠይቅ ስራ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን ይህ ግቡን ሊመታ የሚችለው በእነዚህ አስራ አንድ የኮሚሽኑ አባላት ብቻ አይደለም። ሁሉም ራሱን የኮሚሽኑ አባል እንደሆነ እያሰበ ሊሰራ ይገባል። የሃይማኖት አባላቱም፣ የአገር ሽማግሌውም፣ የጎሳ መሪውም የምክክር ኮሚሽኑን በማጠናከርና በማገዝ፣ ችግሮቻችንን በጋራ ፈተን ወደቀድሞው የመመካከርና የሰላም ታሪካችን መመለስ አለብን፡፡ እያለን ጦም አዳሪዎች ከሆንበት ታሪክ መውጣት አለብን። ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለህዝብና ለህዝብ ብቻ መሆን አለበት፤ ማንም የፖለቲካ ድርጅት ሊዘውረው አይገባም። “ስለ እርቅና ሽምግልና ጉዳይ ለመወያየት ጊዜው አይደለም፤ የሰዎች ቁስል ባልደረቀበትና ሃዘናቸው ባልሻረበት ሁኔታ ስለእነዚህ ጉዳዮች መወያየቱ ተገቢ አይደለም” የሚሉ ወገኖች አሉ። የእርስዎ ሃሳብ ምንድነው?
መቼም በደረሰው ነገር ሁላችንም አዝነናል። በደሉ ግልጽ ነው። ባልተጠበቀ ጊዜና ሁኔታ የተፈጸመ እኩይ ድርጊት ነው። የህዝቡ መጎሳቆል፣ መሰቃየት፣ መሞት፣ መፈናቀል ህመሙ ይሰማናል። በህዝብ ላይ የተፈጸመው በደል በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ነው። በሰው፣ በእንስሳትና በእጽዋቱ ላይ ሁሉ ሠይጣናዊ ስራ ተሰርቷል። ነገር ግን እርቅና ይቅርታን ማሰቡ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ከሌሎች ልንማር ይገባል። አባቶቻችን እኮ ሰው ተገድሎ ጥቁር ደም ፈስሶ 10 ቀን እስኪሞላው እንኳን አይጠብቁም። ይሄዱና የተጎዳውን ወይም ሰው የሞተበትን ወገን በሽምግልና ይይዙታል። ተጎጂው “ተውኝ እንጂ ዓይኑን እንኳን ሳይፈስ…” ይላል። ግን አይተውትም ይይዙታል። “እስከዚያው ድረስ ክፉ ላታስብ ቃል ግባልን” ይሉታል። ባይታረቅ እንኳን ለጊዜው ቃል ያስገቡታል። ልማዳችን ይህ ነው። ከሩዋንዳም ቢሆን የምንማረው ይቅርታ ማድረግን ነው። የሩዋንዳ እልቂት የዓለማችን አሰቃቂ ጠባሳ ነው። እሱንም ቢሆን የፈታው እርቁ ነው። እስቲ ትንሽ እናቆየው ቢባል ችግሩ ይባባሳል። በደመኝነትና በጠላትነት እየተፈላለግን እንቆይ ካልን፣ ወደከፋ ምስቅልቅል ውስጥ እንገባለን። ችግራችንን ሊፈታ የሚችለው ወደ እርቅና ሰላም መምጣቱ ብቻ ነው። #የለም ይህንን ያህል ተበድን በቀላችንን ሳንመልስማ አይሆንም; ካልን፣ ይቺን አገር እንዳትኖር ልናደርጋትም እንችላለን። እናም የምክክር ኮሚሽኑ ሊሰራው የሚገባው ብዙ ስራ አለ። ለፖለቲከኞች መጠቀሚያ የሆነ የወሰን፣ የማንነትና የድንበር ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጠው በህግና በህግ ብቻ መቋጫ ሊያገኝ ይገባል። ለችግራችን  በጋራ መፍትሄ በመፈለግ ከገባንበት ምስቅልቅል ውስጥ መውጣት አለብን።




Read 2169 times