Saturday, 21 May 2022 11:30

ታዋቂው ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ) አረፈ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


               ዶክሌ በሚለው ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ ባጋጠመው የልብ ህመም  በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ፣ በአሜሪካ ዋሽንግተን ሜድስታር ሆስፒታል ውስጥ በ57 ዓመት ዕድሜው ማረፉ ተነግሯል፡፡
“ዶክሌ ቅንና ታዛዥ ባለሙያ ነበረ” ያለው የሙያ አጋሩ  አርቲስት ቴዎድሮስ ለገሰ፤ ኮሜዲያኑ በደረሰበት የልብ ህመም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲረዱት እንደነበር ጠቁሞ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ታሞ ሆስፒታል ገብቶ ህክምና እንዲያገኝ ቢደረግም ህይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ ገልጿል።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ኮሜዲያን ዶክሌ፤ በመድሐኒአለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል።
የእሱንም ሆነ የቤተሰቡን ህይወት ለመምራት በመካኒክነት ሙያ ትምህርት ቀስሞ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም፣በኋላ ላይ የጥበቡን ዓለም በመቀላቀል በኮሜዲ ዘርፍ ተወዳጅነትንና ከበሬታን የተቀዳጀባቸው በርካታ የተዋጣላቸው ሥራዎችን ለማቅረብ በቅቷል፡፡በስታንድ አፕ ኮሜዲ አያሌ  ቁምነገር አዘል ቀልዶችን እንዳቀረበ የሚነገርለት ኮሜዲያኑ፤ በሙሉ ጊዜ የፊልም ስራዎችም ዝናና ዕውቅናን ለማትረፍ ችሏል፡፡ ለዚህም  #የራስ አሽከር; የተሰኘው ታሪክ ቀመስ ፊልም ላይ ያሳየው ድንቅ የትወና ብቃቱ ይጠቀስለታል፡፡
ከስምንት አመት በፊት ለስራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ በማቅናት ኑሮውን በዚያው አድርጎ የቆየው ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ)፤ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበር።
የኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ የቀብር ስነስርአት የሚፈጸመው በትውልድ ሀገሩ ኢትየጵያ ነው የተባለ ሲሆን ለዚህም ማስፈጸሚያ ወጪ ለማሰባሰብና ቤተሰቦቹን ለመርዳት የጎፈንድሚ አካውንት መከፈቱ ታውቋል፡፡


Read 10887 times