Saturday, 21 May 2022 10:54

እናት ፓርቲ “ህገ ወጥ አፈናዎች” እንዲቆሙ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ከህግ አግባብ ውጪ በግለሰቦች ላይ የሚፈጸሙ አፈናዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው ያመለከተው እናት ፓርቲ፤ መሰል አፈናዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙና የታፈኑ ግለሰቦች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ  ጠይቋል።
“አፈና ለደርግና ለህወሃትስ ምን ጠቀመ?” ሲል በመግለጫው የጠየቀው ፓርቲው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የለውጥ ሂደት መልሶ ወደ አፈና ሥርዓት እየሄደ መሆኑ አሳስቦኛል ብሏል፡፡
“የህግ የበላይነት ይመጣል ብለን ስንመኝ የግለሰቦችና የቡድኖች የበላይነት እየሰፈነ መጥቷል” ያለው የእናት መግለጫ፤ ይህ መሰሉ አካሄድ ሃገሪቱን ቁልቁል የሚወስድ አደገኛ አካሄድ ነው ብሏል።
ብልጽግና ወደ ስልጣን ሲመጣ በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ አፈናዎችንና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን በመኮነን፣ ላለፉት ጥፋቶች ይቅርታ በመጠየቅ ጭምር እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፤ ብዙም ሳይቆይ ቀድሞ የተለመደው አፈና፣ ህገ-ወጥ እስርና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ መቀጠሉ  የሃገሪቱ ዲሞክራሲ የቁልቁለት ጉዞ ላይ መሆኑን ያመላክታል ብሏል።
#በተለይም ሃገር ተደፈረች ብለው ከጡረታቸው እየተመለሱ ሃገር ለማዳን የታገሉ ጀግኖችንና ጋዜጠኞችን ማፈን፣ ማጥፋትና ማሳደድ እንደ ትልቅ ክህደት የሚታይ ነው; ያለው መግለጫው፤ ተግባሩም ህዝብን ወደ አመጽ መንገድ የሚመራ አደገኛ አካሄድ ነው ብሏል።
 ላለፉት 50 ዓመታት ተሞክሮ የከሰረን ሥርዓት ለመድገም መሞከር ህዝብን ወደተለመደው የአመጽ መንገድ የሚመራ ተግባር ስለሆነ፣ ከህግ አግባብ ውጪ የሚካሄዱ አፈናዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ የታፈኑ ዜጎች ማን በምን አግባብ እንዳፈናቸው ለህዝብ ይፋ እንዲደረግና በወንጀል የተጠረጠሩ ከሆነም በግልጽ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲሁም ሰዎችን ከህግ ውጪ የሚያፍኑ ሃይሎች በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል፤ እናት ፓርቲ በመግለጫው።

Read 10831 times