Sunday, 15 May 2022 17:37

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
                   የታሪክ ሰናጁ ሰው ታሪክ - እዝራ እጅጉ


           በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ የህትመት ሚዲያው ፈርጣማ ክንዱን ባሳየበት በ1980ዎቹ መጨረሻ፣ ትታተም በነበረች “ኩኩሉ” የልጆች መጽሔት ላይ አንድ የ15 ዓመት ብላቴና የወደፊት ምኞቱን አሰፈረ። በየትኛው የትምህርት ተቋም ምን መማር እንደሚፈልግ፣ ምን ዓይነት መጽሐፍ ማሳተም እንደሚሻ፣ “እግዚአብሔር ብሎለት” ሃብታም ቢሆን መክፈት ስለሚፈልገው ድርጅት... የመሻቱን ሁሉ መጽሔቷ ላይ በዝርዝር አሰፈረ። ምንም እንኳ  የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በዘመኑ ለአቅመ ንባብ ባልደርስም፣ ምኞቱን ያነበቡ አዋቂዎች ግን “ያሳድግህ” ከማለት አልፈው “የምኞቱን ቢያሳካስ” ብለው ያሰቡ አይመስለኝም።
ይህ ከሆነ ከሶስት አስርታት በኋላ፣ የያኔው ብላቴና አሁን ባለው ዘመኑ የሆነውንና በለጋ እጁ ከትቦ የልጆች መጽሔት ላይ ያኖረ የልጅነት ምኞቱን ብናስተያይ መስመር በመስመር ይገጥማሉ። የፈለገውን ተምሮ፣ ያሻውን ጽፎ፣ ያሰበውን ድርጅት ከፍቷል።  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ተመርቆ፣ የተፈጥሮ ውበት ስለሆነው የሰው ልጅ መጽሐፍትን ጽፎ፣ የሥነ ጽሑፍ ፍቅርና ችሎታ ላላቸው ልጆች የስራ እድልን የፈጠረ “ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን”ን አቁሟል፦ እዝራ እጅጉ። የስራ እድሉ በረከት ከደረሳቸው አንዱ ነኝ  እኔ አማረ ደገፋው፤ ዛሬ ሌላ እድል ደርሶኛል፦ የታሪክ ሰናጁን ሰው ታሪክ መሰነድ።
የተወዳጅ መነሻ 1996 ዓ.ም የካቲት ወር ቢሆንም፣ ለታሪካዊ ስራዎች ትኩረት መስጠት የጀመረው ከ2008 ዓ.ም ወዲህ ነው። ያለፈውን አንድ አመት ደግሞ “ዘመነኞቹን በዊኪፒዲያ” በሚል ፕሮጀክት በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ ሰዎች በህይወት እያሉ ታሪካቸውን በወጉ ሰድሮ ስላበረከቱት በጎ ተፅዕኖ ማመስገን ጀመረ። 170 የሚደርሱ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ ሰንዶ ጠንካራ ሽፋን ባለው መዝገበ አዕምሮ (ኢንሳይክሎፒዲያ) ለማሳተም ሲሯሯጥ ከግማሽ በኋላ ያለውን መንገድ አብሬው ስለሮጥኩ፣ ‘የዚህን ሁሉ ሰው ታሪክ እየሰራ እንዴት የራሱን አይጽፍም...? ለራሱ እንዴት ሰነፈ?’ የምትል የጎን ሃሜት ነበረችኝ። መዝገበ አዕምሮ ወደ ማተሚያ ቤት ለመግባት ሳምንት ሲቀረው የእርሱም ታሪክ መሰነድ እንዳለበት ተማምነን ለቃለመጠይቅ ተቃጠርን። ወደ ቤቱ ሄድኩ፤ ላፕቶፑ ላይ ሆኖ ከጽሁፉ ጋር ግብ ግብ ይገጥማል፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ ይይዛቸው የነበሩ ዲያሪዎች ልቅም ባለ የኮምፒውተር ጽሑፍ ተተይበው በዘመን ቅደም ተከተላቸው የሰፈሩበት ዳጎስ ያለ ጥራዝን ሳይ፣ ከአመታት በፊት ለህትመት የበቁ ስራዎቹን የያዙ ባለጠንካራ ሽፋን መዝገቦችን ሳገላብጥ፣ በቃለመጠይቁ ወቅት ከሃያና ሰላሳ አመት በፊት የነበሩ ክስተቶችን ትላንት የሆኑ ያህል ሲያስታውስና ልክ ቅድም ያገኛቸው ይመስል የሰዎችን ስም ድንቅፍ ሳይል መጥራቱን ስታዘብ፤ ‘ለራሱ እንዴት ሰነፈ’ የሚል ትዝብቴን ሽሬ ለረዥም አመታት በትጋት ከተሰነደ ሰፊ ታሪኩ ለአንባቢ እንዲሆን መቀንጨቡን ማሰብ ጀመርኩ። እነሆ የታሪክ ወዳዱ እዝራ እጅጉ ቅንጭብ ታሪክ፦
የታሪክ መውደዱ ማሳያ መቼ እንደተወለደ ሲጠየቅ “የደርግ መንግስት የድል በዓልን ባከበረ በሁለተኛው ቀን እሁድ መጋቢት 30፣ 1971 ዓ.ም ተወለድኩ” ነው መልሱ። በዚያው በ1971 አመት ግንቦት ወር  የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ይሰሩ የነበሩት አባቱ አቶ እጅጉ ሙላት፣  ወደ ጅቡቲ በመዛወራቸው እትብቱ የተቀበረባትን መሬት ሳይድህባት፣ በእናቱ ወይዘሮ በለጥሻቸው ስዩም እቅፍ ሁኖ አባቱን ተከትሎ  ጅቡቲ ገባ። የ4ኛ ዓመት ልደቱን እስኪያከብር በቆየባት የጎረቤት ሀገር ትዝታዎች መካከል አንዱ እሳት ነው። በልጅነት የመመራመር መንፈስ ሆኖ ‘እሳት ያቃጥላል አያቃጥልም?’ የሚለውን ለማረጋገጥ ያደረገው ሙከራ ሙሉ ቤቱን በልቶ አሳይቶታል።
ከጅቡቲ መልስ በ1976 ዓ.ም ‘ማርች ኤይት’ ትምህርት ቤት ገብቶ ለሁለት አመታት የመዋእለ ህጻናት ትምህርቱን ተከታትሏል። ቀጥሎ ወደ ‘ቦሌ ህብረተሰብ’ አቅንቶ በ1978 ዓ.ም 1ኛ ክፍል ገባ፤ እስከ 4ኛ ክፍል በዘለቀ ቆይታው ዝምተኛና ፈሪ እንደነበር ያኔ አብረውት የተማሩ ጓደኞቹ ያስታውሳሉ፤ እርሱም የያኔ ጭምትነቱን ያምናል።
በ1981 ዓ.ም ክረምት አባቱን ድጋሚ የምስራቁ ማግኔት ስቧቸው ወደ ድሬደዋ ሲያቀኑ እርሱም ከታናሽ እህቱ ጋር ሆኖ ተከተላቸው። እርሱም እህቱም ዛሬም ድረስ ‘ልዩ’ ብለው የሚገልጿቸውን ሁለት አመታት በድሬደዋ አሳለፉ። ቦሌ ህብረተሰብ እያለ የተረት መጽሐፍትን ማንበብ ድረስ ብቻ የነበረ የሥነ ጽሑፍ ቅርበቱ፤ በድሬዳዋ ቆይታው በብዙ እጥፍ አድጎ ልቦለዶችን እስከመጻፍ ደረሰ። ጥበብ ትጣራ ከሆነ በሥነ ጽሑፍ በኩል የጠራችው በዚህ ዘመን እንደነበር ራሱም ያምናል።  ዛሬም ድረስ በቃሉ የሚወጣቸውን ግጥሞች የያዘችው የክፍሌ አቦቸር “የኔ ጋሻ” መድበልን ደጋግሞ ማንበቡን ያስታውሳል። አባቱ ቢሮ ይመጡ የነበሩ አዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችንና የካቲት መጽሔትን የማንበብ እድሉም ነበረው።
ልዑል መኮንን የተማሩትና በጅቡቲ አመታትን የሰነበቱት አባቱ ለፈረንሳይኛ ቅርብ ስለነበሩ የፈረንሳይኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ነበራቸው። ብላቴናው እዝራ ገና ያኔ ይህን መጽሐፍ ሲያገላብጥ ነበር አሁን እያሰናዳ ያለውን መዝገበ አዕምሮ (ኢንሳይክሎፒዲያ) የማዘጋጀት ሃሳብ የመጣለት። እንዲህ ባለ የመነቃቃት መንፈስ ውስጥ ሆኖ 5ኛ እና 6ኛ ክፍልን በድሬደዋ ከተማረ በኋላ ወደ አዲስ ተመልሶ ለ7ኛ ክፍል ትምህርቱ በድጋሚ ወደ ቦሌ ህብረተሰብ አቀና። የቀድሞ ወዳጆቹ የቀደመ ጭምትነቱን ሲያጡበት ‘እዝራ ፈነዳ’ አሉ። አብሮ አደጉ ናይእግዚ ህሩይ ይህን ጊዜ ሲያስታውስ፤ “ድሬደዋ ምን አግኝቶ እንደመጣ ገርሞናል” ይላል።
“ከመፈንዳቱ” እኩል ንባቡን አበረታ፤ ግቢያቸው ተከራይ ከነበሩ ሰዎች እየተዋሰ፣ የቅባት ጠርሙሶችን ለቆራሊዮ ሽጦ መጽሔት እየገዛ፣ ናይእግዚና ፍቃዱ ሞላ የተባሉ ጓደኞቹ የሚያመጡለትን መጽሐፍት እየተቀበለ ለንባብ አቀረቀረ፤ እናቱ ወይዘሮ በለጥሻቸው “እስኪ እንደልጆቹ ወጣ ብለህ ተጫወት” እስኪሉት ድረስ ከወረቀት ጋር ተዋደደ። 8ኛ ክፍል ሲደርስ ለተለያዩ መጽሔቶች አስተያየትና ስራዎቹን ‘እዝራ እጅጉ ከቦሌ’ በሚል አድራሻ መላክ ጀመረ። 42ቱ የዩኒቨርስቲ መምህራን ሲባረሩ ስሜቱን ጽፏል፤ በቃሉ ከያዘው የክፍሌ አቦቸር ግጥም አንዱን “አፍሪካ ቀንድ” ለተባለ መጽሔት ምንጭ ሳይጠቅስ ልኮ በመታተሙ እንደተከሰሰም ያስታውሳል። በንባቡና በተሳትፎው ከእኩዮቹ ተለየ፡፡
9ኛ ክፍል ሲሻገር ቦሌ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ገባ። በ1986፡፡ ንባብና ተሰጥዖውን ለማሳደግ ሚኒ ሚዲያ ለመግባት ቢያመለክትም ሳይጠራ ይቀራል። በዚህ ተናዶ የሚኒ ሚዲያው በር ላይ ያገኘው አንተነህ ዓለሙን እንዴት በጉልበት ገፍቶት እንደገባ ሲያስታውስ፤ “ምን አለ ካሜራ ኖሮ ሁኔታውን ይዞት በነበር” ይላል፤ ሳያልፍ በጉልበት በገባበት ቤት ችሎታውን በሚገባ አሳይቶ በ4ኛ ወሩ የሚኒ ሚዲያው ምክትል ሊቀ መንበር ለመሆን በቃ።
በዚያው አመት ወደ ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ አቅንቶ መሳተፍ ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ ለገዳዲ ሲደርስ ተቀብለው፤ ሻይ ጋብዘው፤ ቤተ መጽሐፍቱን አስጎብኝተው ያበረታቱት መምህራንን ዛሬም ድረስ ከነስማቸው ያስታውሳል። “ጣሰው ተፈራ፣ ሃይሉ ማሞ፣ ኤርሚያስ ተገኝ፣ ህሊና ማሞ፣ ከድጃ ሰይድ” እያለ ሲዘረዝራቸው ትላንት ያገኛቸው እንጂ ከ30 አመት በፊት ያዋራቸው አይመስሉም። ቤተ መጽሐፍቱን በአግባቡ ተጠቅሞበታል፤ ‘ዘ ወርልድ ቡክ ኦፍ ኢንሳይክሎፒዲያ... ብሪታኒካ’ ጋር ተዋውቆበታል፣ ለገዳዲ ሬዲዮ የጥያቄና መልስ ዝግጅት ከ300 ያላነሱ ጥያቄዎችን አዘጋጅቶበታል።
በ1989 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረ “አካፑልኮ ቤይ” የተሰኘ ፊልምን ወደ አማርኛ መልሶ ከያኔ የትምህርት ቤት ተጋሪው አርቲስት ስናፍቅሽ ተስፋዬ ጋር በመሆን በቦሌ ሚኒ ሚዲያ ተረከ። በወቅቱ ብቸኛ የመዝናኛ አማራጭ በነበረው ኢቲቪ የሚተለለፈው ይህ ፊልም የብዙዎች መነጋገሪያ እንደነበር ያስታውሳል፤ እግር በእግር እየተከታተለ ተርጉሞ ሲተርክ ተማሪዎች በተለየ ጉጉት ነበር የሚከታተሉት። የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ‘ተማሪ እንዳይፎርፍ ስላደረክ’ ብሎ አመስግኖታል።
ከፊልሙ ትረካ መጠናቀቅ በኋላ የሚዲያዎችን ትኩረት ሳበ። ፋንታሁን ኃይለማርያም ከኢቲቪ፣ መስፍን አሸብር ከሬዲዮ ፋና፣ ሰለሞን ጥዑመልሳን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለሰራው የትርጉም ስራ በየተራ አነጋገሩት። መስፍን አሸብር የፋና ስቱዲዮ ድረስ ወስዶ ቃለመጠይቅ እንዳረገውና ከብዙ ጋዜጠኞች ጋር እንዳስተዋወቀው ያስታውሳል። ከቴሌቪዥን ከሬዲዮና ከጋዜጣ በመጡ ጋዜጠኞች ቃለመጠይቅ ተደርጎ ከትምህርት ቤት ውስጥ ዝናው ከፍ አለ። እንዲህ ያለ አድናቆትና መወደድ ያተረፈለትን የትርጉም ስራ በመጽሐፍ መልክ ቢያሳትመው ምን ያህል ገዥ ሊኖረው እንደሚችል ጥናት አድርጎ አጥጋቢ ውጤት በማግኘቱ ለማሳተም ቢጥርም፣ አሳታሚ በማጣቱ ደብተሩን ቅርጫት ውስጥ ወረወረው።
በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍን ለመማር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማታው መርሃ ግብር ተመዘገበ። ከአብሮ አደጉ ናይእግዚ ጋር በመሆን የሚዲያ ፈቃድ አውጥተው  “ልጅነት” የምትል የልጆች መጽሔት ለማሳተም ቢሞክሩም በስፖንሰር ማጣት ምክንያት  ሀሳባቸውን ሳያሳኩ ቀሩ። በተመሳሳይ አመት ወደ ሪፖርተር ጋዜጣ አምርቶ ቅጥር ጠይቆ ስላልተሳካ በነፃ ማገልገል ጀመረ። ለወራት በዘለቀ የነፃ ግልጋሎቱ ደረጀ ደስታ፣ ከበደ ደበሌ ሮቢ፣ ሰለሞን አባተ፣ እሸቴ አሰፋና አብዱ አሊ ሂጅራን ጨምሮ ከሌሎች አንጋፋዎች ጋር ቢሮ ተጋርቶ ጽሑፎቻቸውን አርሟል፣ ዝንቅና ሌሎች አምዶችን አዘጋጅቷል፣ ደሞ በልጅ እግሩም ለአንጋፋዎቹ ተላልኳል። ከሪፖርተር ጋዜጣ በኋላ በተመሳሳይ ግልጋሎት እፎይታ መጽሔትንም ለጥቂት ወራት አገልግሎ፣ “እፍታ” የተሰኘች የወጎች መድበል ላይ ስራው ወጣለት።
ቀጥሎ አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ አመለከተ፤ ከብዙ መቶዎች ተወዳድሮ ሃይለ ገብርኤል ይመርን ተከትሎ፣ ታገል ሰይፉን አስከትሎ፣ በሁለተኝነት አለፈና ጋዜጠኛ ሆነ። 1992 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ በ21 አመቱ፣ ገና የ3ኛ አመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ፣ በ347 ብር የሙሉ ጊዜ ጋዜጠኛ ሲሆን የተሰማውን ደስታ ሲገልጽ፤ “አሁን ላይ ማርስ ብሄድ የሚሰማኝ ስሜት ነበር ያኔ የተሰማኝ” ይላል።
መዝናኛ ክፍልን እየፈለገ ዜና ክፍል ሲመድቡት መጀመሪያ ላይ አልከፋውም ነበር፤ እንዲያውም ‘በሳምንት 4 ዜና ማምጣት አለብህ’ ያለ አለቃውን በተለየ ጉጉት ሆኖ “7 አይቻልም?” ብሎ ጠይቆት ነበር። የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታትን ሰባትም ስድስትም ዜናዎችን መስራት ቢችልም እየቆየ ሲሄድ ግን እንዳሰበው ቀላል ሊሆንለት አልቻለም። በዜና እጦት ራሱን እያመመው ሻሽ አስሮ ቢሮው ይገባ እንደነበር ያስታውሳል። ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ የአዲስ ልሳን ጋዜጠኝነቱን ተወ።
አዲስ ልሳኖች የጻፉበትን ደብዳቤ ይዞ ከአዲስ አድማሶች ደጅ ደረሰ። “ለኔ የሚሆን ትክክለኛ ሰው” በማለት የሚገልፀው አሰፋ ጎሳዬ፣ በጥሩ ፊት ተቀብሎ በ400 ብር ቀጠረው። ከነቢይ መኮንን፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ ሰለሞን ገ/እግዚአብሔር እና ሌሎችም ጋር ባልደረባ ሆኖ ሲሰራ፣ ዜናንም መዝናኛንም አቀላጥፎ ሰርቷል። አዲስ አድማስ ለአንድ አመት ከሰራ በኋላ ወደ ሩህ ጋዜጣና መጽሄት አቀና፡፡
በ1994 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ በ500 ብር ደመወዝ ‘ዘ ፕሬስ’ ገባ። በዚያ ጋዜጠኝነትን ብቻ ሳይሆን ማስታወቂያ የማፈላለግ ስራንም ሰርቶ ዳጎስ ያለ ኮሚሽን እንደተቀበለ ያስታውሳል። ምን አልባት ይህቺኛዋ ኮሚሽን ሳትሆን አትቀርም ወደ ቢዝነሱ ዓለም ቀልቡ እንዲሳብ ያደረገችው። በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ማርኬቲንግን መማር ጀምሮ ነበር። ዮቴክ ኮንስትራክሽን ውስጥ በፐርሶኔልነት ለ11 ወራት እንዳገለገለም ይናገራል። የቁምነገር መጽሔት ምክትል  ዋና አዘጋጅና ሴልስ ሆኖም ሰርቷል።
በዚህ ሁሉ የስራ ዙረት ውስጥ ልምዶችን ሲቃርም የሰነበተው እዝራ፤ በየካቲት 2፣ 1996 ዓ.ም “ተወዳጅ” ብሎ የሰየማትን ጋዜጣውን ማሳተም ቻለ። ማስታወቂያዎችን ብቻ ይዛ የምትወጣው ይህች ጋዜጣ በነፃ ነበር የምትታደለው። ማስታወቂያ መፈለጉ አያስቸግርም ወይ ተብሎ ሲጠየቅ “ለጥረት ነው የተፈጠርኩት” ነው ምላሹ። ገቢዋ ከሽያጭ ሳይሆን ከማስታወቂያ አስነጋሪዎች ቢሆንም ከመጀመሪያ እትሟ ብቻ 10ሺ 100 በብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ያስታውሳል። በዚያው ሰሞን “አካፑልኮ ቤይ” የትርጉም መጽሐፉ ታትሞ ከ36ሺ ብር አጠቃላይ ትርፍ 30 በመቶውን እንደወሰደ አይዘነጋም።  
1997 ዓ.ም ሲገባ አየሩን ሁሉ ፖለቲካ ሲሞላው የተወዳጅ ገበያም እየቀነሰ መጣ። “ጋዜጠኛ ፖለቲከኛ መሆን የለበትም” ብሎ ስለሚያምን ነው እንጂ ተወዳጅን የፖለቲካ ጋዜጣ ማድረግ ይችል እንደነበር ያስረዳል። ቀጥሎ ለቢዝነስ እየሸፈተ ያለ ልቡን ጠቅልሎ የወሰደ ድርጅትን በሞክሼ ጓደኛው እዝራ ገ/ሥላሴ አማካኝነት ተቀላቀለ። “ጎልድ ኩዌስት” የተባለው ይህ የሆንግ ኮንግ ድርጅት በኔትወርክ ማርኬቲንግ  ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ ሲሆን መንግስት እስኪያግደው ድረስ በሀገራችን ተንቀሳቅሷል። እዚሁ ድርጅት ውስጥ እያለ በእንግሊዝኛ ብቻ የነበሩ የኔትወርክ ማርኬቲንግ ማንዋሎችን ወደ አማርኛ ሲመልስ ከቆየ በኋላ በመጽሐፍ መልክ አሳተመው። ከመጽሐፉ ህትመት ማግስት “ኢትዮ ቪዥን የችሎታ ማግኛ” የሚል የስልጠና ማዕከል ከፍቶ በርካቶችን ከችሎታቸው ጋር ማገናኘት ቻለ።
የጥረት ሰው ስለሆነ አደርገዋለሁ ያለውን ሁሉ አድርጓል። ይህች ዓረፍተ ነገር የወዳጅ የተጋነነ አድናቆት እንዳልሆነች መግቢያዬ ላይ ያሰፈርኩት የኩኩሉ መጽሔት እትም በቂ ማሳያ ቢሆንም ሌላ ምሳሌ እጠቅሳለሁ። መስከረም 22፣ 2000 ዓ.ም ከ22 ወደ ፒያሳ ይጓዝ በነበረ ታክሲ ውስጥ ያገኛትን ወጣት ጥቂት ካዋራት በኋላ ሰባ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ቀድሞ “ኔትወርክ ማርኬቲንግ” የሚል መጽሐፉን እየሳጣት “አንቺን ነው የማገባው” ብሏት ወረደ። ከሁለት አመታት በኋላ የሰርጉ ቀን ከጎኑ የቆመችው ሙሽራ፣ የያኔ ታክሲ ተጋሪው  የዛሬ ባለቤቱ አመለወርቅ ወልደኪዳን ነበረች።
2000 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ ቢወዳደርም ተጠባባቂ ነበር መሆን የቻለው። ከወራት ቆይታ በኋላ ከፋና ተደውሎለት ከፍተኛ ሪፖርተር ሆኖ በ1415 ብር ተቀጠረ። የራሱ ትርፋማ ተቋም እንደነበረውና ማሰልጠኛ ከፍቶ ሰዎችን ከተቀጣሪነት ውጡ እያለ ሲመክር መክረሙን የሚያውቅ ግማሽ ልቡ ‘ለምን ትቀጠራለህ?’ ቢለውም ሌላኛው የልቡ ክፍል ደግሞ ‘ዓላማህን ይዘህ ተቀጥረህ ሞክረው’ ይለዋል፤ ሁለተኛውን ሰማና ተቀጠረ። ተቀጠረና 13 ከዓመታት ከ 5ወር  ፋና ቤት መቆየት ቻለ።
በእነዚህ 13 ዓመታት ብዙ ከፍና ዝቅታዎችን አሳልፏል። 2001 ዓ.ም የአባቱን ማለፍ ተከትሎ ከሃዘኑ በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጠጋ። የትኛውም እምነት ውስጥ ቢሆን የሰው ልጅ መንፈሳዊ መሆን አለበት ብሎ ያምናል። እስከ 2006 ዓ.ም ያሉትንና ‘የዝምታ ጊዜ’ ብሎ በሚገልጻቸው ዓመታት መንፈሳዊነቱ ላይ አብዝቶ ሰራ፤ ብዙ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንም ተማረ። ፋና ውስጥ ቀድመው ያልነበሩ ፎርማቶችን ጀምሯል፣ የሀገር ውስጥ ታሪኮች እንዲለመዱ አድርጓል፣ ቴሌቪዥኑ ሲጀመር ደግሞ በርከት ያሉ አጫጭር ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንና ዶክመንተሪዎችን  ሰርቷል።ለብዙዎች የሬድዮ ኤዲቲንግ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ለታሪክ ያለው ፍቅር የተለየ ነው፤ ይህ ፍቅሩ ለሀገር መልካም የሆነ አበርክቶን እንዲያኖር ረድቶታል። ራሱም ሲናገር “አንዳንዴ ያንተ ፓሽን የሀገሪቱ ክፍተት ይሆንና መሻትህን በመኖር እግረ መንገድ ሀገርህን ትጠቅማለህ” ይላል። እዛው ፋና ቤት እያለ የጀመረው የታሪክ ፍቅሩን መወጣት ቢያስቀጣውም ቢያስነቅፈውም በረታበት እንጂ አልቆመም። ጎን ለጎን በአንጻራዊነት የተሻለ ነጻነት ላለው ድሬ ቲዩብ ታሪካዊ ጽሑፎችን ማድረስ በመጀመሩ ብዙ ትውውቆችን ፈጠረለት።
በ2008 ዓ.ም የግለሰቦችን ታሪክ በሲዲ የመሰነድ ሀሳቡን ሲያነሳ ብዙዎች እንደ እብደት ቢቆጥሩበትም፤ ያለውን ከማድረግ ሰንፎ አያውቅምና የተሾመ ገ/ማርያም ታሪክን በሲዲ በማውጣት ትርፋማ መሆን ቻለ። የጸሃፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ የአርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ፣ የአማረ አረጋዊን ጨምሮ 44 ሲዲዎችን ለማውጣት በቃ። ማማ በሰማይ፣ የኤርትራ ጉዳይ፣ ማህሌት፣ ምንትዋብና ሌሎች 10 የሚደርሱ መጽሐፍትን በኦዲዮ አሳተመ። ከአካፑልኮ ቤይና ኔትወርክ ማርኬቲንግን በተጨማሪ ‘10 ነገሮች ስለኦቲዝም’ እና ‘የአንኮበሩ ሰው በጄኔቭ’ የሚሉ ሌሎች መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል።
ፋና በቆየባቸው ጊዜያት 1476 ፕሮግራሞችን አየር ላይ ሲያውል፣ ከእነዚህ ውስጥ 67 ያህሉ ለቲቪ የተሰሩ ናቸው፡፡ ስራዎቹን ሰንዶ የማስቀመጥ ባህል ያለው እዝራ፤ በየጊዜው ያለፉ ስራዎቹን የማየት ልምድ አለው፡፡
ያለፈውን አንድ አመት 170 የሚደርሱ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ በመዝገበ አዕምሮ ለማስፈር ደፋ ቀና ሲል ከርሞ አሁን ለማሳተም ችሏል። ‘ለሚዲያ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሙያ መዝገበ አዕምሮ እንዲኖር እፈልጋለሁ’ ይላል፤ ካለ ደግሞ ያደርገዋል። ገንዘብ አያስገኝም በሚባልለት የሀገር ውስጥ ታሪክ ስነዳ በትጋት 5 አመታትን ብቻ ተመላልሶ ትርፍ ማግኘቱን በኩራት ይናገራል። ይህ ሁሉ እንዲሆን ከፈጣሪ ቀጥሎ ዋጋ የምትከፍለው ባለቤቱ ድርሻዋ የጎላ መሆኑን ያወሳል። በመጀመሪያ ትውውቃቸው “አንቺን ነው የማገባው” ያለው ሰምሮለት በጥቅምት 7፣ 2002 ዓ.ም በመሰረተው ትዳር፣ ክርስቲያን እዝራ እና ካሌብ እዝራ የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርቷል።
ወደ ሰላሳ ለሚደርሱ ጸሐፍትና ሌሎች ባለሙያዎች የስራ እድል ፈጥሮ ትርፉን እያጋራ ይገኛል፤ አብረውት የሰሩት ሁሉ ስለእዝራ ሲናገሩ ባንድ ድምጽ ስለትጋቱና አንድ ነገር ከጀመረ ሳያሳካ አለመልቀቁን ያወራሉ። ታሪካቸውን ከሰነደላቸው ሰዎች አንዷ ዝናሽ ማሞ ስለእዝራ ስትናገር፤ “ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያሳየውን ትጋትና ጥረትን አስተውያለሁ። እዝራ ከጀመረ አይለቅም ደጋግሞ ለመደወል አይታክትም፤ ለማሳመን አይደክምም፤ ተከታትሎ ታሪኩን በእጁ ለማስገባት አይሰለችም፤ ምንም የሚፃፍ ታሪክ የለኝም፣ ስራ ይበዛብኛል፣ ጊዜ የለኝም የመሳሰሉት መልሶች ተስፋ አያስቆርጡትም። በጥበብ አስተናግዶ የማሳመን ተሰጥኦ አለው።” ትላለች።
ቅድስት ወልዴ የተባለች ባልደረባውም ትናገራለች፤ “የእዝራ ትልቁ ጥንካሬው ራዕዩ ነው፤ እውቀትም ሆነ ገንዘብ  ያለውን የሚያካፍል ነው፤ ሌላው እና ትልቁ ነገር  በእግዚአብሔር ማመኑ ነው። ራዕዩን ለማሳካት እንቅፋቱን አልፎ የትም መድረስ የሚችል እና እሱን እያሳየ ያለ መሆኑ ነው። በታሪክ ስራዎቹ ብዙ ያልተነገረላቸውን የሀገር ባለውለታዎችን ከተረሱበት ታሪካቸውን በመፈልፈል በኦዲዮ ሲዲ እና በዶክመንተሪ ያለመታከት  በመስራት  በሀገራችን ቀዳሚው ባለሙያ ይመስለኛል።’
“38 ዓመታት በትምህርት አብረን ነበርን” የሚለው አብሮ አደጉ ናይእግዚ ህሩይ፤ የእዝራ ንባቡ ላይ የሙጥኝ ማለት እንደ እናቱ ሁሉ ይገርመው ነበር፡፡ “እንደልጅም እንደጎረምሳም ሳይሆን ማሳለፉ ይገርመኛል” ይላል። የራሱን ስራዎች፣ ታሪካዊ ብሎ የሚያምንባቸውን ነገሮች እና በቴሌቪዥን ይተላለፉ የነበሩ ዜናዎች በካሴት ቀርጾ ማስቀመጡን እያስታወሰ “በወቅቱ የግሉ ዩቲዩብ ነበረው ማለት እንችላለን” ይላል።
በርካታ ወዳጆች በተለይ አብረውት የሚሰሩ ከእዝራ ባህሪ የሚገርማቸውን ሲጠየቁ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የሚጠቅሱት የጀመረው ስራ እስኪያልቅለት እረፍት ማሳጣቱና “ችክ” ማለቱን ነው፤ እኔ ግን ይህን ችክታ ትጋት ነው የምለው። ትጋቱ ደግሞ አሁን ላለበት የስኬት ደረጃ ሊያቃርበው ችሏል፡፡


Read 574 times